በቤት ውስጥ እናቶችም ሆኑ ወጣት ሴቶች ከተለያዩ ግብዓቶች ጋር በመቀላቀል ሒናን ጸጉራቸውን ይቀባሉ። አገልግሎቱም እናቶች በጸጉራቸው ላይ ብቅብቅ ያሉ ሽበቶችን ለማጥቆር የሚጠቀሙ ነው። የጸጉር ቀለም መቀባት ያልፈለጉ ሴቶች ሒናን ምርጫቸው ያደርጋሉ። ነገር ግን ሒና ውስን የሆነ ጥቁርና በርገንዲ የምንለውን የቀለም አማራጭ ብቻ የያዘ ነው። በተለያዩ ሰዎች ዘንድ ጥቁር የጸጉር ቀለም የምንጊዜም ተመራጭ ፋሽን ነው። ከዛ ውጭ ያሉ የቀለም ዓይነቶችን ምርጫቸው የሚያደርጉም አልጠፉም። አሁን ላይ የተለያየ ዓይነት የተቀመሙ የጸጉር ቀለሞች በውበት ሳሎኖች ውስጥ ይገኛሉ።
በጸጉር ሥራ ሙያ ከ13 ዓመት በላይ የቆየ ልምድ አለው። ወጣት ነው፤ ሙሉዓለም አሸናፊ ይባላል፤ አሁን ላይ ከባለቤቱ ጋር በመሆን በአምስት ኪሎ ብሔራዊ ሙዚዬም አካባቢ ‹‹ፒንክ›› የተሰኘ የውበት ሳሎን ውስጥ የሚሰጡ የሹሩባ የጸጉር ሥራ፣ ጥፍር መሥራት፣ የእጅ እና የእግር ፔዲኪዩር እና ሜኒኪዩር አገልግሎቶችን ይሰጣሉ። ሙሉዓለም ሙያውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሠርግ የሙሽራ ሥራዎችን ፍሸና የምንለውን ሜካፕንም ጨምሮ ይሠራል። የጸጉር ቀለም መቀባት ሙያን በፕሮፌሽናል ደረጃ ከጀመረ ከሰባት ዓመት በላይ እንደሆነውም ይናገራል።
‹‹ከዚህ ቀደም የነበረው የጸጉር ቀለም ግብዓት ትንሽ በመሆኑ ፋሽኑም ብዙ አልነበረም። አሁን ግን በደንብ እየታወቀ እና ሌሎች ሀገራት ላይ ያለው ፋሽን እኛ ሀገር እየመጣ ነው›› በማለት የወቅቱን የቀለም ፋሽን ይገልጸዋል። ለዚህ እንደ ምክንያት የሚነሳው ደግሞ በአሁን ሰዓት በሀገራችን ያለው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በብዙዎች ዘንድ እየተለመደ በመምጣቱ ሰዎች በጸጉር ቀለም እና በፋሽን ዙሪያ በየጊዜው የሚተዋወቁ አዳዲስ ፋሽኖችን ቶሎ ቶሎ የማየት እድሉ ስላላቸው መሆኑን ያነሳል።
አንዲት እንስት ጸጉሯን ቀለም ለመቀባት ስትመጣ ምናልባትም በእጅጉ ራሷን ሙሉ በሙሉ የሚቀየራት ወይንም አዲስ እይታ የሚፈጥርላትን ውሳኔ ነው የምትወስነው። ታዲያ ሙሉዓለም የጸጉሯን ቀለም ለመቀየር የመጣችን እንስት የመረጠችውን ቀለም ከተመለከተ በኋላ ከእርሷ የጸጉር ባህሪ ጋር እንዲሁም የፊቷ ቀለም ጋር ‹‹ይሄዳል አይሄድም›› የሚለውን እንደ ባለሙያ ያማክራታል።
‹‹ስለ ጸጉር ቀለም እውቀት ኖሯቸው የሚቀቡትን ቀለም ምንነት አውቀው የሚመጡ ሴቶች 10 በመቶ የሚሆኑት ናቸው›› የሚለው ሙሉዓለም አንዳንድ እንስቶች ደግሞ በሚኖርባቸው የተጣበበ የሥራ ጊዜ ምክንያት ጸጉራቸውን ባለመንከባከባቸው ምክንያት በቀላሉ መጠቀም እንዲችሉ ጸጉራቸውን ቀለም ለመቀባት ወደ ውበት ሳሎኑ ጎራ እንደሚሉ ይናገራል። የጸጉር ቀለም ኢንዱስትሪም በየሁለት እና በየሶስት ዓመቱ እንደሚቀያየር በማንሳት አንዲት ሴት በዓመት አንድ ጊዜ የጸጉሯን ቀለም የመቀየር ፍላጎት ሊኖራት እንደሚችል ይገልፃል።
የጸጉር ቀለም መቀባት ከፋሽን በዘለለ ጸጉር በራሱ ለአንዲት ሴት መገለጫዋ ነው። ታዲያ የጸጉር ቀለም መቀባት ያሰበች እንስት የሚቀባትን ባለሙያ መምረጥ ፣ የቀለሞቹን ጥራት መመልከት ጸጉሯን ቀለም ለመቀባት ስታስብ ትኩረት መስጠት ያለባት መሆኑን ባለሙያው ሙሉዓለም አንስቷል።
ኢትዮጵያውያን ላላቸው የቆዳ ቀለም ጠቆር ያለ መልክ ያላቸው እና ሙሉ ለሙሉ ያልተሸፈነ የጸጉር ቀለም (Dark shade) እንዲሁም አለፍ አለፍ ተብሎ የተቀባ የጸጉር ቀለም (Highlight) ተለምዷል። በሁለተኛው የቀለም ዓይነት ውስጥ ወደ 12 የሚጠጉ የአቀባብ መንገዶች አሉ። በሀገራችንም ሚዲዬም ላይት፣ ሀይላይት፣ ሎው ላይት የሚባለው በብዛት ይመረጣል፣ ሌላኛው የቀለም አቀባብ ዓይነት ኦምብሬ ወይንም በተለምዶው ስግስግ የሚባለው ነው። ጸጉርን ቀለም በመቀባት ሒደት ውስጥ የመጀመሪያው ሥራ እንስቷ የመረጠችው ቀለም ከጸጉሯ ባህሪና ከፊቷ ቀለም ጋር አብሮ ይሄዳል የሚለው ይታያል።
‹‹የጸጉሯ ቀለም ቢቻል ከፊቷ ቀለም በአንድ ያነሰ ቢሆን ይመረጣል›› የሚለው ሙሉዓለም፤ ይህም ፊቷን እንዲያጎላው እንደሚያደርግ ይገልፃል። የጸጉር ቀለም የተለያየ በመሆኑ አንዱን ቀለም ከሌላው ጋር በመቀላቀል እንደሚቀመም ይገልፃል። ከዚያም ጸጉሯ ቀለሙን እንዲይዝ ሊፍቲንግ ሲስተም የሚባለውን ጸጉሯ ቀለሙን እንዲይዝ ለማድረግ ነጭ የማድረግ ሥራ ይሰራል። ታዲያ የተለያዩ ሂደቶችን አልፎ የፈለገችው የጸጉር ቀለም እስከሚይዝ ሶስት ሰዓት እስከ አምስት ሰዓት ጊዜን ይወስዳል። ባለሙያው የሚጠቀመው የቀለም መጠን እንዲሁ በእንስቷ የጸጉር ብዛት የሚወሰን ሲሆን ሙሉዓለም ለአንድ ጸጉር ከ40 እስከ 50 ሚሊ ሊትር ያለ ቀለም እንደሚጠቀም ይናገራል። እርሱ የጸጉር ቀለም ምርቶች ከጣልያን ፣ ከቱርክና አሁን አሁን ደግሞ በብዛት ከአሜሪካ የሚመጡ ቀለሞችን በሳሎኑ ውስጥ ይጠቀማል።
ጸጉር ውበት ነው የሚለው አባባል ብዙዎች ይስማሙበታል። በመሆኑም የጸጉሯን ቀለም ለመቀየር የወሰነች እንስት ስትቀባ የመጀመሪያዋ ጊዜ ከሆነ መጨረሻውን እስከምታየው ድረስ አጓጊ ይሆንባታል። በመሆኑም መጨረሻ ላይ ይህን የጸጉር ቀለም ባትወደውስ የሚል ጥያቄ ለሙሉዓለም አንስተንለት ነበር። እርሱም ‹‹በጸጉር ቀለም መቀባት ሙያ አንድ ደረጃ ማውረድ እና ከፍ ማድረግ የሚባል ነገር አለ። ስለዚህ አንድ ደንበኛችን የጸጉሯ ቀለም ባትወደው በፈለገችው መጠን ከፍ ወይም ዝቅ በማድረግ እናስተካክላለን›› የሚል ምላሽ ይሰጣል።
አንድ ጸጉሯን ቀለም የተቀባች እንስት ቀለሟ ለረጅም ጊዜ እንዲቆይ አልያም ቶሎ እንዳይለቅ የምትጠቀማቸውን ቅባቶች፣ ጸጉሯን ለመንከባከብ የምትጠቀማቸውን ግብዓቶች መምረጥ፣ የምትታጠብበትን ጊዜ ማራዘም ይጠበቅባታል። ሙሉዓለም እነዚህን እና ሌሎች በውበት ሳሎን ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሲሆን በተለያየ ጊዜ ሙያውን ለማሳደግ ስልጠናዎችን ይወስዳል። በውበት ሳሎኑ ውስጥ የጸጉር ቀለም ለመቀባት ከአምስት ሺህ ብር ጀምሮ አገልግሎቱን ይሰጣል። ዋጋውም እንስቷ እንደመረጠችው የቀለም ዓይነት እንደተጠቀመው የቀለም መጠን ይወሰናል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም