‹‹ለወደብ ዝግጁ የሆነ የመንገድ መሠረተ ልማት ይዞ መገኘት ትልቅ ነገር ነው›› አቶ ፈትሂ ረመዳን እድሪስ የሀረሪ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ምክትል ቢሮ ኃላፊ

የተሟላ የመንገድ መሠረተ ልማት ሲኖር የገጠሩን ነዋሪ ከከተማው በማገናኘት፣ የትራንስፖርት አገልግሎትን በማሳለጥ፣ ለተሽከርካሪ ደህንነት፣ ለተጓዡም ምቾት በመስጠት፣ ኢኮኖሚን ለማነቃቃት፤ አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት ገበያ ለማውጣት፣ ሸማቹም በበቂ አቅርቦትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸመት ያስችላል።

ለአካባቢ መልካም የሆነ ገጽታን በመስጠትም አስተዋጽኦ አለው። የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ እንደሆነም አይዘነጋም። እየሰጠ ካለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንጻር መንግሥት በግንባታው ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ሲሆን፣ በተለይም ለገጠር መንገድ መሠረተ ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል።

የሀረሪ ክልል ሶስት የገጠርና ስድስት የከተማ ወረዳዎች ያሉት ሲሆን፣ በሥሩም ወደ 36 ቀበሌዎች ይገኛሉ። በክልሉም በርካታ የመሠረተ ልማት ግንባታ በመከናወን ላይ ሲሆን እኛም ይህንኑ አስመልክቶ ከሀረሪ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ፈትሂ ረመዳን እድሪስ ጋር ቆይታ አድርገናል።

አቶ ፈትሂ የመንገድና የትራንስፖርት ዘርፍ ለመምራት፤ በዘርፉ የትምህርት ዝግጅት አላቸው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአርክቴክቸር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኤንድ ኢንጂነሪንግ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀዋል። በሥራ ዓለም ደግሞ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የአርክቴክቸር መምህር ሆነው ነው ሥራ የጀመሩት።

በዩኒቨርሲቲው ለሁለት ዓመት ካገለገሉ በኋላ ደግሞ በሀረሪ ክልል በቤቶች ልማት መንግሥት ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ባለሙያ፣ በመቀጠል በክልሉ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት የከተማ ልማት ዘርፍ አማካሪ፣ ተመልሰው ደግሞ ባለሙያ ሆነው ባገለገሉበት ቤቶች ልማት መንግሥት ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። በመቀጠል ደግሞ የከተማ ማዘጋጃ ቤት የከተማ ተቋማዊና መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። አቶ ፈትሂ አሁን በምክትል ቢሮ ኃላፊ ደረጃ እየሰሩ የሚገኙበትን የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ጨምሮ በመንግሥት ሥራ ኃላፊነት ለስምንት ዓመታት አገልግለዋል።

አዲስ ዘመን፤ በቅድሚያ በክልሉ ለመንገድ የልማት ሥራ የተሰጠውን ትኩረትና እስካሁን የተከናወኑትንም ቢገልጹልን?

አቶ ፈትሂ፤ ሀረሪ ነባር ከተማ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የመንገድ መሠረተ ልማት ዝርጋታውም በዚያው ልክ ውስብስብ ነው የነበረው። ይህን ክፍተት ለመቀየር ብዙ ሥራዎች ተሰርተዋል። በክልሉ ለመንገድ መሠረተ ልማት ልዩ ትኩረት እንደተሰጠ የተሰሩት ሥራዎች ማሳያ ናቸው። ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ቅድሚያ በመስጠት በቅደም ተከተል እየተከናወኑ ባሉ ሥራዎች የመንገድ ሽፋኑን ከፍ ማድረግ ተችሏል። በክልሉ ሶስት የገጠር ወረዳዎች የገጠር የጠጠር መንገድ ፕሮጀክት ተቀርጾ ሥራ ላይ ውሏል። የቅርቡን እንኳን ብናነሳ በ2016 በጀት ዓመት ብቻ የክልሉ መንግሥት ከአንድ መቶ ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የመደበላቸው ከ11 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ፕሮጀክቶች ናቸው ያሉት።

በዚህ የገጠር ጠጠር መንገድ ፕሮጀክት፤ አዲስ መንገድ የማውጣት ሥራን ጨምሮ በሶስት ሥራ ተቋራጮች በመከናወን ላይ ሲሆን፣ መንገዶቹ ገጠሩን ከከተማው ጋር የሚያስተሳስሩ፣ አንዳንዶቹም አጎራባች ከሆኑ ክልሎች ጋር የሚያገናኙ ናቸው። ከጊዜ አንጻርም ፕሮጀክቶቹ ጥሩ በሚባል የአፈፃፀም ደረጃ ላይ ነው የሚገኙት። ከሶስቱ የገጠር ጠጠር መንገድ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች መካከልም ሁለቱ በድሬ ጥያራና በኤረር ወረዳዎች የተከናወኑት ተጠናቅቀው ለአገልግሎት በቅተዋል። ቀሪው ሶስተኛ በሶፊ ወረዳ ውስጥ እየተከናወነ ያለውም የመንገድ ሥራ ወደ 72 በመቶ ደርሷል።

ገጠሩን ከከተማው ለማስተሳሰር፣ ክልሉን ከአጎራባች ክልሎች ጋር ለማገናኘት የሚሠራው የመንገድ መሠረተ ልማት ሥራ ትልቅ ትርጉም ያለው ተደርጎ ይወሰዳል። ሀረሪ ክልል ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ከኦሮሚያ ክልል ጋር የሚዋሰን ሲሆን፣ ጉርሱም፣ ፈዲስ፣ ኮምቦልቻ፣ ዓለማያ ወረዳዎች ጋር ይዋሰናል። ሶማሌ ክልልም ሌላው አዋሳኝ ነው።

ትስስሩ በተለያየ አቅጣጫ ሲፈጠር በገጠር የተመረተው ሰብልም ሆነ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎች፣ በአጠቃላይ የግብርና ውጤቶችን በቀላሉ ወደ ከተማ በማጓጓዝ ለገበያ በማዋል ተጠቃሚነትን ማሳደግ ያስችላል። በዚህም ኢኮኖሚው ይነቃቃል። ከሌሎች ክልሎች ጋር ወሰንተኛ መሆንም በኢኮኖሚ ለማደግ ያግዛል። በመንገድ መሠረተ ልማት የጋራ ትብብር ለመፍጠርም ይጠቅማል። ሕዝብና ሕዝብን ለማቀራረብም ትልቅ ትርጉም አለው። ለምሳሌ ከሀረሪ ክልል ወደ ጉርሱም ወረዳ የተሠራው መንገድ አቋራጭ ወይንም አማራጭ ነው። ይሄ ለመልካም ግንኙነት ይጠቅማል።

በክልሉ ለአዳዲስ የመንገድ መሠረተ ልማት ሥራ ብቻ ሳይሆን፤ ቀድመው የተገነቡ መንገዶች ጥገናም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል። በወረዳዎች ካፒታል በጀትና በራስ አገዝ እንዲሁም በሮድፈንድ ጭምር ሰፋ ያለ የመንገድ ጥገና ሥራ እየተሠራ ነው። በጥገና ሥራውም የተጎዱ መንገዶች መልሰው እንዲለሙ ማድረግ ተችሏል።

በ2016 በጀት ዓመት በከተማ ወደ አምስት ነጥብ ስድስት ዘጠኝ (5.69) ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ሥራ ለማከናወን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከተባለ የቻይና ኩባንያ ጋር ውል ተፈጽሞ ሥራ ለመጀመር የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል። የጥገና ሥራ የሚያስፈልጋቸው የከተማዋን መንገዶች ለመጠገንም እንዲሁ በራስ አቅም ለመፈጸም በክልሉ ውስጥ የሚሰሩ የልማት አጋሮችንና ነዋሪውን በማስተባበር እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

የጥገና ሥራው በአሽከርካሪዎችና በነዋሪው ሰፊ ቅሬታ የሚነሳባቸውን መንገዶች ቅድሚያ በመስጠት የሚከናወን ይሆናል። የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ሥራም በተጨማሪ ይከናወናል። በአጠቃላይ የሀረሪ ከተማን ጥሩ እይታ በሚያላብስና ገጽታን በሚቀይር መልኩ ነው በከተማዋ ወደ 31 ኪሎ ሜትር መንገድ እየተሠራ ያለው።

በአጠቃላይ በገጠርና በከተማ በ2016 በጀት ዓመት እየተከናወነ ያለው የመንገድ መሠረተ ልማት የፋይናንስ አጠቃቀም፣ የፕሮጀክት አፈጻጸምና ተያያዥ ሥራዎች በመልካም ጎን የሚወሰዱ ናቸው። ጥሩ አፈጻጸም ማስመዝገብ የተቻለው ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን፣ ከመሬት ልማት ቢሮዎችና ከሌሎችም ባለድርሻ ጋር በቅንጅት በትኩረት በመሠራቱ ነው።

ሌላው የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታውን ለየት የሚያደርገው በየዓመቱ ሐምሌ ወር የሚከበረውን ዓለም አቀፍ 26ኛውን የሀረሪ ቀን ፌስቲቫል ዘንድሮ ክልሉ ስለሚያስተናግድ፤ ከመንገድ ጋር ተያይዞ ያሉትን ክፍተቶች መፍታትና የማስዋብ ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ ማከናወን ይጠበቃል። ፌስቲቫሉን ታሳቢ ባደረገ መልኩም ጭምር ነው ለመንገድ መሠረተ ልማት ሥራ ትኩረት የተሰጠው።

አዲስ ዘመን፤ በ2016 የተጀመሩት የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታዎች በምን ያህል ጊዜ የሚጠናቀቁ ናቸው ?

አቶ ፈትሂ፤ የፕሮጀክት ቆይታው ስምንት ወር ነው። በከተማዋ አምሳ ስድስት ነጥብ ዘጠኝ (56.9) ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የመንገድ ሥራ በሶስት ምዕራፎች ወይንም አቅጣጫዎች የተከፋፈለ ነው። አንደኛው ግንባታ ወደ ሀረሪ ከተማ መግቢያ ሀማሬሳ ላይ ነው። ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶች መቀበያ በመሆኑ ቅድሚያ ተሰጥቶታል። በዚህ በኩልም የመግቢያና የመውጫ ድልድዮችን የማገናኘት ሥራ ነው የሚከናወነው።

ሁለተኛው ግንባታ ደግሞ ከአጂፕ እስከ ሰላም አደባባይ ተብሎ በከተማዋ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን፣ ወደግንባታው ለመግባት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቅቀዋል። በዚህ አካባቢ የሚከናወነው ግንባታን ለየት የሚያደርገው ደግሞ አካባቢው የከተማዋ ማዕከል ከመሆኑ በተጨማሪ ለቱሪዝም መዳረሻ የሚውል ነው። የግንባታ ሥራውንም እስከ ስድስት ወር ባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ ነው በእቅዱ የተካተተው።

ሶስተኛው ግንባታ ስቴድየም፣ በኤኮፓርክ አድርጎ እስከ ጀጎል በሚወስደው የሚከናወነው የአንድ ነጥብ ስምንት (1.8) ኪሎ ሜትር መንገድ ሥራ ነው። በሶስቱም አቅጣጫዎች የሚከናወኑት መንገዶች ተገናኝተው የአንድ ከተማ አካል ነው የሚሆኑት። በዚህ መልኩ መከናወኑ በከተማዋ የሚሰጡ አገልግሎቶች እንዲተሳሰሩ ያደርጋል።

ለአብነትም ከአጂፕ እስከ ሰላም አደባባይ በሚሰራው መንገድ አካባቢ ሕይወት ፋና ፣ ሀሮማያ ጤና ኮሌጅ፣ ሀምሊን ፌስቱላ ሆስፒታልን ጨምሮ በሚሰጡት አገልግሎት ትላልቅ የሚባሉ ከአምስት ያላነሱ የመንግሥት ሆስፒታሎች እንዲሁም የምሥራቅ ዋና እዝ፣ የሃይማኖት ተቋማት ይገኛሉ። ከፍተኛ የሰው ፍሰት ያለበትና ለገበያም ቅርብ የሆነ አካባቢ ነው። እየሰጠ ካለው ሰፊ አገልግሎት አኳያም መንገዱ በ30 ሜትር እንዲሰፋ ነው የተደረገው።

በሀረር ብስክሌት መንዳት የተለመደ ባይሆንም በግራና ቀኝ ባለሶሰት መስመር የብስክሌት መንገድ እንዲኖረው ተደርጎ ነው የተሠራው። በአካባቢው ብስክሌት መንዳት የተለመደ ባይሆንም እድሎችን መፍጠር ያስፈልጋል ከሚል ነው በመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት እቅድ ውስጥ ተካትቶ የተከናወነው። የመኪና፣ የብስክሌት፣ የእግረኛ ተብለው ተካትተው የተከናወኑት ሥራዎች አዳዲስ ልማዶችንም በማምጣት የማለማመድ ሥራ ጭምር ነው። ይህ ሥራ ከተማዋን በአንድ ደረጃም ቢሆን በመንገድ መሠረተ ልማት ከፍ ያደርጋታል።

በከተማዋ ከአጂፕ እስከ ሰላም አደባባይ ያለው መንገድ ወደ ሶማሌ ክልል የሚወስድ ኮሪዶር ነው። እንደ ሀገር እየቀረበ ያለው የወደብ ጥያቄ ወደፊት ምላሽ ካገኘ፤ ለወደብ ዝግጁ የሆነ የመንገድ መሠረተ ልማት ይዞ መገኘት ትልቅ ነገር ነው። ክልሉ የመንገድ መሠረተ ልማት ሥራን እንዲህ ባለው ከፍ ባለ እሳቤ ነው እየሠራ የሚገኘው። በአጠቃላይ በመንገድ መሠረተ ልማት እየተከናወነ ባለው ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሕዝብ ርካታ ይመለሳል የሚል ተስፋም ተጥሏል።

አዲስ ዘመን፤ በወሰን ማስከበር በኩል ችግር አልገጠማችሁም ? እንደ መብራት ኃይልና የውሃ አገልግሎት ካሉ ተቋማት ጋር ተናብቦ በመስራት በኩል ያለውንም አያይዘው ይግለጹልን።

አቶ ፈትሂ፤ ከወሰን ማስከበር ጋር ለተነሳው ጥያቄ በዚህ በኩል ምስጋና እንጂ በክልላችን እንደ ችግር የምናነሳው ነገር የለም። ህብረተሰቡ ሙሉ መልካም ፍቃደኝነቱን ነው ያሳየው። የተለመደው ለሚለቀው ቦታ ምትክ የሚሆን የካሳ ክፍያ መፈጸም ነው። ሀረሪ ክልል በሶስት አካባቢዎች ለሚያከናውነው የገጠር የጠጠር መንገድ ፕሮጀክት ሥራ ለመንገዱ ሥራ ለተነሱ የአካባቢው ነዋሪዎች የፈፀመው ክፍያ የለም። ወይም የሰጠው የካሳ ክፍያ የለም።

ለአዳዲስ የመንገድ መሠረተ ልማት ሥራ አርሶ አደሩ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ገቢ የሚያገኝበትን የጫት ማሳውን ነው ለመንገድ ሥራ የሰጠው። መኖሪያ ቤቱ እንዲፈርስ ነው የፈቀደው። ንብረቱን ነው ያነሳው። ይህን ያደረገው የወደፊት ጥቅሙን ታሳቢ በማድረግ ነው። መንገድ ሲሰራ የገበያ እድሉ እንደሚሰፋ ቀድሞ ተገንዝቧል።

ወደ መንገድ መሠረተ ልማት ሥራ ከመገባቱ በፊትም ከማህረሰብ፣ ከተለያዩ ተቋማት፣ የመንግሥት መዋቅሮች፣ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ አባላት የተካተቱበት የልማት ኮሚቴ ተዋቅሮ የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ ምክክር ከተደረገ በኋላ ነው። ለመንገድ መሠረተ ልማት ከስምንት እስከ አስር ሜትር ስፋት ያለው ስፍራ ነው ህብረተሰቡ የለቀቀው። በከተማ ደረጃም በተመሳሳይ ነው የተፈጸመው።

ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ያለው መናበብን በተመለከተም፤ በዚህ በኩልም ጥሩ የሆነ ልምምዶችን መፍጠር ተችሏል። የመሠረተ ልማት ቅንጅት የጋራ ግብረ ኃይል አለን። የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ማዕከሉ ሀረሪ ክልል ላይ ነው የሚገኘው። ኢትዮ ቴሌኮም ጋርም ተያይዞ ምሥራቅ መካከል ሪጅን ሀረሪ ላይ በመኖሩ ከየተቋማቱ ኃላፊዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት አለን። በቴክኖሎጂ በመጠቀምም የቴሌግራም ቻናሎች በጋራ ፈጥረናል።

በዚህ በኩል ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶችን ማስተካከል ተችሏል። የተሻለ ነገርም እየታየ ነው። በጋራ ማቀድ፣ ተናብቦ መሥራት ጥሩ ተሞክሮ እየታየ ነው። እነዚህ ጅምሮች ይበረታታሉ። የሚቀሩ ነገሮች ስላሉ አሁን ላይ ከታየው ቅንጅታዊ አካሄድ በላይ መጠናከር ይጠበቃል። ለምሳሌ በመንገድ መዋቅሩ 20 ሜትር ተብሎ ሰፍሮ አንዱ የመሠረተ ልማት ተቋም በአራት ሜትር ላይ ተከላ ሊያከናውን ይችላል። በተቀመጠው ፕላን መሠረት ተከትሎ አለመሥራት፣ አለመናበብ ገና ያልተቀረፉ ችግሮች ናቸው።

የፈጠርነው የቅንጅት ሥራ ባይኖር ኖሮ በተለይ በከተማ መሀል የተሰሩት የመንገድ መሠረተ ልማቶች ስኬታማ አይሆኑም ነበር። የቴሌ መስመር እስከ ሶማሌ ክልል ድረስ የሚዘልቅ መስመር ነው የነበረው። የተዘረጋው የውሃ መስመር ዋና የውሃ ማሰራጫ ነው የነበረው። የመብራት ፖሎች እንዲሁ ጥንቃቄ የሚፈልጉ ነበሩ። በነዚህ መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ሳይደርስ የመንገድ መሠረተ ልማት ሥራው መሰካቱ የቅንጅት እና የመናበብ ሥራ ውጤት ነው።

አዲስ ዘመን፤ ክልሉ በመንገድ መሠረተ ልማት እያከናወናቸው ያላቸው ተግባራት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችል ነው ማለት ያስችላል?

አቶ ፈትሂ፤ በክልላችን አንድ የኢንዱስትሪ ዞን ወይንም ፓርክ ይገኛል። አብዛኞቹም ከመሠረተ ልማት አቅርቦት የራቁ ባለመሆናቸው የከፋ ችግር ውስጥ አይደሉም። ሆኖም ግን እጅግ ምቹ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚሁ መሠረትም በአካባቢው የአስፓልት መንገድ ሥራን ጨምሮ የመንገድ ተደራሽነት እንዲኖር ጥረት ተደርጓል። ለምሳሌ የፌዴራል መንግሥት የሚሰራው ከሀረር፣ ጉርሱም፣ ኮምቦልቻ የሚሰራው የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክት አለ። ስለዚህ ኢንዱስትሪ ዞኖች በአንድ መንገድ ብቻ የታጠሩ እንዳይሆኑ ከሌሎች አማራጭ መንገዶች ጋር የማስተሳሰር ሥራ እየተሠራ ነው። በ2016 በጀት ዓመት የሠራነውም በሶስትና በአራት አቅጣጫዎች አማራጭ እንዲኖራቸው፣ በትላልቅ ሀገር አቀፍ የመንገዶች መስመር ጋር እንዲገናኙ ነው የተደረገው።

በራስ አቅም ለመሥራት የሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶችም አሉ። ባለሀብቶቹ ለሥራቸው ለመንገድ ሥራ የሚውሉ ማሽኖችንና አንዳንድ ትብብሮችን ሲጠይቁ እገዛ እናደርጋለን። ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ባለበት አካባቢ የመንገድ መሠረተ ልማት ሥራው በዚህ መልኩ ነው እየተከናወነ ያለው። የመንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በተቻለ መጠንም እየተሠራ ነው። በዚህ አጋጣሚም በክልላችን በተለያየ ኢንቨስትመንት ዘርፍ መሠማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች በመንገድ መሠረተ ልማት በኩል ስጋት እንዳይገባችሁ እናሟላለን ብዬ ጥሪ ማቅረብም እፈልጋለሁ።

አዲስ ዘመን፤ ለፕሮጀክቶች መጓተት አንዱ ምክንያት የሆነውን ሙስና በመዋጋት ረገድ ስላለውና ክልሉ ለመንገድ መሠረተ ልማት የሚበጅተው በጀት አያይዘው ቢገልጹልን።

አቶ ፈትሂ፤ ከፕሮጀክት ጋር ተያይዞ ጨረታ ወጥቶ፣ ሕጋዊ የሥራ ፈቃድ ያላቸው መሆናቸው ተረጋግጦ በውድድር እንዲያሸንፉ ነው የሚደረገው። መስፈርቱን አሟልተው በውድድር ያሸነፉ ናቸው ሥራው የተሰጣቸው። የገጠር ጠጠር መንገዶች የተሠሩት በሀገር ውስጥ የሥራ ተቋራጮች ነው። የከተማ መንገድ ሥራዎችን ያሸነፈው ተቋራጭ፣ የቻይና ኩባንያ ነው።

ከዚህ ቀደም በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በፌዴራል መንግሥት የገጠር መንግድ ተደራሽነት (ዩራፕ) የሚባል ፕሮግራም ነበር። ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት የገጠር መንገዶች በዚህ ፕሮግራም ነበር የሚሰሩት። ከአምስት ዓመታት ወዲህ ግን በክልላችን በዚህ ፕሮግራም የተከናወነ ነገር የለም። በዚህ ፕሮግራም የመንገድ ሥራው የተቋረጠ ቢሆንም፣ የፕሮግራሙ ሃሳብ ጥሩ ዓላማ ያለው በመሆኑ በዚህ መንገድ መተግበር የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል።

እያንዳንዱ ቀበሌ ከዋና አስፓልት መንገድ ጋር እንዲገናኙ ማድረግ በወሊድ ጊዜ በወሳንሳ ወደ ሆስፒታል የምትወሰድ እናት እንዲሁም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ የሚቸገሩትን ሁሉ ለማስቀረት ያግዛል። በመሆኑም የክልሉ መንግሥት የፕሮግራሙን ሃሳብ ይዞ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማስፈንና ብልጽግናንም ለማምጣት በየዓመቱ ከአንድ መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ለመንገድ መሠረተ ልማት ሥራ ወደ አንድ መቶ ሚሊዮን ብር ለገጠር መንገድ ሥራ ፕሮጀክት ይመድባል።

በ2014 በጀት ዓመት ላይ ሥራዎች የመዘግየት ሁኔታ ታይቷል። መዘግየቶችን ለማስቀረት ክትትልና ቁጥጥሩን ጠበቅ ማድረግ ያስፈልጋል። የመንግሥትንና የተጠቃሚውን ፍላጎት የሚያስጠብቅ፣ በትክክል መሠራቱንም የሚያረጋግጥ መሀንዲሶች በየቦታው እንዲኖሩ ማድረግና የእርማት ሥራ መሥራት፣ በየጊዜው ፕሮጀክቶችን መገምገም፣ የበላይ አመራሩም በሪፖርት ከሚቀርብለት ባሻገር በመስክ ተገኝቶ ማየት እንዲችል ማድረግ ያስፈልጋል።

እኛም በዚህ መልኩ በመሥራትና በትክክል ኃላፊነታቸውን ያልተወጡትንም በመቅጣት ጭምር ነው የነበሩ ክፍተቶችን ማረም የቻልነው። በ2016 በጀት ዓመት የተከናወነው የመንገድ መሠረተ ልማት ሥራ ከተቀመጠለት ጊዜ ገደብ በፊት ፈጥኖ እንዲከናወን ማድረግ የተቻለውም ሥራዎች በዚህ መንገድ በመሠራታቸው ነው።

በቢሮ ውስጥ ያለው ቢሮክራሲም ሌላው ማነቆ ነው። በዚህ በኩልም ፕሮጀክቶችን ማዕከል ያደረገ ሥራ እንዲሠራ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ያለበቂ ምክንያት የሚፈጠረውን መጓተት ለማስቀረት ተችሏል። ይህም ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው በጀትና ጊዜ በታሰበው ጥራት እንዲሠራ አስችሏል። በዚህ ሂደት አልፎ የተሠሩት የመንገድ መሠረተ ልማቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንዲውሉ የሚደረገው በሕዝብ ፊት ነው።

አዲስ ዘመን፤ ቢሮው የትራንስፖርት ዘርፉንም የሚመራ በመሆኑ በዚህ በኩል የተከናወኑ ሥራዎችንም ቢገልጹልን።

አቶ ፈትሂ፤ በትራንስፖርት ዘርፍ በአምስት ዘርፎች ነው እየሰራን ያለነው። የተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጥ አንዱ ነው። ከመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ብልሹ አሠራሮች ነበሩ። አሁንም ገና ብዙ ሥራን ይጠይቃል። የእያንዳንዱን አሽከርካሪ መረጃ በአንድ ቋት ወይንም ዳታ የማስገባት ሥራም እየተሠራ ነው። ለጊዜውም አዲስ መንጃ ፈቃድ የመስጠት አገልግሎት ተቋርጧል። ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የክትትልና ቁጥጥር ሥራውን እያከናወንን እንገኛለን። ወደዚህ አሠራር የገባነው ዘግይተን በመሆኑ ውጤቱ ወደፊት ይጠበቃል።

ሌላው ከመናኸሪያ አገልግሎት ጋር የተያያዘ ሥራ ነው። ተገልጋዮች በደረሰኝ እንዲጠቀሙ በማድረግ ከታሪፍ በላይ የሚጠየቅ ክፍያን ለማስቀረት ጥረት እየተደረገ ነው። በመንገድ ደህንነትም በየመንገዱም የቁጥጥር ሥራን በማጠናከርና ጎን ለጎንም ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሠራ ነው። በዚህ ረገድም በሀረሪ ክልል ፕሬዚዳንት የሚመራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሠራ ሲሆን፣ በተጨማሪ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም የየራሳቸውን ሚና እንዲወጡ እየተደረገ ነው። ደንብ የሚተላለፈውንም በቅጣት እንዲታረም የማድረግ ተግባርም ይፈጸማል። በአጠቃላይ ብልሹ የነበረውን የትራንስፖርት ሥርዓት ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

አዲስ ዘመን፤ በክልሉ በመንገድ መሠረተ ልማትና በትራንስፖርት ዘርፉ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ የተቀመጡ እቅዶች ምንድን ናቸው በሚለው ላይም ማብራሪያ ቢሰጡን?

አቶ ፈትሂ፤ በክልሉ የአስር ዓመት እቅድ ተነድፎ ነው እየተሠራ ያለው። ሀረሪ የዓለም ቅርስ ከተማ ናት። የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን በተባበሩት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት አስመዝግባለች። በተጨማሪም ሀረሪ በሰላም፣ በፍቅር፣ በመቻቻል ትታወቃለች።

የሰላም ከተማ ስትባል ቃሉ ብቻ አይደለም። የትራንስፖርት ሥርዓቷ የተሳለጠ፣ ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም የሚገቡባት እንድትሆን ነው። እስካሁን የተሠሩት ሥራዎችም ይህንን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ናቸው።

ከመንገድ መሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ፤ በአስር ዓመት መሪ እቅድ 30 በመቶ ለመንገድ፣ 30 በመቶ ደግሞ ለአረንጓዴ ልማት፣ 40 በመቶ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ መለኛዋን ከተማ ደግሞ 25 በመቶ መሠረተ ልማት የተሟላለት ማድረግ ነው። አሁን እየተከናወነ ባለው አካሄድ መጓዝ ከተቻለ የአስር ዓመት መሪ እቅዱን ማሳካት ይቻላል። በአጠቃላይ በሰባት ግቦችና ሰፊ ዝርዝር እቅዶችን የያዘ ሰነድ (ሮድ ማፕ) ተዘጋጅቶ ሀረሪ የት ትደርሳለች በሚል እየተሠራ ነው። ስኬት ላይ ለመድረስም ከክልሉ መንግሥትና ፕላን ኮሚሽን ጋር የተናበበ ሥራ ይሠራል።

አዲስ ዘመን፤ ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን

አቶ ፈትሂ፤ እኔም አመሰግናለሁ።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You