ከፍታችን ከሀገር ለመቀበል ሳይሆን ለሀገር በመስጠት ውስጥ የሚመጣ ነው

ሀገር የግለሰቦች የሀሳብ፣ የአብሮነት፣ የምክክርና የአብሮ መቆም ውህድ ናት፡፡ ሀሳብና አብሮነትን በቀየጠ በዚህ የሰው ለሰው መስተጋብር ውስጥ የምንፈልጋትን ሀገር መፍጠር እንችላለን። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ሀገራችን ከእኛ፣ እኛም ከሀገራችን የምንፈልገው ነገር አለ፡፡

ይሄ መሻት የሰጥቶ መቀበል ወይም ደግሞ ‹GIVE AND TAKE› የሚለውን ሳይንሳዊ እሳቤ የታከከ ነው፡፡ አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ሀገራችን ከእኛ ምንድነው የምትፈልገው ብሎ መጠየቅ? ለጋራ መጠቃቀሙ የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው፡፡ ሀገራችን ምን እንደምትፈልግ ካልጠየቅንና ካልመለስን፤ በተዘዋዋሪ እኛ ምን እንደሚያስፈልገን አልተረዳንም ማለት ነው፡፡

በዚህ ሀሳብ ውስጥ የሚገለጸው ደግሞ የሀገር ፍላጎት የሕዝብ ፍላጎት ነው፡፡ የሀገር መሻት የትውልዱ ዋነኛ ጥያቄ ሆኖ የሚገለጽ ነው፡፡ ለዚህ ሀገርና ሕዝብን አቅፎ ለያዘው የጋራ ጥቅም እንደቅድመ ሁኔታ የሚወሰደው ‹ሀገር ከዜጎቿ ምን ትሻለች?” የሚለው፤ ወይም ደግሞ ከፍ ብዬ እንደገለጽኩት ባለው ወቅታዊ ሁኔታ “የሀገራችን መሻት ምንድነው?” የሚለው ይሆናል፡፡

ይሄ ጥያቄ ደግሞ “ሀገሬ ለእኔ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን እኔ ለሀገሬ ምን አደረኩላት?” የሚለውን የአሜሪካውን የቀድሞ ፕሬዝዳንት የጆሴፍ ኬኔዲን አባባልና ፍልስፍና ታኮ የሚመጣ ይሆናል፡፡ ከዚህ አኳያ ስለሀገርና ሕዝብ ከተነገሩና እውነትነት ሆነው ከፊት ከተቀመጡ አባባሎች ውስጥ ቀዳሚው ‹ሀገሬ ለእኔ ሳይሆን እኔ ለሀገሬ ምን አደረኩ? ብሎ መጠየቅ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ የታመነ ነው፡፡

ብዙዎቹ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ብሎም በሕዝባዊ አንድነት ሀያልነትን የገነቡ ሀገራት ባልዳበረ ተፈጥሮ ሀብትና በውስን የሰው ኃይል እንዴት ገናናነትን አገኙ ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው የመጀመሪያ መልስ ከሀገር የሚቀበሉ ሳይሆኑ ለሀገር የሚሰጡ መሆናቸውን ነው፡፡ ከሀገር መቀበልና ለሀገር መስጠት አንድ የሚመስል ግን ደግሞ እጅግ የሰፋ ልዩነት ያለው አስተሳሰብ ነው፡፡

እናም ይሄ በቀድሞውም ሆነ አሁን ባለው ትውልድ መካከል የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የሉአላዊነት፣ የዲፕሎማሲ ልዩነትን የፈጠረ አስተሳሰብ ነው፡፡ ያለመጠራጠር አሁን ላለው ዓለም እድገትና ስልጣኔን የሰጠና የነጠቀ የሁለት ጎራዎች የተለያየ ምልከታ ነው፡፡ ብዙ ሀገራት ከራስ በፊት ሀገርን በማስቀደም፣ ከራስ ፍላጎት የሕዝብን ፍላጎት በማስቀደም ከሰጪነት ወደ ተቀባይነት ዞረዋል፡፡ በተቃራኒው እንደ እኛ ያሉ ሀገራት ከሀገር በፊት ራስን ባስቀደመ ፖለቲካና ማኅበረሰባዊ ልምምድ ያልሰጠነውን ለመቀበል እጃችንን የዘረጋን ነን፡፡

ዋናውና መሀሉ ሀገር በመገንባት ሂደት ውስጥ ከፊት የሚመጣው ልዩነት ይሄ ነው፡፡ ያልሰጡትን መጠበቅ ለድህነትና ለኋላ ቀርነት ብሎም ለተቃርኖ መንገድ የሚከፍት የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ወድቀን ሀገራችንን ስንተች፣ ያለፈውን ስንወቅስ መጥተናል፡፡ ለአለውና ለሚኖረው ምቹና አስፈላጊዎች መሆን አቅቶን፣ ሰጥቶ ከመቀበል ይልቅ ተቀብሎ ለመስጠት የተሰለፍን ነን፡፡

በዚህ ይሄ ተቀብሎ የመስጠትን እንጂ የሰጥቶ መቀበልን መርህ እሳቤ ላይ አደገኛው ነገር የአመለካከት ክፍተቱ ብቻ ሳይሆን፤ በልምምድ የመጣ የረጅም ጊዜ ሂደት መሆኑም ነው፡፡ በሁሉም መስክ ላይ ማለት ይቻላል ከእኛ ምን እንደሚጠበቅ አለማወቃችን ሀገራችንን ያቀነጨረ ድርጊት ነው ባይ ነኝ፡፡ የሀገር እድገት፣ የማኅበረሰብ ለውጥ የሕዝብ ሀሳብና ድርጊት የተውጣጣበት ነው፡፡ ጥያቄችን ሰላም ከሆነ፣ ለልማትና ለአንድነት ጽኑ መሻት ካለን ለነዛ የሚሆን የሀሳብና የአብሮነት ልዕልና ልናዳብር ይገባናል፡፡

የሀገር ሰላም የእኔና የእናንተ ተግባቦትና ምክክር ነው፡፡ ልማትና እድገትም ከእኛው በእኛ የሚመጣ እንጂ በተዐምር የሚሆን አይደለም። በእኔ ምልከታ እስካሁን ድረስ ለሀገራችን የሰጠናት ነገር የለም፡፡ ሆኖም ያልሰጠነውን ለመቀበል የሌለንን ለመውሰድ ግን በብዙ ትችትና ሙግት የቆምን ነን፡፡ የአሜሪካንን የታሪክና የስልጣኔ ሰነድ ብታገላብጥ በወርቅ ቀለም ደምቆ የምታገኙት የመጀመሪያው እውነት እኔ ለሀገሬ ምን አደረኩ? የሚል ጥያቄ ያዘለ ግን ደግሞ ለሁሉም ሕዝባዊ መሻት መልስ የሚሰጥን እውነታ ነው፡፡

ይሄ እሳቤ ማንንም ከምንምነት የሚያነሳ፣ ከብርቱ እጆችና ከበሳል ጭንቅላቶች በላይ ኃይል ያለው ነው፡፡ የቱንም ያህል በርትተን የምንሰጠው ሳይኖረን ጠባቂዎች ብቻ ከሆንን ኃይላችን ትርጉም አይኖረውም፡፡ የሰጥቶ መቀበል መርህ ከገባን ግን ምንም ያክል ተስፋቢሶች ብንሆን ያለንን በመስጠት፣ የሚጠበቅብንን በማድረግ ሂደቱን መጠበቅ እንጀምራለን፡፡ አሁን ባለው የሀገራችን ነባራዊ አውድ ስር እንደሰላምና ልማት ያሉ የሚነሱ ብዙ ሕዝባዊ መሻቶች አሉ፡፡ እኚህ መሻቶች የጋራችን ከመሆናቸው እኩል በጋራ የሚተገበሩ የጋራ ውጤቶች እንደሆኑ ሊገባንም ይገባል፡፡

ፍላጎታችን ሰላም ከሆነ ለሰላም የሚሆኑ ሀሳቦችን ከማመንጨት ጀምሮ ለተግባቦትና አብሮ ለመስራት ራሳችንን ማዘጋጀት ቀዳሚውና ለሀገር ሰጥተን ከሀገር የምንቀበለው የሰላም መሻት መሆን ይችላል፡፡ ፍላጎታችን የፖለቲካ ጉዳይ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ጥያቄ ከሆነም መጀመሪያ ከእኛ የሚጠበቅ ለውይይትና ለምክክር ልብና አእምሮውን መክፈት ፊተኛው ሀቅ ነው፡፡ ሰጥቶ መቀበል ማለት በልዩነቶቻችን ላይ የበላይ መሆን ማለት ነው፡፡ ትናንሽ የሀሳብ፣ የታሪክ ልዩነቶች እንዳያቃቅሩንና ወደጦርነት እንዳይወስዱን ሰላም አመንጪ በሆነ ሀሳብ ማጥበብ ማለት ነው፡፡

የትኛውም ሕዝባዊ ጥያቄ በሰጥቶ መቀበል መልስ ማግኘት ይችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክክር ቀዳሚው መሳሪያ ሲሆን፤ ይሄን እንዲከውን የተሰየመው ብሄራዊ ምክክር ኮሚሽንም ላለፉት ዓመታት ሰላምና አብሮነትን ማዕከል ባደረገ መልኩ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ከኮሚሽኑ ዓላማዎች ውስጥ አንዱ በሰጥቶ መቀበል የተበላሹ ትርክቶችን ማስተካከል፤ ያደፉ ታሪኮችን ማጽዳትና የተጣመሙትን ማቃናት ይገኝበታል፡፡

ይሄን ዓላማ ሰንቆ ስራውን እውን ሲያደርግ ደግሞ በእርቅና በይቅርታ ከምንም በላይ ደግሞ በኢትዮጵያዊነት ወግና ልማድ የነበረንን የአብሮነት ትስስር የመመለስ ግብ አለው፡፡ ሂደቱ ሰጥቶ መቀበል የጎላበት ለመሆኑ እንደማሳያ የሚነሳው የሀሳብ ቅብብሎሽ፣ ነጻ መድረክና ገለልተኛነት ያለው መሆኑ ነው፡፡ ሀገርን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሀሳብ ሰጥተን ሀሳብ ስንቀበል፣ የእርቅና አስታራቂ ሀሳቦችን ስናቆራኝ የበለጠ እንድንሰጥና የበለጠ እንድንቀበል ተአማኒነትን ይፈጥርልናል፡፡

እናም መልካም እሴቶችን ስናጎላ፣ የቀደሙ የኅብረብሄራዊ ገድሎቻችንን ስንዘክር፣ አብሮነታችንን ስናውጅ ለሀገር እየሰጠን ነው፡፡ ተምረን ለቁም ነገር ስንበቃ፣ ወልደን ስንስም፣ ሰርተን ስንከብር፣ በፍቅርና በአብሮነት ስንጠያየቅ በምትኩ ሀገር እየሰጠችን ነው፡፡ ይሄ እውነታ በአንድ ቃል ቢገለጽ ሰጥቶ መቀበል ይሆናል፡፡ ለሀገራችን የሰጠናትን ሀገራችን መልሳ ሰጠችን ማለት ነው፡፡

በየትኛውም ሀገር ሰጥቶ መቀበል አንድ አይነት ትርጉም ነው ያለው፡፡ እየሞትንና እየገደልን፣ እየሰረቅንና እያጭበረበርን፣ እየተገፋፋንና እየተጠላላን ሀገራችን የምትሰጠን ሰላም የላትም። በቂምና በቀል፣ በዘርና በብሄር ተቧድነን ሀገራችን የምትሰጠን ወንድማማችነት የለም። ያንጸባረቅነው ነው የሚንጸባረቅልን፡፡ ሀገር ማለት ሰው ነው የሚለው አባባል ከዚህ እውነታ የተጸነሰ ነው፡፡ የምንፈልገው በእኛ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ለምንፈልገው የሚሆን ትስስርና ቁርኝትን ከፈጠርን ይሆንልናል፡፡ ያቃተን ለምንፈልገው ነገር ዋጋ መክፈል ነው፡፡ ያልቻልነው በመነጋገር የሚያግባቡንን ሀሳብና ተግባቦት መፍጠር ነው፡፡

የሆነው፣ እየሆንን ያለውና ወደፊትም የምንሆነው እርሱ ነው፤ እጣ ፈንታችን፡፡ የነበረውን ካስታወስን ለዛሬ ሰላም እና አንድነት ማጣታችን ቁርሾ የተቀመጠበት፣ ትርክት የተተረከበት እንደሆነ ማስታወስ ይቻላል፡፡ እየሆንነው ያለውን መዘከር ካስፈለገ ደግሞ በትላንት ትርክቶች ዋጋ እየከፈልን ያለንበትን ሁኔታ ማስታወስ ሌላው እውነታ ነው፡፡ ወደፊት የምንሆነውም እጣ ፈንታችን ወሳኝ ሆኖ ከፊት የሚቀመጥ ነው፡፡ ወደመፍትሄው ከመጣን ትላንትን በዛሬ መሻር ነገን በአሁን ማቅናት የሚል ይሆናል፡፡

ትላንትን በዛሬ መሻር አሁን ላሉብን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ ምስቅልቅሎች እልባት የሚሰጥ የመፍትሄ አቅጣጫ ነው፡፡ ትላንትን በዛሬ ካልሻርን ነገን የጋራችን፣ ነገን የኢትዮጵያ ማድረግ አንችልም፡፡ በመጣንበት የዘርና የጎሳ ክፍፍል፣ በእኔ እና በየአንተ ንትርክ ትውልዱን ሀገር እና ወገን እናሳጣዋለን፡፡ ይሄ ደግሞ በራስ ላይ እሳት እንደማንደድ የሚቆጠር በሀገር ላይ የሚያስጨክን ድርጊት ነው፡፡ ራሳችንን ነጻ በማውጣት ለሕዝብና ለትውልድ የምንተርፈው ከእዳ ወደ ምንዳ፣ ከፈተና ወደልዕልና፣ ከአንባጓሮ ወደአብሮነት በሚወስድ የእርስ በእርስ ጎዳና ላይ ስንቆም ነው፡፡

ዛሬን የትላንቱን በይቅርታ ለማለፍ፣ ነገን ፍቅር ለመቀበል፣ የእርቅና የአብሮነትን ለማጽናት የሚያስችል የትስስር ቀናችን አድርጎ መቀበል ይገባል፡፡ ይሄ ስለሰላም፣ ስለአብሮነት የተሻለው መንገድ ነው፡፡ እንዲህ ካልሆነ ለአብሮነታችን አቅም የሚፈጥር ሌላ ነጻ አውጪ ኃይል አናገኝም፡፡ በትላንት ቁርሾ ዛሬን መገፋፋት፣ ለነገ ስቃይ ማስቀመጥ የሚበቃን ጊዜ ላይ ነን፡፡ ስቃይ በሰላም ካልዳነ፣ በቀል በይቅርታ ካልሻረ፣ ጥላቻ በፍቅር ካልታከመ ለሀገራችንም ሆነ ለሌላው ሰጥተን የምንቀበለው አንዳች አይኖረንም፡፡ ጣት በመጠቋቆም ወደነገ ከመሄድ ባለፈ መዳኛ አይሰጠንም፡፡ አንዲት ክፉ ትርክት በጊዜ ካልታከመች እየሰፋችና እየበዛች ከዘመን ዘመን የመሄድ ጉልበት አላት፡፡ ልክ እንደዚህ በጎ ታሪኮችም ጠባሳ ማጥፊያ፣ ሰንበር ማከሚያ ሆነው መጽናናትም መሆን ይችላሉ፡፡

ነገር እያቦካን ብንጋግር ለጥቂቶች ጥጋብ፣ ለብዙሀኑ ደግሞ የሞት ህብስት ነው የሚሆነው። ጥላቻ ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ ነው፡፡ በእርቅ ካልሆነ በምንም እንዳይረግብ ሆኖ የተቀመጠ እንጦሮጦስ ነው፡፡ ይሄ እውነታ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ጥቁር ጠባሳን ከሚተው መጥፎ አጋጣሚዎች ጋር ምስስል ነው፡፡ ማገገሚያችን ውይይትና የጋራ ትርክቶች ናቸው፡፡ ተወያይቶ መግባባት፣ ስለሰላም ዋጋ መክፈል፣ ስለአብሮነት እርባና ያላቸውን ትርክቶች መፍጠር፣ የፖለቲካውን ምህዳር ማስፋት፣ ከአሉባልታና ከትችት ወንበር ስቦ መነጋገር ይሄ ነው እኔ ለሀገሬ ምን አደረኩላት ማለት፡፡

ጨለማው ላይ ብርሀን ሳናበራ ስለጨለማው ብናወራ ምን ይጠቅመናል? እንዴት መጣ? ማን አመጣው? ለምን መጣ? እና ከየት መጣ? የሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ሳንመልስ ወደ መፍትሄው ብናተኩርም ትርጉም የለውም፡፡ አንድ ችግር ከስሩ እንዲነቀል ምንጩ መታወቅ አለበት። ችግሮቻችን እንዲረግቡ ምንጫቸውን ማወቁ ቀዳሚው ርምጃ ነው፡፡ ጨለማችን ላይ ብርሀን የምንረጨው እንዲህ ባለው መንገድ ነው፡፡ ጨለማችን ላይ ብርሀን መዝራት አቅቶን ሁልጊዜ ስለጨለማው ብናወራ ትርጉም የለውም፡፡ የሰጥቶ መቀበል ወይም ደግሞ እኔ ለሀገሬ ምን አደረኩ የሚለው ጽንሰ ሀሳብ ነፍስ የሚዘራው ጨለማው ላይ ማተኮራችንን ትተን ጨለማው የሚገረሰስበትን ብርሀናማ የመፍትሄ አማራጭ ስንፈልግ ነው፡፡

እኔ ለሀገሬ ምን አደረኩ? የሚለው ንግግር ዓለም ላይ ከታዩ የለውጥና የተሀድሶ እሳቤዎች ቀዳሚው ነው፡፡ ብዙዎች በዚህ ፍልስፍና በኩል በትውልዱ ላይ ንቃትን በመፍጠር ታሪኮቻቸውን አድሰዋል፡፡ እኛም ከችግሮቻችን ተላቀን ወደፊት እንድንራመድ ከዚህ የተሻለ የንቃትና የብርታት ምንጭ እንደሌለን ስናገር ባለው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ላይ ተመስርቼ ነው፡፡ ለሌላቸው ያለንን በመስጠት ካላቸው የሌለንን መቀበል እንችላለን፡፡

ከሀገር መቀበል ሰጪነት የሌለው ጠባቂነት ነው፡፡ ያልሰጠነውን ለመቀበል መጠበቅ ምን አይነት ስሜት እንዳለው አይጠፋንም፡፡ ይሄ እውነታ አሁን ያለነውን እኛንና ሀገራችንን የሚገልጽ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ ብዙዎቻችን ያልሰጠነውን የምንጠብቅ ነን፡፡ ሀገሬ ለኔ ምን አደረገችልኝ? በሚል ቅደም ተከተሉን በሳተ መጠየቅ መንግስትን የምንተች፣ ማኅበረሰቡን የምንወቅስ ወቃሾችና ተቺዎች ነን፡፡ ለመቀበል መስጠት ይቀድማል፡፡ ያለንን በጎ ነገር በመስጠት የሌለንን በጎ ነገር ማግኘት ይቻላል መቋጫ ሀሳቤ ነው፡፡

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2016 ዓ.ም

Recommended For You