ኢትዮጵያ በዋጋ የፀናች፤ በመስዋዕትነት የዘለቀች፤ በሕዝቦች ዘርፈ ብዙ ተጋድሎ ከፍ ያለ ስምና ዝናን የተጎናጸፈች ሀገር ናት፡፡ ምድረ ቀደምትነቷ፤ የነፃነትና ሉዓላዊነት ገጿ፤ የእኩልነትና ኅብር መልኳ፤… የተሳሉት በሕዝቦቿ ብርቱ ጥረትና ትጋት፤ በጀግኖቿ ከፍ ያለ መስዋዕትነት ታግዞ ነው፡፡
ይሄ ስምና ዝና፤ ነፃነትና ክብር፤ በጥቅሉም የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ገድል ታዲያ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም በአያሌ ፈተናዎች የታጀበ ስለመሆኑ እሙን ነው፡፡ በተለይ በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ዘመኑን መስላና ከዘመኑ እውነታ ጋር ተላምዳ ለመሻገር፤ ክብርና ነፃነቷንም በዛው ልክ ለማዝለቅ በምታደርገው ሂደት ውስጥ አያሌ ፈተናዎችን መጋፈጧ የግድ ሆኗል፡፡
ዛሬ ዛሬ ከሀገር ይልቅ ክልልና መንደር፤ ከሕዝብ ይልቅ ብሔርና ቡድን የሚያስጨንቃቸው፤ ሆዳቸው ክብራቸው የሆኑ ኃይሎች እዚህም እዚያም እያቆጠቆጡ ይገኛል፡፡ እነዚህ ኃይሎች ደግሞ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር፤ ኢትዮጵያውያንም እንደ ሕዝብ በሚያደርጉት የሠላም፣ የልማትና የሁለንተናዊ ብልጽግና እውን መሆን ሂደት ላይ ከፍ ያለ ጥላን ማጥላታቸው አይቀርም፡፡
ከዚህ አኳያ ሕዝቦች የኢኮኖሚ ነፃነት ናፍቀው ልማትና ሁለንተናዊ ብልጽግናቸውን እውን ለማድረግ በሚተጉበት በዚህ ወቅት፤ ጦርነት እና ግጭትን አማራጭ ያደረጉ እኩያን ተበራክተው ይታያሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች ደግሞ ሠላም አይጥማቸውም፤ ምክንያቱም የሚያተርፉት ከግጭትና ጦርነት ስለሆነ፡፡
ለዚህም ሲሉ በሕዝቦች መካከል መቃቃርን ለመፍጠር ይሠራሉ፤ ቂምና ቁርሾን ያስፋፋሉ፤ የበዳይና ተበዳይነት እሳቤን ለማስረጽ ይተጋሉ፡፡ በዚህም፣ ሕዝቦች ቅሬታ እንዲሰማቸው፤ የተበዳይነት ስሜት እንዲፈጠርባቸው፤ ከልማት ሂደቱ የራቁ ሆነው እንዲሰማቸው የሚያደርጉ አያሌ ተግባራትን ይፈጽማሉ፡፡
እናም የመሠረተ ልማቶችን ከማውደም ጀምሮ የዜጎችን ሃብት ንብረት የመዝረፍ፣ ዜጎችን የማፈናቀል፣ በዜጎች ላይ የአካልም የሕይወትም ጥቃት የማድረስ ክፋታቸውን ይገልጣሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ዜጎች ሠላምና ደኅንነት እንዳይሰማቸው፤ ፍቅርና አብሮነት እንዳይኖራቸው፤ ከመንግሥት ጋርም ወደ አለመተማመን እንዲገቡ እና የእነሱን እኩይ ሃሳብ እንዲላበሱ ማድረጊያ ስልታቸው ነው፡፡
ይሄ የሀሳብም፣ የተግባርም መንገድ ደግሞ ሀገርንም፣ ሕዝብንም ዋጋ እያስከፈለ፤ መንግሥትም በሙሉ አቅሙ ወደ ልማት ሥራዎች እንዳያተኩር እያደረገ ይገኛል፡፡ ለዚህም ነው በአንድ በኩል ሰላም በማስከበር፤ በሌላ በኩል የልማት ተግባራትን በማከናወን ሁሉን አቀፍ ጥረት እየተደረገ ያለው።፡
እነዚህን የሕዝብን ሠላም እና ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመንግሥት ለሚከናወኑ ሥራዎች አቅም ከመሆን አኳያ ደግሞ በርካታ አካላት የማይተካ ዋጋ እየከፈሉ ይገኛሉ፡፡ የፀጥታ አካላት፣ ባለሃብቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ ምሑራን፣ እና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት በዚህ ረገድ ከፍ ያ ለ ሥራን እየሠሩ መሆኑ እሙ ን ነው፡፡
ለምሳሌ፣ የፀጥታ ኃይሎች ሚና ሲታይ፤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር፣ ኢትዮጵያውያንም እንደ ሕዝብ ነፃና ሉዓላዊ ሆነው፤ ሠላማቸው ተጠብቆ በሙሉ የደኅንነት ስሜት ወደ ልማታቸው እንዲያተኩሩ የማድረጉን ከፍ ያለ ድርሻ እየተወጡ ይገኛል። በዚህ በኩል የመከላከያ ሠራዊቱ፣ የደኅንነት ተቋሙ እና የፖሊስ ኃይሉ ቀዳሚ ናቸው፡፡
እነዚህ አካላት፣ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ሕልውና እና ሁለንተናዊ ብልጽግና ተኪ የሌለው ሕይወታቸው እስከመስጠት የሚደርስ ዋጋን እየከፈሉ የኖሩ፤ የሚኖሩም ናቸው፡፡ በተለይ የመከላከያ ሠራዊቱ ከቤት ወጥቶ፣ ከቤተሰቡ ርቆ፣ በዱር በገደሉ ውሎ እያደረ፤ ብርድና ሓሩሩ ሳይበግረው፤ ጋራና ሸንተረሩ ሳያዝለው ለሀገሩ ክብር፣ ለሕዝቡም ደኅንነት እየከፈለው ያለው ዋጋ ከማንም ልብና አዕምሮ የሚፋቅ አይሆንም፡፡
ለዚህም ነው፤ የመከላከያ ሠራዊቱ መልኩ ኢትዮጵያዊ፣ ገጹም ኢትዮጵያ ነው የሚባለው፡፡ ለዚህም ነው መከላከያ ሠራዊቱን መደገፍ፣ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን መቆም፤ ኢትዮጵያን እንደ መደገፍ፣ ከኢትዮጵያ ጎን እንደመቆም የሚታየው፡፡ ምክንያቱም ይሄ ኃይል ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ሲል የሚሰስተው አንዳችም ዋጋ የለምና ነው፡፡
ከሰሞኑ በመከላከያ ሠራዊት እውነተኛ ታሪክ ላይ ተመሥርቶ “ስለ እናት ምድር” የተሰኘ ፊልም ተመርቋል፡፡ ይሄ ፊልም ደግሞ ከበዛው የመከላከያ ሠራዊቱ ተጋድሎና የልዕልና መገለጫዎች መካከል በወፍ በረር ለማሳየት የተሞከረበት እንጂ፤ ሙሉ እሱነቱን ያሳያል ተብሎ የሚወሰድ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ሁነቱ ውቅያኖስን በጭልፋ እንደማለት ነውና፡፡
ለምሳሌ፣ የመከላከያ ሠራዊቱ ባለፉት ዓመታት አያሌ ተጋድሎዎችን ፈጽሟል፤ በዚህ ረገድ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የፈጸመው ገድልና ሥነምግባር የተሞላበት ተግባር ተጠቃሽ ነው፡፡ በዛው ልጅ የጦር አቅሙንም ገንብቷል፡፡ ዛሬም ቢሆን በዚሁ መልኩ ተጋድሎውን እየፈጸመ፤ አቅሙንም እያሳደገ ያለ ተቋምና ሠራዊት ነው፡፡
ለዚህም ነው፣ በፊልሙ ምርቃት ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የተመረቀው ፊልም እዚሁ የመከላከያ ሠራዊቱ ተግባር ላይ የተመሠረተ ስለመሆኑ ከመግለጽ ባሻገር፤ መከላከያ ሠራዊቱ የኢትዮጵያ ሠላምና ደኅንነት የመጨረሻው ምሽግ ስለመሆኑ አፅንዖት ሰጥተው፤ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር መቆም፣ ከኢትዮጵያ ጋር መቆም መሆኑንም የተናገሩት፡፡
መከላከያ ሠራዊትን የመሰሉ ሁሌም ታሪክ የሚሠሩ ኃይሎች ደግሞ፣ ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ሲሉ ዋጋ የሚከፍሉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ኃይሎች ጎን መቆም እና አብሮ መሥራት ደግሞ ከኢትዮጵያ ጎን መቆምና ለኢትዮጵያ መሥራት ከመሆኑም ባሻገር፤ ከፍ ያለ ክብርን የሚያጎናጽፍ ሠናይ እሴትም ነው፡፡ እናም ስለ ኢትዮጵያ ሲባል ለኢትዮጵያ ዋጋ ከሚከፍሉት ጋር መተባበር ይገባል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 17 ቀን 2016 ዓ.ም