የሳይበር ደህንነት ቀዳሚ የዓለም ስጋት እየሆነ መጥቷል፡፡ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መስፋፋትን ተከትሎ ከሚመጣው የሳይበር ደህንነት ስጋት በተጨማሪ የሚፈጠሩት ጥቃቶች በዲጂታል ጉዞ ላይ እንቅፋት መሆናቸው እየተጠቆመ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ተከትሎም የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል፡፡
የሳይበር ጥቃት ሆነ ተብሎ በኮምፒውተር ሥርዓቶች፣ መሰረተ ልማቶች፣ ኔትዎርኮች ላይ ያልተፈቀዱ አጥፊ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም በሕገወጥ መንገድ መረጃዎችን መበዝበዝና አገልግሎት በማስተጓጎል የሚፈጸም ጥቃት ነው፡፡ የሳይበር ደህንነት ስጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሳይበር ጥቃቶች የሚያስከትሉት ኪሳራም ተበራክቷል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ በ2022 ከ5ነጥብ6 እስከ 7 ትሪሊዮን ዶላር፤ በ2023 ስምንት ትሪሊዮን ዶላር በሳይበር ጥቃት የተነሳ ኪሳራዎች ደርሰዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2025 አሥር ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ ሊደርስ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
የኢንፎርሜሽን ደህንነት መረብ አስተዳደር መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣው የሳይበር ጥቃት በኢትዮጵያም በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል፡፡ ለዚህም በቅርብ ዓመታት የተደረጉት የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን መመልከት ይቻላል፡፡
በ2008 በጀት ዓመት 214፣ በ2009 በጀት ዓመት 479፣ በ2010 በጀት ዓመት 576 እና በ2011 በጀት ዓመት 791 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ በ2012 በጀት ዓመት አንድ ሺ075፣ በ2013 በጀት ዓመት ሁለት ሺ 898 እና በ2014 በጀት ዓመት ስምንት ሺ 845 ጥቃት ሙከራዎች ተደርገዋል፤ በ2015 በጀት ዓመት 6ሺ959 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ተካሂደዋል፡፡ በተለይ ከ2012 ጀምሮ ባሉት በእነዚህ ሦስት ዓመታት የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች እየጨመሩ መምጣታቸው መረጃዎቹ ያሳያሉ፡
ኢትየጵያ ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ እንድትሆን እና ተጋላጭነቱ እንዲጨምር ካደረጉት ምክንያቶች መካከል የሳይበር ምህዳር ተለዋዋጭ በመሆኑ በየጊዜው የሚፈልገውና የሚጠበቀውን አይነት ሆኖ አለመገኘት፣ የአገልግሎቶች ዲጂታላይዝድ መድረግና የአገሪቱ የጂኦፖለቲካ ሁኔታ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የሳይበር ጥቃት መመከት ሳይቻል ቀርቶ ከተከሰተ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለው ውድመት ከፍተኛ በመሆኑ የሚያደርሰው ተጽእኖ ከባድ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በሀገር ላይ ከፍተኛ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳይ የሚጠበቀው ደህንነቱ የተጠበቀ የሳይበር አገልግሎት ሲኖር ነው። በተለይ ኢትዮጵያ በ2025 ሙሉ ለሙሉ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመተግበር የምታደርገውን ጥረት የሚያግዝ ስርዓት ለመዘርጋት የማይበገር የሳይበር ደህንነት አቅምን መገንባትን ይጠይቃል፡፡
ዲጂታል 2025 ስትራቴጂን ለማሳካት ከተቀመጡ ዋናዋና እቅዶች አንዱ የሳይበር ስነምህዳርን /ኢኮሲስተም/ን በመጠቀም ሲስተሞች ከመዘርጋትና የዲጂታል ኢኮኖሚውን ሊመጥን የሚችል ምህዳር መገንባት ሲቻል መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ያመላክታሉ፡፡
የአገሪቱን የሳይበር ምህዳር ደህንነት ለማስጠበቅና ሉአላዊነትን ለማስከበር የሳይበር ጥቃቶችን መመከት ኃላፊነት የተሰጠው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሳይበር ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ አስተዳደሩ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን የሳይበር ደህንነትን በማስጠበቅ ረገድ የኀብረተሰቡን ግንዛቤ ለማስፋት የሚያስችሉ ሥራዎች ሲሰራ ቆይቷል፡፡
በቅርቡም የኢንፎርሜሽን ደህንነት መረብ አስተዳደር እና የኢትዮጵያ ሳይበር ደህንነት ማህበር የግሉ ዘርፍና የመንግሥት ተቋማት በተቀናጀ መልኩ የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚያስችል ሥራ ለመስራት የሚጠቅም ምክክር አድርገዋል፡፡
ምክክሩ የሳይበር ደህንነትን ከሚመራው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ ከኢትዮጵያ ሳይበር ደህንነት ማህበር ጋር በመተባበር በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ጥናትና ምርምር ከሚሰሩ የተለያዩ ምሁራን ጋር ውይይት ለማድረግ ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑን የሚናገሩት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትዕግሥት ሃሚድ ናቸው፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ አሁን ላይ የሳይበር ደህንነትን በተመለከተ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው። በተለይ በየዓመቱ በጥቅምት ወር የሳይበር ደህንነት የተመለከቱ በርካታ ሥራዎች ይሰራሉ። ይህን ፕሮግራም ለየት እንዲል የሚያደርገው የሳይበር ደህንነት ለማስጠበቅ ከምሁራን፣ ከግልና ከመንግሥት ተቋማት ጋር በተቀናጀ መልኩ መስራት የሚያስችል መሆኑ ነው፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ተልዕኮ ቁልፍ የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማትን ደህንነት ማስጠበቅ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡ ይህን ተልዕኮ ለማሳካት 24/7 የተሰኘ የሳይበር ኤመርጀንሲና ሪስፖንስ/ድንገተኛ አደጋና ምላሽ/ ቡድን ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፤ ይህም በቁልፍ መሠረተ ልማቶች እና በፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅ የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ ዝግጁ ሆኖ ሁልጊዜም በንቃት የሚከታተል ክፍል መሆን ገልጸዋል። በተጨማሪም የፋይናንስ ተቋማት፣ ቁልፍ የመንግሥት ተቋማት እና ግለሰቦች ላይም ጭምር ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ብዙ እየተሰራ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
እንደ አገር ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እየተስፋፋ መሆኑን ተከትሎ እየጨመረ የመጣውን የሳይበር ጥቃት ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችን በጋራና በትብብር መስራት ያስፈልጋል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ‹‹ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂም የሚያስገነዝበውም በትብብር መስራትን ነው፡፡ ዲጂታል ኢኮኖሚው አካታች ሆኖ እንዲሰራ፤ ደህንነቱ የተጠበቀ ሆኖ እንዲሄድ የተማከለ መሆን እንዳለበት ይታመናል፡፡ ለዚህ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን በጋራ የመጠቀም፣ አገልግሎቶችን ክላውድ ማድረግ ያስፈልጋል›› ይላሉ፡፡
መሠረተ ልማቶችን በጋራ ለመጠቀም፣ አገልግሎቶችን ክላውድ ለማድረግም ያስችል ዘንድ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና አርተፊሻል ኢንተለጀስ ኢንስቲትዩት በጋራ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የሚመራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል፡፡ የሳይበር ደህንነትን ማስጠበቅ ስራ ጥቃቶች ሳይደርሱ በመመከት በአገር ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ከመቀነስ አንጸር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ያስረዳሉ፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃት እየጨመረ ነው። በተያዘው በጀት ዓመት በስድስት ወራት ውስጥ 4ሺህ 363 የሳይበር ጥቃቶች ደርሰዋል። እነዚህ የሳይበር ጥቃቶች በአይነታቸው የተለያዩ ሲሆኑ፣ የኢሜልና የፊሺንግ ጥቃቶች ተከስተዋል፤ አብዛኛዎቹ ደግሞ የዳታ ስርቆት ጥቃቶች ናቸው፡፡
በአገሪቱ ላይ በተቃጡት የሳይበር ጥቃቶች በአብዛኛው ተጠቂ እየሆኑ ያሉት የሚዲያና የፋይናንስ ተቋማት ናቸው፤ እስካሁን የተሰነዘሩት ጥቃቶች መሠረታዊ የሚባሉት መሠረተ ልማቶች ማቋረጥ ላይ አልደረሱም፡፡ እነዚህ ጥቃቶች የተለያዩ ቢሆኑም፣ አብዛኛውን ጊዜ በንቃተ ህሊና እጥረት የሚመጡ ናቸው፡፡
ተቋሙ የሳይበር ደህንነትን በተመለከተ ግንዛቤ በመስጠት እና ተቋማት እንዲጠነቀቁ በማድረግ የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የሳይበር ደህንነት ሁሉንም ሰው የሚመለከት ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ግንዛቤን በማስፋት መከላከል ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሳይበር ደህንነት ማህበር ፕሬዚዳንት ብርሃኑ በየነ (ዶክተር) በበኩላቸው፤ ማህበሩም የሳይበር ደህንነት አንደሚመለከተው ጠቅሰው፣ መቋቋሙ እጅግ አስፈላጊነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የተቋቋመበት ዓላማ በሳይበር ደህንነትና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች ከአገር ውስጥ ከውጭም በማሰባሰብ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እንዲያግዙ የሚያደርግ ፕላትፎርም እንዲኖር ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል፡፡
ማህበሩ አሁን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ በሳይበር ደህንነትና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የግንዛቤ ተሳትፎ እንዲኖራቸው እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ ወደ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የገቡት የፋይናንስ፣ የኢንሹራንስ እና የመንግሥት የተለያዩ ድርጅ ቶችን አንድ ላይ በማሰባሰብ በሚቀጥሉት ጊዜያት በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ቴክኖ ሎጂ ፕሮጀክት ውስጥ የሳይበር ደህንነት የማኔጅንመንት ጉዳይ ተቀናጅቶ ለመስራት የሚያስችል አሠራር እንዲኖር እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ማህበሩ ቀደም ሲል የተለያዩ የምክክር መድረኮችን አዘጋጅቶ ነበር፤ አገር አቀፍ የኢስትሪንግ ኮሚቴ ተቋቁሞ በሳይበር ደህንነት ዙሪያ የተለያዩ ድርጅቶች (ኢትዮ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የገንዘብ ሚኒስቴር፣ ገቢዎች ሚኒስቴር እና ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ሌሎችም ተቋማት) የተካተቱበት ምክክር ተካሄዷል፡፡ የጥናትና ምርምር ሥራዎች በተጠናከረ መንገድ እንዲካሄዱና እንዲታተሙ ምክክር ከተደረገ በኋላ ጥሩ ውጤት ተገኝቷል፡፡
እንዲህ አይነት የምክክር መድረኮች ማጠናከር እንደሚገባ ጠቅሰው፣ ይህን በማጠናከር የሳይበር ደህንነትን አስመልክቶ በተለይ ጥናት ላይ የተመሰረቱ ሥራዎች እንዲሰሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ይህም መድረክ ከሁሉም ዘርፍ የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተገኙበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ጥሩ ውጤት እንደሚገኝበት እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን ዓለማየሁ (ዶክተር) ሀገሪቱ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን ለማስተግበር ከጀመረቻቸው አራት መሰረታዊ ጉዳዮች መካከል የመጀመሪያው የዲጂታል መሠረተ ልማት አስቻይ ሥርዓቶችን መዘርጋት መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ውስጥ በዋናነት የሚታየው የሳይበር ደህንነት ፕላትፎርም መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የሳይበር ምህዳር ደህንነት የመጠበቅ ጉዳይ ለማንም የሚተው ሳይሆን ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል፡፡ የዲጂታል መሠረተ ልማት አስቻይ ሥርዓቶችን በመዘርጋት ሂደት የሳይበር ደህንነት ምህዳሩን ለመጠቀም አሁን አገልግሎት እየተሰጡ ያሉት እንደ ዲጂታል መታወቂያ እና ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት አይነት ፕላት ፎርሞች የሳይበር ምህዳሩን መጠበቅ ካልተቻለ አደጋ ላይ ይወድቃሉ።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ሌላው ኢ ገቨርንመንት፣ ኢ ሰርቪስ እና ኢ ኮሜርስን የመሳሰሉት የዲጂታል ፕላትፎርሞች የሳይበር ምህዳሩ ጤናማ ካልሆነና ችግር ካለበት ደህንነታቸው በሚገባ ተጠብቆ ታአማኒ በሆነ መንገድ ሊካሄዱ አይችሉም፡፡ የሳይበር ደህንነት መጠበቅ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህም አንጻር እያንዳንዱ በመንግሥት፣ በግሉ ዘርፍ፣ በማህበራት በምርምር ተቋማት እና፣ በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የሚሰሩ ሥራዎች ተደምረው እንደ አገር ትልቅ አቅም ይፈጥራሉ፡፡
በኢንስቲትዮቱ መገንባትና አቅም በመፍጠር ረገድ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳዳር የሚሰሩ ብዙ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቅሰውም፤ የዲጂታል ዘርፉን የሚመራው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በሚባል ደረጃ ሁሉንም ዘርፍ በመደገፍ እንደ አገር በዲጂታል፣ በሳይበር፣ በአይሲቲ እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ላይ ድጋፍ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2016 ዓ.ም