ለብሔራዊ ጥቅም በአንድነት እንቁም

ኢትዮጵያውያንን፣ በማስተባበር የሀገሪቱን ዳር ድንበርና ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት በማስከበር እንዲሁም የአውሮፓ የወቅቱ ልዕለ ኃያል ሀገር / የፋሽስት ጣሊያን የቅኝ ግዛት ቅዠት የወለደውን ወረራ በመጣበት አግባብ ተፋልሞ ከመቀልበስ ረገድ የበኩላቸውን ኃላፊነት በልኩ መወጣት የቻሉ የወቅቱ መሪ ናቸው ዳግማዊ አፄ ምኒልክ። ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፤ ትውልዱ ከእርሳቸውና ከመሰሎቻቸው ትምህርት በመውሰድ ሀገሩን ዘውትር በሁሉም ግንባር ልጠብቅ እንደሚገባው በማሳሰብ በዚህ መልኩ ያስተላለፉት መልዕክት በታሪክ መዛግብት ተሰንዶ ይገኛል።

“እናንተ አንድ ልብ ሆናችሁ በምቀኝነት እርስ በርሳችሁ ተዋግታችሁ ካላለቃችሁ በቀር ኢትዮጵያን ሀገራችንን ለሌላ ለባዕድ አትሰጧትም፤ ክፉም ነገር ሀገራችንን አያገኛትም። ነፋስ እንዳይገባባችሁ ሀገራችሁን በያላችሁበት በርትታችሁ ጠብቁ፤ ወንድሜ ወንድሜ እየተባባላችሁ ተደጋገፉ፤ የኢትዮጵያን ጠላት ተጋግዛችሁ ተድንበር መልሱ። የኢትዮጵያ ጠላት ባንዱ ወገን ትቶ ባንድ ወገን ቢሄድና ድንበር ቢገፋ፤ በኔ ወገን ታልመጣ ምን ቸገረኝ ብላችሁ ዝም አትበሉ፤ ያ ጠላት በመጣበት በኩል ሁላችሁም ሄዳችሁ አንድነት ተጋግዛችሁ ጠላታችሁን መልሱ እስከ እየቤታችሁ እስኪመጣ ዝም ብላችሁ አትቆዩ” ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፤ ግንቦት ፲ ቀን ፲፱፻፩ ዓ.ም. በዚህ መልኩ ትምህርት የሚሰጥ መጪውን ትውልድ ያገናዘበ መልዕክት ያስተላለፉም መሆናቸው በታሪክ እንዲህ ይታወሳል።

ለኢትዮጵያ፣ ነፃነትና ዘመናዊ ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት እንደጣሉ የሚነገርላቸው ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፤ ለሀገር ክብርና ብሔራዊ ጥቅም በአንድነት መቆም የጥንካሬ ሁሉ ምንጭና የማድረግ ኃይል መሆኑን በአጽንኦት የሚያምኑ ከመሆናቸውም ባሻገር ኩርፊያና ቅራኔን በማስወገድ ኃይል ለማሰባሰብ እንዲቻል ልዩ ልዩ ስምምነቶችን ከባላባቶች ጋር ያደርጉ እንደነበር አንዳንድ የታሪክ መጻሕፍት በልዩነት ታሪኩን ጽፈዋል።

በዓድዋ የህልውና እና ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ የነፃነት ትግል ወቅት ኢትዮጵያውያን፤ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ለግዛት አስተዳዳሪዎች ሀገራቸውን ከወራሪ እንዲከላከሉ አድርገውላቸው የነበረውን ጥሪ ተከትሎ፤ የውስጥ ጉዳዮቻቸውን እርግፍ አድርገው በመተውና ፈጣን ምላሽ በመስጠት ከሀገር ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም የሚበልጥ ምንም እንደማይኖር በተጨባጭ አሳይተዋል።

በዓድዋ የህልውና ትግል ወቅት የነበሩ የሁሉም ግዛት አስተዳዳሪዎች፣ አርሶ አደሮችና ሴቶችን ጨምሮ ያሏቸውን ኃይሎች በግላቸው መሪነት አስከትለው ወረራው ካጋጠመበት የዓድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች ከተው በመድረስ የነጭ ወራሪን ድል ማድረግ ችለዋል። ይህም በዓለም ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያውያን በአንድነት የካቲት 23/1888 ዓ.ም (March 1/1996) የነጭ/የጣሊያን ወራሪ ላይ የተቀዳጁት የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ብቸኛ ድል ሆኖ በዓለም ታሪክ ይታወሳል።

ኢትዮጵያውያን፣ ለሀገር ብሔራዊ ጥቅምና ክብር መረጋገጥ ከተግዳሮቶቻቸው ሁሉ ባሻገር በዘር፣ በቋንቋና ሃይማኖት ሳይከፋፈሉ በአንድነት በመቆም መሪዎቻቸውን ታዘው ከ16ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አንስቶ ወራሪዎችን ድባቅ በመምታት ሀገረ መንግሥቱን ከማጽናትም ባለፈ ጠብቀው ማቆየት ችለዋል።

ለዚህም ማሳያ የሚሆነን ኢትዮጵያውያን ከቱርክ፣ ከእንግሊዝ፣ ከግብጾች ጋር በተደረገው የጉንዴትና ጉራ ጦርነት፣ ከሱዳን ደርቦሾች፣ በካራማራ ከዛይድ ባሬ ወራሪ ኃይልና በኢትዮ -ኤርትራ የህልውና ትግል ወቅት ድንበር ጥሰው ከደጃፋቸው የመጡ መራሪ ኃይሎችን በጀግንነት መክተው በሁሉም ድል በመንሳት ጽኑ ሀገር መንግሥት ጠብቀው በማቆየት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት ፈለጋቸውን እንድንከተል ምሳሌ ሆነውናል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ፣ ለዘመናት ጦርነትና የህልውና ትግል የምትገኝበት መልክዓ -ምድራዊ አስፈላጊነትን ተከትሎ ተለይቷት አያውቅም። ጦርነት የታሪኳ አካል ሆኖ የዘለቀው ወራሪዎችን ለመመከት፣ ብሔራዊ ጥቅሞቿንና ሀገራዊ ክብሯን ላለማስደፈር ዜጎቿን በአንድነት አስተባብራ በፈጸመችው ተጋድሎ እንጂ የየትኛውንም ሀገር ድንበር ገፍታ በእብሪት ወረራ ፈጽማ እንደማታውቅ የረጅም ዘመናት የሀገረ-መንግሥት ታሪኳ ያስረዳል።

ኢትዮጵያውያን፣ በዘመናት መሃል በአንድነት ሀገሪቱ የገጠማትን የህልውና አደጋ/ወረራ መክተው ሀገረ-መንግሥቱን ማጽናት ከመቻላቸውም ባሻገር በውጤቱም ኢትዮጵያ፤ በዓለም ፖለቲካና የዲፕሎማሲ መድረክ እንደ ጥንታዊነቷ ሁሉ እስከ ሙሉ ክብሯ የሚገባትን ማግኘት እንድትችል፣ እንድትታወቅና እንድትከበር አድርገዋታል።

ኢትዮጵያውያን፣ በህልውና ትግሎች ሁሉ ድል በማድረግ ባሳዩት ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም በአንድነት የመቆም የዓላማ ጽናት መነሻነት የፓን አፍሪካኒዝም የአፍሪካውያን የአንድነት እንቅስቃሴ እንዲቀጣጠል አንቀሳቃሽ አቅም ከመሆናቸውም በተጓዳኝ የካሪቢያን ሀገራትን ጨምሮ ሌሎችም የዓለም ጭቁን ሕዝቦች በገዛ ክንዳቸው ታግለው ነፃ መውጣት እንደሚችሉ ያስተማረም ነው።

ኢትዮጵያውያን፣ ፋና ወጊ ሆነው ላሳዩት ምሳሌነት በጎርጎሮሳዊያኑ ሜይ 25/1963 ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡ የአፍሪካ ሀገራት፤ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫውን በአዲስ አበባ አድርጎ እንዲመሠረትም አድርገዋል። በተመሳሳይ ኢትዮጵያውን፣ ከታላቁ የዓድዋ ጦርነትም በኋላ ዜጎች በአንድነት ለሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም በጽናት በመቆም በዓለም የፖለቲካና የዲፕሎማሲ መድረክ ላይ በፈጠሩት ተጽዕኖ፤ ሀገሪቱ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተመሠረተው ሊግ ኦፍ ኔሽኝ የተሰኘው ዓለም አቀፍ የሰላምና ደህንነት ተቋም ብቸኛ አፍሪካዊት አባል ሀገር በመሆን በ1923 መሥራች ሀገር ሆና እንድትቀላቀል አስችሏታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሀገሪቱ አሁን ላይ በውስጥ የምታከናውናቸውን ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ጨምሮ በዲፕሎማሲው ረገድም በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ብሄራዊ ጥቅሟቿን ለማስከበር በምትወስዳቸው ጊዜውን የሚመጥኑ የሪፎርም ርምጃዎች ሳቢያ፤ በምንገኝበት ቀጠና እና በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅ የመጠምዘዝ ዛቻና ማስፈራሪያን ያካተተ የተደራጀ ዘመቻና ጫና እየተደረገባትም ይገኛል።

ከኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት በኋላ፣ በተደረገው የድንበር ማካለል ወቅት በግልጽ ይሄ ነው ተብሎ በማስረጃነት በማይወሰድ ልዩ ልዩ ፖለቲካዊ ምክንያት፤ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ላይ በታዩ የአቋም መለሳለስና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ውስንነት ከሦስት አስርት ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ሀገሪቱ ከቀጠናው ዲፕሎማሲና ፖለቲካ እንድትገለል ተደርጋ ኖራለች።

በውጤቱም ሀገሪቱ፣ የባህር በሯን ጨምሮ በባለቤትነት የምታስተዳድራቸውን ወደቦቿን ፍታሐዊነት በጎደለው ፍርደ ገምዲል ውሳኔ እንድታጣ ከመደረጓም ባለፈ በቀጠናው ለብሔራዊ ጥቅሟቿ መከበር አበክሮ ሲሰራ የነበረው የባህር ኃይሏም እንዲበተን ሆኗል።

ኢትዮጵያ፣ በቀጠናው በሁሉም ረገድ አስቀድሞ ወደ የነበራትን ብሔራዊ ጥቅሞቿን ጨምሮ ክብሯን ለመመለስ በምታደርጋቸው ዲፕሎማሲያው ጥረቶች፤ ከራስ ገዟ ሶማሌላንድ ጋር በቅርቡ የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረመች መሆኗ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ከሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ጋር ታህኅሣሥ 22፤ 2016 የመግባቢያ ስምምነት ፊርማቸውን ካኖሩ በኋላ፤ የሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ሶማሊያ ብርቱ ተቃውሞ እንድታሰማ እየገፋፏትም ሲሆን፤ በዚህ መነሻነት ፈጽሞ ያልተገባትን ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ለማግኘት በቅርቡ የተካሄደውን የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ስብሰባን ጨምሮ በመንግሥታቱ ድርጀት የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤትና በሌሎችም አጀንዳ ሆና ለመቅረብ በሎቪስቶች የተደገፈ ሁሉን አቀፍ ጥረት እያደረገች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ከሶማሌላንድ ጋር በተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት ምክንያት፤ ከሀገሪቱ ጋር ውዝግብ ውስጥ እንድትገባ በሌሎች አላስፈላጊ ጫና የተደረገባት ሶማሊያን እንደ proxy መጠቀም የሚፈልጉ ኃይሎች መኖራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ የተናገሩም ሲሆን፤ በሁለቱ ሀገራት በኩል የጦርነት ፍላጎት አለመኖሩንም በአጽንኦት አስገንዝበዋል።

ራስ ገዟ ሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት በሀገራቱ መካከል የመጀመሪያ ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም። ሀገሪቱ የበርበራ ወደብን ለማልማት እና ለማስተዳደር የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ንብረት ከሆነው ዲፒ-ወርልድጋር ከስምንት ዓመት በፊት በተመሳሳይ ውል ገብተው በጋራ እየሠሩ መሆናቸውም የሚታወቅ ነው።

ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት፤ የራስ ገዝ አስተዳደሯ ከሌሎች ሀገሮች ጋር ከፈጠረቻቸው ግንኙነቶችም የተለየ አይደለም። ለዚህም ተጨባጭ ማስረጃ የሚሆነን በርካታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሀገራት ለሶማሌላንድ የሀገርነት ዕውቅና ባይሰጡም በሃርጌሳ አገናኝ የዲፕሎማቲክ ጽሕፈት ቤቶች አሏቸው። በሶማሌላንድ(“ሃርጌሳ”) ወደ 20 ገደማ የሚሆኑ የተመድ አባል ሀገራት የቆንስላ ጽሕፈት ቤት መቀመጫም መሆኗ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ እንጂ ለማንም በሰበር ዜና የሚነገር ጉዳይ አይሆንም።

ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት፤ ለንግድ እና ወታደራዊ የጦር ሰፈር ለማቋቋም የሚያስችል የባህር ወደብ /ጠረፍ ሀገሪቱ እንድታገኝ የሚያስችላትም ይሆናል። የጎረቤቶቿ ሰላም መሆን አስተማማኝ የሰላም ዋስትና እንደሚሰጣት በጽኑ የምታምነዋ ኢትዮጵያ፤ ጎረቤቶቿን ባስቀደመ የዲፕሎማሲ መርህ በመንግሥታት የለውጥ ሂደት በአቋማ በመጽናት አስፈላጊ ድጋፎችን ሁሉ ባልተቋረጠ መልኩ በማድረግ ላይ ትገኛለች።

በምሥራቅ አፍሪካ ጎረቤቶቹን በመውረር ታላቋን ሶማሊያ እመሰርታለሁኝ ብሎ ተነስቶ ከነበረው የዛይድ ባሬ መንግሥት ውድቀት/ሽንፈት ማግሥት፤ እንደ ሀገር የመፈራረስ /በየአቅጣጫው የመበታተን አደጋ ላጋጠማት ሶማሊያ፤ ኢትዮጵያ ሠራዊቷን በሚፈለገው ልክ በማሰማራት ሶማሊያ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥት እንዲኖራት ማድረግ ችላለች። በተግባሯም ለ17 ዓመታት ጸንታ የሶማሊያን ማዕከላዊ መንግሥት በመደገፍ ላይ ትገኛለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፤ በተለያዩ ግዚያት ሶማሊያ ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋር የድንበር ግጭትና ፖለቲካዊ አለመግባባት ሲያጋጥማት ለማግባባት ብዙ ርቀት ሄዳ ተግባሯን ማሳካት መቻሏ ይነገራል። ለዚህም ሶማሊያ ከኬንያ ጋር የገባችበትን የድንበር ግጭት ለመፍታት ኢትዮጵያ የሁለቱን ሀገራት መሪዎች አገናኝታ ማስማማት መቻሏ ማሳያ የሚሆን ነው።

በረጅም ዘመናት የሀገረ-መንግሥት ታሪኳ በትኛውም ሀገር ላይ ወረራ ፈጽማ የማታውቀው እና ነፃነቷን በትውልድ ሂደት በጽኑ በመጠበቅ የምትታወቀዋ ኢትዮጵያ ፤ በዓለም አቀፉ የሰላም አስከባሪ ጦር በኩል ልክ እንደሷ ሁሉ የሌሎችም ሀገራት ነፃነት እንዲጠበቅ በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በላይቤሪያ፣ በሱዳን እና በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በመሰማራት ሰላም የማረጋገጥ ዓለም አቀፋዊ ግዴታዋን በላቀ ኃላፊነት መወጣት መቻሏ የሚታወስ ነው።

አሜሪካና አውሮፓ፣ የሩቅና የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በቀይ ባህርና ኤደን ባህረ-ሰላጤ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ብልጫን ለመያዝ የቀጠናውን ሀገራት ብሔራዊ ጥቅም በሚጻረር መልኩ ሁሉን አቀፍ ተደራራቢ ጫና እያደረጉ የሚገኙ መሆናቸው የቀጠናውን ዲፕሎማሲና ፖለቲካ ተለዋዋጭና አይገመቴ እንዲሆን ማድረጉ በበርካቶች የሚነገር ከመሆኑም ባለፈ የሚታይ ነው።

በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ መስኮች ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟቿን በቀጠናው ለማስከበር የምታደርገውን ሁሉን አቀፍ ጥረት ኃይል አሰባስቦ መደገፍ መቻል፤ ከአንድ ፓርቲና መሪ ጉዳይ አስፈጻሚነት ከፍ ያለ በሁሉም ረገድ የሀገሪቱ ስብራቶች እንዲታከሙ የሚያደርግ የዚህ ትውልድ ጀብድ ሆኖ በታሪክ ልታወስ የሚችል የጋራ ኃላፊነትም ጭምር ነው።

በምንገኝበት ቀጠናም ሆነ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ መድረክ፤ ብሔራዊ ጥቅምና ክብራችንን ለማስጠበቅ እንድንችል፤ በውስጥ እንደ ልዩነት የሚታዩ ጉዳዮችን ሁሉ ደረጃ በደረጃ በሰከነና መደማመጥ በሰፈነበት የውይይት አግባብ ልዩነቶች በሰጥቶ መቀበል መርህ በሚፈለገው ልክ እንዲጠቡ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል። ለሀገር ሁለንተናዊ ግንባታ አቅም በሚሆን ሁናቴ ልዩነቶችን በሚፈለገው ልክ በመግራትና በማስተናገድ ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ኃይል በማሰባሰብ በአንድነት መቆም ወቅቱ የሚጠይቀው ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው።

በተለመደው የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ግንኙነት መርህ በቀጠናው የመንግሥት የሥርዓት ለውጦችን ተሻግረው በይደር የቆዩና በዚህኛው ትውልድ ጫንቃ ላይ የወደቁ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ተደራራቢ ችግሮች በቀላሉ መልስ እንዲያገኙ ማስቻል አዳጋች እንደሚሆን ይታመናል።

ይሁንና አዳዲስ ነባራዊ የቀጠናውን አሁናዊ ተጨባጭ ባህሪ ያገናዘበ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ አማራጭ ሃሳቦችን፣ ፖለቲካዊ ታክቲኮችን ፣ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ ቀናኢ የሆኑ የውስጥና የውጭ ኃይሎችን ለብሔራዊ ጥቅም የማሰለፍ ዲፕሎማሲዊ ስልትና ልዩ ልዩ አዳዲስ የፖሊስ ሃሳቦችን ለይቶ ተግባራዊ ማድረግን ይጠይቃል።

ቀደምት ኢትዮጵያውያን ፣ለብሔራዊ ጥቅምና ሀገራዊ ክብር መረጋገጥ ሲያደርጉት የነበረውን የትብብር መርህ አጠናክረን በማስቀጠል፤ የውስጥ ኃይልን በማሰባሰብና አዳዲስ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ስልቶችን በመንደፍ በምንገኝበት ቀጠናም ሆነ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ ለብሔራዊ ጥቅሞቻችን መረጋገጥ በአንድነት መቆም መቻል፤ ወደምንፈልገው ስኬት ለመድረስ የምናደርገውን መንገድና ጉዞ አጭር እንደሚያደርገው ከታሪካችን ውጭ ማስረጃ የሚያሻን አይሆንም።

በጋዜጠኛና ሲኒየር የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ ላንዱዘር አሥራት

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You