በከተማዋ 300 ኪሎ ሜትር የውሃ ማፋሰሻ ቱቦዎች ፀድተዋል

አዲስ አበባ፡- በመዲናዋ 300 ኪሎ ሜትር የመንገድ ዳር ውሃ ፍሳሽ ቱቦዎችን የማስተካከልና የማፅዳት ሥራ መከናወኑን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ።

የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ ሰሎሞን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የ2016 በጀት ዓመት በተጠናከረ ሁኔታ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችን የመጠገንና የማጽዳት ሥራ እየሠራ ይገኛል።

በመዲናዋ የውሃ ማፍሰሻ ቱቦዎች በቆሻሻ መደፈናቸውን ተከትሎ በዝናብ ወቅት ፍሳሽ ወደ መንገድ ላይ እንደሚፈስ አስታውቀው፣ እስካሁን 300 ኪሎ ሜትር የፍሳሽ ማስወገጃዎችን የማፅዳት፣ የመጠገንና በአዲስ የመተካት ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል።

የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው እንደገለጹት፤ ባልተገባ የመንገድ አጠቃቀም ምክንያት የመንገድ ቱቦዎች በበልግ ወቅትና በክረምት ዝናብ በሚዘንብባቸው ጊዜ ይደፈናሉ። በዚህም ከመጠገንና ከማጽዳት ሥራው በተጨማሪ የፍሳሽ ውስጥ ለውስጥ መንገዶቹን የመፈተሽ ተግባር የሚሠራ ሲሆን፤ አሁንም ሥራው እንደቀጠለ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

አቶ እያሱ እንደገለጹት፤ ድልድዮች አካባቢ በተለይ በግንባታ ተረፈ ምርቶች የጎርፍ ማመላለሻ ቱቦዎች ይደፈናሉ። የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት፤ መሥሪያ ቤቱ ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎች በመለየት እየተሠራ ይገኛል።

በዚህም ከእሳትና አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በኩል ተለይተው የተሰጡ ቦታዎችን ባለፈው ዓመት ተጀምረው ያልተጠናቀቁትን እና አዳዲስ አካባቢዎች ላይ እየተሠራ ይገኛል ሲሉ አስረድተዋል።

እንደ አቶ እያሱ ገለጻ፤ ለመንገድ መደፈኑ ሌላው ምክንያት፤ ነዋሪዎች የመንገድ ቱቦዎቹን ከተሠሩበት ዓላማ ውጭ ስለሚጠቀሙበት ነው።

ነዋሪዎቹ ወደ ጎርፍ ማፋሰሻ ቱቦዎች ደረቅ ቆሻሻ ከመጣል እንዲቆጠቡና በተቻለ አቅም በአከባቢያቸው የሚገኙ የውሃ ማስተላለፊያዎችን እንዲያፀዱ አቶ እያሱ አሳስበዋል።

በየአካባቢው የሚገኙና የተፀዱ ቱቦዎች ዳግም እየተበላሹ በመሆኑ ይበልጥ ውጤታማ መሆን እንዳልተቻለ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በክረምት ወቅትና በሌሎች ወቅቶች የመበላሸት አደጋ የገጠማቸው መንገዶች መጠገናቸውን ተናግረው፤ እስካሁን ድረስ ባለው ሂደት ከ64 ኪሎ ሜትር በላይ ጥገና ተከናውኗል ሲሉ ገልጸዋል።

በመጨረሻም ኅብረተሰቡ የሚሠሩትን የውሃ ማፍሰሻ ቱቦችንና መንገዶችን በባለቤትነት ስሜት ሊጠቀም ይገባል ሲሉ መልክት አስተላልፈዋል።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን  መጋቢት 17 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You