የተማሪዎችን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤታማ ያደርጋል የተባለው ስምምነት

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአካዳሚክ ነጻነት እንዲረጋገጥ፣ ከፖለቲካዊም ሆነ ከአስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆነው የመማር ማስተማር ሥራዎችን ማካሄድ እንዲችሉ በሚል እሳቤ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎችን ለማቋቋም የሚያስችል አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁን (ግንቦት 2015 ዓ.ም) ተከትሎ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን መወሰኑ ይታወቃል።

አንድ የትምህርት ተቋም ራስ ገዝ ሆነ ማለት ተማሪዎችን ያለ መንግሥት ምደባ በራሱ የመግቢያ ፈተና አወዳድሮ የሚቀበል፣ የራሱን ሠራተኞች መቅጠር እና ማሰናበት የሚችል፣ ግዢን ጨምሮ የራሱን የፋይናንስ እንቅስቃሴ በራሱ የመምራት ነፃነት ይኖረዋል የሚለው ድምዳሜ የብዙዎች ስምምነት አለ። ራስ ገዝነቱ ተቋማቱ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲስያስተዳድሩ ስለሚፈቅድ በአስተዳደርም ሆነ አካዳሚክ ነፃነት ይኖራቸዋል ነው የሚሉት የሚመለከታቸው። በተቋማቱ የሚሰሩ መምህራን እና ሌሎች ሠራተኞችም የተሻለ ክፍያን እንደሚያገኙም ነው እነዚሁ ወገኖች የሚናገሩት።

ዛሬ፣ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (ኮሌጆችን ሳይጨምር) ወደ 50 ተጠግተው ይገኙ እንጂ የሁሉም ወላጅ እናት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አይደለም ማለት አይቻልም። በተለይ የአዲስ ተከፋቾቹን ዩኒቨርሲቲ መምህራን ያበቃው እሱ እንደ መሆኑ መጠን እናትነቱ ግልፅ ነው። በመሆኑም ነው እነ ኤመሬት ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላና ሌሎችም “አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ‛አንደኛው ትውልድ’ የሚለው አይመጥነውም፤ ‛እናት ዩኒቨርሲቲ’ ነው መባል ያለበት” በማለት በየንግግር ጥናቶቻቸው መካከል ሻጥ ሲያደርጉ የሚሰማና እሚነበበው። የሌሎችም “ራስ ገዝ መሆን ያለበት ዛሬ ሳይሆን ቀድሞ ነበር” ማለታቸው ሁሌ የሚሰማ ድምጽ ነው።

የዚህ ጽሑፍ ዐቢይ ርዕሰ ጉዳይ ደረጃ የመስጠት ጉዳይ ሳይሆን የፊርማ ጉዳይ በመሆኑ ወደዛው እንሂድ።

ባለፈው ማክሰኞ አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የፋሪስ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በዓይነቱ ለየት ያለና “የቴክኖሎጂ ፈጠራ ክሂሎት ያላቸውን ተማሪዎች ውጤታማ ለማድረግ ያስችላል ተብሎ የታመነበት”ን የመግባቢያ ሰነድ በዩኒቨርሲቲው ራስ መኮንን ሴኔት አዳራሽ ተፈራርመዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከፋሪስ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ጋር በጥናትና ምርምር ክሂሎት ማበልጸግ ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት በተፈራረመበት ወቅት እንደተገለፀው ስምምነቱ እንደ ተቋም ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርና አህጉርም (በአፍሪካ ደረጃ) የሚኖረው ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተለይ የቴክኖሎጂ ምርቶችንና የዘርፉ ባለሙያዎችን ከማስተዋወቅ አኳያ ፋይዳው ትልቅ ነው።

በስምምነቱ ወቅት የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ ዶ/ር እንደገለጹት፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ወደ ሀብት የሚቀየሩበትን ዕድል ለማመቻቸት እየሠራ ነው። እንደ ዶ/ር ሳሙኤል ከሆነ፤ ስምምነቱ የተማሪዎችን ፈጠራ በመደገፍ ተግባር ላይ እንዲውልና ሥራዎቻቸውን ወደ ገበያ እንዲያወጡ ጭምር ያስችላል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጦች ላይ ጉልህና ታሪካዊ ሚና ማበርከቱን ጠቅሰው፤ የትምህርት ጥራትን፣ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ኢንዱስትሪዎችን ውጤታማና ተወዳዳሪ ከማድረግ አኳያም የበለጠ እንደሚሠራና መሥራትም እንደሚጠበቅበት ፕሬዚዳንቱ አመልክተዋል።

ተማሪዎች ያላቸውን ተሰጥኦ ለማሳደግና፣ ኢንዱስትሪውና የግሉ ዘርፍ ስለሚሠሩበት አውድ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ስምምነቱ ፈጠራዎችን ወደ ኢንዱስትሪው ለማሸጋገር፣ ወደ ሀብት በመቀየር ሥራ ፈጣሪ ለማድረግ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

ዶ/ር ሳሙኤል ከግሉ ዘርፍ ጋር በቅንጅት የሚሰጡ የትምህርትና ሥልጠና ፕሮግራሞች፣ የምርምር ሥራዎችና ቴክኖሎጂዎች ችግር ፈቺ የሚሆኑበትን መንገድ ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመው፤ የሁለትዮሽ ፊርማው የግሉ ዘርፍ ተጨማሪ አቅም እንዲሆን በማድረግ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ወደ ሀብት የሚቀየሩበትን ዕድል ለማመቻቸት የሚያስችል ስምምነት መሆኑንም አስታውቀዋል።

ምንም እንኳን በሽግግር ላይ ቢሆንም፣ ዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ፈጠራ ክሂሎት ያላቸውን ተማሪዎች ውጤታማ ለማድረግ እየሠራ ሲሆን፤ በራስ ገዝነት መደራጀት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የአምስት ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ በማውጣት በትምህርት፣ ምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ ጉዳዮች ላይ እየሠራ እንደሚገኝ፤ ከዚህ አኳያ የተማሪዎችን የፈጠራ ሃሳብ ወደ ሀብት ለመለወጥ በሚደረገው ጥረት ስምምነቱ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ሳሙኤል፣ ከግሉ ዘርፍ ጋር ለተማሪዎች ዘላቂ ስኬታማነትና ኢንዱስትሪዎችን ውጤታማ ማድረግ ላይ ያተኮረ ስምምነት መሆኑንም አስረድተዋል።

ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዩኒቨርሲቲው በተለይ በሚቀጥለው የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱ ተማሪዎች ያላቸውን ክሂሎት ተግባራዊና ውጤታማ ለማድረግ ተግቶ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ስምምነቱ የተማሪዎችን ፈጠራ ሀብት ማልማት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የፋሪስ ቴክኖሎጂ ግሩፕ መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤሊያስ ይርዳው በበኩላቸው፣ ድርጅቱ ለቀጣይ ትውልድ አዳዲስ ሥራዎችን መፍጠር የሚያስችሉ ችግር ፈቺ ምርምሮችን ለሚሰሩ አካላት ድጋፍ እንደሚያደርግ የተናገሩ ሲሆን፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያለውን እምቅ አቅም ለመጠቀም ስምምነቱ መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ተናግረዋል።

ድርጅታቸው በዓለማችን ከሚገኙ፣ ከተለያዩ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት ፕሮጀክቶችን በመቀበል የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት እንደሚሠራ ጠቅሰው፣ በተለይም በዩኒቨርሲቲዎች ያለውን ዕውቀትና ተሰጥኦ በመጠቀም የሥራ ዕድል ለመፍጠር ጥረት እንደሚያደርግ አስረድተዋል። ስምምነቱ የተለያዩ ወጣት ኢንጂነሮችን ዕውቀት በዓለም አቀፍ ተቋማት ለማስተዋወቅ የሚያስችል መሆኑ ታምኖበት መደረጉንም ገልጸዋል።

ስምምነቱ ለአምስት ዓመታት የሚቆይና የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ሲሆን፤ የተማሪዎችን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች ተግባራዊ በማድረግ ስኬታማ ማድረግን ያለመ መሆኑም ተገልጿል።

ባለፉት 73 ዓመታት (እንደ አ.አ 1950 ተመሰረተ) ከ280ሺህ በላይ ምሩቃንን ከሀገራችንም ባለፈ ለዓለማችን ያፈራ መሆኑ የሚነገርለት፤ አንጋፋና ስመ ጥሩው አ.አ ዩኒቨርሲቲ ከላይ የተናገርልነትን ብቻ አይደለም የተፈራረመው፤ የአሁኑ የሽግግር ጊዜው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ “አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአምስት ዓመቱን ስትራቴጂክ እቅድ ለማሳካት ከግሉ ዘርፍ ጋር በትብብር ይሰራል” ያሉት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ በፊትም፤

  • በኢትዮጵያ ከጃፓን ኤምባሲ ጋር በጤና መስክ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል (ሜይ 2021)፤
  • በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና እና በሰሚ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተወካይ በዶ/ር ቴትያና ሜይቦሮዳ የዩኒቨርሲቲው የውጭ ግንኙነትና ትብብር ተባባሪ ዳይሬክተር አማካኝነት ከዩክሬኑ ሰሚ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር መሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል (2021)፤
  • ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሙዌኔ ዲቱ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል (የካቲት 2016 ዓ∙ም)፤
  • የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐናን ጨምሮ የፈረንሳይ ቦርዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት፣ የኮትዲቫር ፌሊክስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት እና የሞሮኮ ራቫት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በተገኙበት፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከአራት ሀገራት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር የ”ኢንተር ዲሲፕሊነሪ ፖሊሲ ኦሬንትድ ሪሰርች ኦን አፍሪካ” የሚባል ፕሮጀክት በጋራ ለመሥራት በኮትዲቯር፣ አቢጃን (የአራትዮሽ) የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል (ጥር 2015 ዓ∙ም)። (ይህ ከ8 ሚሊየን ዩሮ በላይ ወጪ የመጠይቅ ፕሮጀክት አአዩን ይመጥነዋል፤ ወይስ፣ አይመጥነውም የሚለውን ለመገንዘብ የ“ኢንተር ዲሲፕሊነሪ ፖሊሲ ኦሬንትድ ሪሰርች ኦን አፍሪካ” ፕሮጀክት በፈረንሳይ ዩኒቨርሲቲ ቦርዶ የሚደገፍ እና ፖሊሲን ያማከለ አለማቀፍ እና ጥናታዊ የምርምር መድረኮችን የሚያዘጋጅ ፕሮግራም መሆኑ በወቅቱ የተነገረ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ይሆናል።)

እነዚህ ብቻም አይደሉም፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ እንደ እድሜው ሁሉ፣ ከበርካታ ሀገር አቀፍ፣ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የመግባቢያ፤ ከዛም ተከትሎ የሚመጣውን የትግበራ ሰነድ ሲፈራረም የኖረ ተቋም ነው።

መግባቢያ ሰነድ የግድ በሁለት አካላት ብቻ መወሰን የለበትም፤ ከዛም በላይ በሆኑ አካላት ሊፈረም የሚችል ሰነድ ስለመሆኑ ማሳያዎች ያሉ ሲሆን፤

“የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) እና በጥናት እና ምርምር መስከ የተሰማሩ 8 የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች በሳይበር ደህንነት ዘርፍ በጥናትና ምርምር፣ አቅም ግንባታ እና በታለንት ልማት ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የጋራ ስምምነት (ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ እና የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ) ተፈራረሙ፡፡”

የሚለው፣ በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስምምነት ሰነድ መፈራረምን በተመለከተ ያለውን ሁኔታ የሚያሳይ ሲሆን፤ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና 8ቱ ዩኒቨርሲቲዎች የተፈራረሙት ይህ የትብብር ሰነድ በዋናነት ሶስት ቁልፍ መሠረታዊ ነገሮችን ትኩረት አድርጎ የያዘ ሲሆን፤ እነሱም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ጋር በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ብቁ የሆነ የሰው ኃይልን ለማፍራት፣ በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎችና ውጤቶቻቸው በተጨባጭ ወደ ተግባር የሚውሉበት አስቻይ መደላድል ለማመቻቸት እና በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ልዩ ተሰጥኦ (Talent) ያላቸውን ታዳጊ ወጣቶች በመደገፍ ወደ ውጤት ማሸጋገርን ያለመ እንደሆነ በወቅቱ ተጠቅሷል፡፡

ወደ አአዩ ስንመለስ፣

  • ወጋገን ባንክ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጥናት እና ምርምር ዙሪያ አብሮ ለመሥራት የሚያስችል የሁለትዮሽ ስምምነት ተፈራረመ (በዚሁ በያዝነው ዓመት)፤
  • ኢትዮ ቴሌኮም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የኮኔክቲቪቲ እና ዲጂታል አገልግሎቶች አቅርቦት ስትራቴጂያዊ የአጋርነት ስምምነት አደረገ (ሜይ 2023)፤

እና ሌሎች በርካታ ተቋሙ የተፈራረማቸው የመግባቢያ ሰነዶችም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጉዳዩ እንደገፋበት (የመግባቢያ ስምምነቶቹ ወደ ትግበራ ስምምነት መሸጋገራቸውን ለጊዜው መረጃ ባይኖረንም) ያሳያልና ይበል የሚያሰኝ ብቻ ሳይሆን ሌሎች መሰል የሀገራችን ተቋማትም፤ በተለይም በጥናትና ምርምሩ፤ እንዲሁም በፈጠራው ዘርፍ አብረው መሥራት የሚችሏቸውን፤ ለሀገርና ሕዝብ የሚጠቅሙ ተቋማትን በማደን የዚህ ዓይነቱን ተግባር ሊያከናውኑ እንደሚገባ አርአያ ሊሆን የሚችል ራስ ገዝ ተቋም ነው።

የአአዩ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ “ከፋሪስ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ሁለተኛው የትኩረት አቅጣጫ የሆነውን የተማሪዎች ስኬታማነት ግብን እውን ለማድረግ ያግዛል” በማለት የገለፁት የመግባቢያ ሰነድ በዚሁ ሳይገታ ወደሚቀጥለው፤ ወደ ተግባር ስምምነት እንደሚሸጋገር እምነታችን ነው። የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብም፣ በተለይም ተማሪዎች አጋጣሚውን እንደ አንድ ልዩ እድል ቆጥረው በአግባቡ ይጠቀሙበታል ብለንም ተስፋ እናደርጋለን።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You