የባሕርበር የማግኘት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችና እያስገኙት ያለው ውጤት

ኢትዮጵያ ትገለገልባቸው የነበሯትን ምጽዋና አሰብ ወደቦችዋን ካጣች ጊዜ ጀምሮ የባሕር በር አልባ ከሆነችም ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አሁን ደግሞ በሰለጠነ ዲፕሎማሲና በሰጥቶ መቀበል መርህ በሊዝ የወደብ ባለቤት ለመሆን የሚያስችላትን ከሶማሊ ላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሟ ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና በሶማሊ ላንድ ፕሬዚደንት ሙሴ ባሂ መካከል ከሶሰት ወራት በፊት የተደረገው ስምምነት ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘትና ለማልማት የሚያስችል ነው፡፡ ይሄን ተከትሎ ኢትዮጵያ ትክክለኛ የሆነ እርምጃ መውሰዷንና መብቷም እንደሆነ ብዙዎች የድጋፍ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡

በአንፃሩ ደግሞ ስምምነቱ ከተፈፀመበት ጊዜ ጀምሮ ሶማሊ ላንድ በዓለም እውቅና የተሰጣት ሉዓላዊ ሀገር እንዳልሆነችና የወደብ አማራጭ መሆን እንደሌለባት በመንቀፍ፣ ስምምነቱ ወደ ተግባር እንዳይለወጥ የተለያዩ ኃይሎች ተንቀሳቅሰዋል። በተለይም ጉዳዩ በቀጥታ የማይመለከታቸው ሀገራት ጉዳዩን ለማራገብ ሲሞክሩ ቆይተዋል፡፡

ኢትዮጵያ አበጀሽ ብለው የደገፏት አቅም ሆነዋት፤ ለነቀፏትም ጆሮ ሳትሰጥ በአቋሟ ፀንታ የባሕርበር ባለቤት የምትሆንበትን አማራጮች ከመፈለግ ወደኋላ አላለችም፡፡ ይሄ ቁርጠኝነት በምን መልኩ መቀጠል አለበት? ከማኅበረሰቡስ ምን ይጠበቃል? ለሚለው በኢፌዴሪ የሕገመንግሥት አጣሪ ጉባኤ ከፍተኛ የሕገመንግሥት ተመራማሪ አቶ ዓምደገብርኤል አድማሱ አነጋግረን የሚከተለውን ሀሳብ ሰጥውናል፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት በኢትዮጵያ እና በሶማሊ ላንድ መካከል ስምምነት ላይ የተደረሰው የባህር በር የማግኘት ጉዳይ ወደ ተግባራዊ ሂደት እንዲሸጋገር፤ ዲፕሎማሲው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

እንደ አቶ ዓምደገብርኤል ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ በዓለም ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተደማጭነት ያላት፣ በዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዋም ጫና መፍጠር የምትችል ሀገር ናት፡፡ የተባበሩት ምንግሥታት ድርጅት ከመመስረቱ በፊት አፍሪካን ወክላ ሊግኦፍኔሽን ላይ በመሳተፍ የአፍሪካን መብት ያስከበረች፣ ለአፍሪካ ድምጽ መሆን የቻለች ሀገር ናት፡፡

የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫም በመሆኗ ከሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት በተሻለ ታላቅ ስም አላት፡፡ እነዚህ ሁሉ በዲፕሎማሲው ተጽእኖ እንድትፈጥር ያስችሏታል፡፡

ተቀባይነቷን በመጠቀም በዲፕሎማሲው የምታደርገው እንቅስቃሴ እየተቃወሟት ያሉ ሀገራትንም ሆኑ ግለሰቦችን ማሳመንና ከድርጊታቸውም እንዲቆጠቡ ማድረግ ትችላለች። በተጨማሪም የባሕር በር ለማግኘት ከሶማሊ ላንድ ጋር በፊርማ ያደረገችው የውል ስምምነት ወደ ተግባር እንዲቀየር ያስችላታል፡፡ በመሆኑም በዲፕሎማሲ መግፋትና መበርታት የተሻለ ነው፡፡

አካባቢ ላይ ሁከት፣ ትርምስና ግጭት ለማስነሳት የሚንቀሳቀሱ አካላት ትክክል እንዳልሆኑ ለማሳየት እንዲሁም ከሶማሊ ላንድ ጋር የተደረገው ስምምነት ሕጋዊነትና ጠቀሜታውን በተመለከተ ሌላው ዓለም እንዲያውቀው በማድረግና መረጃም በመስጠት ተከታታይነት ያለው የዲፕሎማሲ ሥራ ያስፈልጋል፡፡

መታወቅ ያለበት ነገር ኢትዮጵያ እያደረገች ያለው ሕጋዊና በዓለምአቀፍም ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ ተጠቃሚ ለመሆን የወሰደችው አማራጭም በኃይል ሳይሆን፣ በሰጥቶ መቀበልና በስምምነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ፍላጎትዋ እንዲሳካ፣ ዓለምአቀፍ እውቅና እንዲያገኝ እንዲሁም ተቀባይነቱ ሥር እንዲሰድ ጠንካራ የሆነ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት ይጠበቅባታል፡፡

መንግሥት የጀመረውን የባሕር በር የማግኘት ጥረት ከዳር ለማድረስ ሕዝቡን የበለጠ ማሳተፍ እንደሚገባም አቶ ዓምደገብርኤል ይመክራሉ፡፡ ይህ ሲሆን መንግሥትንና ሕዝብን መነጣጠል እንደማይቻልና ጉዳዩ የአንድ አካል ሳይሆን፣ የጋራ እንደሆነ ማሳየት ያስችላል ይላሉ፡፡

እርሳቸው እንዳሉት በሕዝብና በሕዝብ መካከል ወይንም በመንግሥትና በሕዝብ መካከል የሚያነጋግሩ፣ የሚያከራክሩና የሚያጨቃጭቁ ነገሮች ቢኖሩም፤ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ ግን የጋራ ጉዳይ ነው፡፡

እንደ ሀገርም ታሪክ የሚሰራበትና ለሚመጣውም ትውልድ የሚቆይ ታሪክ በመሆኑ ጉዳዩ የአንድ ወገን ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ ከዛሬ 40 ዓመት በፊት አንድ ወደብ ብቻ ሳይሆን ወደቦች የነበራት ሀገር ናት፡፡ በሂደት በታሪክ አጋጣሚዎች ነው ወደብ አልባ ለመሆን የቻለችው፡፡

የኢትዮጵያን የቀድሞ ገናናነቷንና ከፍ ያለውን ታሪኳን ወደነበረበት መመለስ የዜጎችዋ ድርሻ ስለሆነ በተለያየ መንገድ ማገዝና መደገፍን ይጠይቃል፡፡ መደበኛ የሆኑ የመገናኛ ብዙሃንና ማኅበራዊ ድረገጾችን (ሶሻል ሚዲያ) የመገናኛ ዘዴዎች አማራጮች ማድረግ ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ በውስጥ የገጠማት አለመረጋጋትና የሰላም ሁኔታ የባሕርበር ለማግኘት በኢትዮጵያና በሶማሊ ላንድ መካከል የተደረገው ስምምነት ላይ ሊኖረው ስለሚችለው ተጽእኖ በአንዳንዶች የሚነሳውንም ስጋት አቶ ዓምደገብርኤል አንስተዋል፡፡

እንደርሳቸው ማብራሪያ የባሕር በር ስምምነቱ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ቀጥሎ እንደ አንድ ሀገራዊ ፕሮጀክት ማየት ይቻላል፡፡ የባሕርበር ማግኘት ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን እጅግ ከፍተኛ የሆነ ክፍያ በመፈጸም ነው የጅቡቲ ወደብን እየተጠቀመች ያለችው፡፡

የራሷን ወደብ ቢኖራት ግን ወጪን ይቀንስላታል፡፡ ታወጣ የነበረውን ገንዘብም ሀገርንና ሕዝብን የሚጠቅም የልማት ሥራ ላይ ታውላለች፡፡ የባሕር በር ጉዳይ የሉአላዊነት ነጻነትም ጉዳይ ነው፡፡ የበለፀጉት እንደነቻይና፣ አሜሪካን፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ የመሳሰሉት ሀገራት ለራሳቸው ልእልና ማሳያ ጅቡቲ ላይ የባሕር በር ቦታ ላይ መሬት የገዙበት አጋጣሚ መኖሩ አይዘነጋም፡፡

ለዚህ ነው የባሕርበር ጉዳይ እንደዋዛ መታየት የሌለበት። በሀገር ውስጥ ያለው አለመረጋጋትና የሰላም ጉዳይ ወደብ የማግኘት ጥያቄ ላይ ተጽእኖ ማሳደር የለበትም፡፡ የኢትዮጵያን እድገት ለማይፈልጉ መንገድ መክፈት አያስፈልግም፡፡ የውስጥ አለመረጋጋቱ የኢትዮጵያን እድገት በማይፈልጉ አካላት ተገቢውን እውቅና እንዳያገኝ ማድረግና ጉዳዩንም ሁሉም ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ዓምደገብርኤል ማብራሪያ፤ ውል በተዋዋዮች መካከል ሕግ ነው፡፡ በሀገራት መካከል የሚደረግ የሁለትዮሽ ስምምነት ደግሞ ሌሎች ዓለምአቀፍ ሕግጋቶችና ስምምነቶች የማይጣረስ ከሆነ እንደሕግ ነው የሚቆጠረው፡፡

ስለዚህ ኢትዮጵያ የወደብ አገልግሎት ለማግኘት ከሶማሊ ላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት ሰጥቶ መቀበልን መርህ የተከተለ ነው፡፡

ኢትዮጵያም ሆነች ሶማሊ ላንድ የሄዱበት መንገድ ሕገወጥ ቢሆን ኖሮ፣ የዓለምአቀፍ ሕግጋትንም የሚጥስ ቢሆን ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጠርባት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የፈፀመችውን የውል ስምምነት ከግብጽና ሶማሊ ሪፐብሊክ በስተቀር በተባበሩት መንግሥታት ዓለምአቀፍ ድርጅቶችም ይሁን በአፍሪካ በቀጠናው ትክክል አይደለም ወይንም ሕገወጥ ነው በሚል እስካሁን የቀረበ ነገር የለም፡፡

ግብጽ፤ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ አካላት ታሪካዊ ጠላትነት ስምምነቱን ተቃውማለች። ግብጽ በቀጠናው ላይ ትርምስ ለመፍጠር ማንኛውንም አይነት መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኗን በግልጽ አሳውቃለች።

ሶማሊም የሶማሊ ላንድ ግዛት የኔ ነው፤ የኔን ሉዓላዊነት መድፈር ነው በሚል በተመሳሳይ በኢትዮጵያና በሶማሊ ላንድ መካከል የተደረገውን ስምምነት አልተቀበለችውም፡፡ የሶማሊው ፕሬዚደንትም ስምምነቱ ሉዓላዊነታቸውን የሚነካ መሆኑን ሲጠቅሱ ይሰማሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ስምምነቱን በጥሩ መልክ ለመቀበል ፈቃደኛ ሆነው ያልተገኙት፣ በቀጠናው ብጥብጥ እንዲነሳና ጉዳዩም እንዳይሳካ እያደረጉ ያሉት እነዚህ ሁለቱ ሀገራት ናቸው፡፡

ግብጽም ሆነች ሶማሊያ ስምምነቱ ትክክል እንደሆነ ሳይገነዘቡት ቀርተው ሳይሆን፤ ከኢትዮጵያ ጋር ባላቸው ታሪካዊ ጠላትነት የተነሳ ነው፡፡ ሁለቱ ሀገራት በዚህ መልኩ መንቀሳቀሳቸው ስምምነቱ በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይሄድ ሊያደርግ እንደሚችልም አቶ ዓምደገብርኤል ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ኢትዮጵያውያን የያዙት ሀሳብ ትክክል ስለሆነ የባሕር በር የማግኘት ጥረታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸው የማይቀር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት አካሄድ በቀጠናው ግጭት እንዲስፋፋ ሊያደርግ ይችላል የሚለውን ስጋት በተመለከተ አቶ ዓምደገብርኤል ሲናገሩ፤ ‹‹በስምምነቱ ውስጥ ኃይል የሚባል ነገር የለም፤ ኢትዮጵያና ሶማሊ ላንድ በግዴታ ሳይሆን፣ በስምምነት የፈጸሙት ጉዳይ ነው፡፡ ሁለቱ ያደረጉት ስምምነት ለጦርነት የሚያነሳሳ ባለመሆኑ ኃይል ወደመጠቀም የሚያደርስ ነገር የለም፡፡›› ብለዋል

አቶ አምደ ሚካኤል አክለው እንደሚገልጹት በዚህ ስምምነት ውስጥ ደግሞ ማንም ከልካይ አካል የለም፡፡ ሊኖርም አይችልም፡፡ ግብጽና ሶማሊያም ቢሆኑ መከልከል አይችሉም፡፡ እናም መከልከል የማይችሉት ነገር ላይ ግችትና ሁከት ቢፈጥሩ ችግሩ መልሶ ለእነሱ እንደሚተርፍ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የባሕርበር ማጣት ማለት በቅኝ መገዛት ማለት ነው የሚሉት አቶ ዓምደገብርኤል፤ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በጣም ጥቂት ሲሆኑ፣ እነርሱም በሕዝብ ብዛታቸውና በቆዳ ስፋታቸው ትንሽ የሚባሉ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ግን ከአንድ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያላት ሀገር ናት፡፡ የባሕር በር አልባ መሆን አይገባትም፡፡ የኢኮኖሚ የእድገት እንቅስቃሴን ወደኋላ የሚጎትትና በተለያየ መልኩ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ የባሕር በር መኖሩ ግዴታ ነው ሲሉ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

የአፋር ክልል ፕሬዚደንት አማካሪ አቶ አህመድ ያሲን ሊሊሳ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ በኩል የተጀመረው የወደብ ባለቤት የመሆን ጥያቄ መቀጠል አለበት ይላሉ፡፡ ለዚህ ቁልፉ መሳሪያ ደግሞ ዲፕሎማሲ መሆኑን አስምረውበታል። ‹‹ሰላማዊ ድርድር ዘለቄታዊ መፍትሄ ያስገኛል፡፡ የኃይል አማራጭ ግን ዓላማን ያሰናክላል፡፡ እቅድንም ወደኋላ ይጎትታል፡፡ ከጥፋት በስተቀር ውጤት ላይ አያደርስም፡፡ ለዚህ ነው ኃይልን በአማራጭነት መውሰድ የማይመከረው›› ሲሉም በዲፕሎማሲ መጠንከሩ የተሻለ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ዜጋውም መንግሥት ለሚጠይቀው ድጋፍ ተባባሪ ሆኖ ለመገኘት ዝግጁ መሆን አለበት ይላሉ፡፡ መንግሥት እንዲበረታታ፣ የባሕር በር ለማግኘት የተፈፀመው የውል ስምምነት ፊርማ ወደ ተግባር እንዲለውጥ የሕዝብ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በአፋር በኩል መንግሥት የጀመረውን ከዳር እንዲያደርስ ለማገዝ ዝግጁ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በመንግሥት የተጀመረው እውን ሆኖ ለማየትና ኢትዮጵያ የባሕርበር እንዳታጣ የአፋር ሕዝብ ቀድሞውኑ ያሰማ የነበረው ጩኸትም መልስ እንደሚያገኝ ተስፋ አድርገዋል፡፡ ከአሰብ ባሕር ውስጥ የሚጠመድ አሣ እንደናፈቃቸውም ገልጸዋል፡፡

አቶ አሕመድ ታሪክንም ወደኋላ መለስ አድርገው እንዳስታወሱት፤ ኢትዮጵያን የባሕር በር ያሳጣት የቀኝ ግዛት አባዜ ያለባቸው ለሀገር ጥቅም የማያስቡ ናቸው ይላሉ፡፡ ሪፈረንደም በሚል ሰበብ የተፈፀመው መለያየት የፈጠረው ጠንቅ ነው ሲሉም ይገልጻሉ፡፡

እርሳቸው እንዳሉት በወቅቱ ሕዝብ የሚሰማው አጥቶ እንጂ ሪፈረንደም ሊያስከትል የሚችለውን መዘዝ አስመልክቶ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡ እስካሁንም የቀይ ባሕር አፋሮች በተለያየ መንገድ ከመታገል ወደኋላ አላሉም፡፡ አፋርን ሲያስተዳድሩ የነበሩት ሱልጣን አሊሚራ ሀንፍሬ ቀይ ባሕር የአፋር እንደሆነ ጭምር በመናገር ኢትዮጵያ ወደብ አልባ እንዳትሆን ብዙ ታግለዋል፡፡

‹‹በአፋር ባሕል ድንበር የለም፡፡ የአፋር ልጅ ወይ አባቱ ወይንም እናቱ፣ ወገኑ በጅቡቲ፣ በኤርትራ ስለሚኖር በመካከላችን ልዩነት አለ ብሎ አያምንም›› ሲሉም ያስረዳሉ። የክልሉ መሪ ያደረጉት ትግልም ሆነ የህሕቡ ጩኸት መቀማቱን ነው አቶ አሕመድ የገለጹት፡፡

ያን ጊዜ ሕዝብ ያሰማው የነበረው ጩኸት ትክክል እንደሆነና በወቅቱ ጩኸቱ ባለመሰማቱ ኢትዮጵያን ዋጋ እንዳስከፈላት እማኝ መጥራት አያስፈልግም ያሉት አቶ አሕመድ፤ የባሕር በር አለመኖሩ እያስከተለ ያለው ችግር እየታየ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

ለወደብ ኪራይ የምታወጣው ወጪ የኢኮኖሚ አቅሟን እየተፈታተነ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ኢትዮጵያን የሚያክል ሀገር የባሕር በር አልባ መሆን ቁጭት ውስጥ የከተተው ሕዝቧን ብቻ ሳይሆን፤ ወዳጆችዋ የሆኑትን የዓለም ሀገራት ጭምር እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

ያለፉ መሪዎች ኢትዮጵያ ትገለገልባቸው የነበሩ የባሕርበሮችዋን አስጠብቃ እንድትቆይ ከማድረግ ይልቅ፤ አሳልፈው ለሌላ መስጠታቸው ታሪካዊ ስህተት እንደሆነ የሚገልጹት አቶ አሕመድ፤ የባለቤትነት መብቷ እንዲረጋገጥላትና ከሶማሊ ላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት ተግባራዊ ሆኖ ተጠቃሚ ለመሆን እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው ይላሉ፡፡

የሕገመንግሥት ተመራማሪው አቶ ዓምደገብርኤልም ሆኑ የአፋር ክልል ፕሬዚደንት አማካሪ አቶ አሕመድ ስምምነቱን ተፈፃሚ ማድረግ የሚቻለው ዲፕሎማሲውን በማጠናከር እንደሆነ አስምረውበታል፡፡

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2016 ዓ.ም

Recommended For You