ሕዝባዊ ውይይቶች ለዘላቂ ሀገራዊ ሠላም

በአንድ ሀገር የተረጋጋ ፖለቲካና ኢኮኖሚ መገንባት የሚቻለው የተረጋጋ ሠላምና ፀጥታን ማስፈን ሲቻል መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። የተረጋጋ ሠላምና ፀጥታን ለማስፈን ደግሞ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው መንግሥት ቢሆንም፤ ሕዝብም እንደ ሕዝብ በሀገሪቱ ሠላምና ፀጥታ እንዲሰፍን ያለው ድርሻ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ሁሉም ሰው ሊባል በሚችል ደረጃ ለሠላሙ ዘብ ሲቆም የሚታየው፡፡ ብዙዎች ከቤታቸው አልፎ ጎረቤታቸው፣ አካባቢያቸውና ሀገራቸው ሠላም ውላ ሠላም እንድታድር የየዕለት ልመናና ጸሎታቸው ነው፡፡

በተቃራኒው ደግሞ ከብዙ በጥቂቱ የሁሉ ነገር መሠረት የሆነውን ሠላም ለማደፍረስ እንቅልፍ የሚያጡ ኃይሎች አሉ፡፡ በእነዚህ ኃይሎች እኩይ ተግባር የተነሳ በተለያዩ ሕዝቦች ሠላምና መረጋጋት እንዲርቃቸውና በአንጻሩ ጦርነት፣ የእርስ በርስ ግጭት፣ ሽብርተኝነትና ወንጀል ተንሰራፍቶ የሰዎች ዕለታዊ እንቅስቃሴ እንዲገታ ሲያደርጉ ኑሯቸው እንዲታወክ፣ የሚሊዮኖች ሕይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም ሆኗል፡፡ እየሆነም እያየን ነው፡፡ በሠላም እጦት ምክንያትም በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለኪሳራ እንደሚዳረግ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ኢትዮጵያም ከዓለም የተለየች አይደለችምና ዓለም ባለፈባቸው ምቹና ምቹ ባልሆኑ መንገዶች ሁሉ ለማለፍ ትገደዳለች፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ችግሮች ሲገጥሟት የሚስተዋለው፡፡ ያም ቢሆን ታዲያ ኢትዮጵያዊ ብልሃትና እሴቶቿን ተጠቅማ የገጠሟትን ችግሮች በመልካም እሴቶቿ ስትፈታ ኖራለች። ዛሬም እየሆነ ያለው ይኸው ነው፡፡ በሀገሪቱ ሊሆኑ አይደለም ሊታሰቡ የማይችሉ ድርጊቶች ተከናውነው አይተናል፡፡ በድርጊቱም ብዙዎች ታመዋል፡፡ ያም ቢሆን ‹‹ዓይን አያየው፤ ጆሮ አይሰማው ነገር የለም›› በማለት በኢትዮጵያዊ ጨዋነት አይተን እንዳላየን ሰምተን እንዳልሰማን ቻል አድርገን አልፈናል፡፡

‹‹ሁሉም ያልፋል…›› እንዲል ታላቁ መጽሐፍ፣ ኢትዮጵያውያን ብዙ ሺህ መከራዎችን ችለው ማሳለፍ የቻሉት አንድም ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው በመሆናቸው ሁለትም የበዙ መልካም እሴቶች ያሏቸው በመሆናቸው ነው ቢባል ስህተት የለውም፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ ለሠላም የሚተጉ ውድ ልጆች እንዳሏት ሁሉ፤ ሠላሟ እረፍት የሚነሳቸውና ሰላም በማጣቷ ብዙ የሚያተርፉ የሉም ማለት አይቻልም፡፡

በብዙዎች ዕንባ፣ ኀዘንና ሰቆቃ የሚደሰቱ፣ ኪሳቸው ሞልቶ የሚትረፈረፍና ኑሯቸው እንደ ጠዋት ፀሐይ የሞቀና የደመቀላቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ የሀገር ሠላም ሲናጋ ንጹሐን ለከፋ የሕይወት ምስቅልቅሎሽ ቢጋለጡም፣ በሰዎች ስቃይ ለሚያተርፉ ግን ሠርግና ምላሽ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ሠላምን አጥብቆ መሻት ለተግባራዊነቱም በብዙ መትጋት ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል፡፡

እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁን ወቅት ለሠላም ያላትን ዝግጁነት በተለያየ መንገድ እየገለጸች ትገኛለች፡፡ ለዚህም ቀዳሚውን ድርሻ የሚወስደው መንግሥት እንደመሆኑ መንግሥት ሠላም በሰዎች ሕይወት ውስጥ ያለውን ትልቅና ውድ ዋጋ በመረዳት ከትናንት እስከ ዛሬ እጆቹን ለሠላም ዘርግቷል። አሁንም ለሠላም የተዘረጉ እጆቼ አይታጠፉም በማለት የሀገር ሠላም እንዲጸና ሕዝቦች በአንድነት ተዋደውና ተፋቅረው በሠላምና በጋራ እንዲኖሩ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል፡፡

ከሰሞኑ በሀገሪቱ ሲካሄዱ የነበሩት ሕዝባዊ ውይይቶች ለዚህ ዋነኛ ምስክሮች ናቸው፡፡ ሰሞነኛው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሀገሪቱ ከሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎችና ቤተ ዕምነቶች ከተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያደረጓቸው ሕዝባዊ ውይይቶች ሀገሪቱ ለምትፈልገው ዘላቂ ሠላም፣ መረጋጋትና አንድነትን ለማምጣት ያላቸው ፋይዳ እጅግ የጎላ ነው፡፡ በመሆኑም መሰል ሕዝባዊ ውይይቶች መለመድ ያለባቸውና ይበልጥ ሊጎለብቱ የሚገባቸው እንደሆኑ ይታመናል፡፡

ችግሮችን ለመፍታት መወያየትና መነጋገር ቀዳሚው አማራጭ መሆን እንዳለበት ከሰሜኑ ጦርነት መማር ችለናል፡፡ በተለይም መንግሥት ታች ካለው የማኅበረሰብ አካል ጋር በሀገሪቱ አሉ የተባሉ ችግሮችን ለመፍታት በሚያስችል መንገድ መወያየት መጀመሩ ትልቅ ውጤት ነው፡፡ መንግሥት ከተለያዩ የሃይማኖት አባቶች ጋር እንዲሁም ከተለያዩ የማኅበረሰቡ ክፍሎች ከተወጣጡ አካላት ጋር ውይይት ማድረጉ ሀገሪቷ አሁን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ፍንትው አድርጎ ማየትና መረዳት የሚያስችለው በመሆኑ ትልቅ ዕድል ይፈጥርለታል፡፡

መንግሥት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት እንዲችል ውይይትን በማኅበረሰቡ ዘንድ ማዳበር ከማስቻሉ ባሻገር ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥ ያለው አማራጭ ከፍተኛ እንደሆነም ይታመናል፡፡ ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥ ችግሮችን ከማኅበረሰቡ ከራሱ ማድመጥ ችግሮችን በማስወገድ ረገድ ተጨባጭ ለውጦችን ማምጣት የሚችልና የሠላም በሮች የሚከፈቱበትን ዕድል የሚያሰፋ ነው፡፡

ሰሞንኛ ሕዝባዊ ውይይቶች መረጃን መሠረት ያደረጉና መሬት ላይ ያለውን እውነታ መሠረት ያደረጉ በመሆናቸው ችግሮቹን በግልጽ ለመረዳት አበርክቷቸው የጎላ ነው። በሀገራችን ባልተለመደ ሁኔታ መንግሥት ሕዝባዊ ውይይቶችን ማድረጉ በብዙዎች ዘንድ የሚደገፍ ከመሆኑም በላይ ተጨባጭ ለውጦችን ማምጣቱም አይቀሬ ነው፡፡ ውይይቱ በተለይም በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጸና፣ ግልጸኝነትን የሚያመጣና ችግሮችን እያጠበበ የሚሄድ እንዲሁም ችግሮቹ እንዴት መፈታት እንዳለባቸው አቅጣጫ የሚያሳይ እንደሚሆን ይታመናል፡፡

መረጃን መሠረት ያደረገው ይህ ሕዝባዊ ውይይት፣ ለመንግሥትና ለመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች በሙሉ የማንቂያ ደውል የመሆን ዕድሉም የሰፋ ነው፡፡ እስካሁን የተካሄዱት ሕዝባዊ ውይይቶችም የችግሮቹ መነሻ ከየትም ይሁን ከየት እውነታውን ፍንትው አድርገው ማሳየት የሚችሉ በመሆናቸው ለዜጎች ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፋይዳቸው የጎላ ነው፡፡ ሕዝባዊ ውይይቱ በሰላምና ደኅንነት፣ በመልካም አስተዳደር፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱንን ያደረገ በመሆኑ መንግሥት ቃል ገብቶ ያልፈጸማቸውን ተግባራት ሕዝቡ ለምን ሲል መጠየቅ እንዲችል ዕድል ፈጥሮለታል፡፡

በመጨረሻም፣ ለሠላም ትልቅ ድርሻ ያላቸው ሕዝብና መንግሥት መቀራረብ፣ መነጋገርና መደማመጥ ከቻሉ፤ ኢትዮጵያ የራቃትን ሠላም መልሳ ታገኛለች፡፡ ሕዝብና መንግሥት ተቀራርበውና ተማምነው መሥራት ከቻሉ ዘላቂ ሠላምን ማስፈን ይቻላል፡፡ ዘላቂ ሠላምን ማምጣት ከተቻለ ደግሞ ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ከባድ አይሆንም፡፡ ለዚህ ሁሉ ታዲያ ሕዝባዊ ውይይቱ የታለመለትን ዓላማ ማሳካት የግድ ይለዋል፡፡ መንግሥት ከሕዝባዊ ውይይቱ ያገኘውን ግብዓት ተጠቅሞ መሥራት ያለበትን የቤት ሥራ እንደየቅደም ተከተሉ መሥራት የሚጠበቅበት ሲሆን፤ በተለይም ሕዝብ በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዲያጣ የሚየሩ አሻጥሮችን መለየትና ከስሩ መንቀል ከመንግሥት የሚጠበቅ ጥልቅ ሥራ ነው፡፡ አበቃን!

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2016 ዓ.ም

Recommended For You