ለወተት ሀብት ልማት ስኬት – የምርምር ተቋማቱ ሚና

ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ሀብቷ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ከፊት የተሰለፈች ሀገር ብትሆንም፣ ከዚህ ሀብቷ በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ እንዳልሆነች ይገለጻል። የህብረተሰቡ አመጋገብ ሥርዓትም በእንስሳት ተዋፅኦ ምርትና ምርታማነት ያልተደገፈና ያልጎለበተ መሆኑን በተደጋጋሚ ይነሳል።

በተለይ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሕፃናት ላይ ለሚስተዋለው የመቀንጨር (Stunting) ችግር የራሱን ተፅእኖ እንዳለው የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ። ዜጎች በተለይ ደግሞ ሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ከሚያግዙት መካከል ሥጋና ወተት ቀዳሚዎቹ እንደሆኑ ይገለፃል። ይሁን እንጂ እነዚህን ምርቶች በገበያ ውስጥ በቀላል ዋጋና በሚፈለገው መጠን ማግኘት አዳጋች መሆኑ ይታወቃል።

በሀገሪቱ እንደ ወተትና ያሉ የእንስሳት ተዋፅኦ ውጤቶች ፍላጎትና ገበያው ያልተጣጣሙበት ሁኔታ ምርቶቹን ከውጭ ሀገራት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማስገባት ተገዳለች። መረጃዎች እንደሚያሳዩትም፤ በሀገሪቱ በየዓመቱ የሚመረተው የወተት መጠን ከሕዝቡ ፍላጎት አንፃር ሲታይ በጣም ዝቅተኛ የሚባል ነው።

በሌላ በኩል የዓለም ጤና ድርጅት አንድ ሰው በአማካይ በዓመት 200 ሊትር ወተት መጠጣት እንዳለበት ይመክራል፤ ሆኖም በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በአማካይ አንድ ሰው 19 ሊትር ወተት ብቻ እንደሚጠጣ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ችግሮች እንደ ምክንያት ይጠቀሳሉ። ከእነዚህም መካከል በሀገሪቱ የወተት ሀብት ዘርፉ በተለያዩ መዋቅራዊ ችግሮች የተበተበ በመሆኑ ለዘርፉ ምርትና ምርታማነት አለመጎልበት ዋናው ሰበብ እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል። በተለይም የወተት እሴት ሰንሰለቱ ወደኋላ የቀረ መሆኑ፤ የትምህርት፤ የምርምር፤ የኤክስቴንሽን ሥርዓቱ ያለመዘመን ለዘርፉ እድገት ማነቆ ሆኖ ቆይቷል።

መንግሥት ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና ሀገሪቱ ባላት ሀብት በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ ትሆን ዘንድ ‹‹የሌማት ቱሩፋት›› የተሰኘ መርሃ ግብር ቀርጾ እየተገበረ ይገኛል። በመርሃ ግብሩ የእንስሳትና የእንስሳት ተዋፅኦን ጨምሮ አትክልትና ፍራፍሬ ሰብልና መሰል የግብርና ውጤቶችን ምርታማነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሻገር ዘርፈ ብዙ ሥራዎች በመከወን ላይ ናቸው። የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚመረተውን የወተት ምርት በሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብሩ በቀን ከአንድ ላም የሚገኘውን ወተት ወደ 45 ሊትር ለማድረስ እየተሠራ ነው።

በሌማት ቱሩፋት መርሀ ግብሩ በየክልሉ እየተከናወነ ላለው የወተት መንደር ውጤታማነት የምርምር ዘርፉ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ይገኛል። የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን ከማፍለቅ ባሻገር መርሀ ግብሩ በተጨባጭ እንዲተገበር ለአርሶና አርብቶ አደሮች ተከታታይነት ያለው ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛል።

በኢንስቲትዩቱ የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል የብሔራዊ ወተት ከብቶች ምርምር ፕሮግራምና በሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል የወተት ልማት ኃላፊ ዶክተር ኡልፍነህ ገልሜሳ እንደሚሉት፤ ማዕከሉ በተለይም በእንስሳትና እንስሳት ተዋፅኦ ምርምር አንጋፋ ተቋም እንደመሆኑ በዘርፉ ያለውን የምርትና ምርታማነት ችግር ለመፍታት በርካታ ምርምሮችን አካሂዷል፤ በማካሄድም ላይ ነው። ለዓመታት ሀገር በቀል እንስሳቶችን ከውጭ ምርጥ ዝርያዎች ጋር በማዳቀል፤ በቴክኖሎጂ በመደገፍ ምርታማነት በማጎልበት ውጤቶችን አስመዝግቧል።

ከዚህ በፊት በቀን ከአንድ ላም ይገኝ የነበረውን ሁለት ሊትር ወተት ወደ 17 ሊትር ማድረስ መቻሉን ዶክተር ኡልፍነህ ያመለክታሉ። በሀገር አቀፍ ደረጃ የሌማት ቱሩፋቱ በይፋ ከተጀመረ ወዲህ ደግሞ በቀን ከ35 እስከ 42 ሊትር ወተት ከአንድ የተሻሻለ ዝርያ ካላት ላም ለማግኘት እየተሠራ መሆኑን ያስረዳሉ።

‹‹በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሩ መሠረት የተሻሻሉ ላሞችና ጊደሮችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው። ይሄ ደግሞ የወተት መንደር ለማቋቋም የምናደርገው ፕሮጀክት አካል ነው›› ይላሉ። እስካሁንም በየዓመቱ 100 የተሻሻሉ ጊደሮችና ላሞችን በመደበኛነት ተደራሽ መደረጉን ጠቅሰው፤ ይህንን መጠን በእጥፍ በማሳደግ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የወተት መንደር ሥራ እንዲጠናከር ርብርብ እየተደረገ ስለመሆኑ ያብራራሉ።

‹‹በሌማት ቱሩፋቱ ደግሞ የተለየ ትኩረት አድርገን እየሠራን ነው፤ በገበሬ ማህበራቱ ሲደገፉ ያሏቸውን የወተት ላሞችና ጊደሮችን አንድ ላይ ስብስብ አድርገን በከተማ ዙሪያና በወተት መንደር ላይ ነው እየተሠራ ያለው›› ይላሉ። ይኸው በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው መርሃ ግብር አፈፃፀሙ ጥሩ የሚባል እንደሆነም ነው የጠቆሙት።

እንደ ዶክተር ኡለፍነህ ማብራሪያ፤ ግብርና ምርምር ማዕከሉ የወተት ምርምር ቴክኖሎጂዎችን ከማውጣት ባሻገር የሰርቶ ማሳያ ሥራ ይሰራል። ይሁንና በየገበሬ ማህበራቱ ሲሰራ የነበረው ሥራ የተበተነ ስለነበር ውጤቱ ብዙም አይታይም ነበር። የሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብሩ እንደሀገር ከተጀመረ ወዲህ ግን በመንደር ደረጃ አርሶ አደሮችን በማደራጀት የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን ላሞችና ጊደሮች ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ድጋፎች የመስጠት ሥራ በመከናወኑ አመርቂ የሚባል ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል።

‹‹በተለይ ከሌማት ቱሩፋቱ ጋር ተያይዞ በከተማ ዙሪያ በመንደር አደራጅተን እያከናወንን ባለነው የድጋፍ ሥራ ጥሩ ውጤት እየተገኘ ነው›› የሚሉት ዶክተር ኡልፍነህ፤ ይህ ደግሞ ሊመጣ የቻለው ሁሉም ዓይነት አገልግሎት በአንድ ላይ መስጠት የሚቻልበት እድል በመፈጠሩና በተለይም ቴክኖሎጂና ግብዓት በተፈለገው ጊዜና መጠን እንዲያገኙ በመደረጉ እንደሆነ ያስረዳሉ። በተመሳሳይ የወተት መንደር አደረጃጀት በመፈጠሩ ሰው ሠራሽ የማዳቀል አገልግሎት፣ ሕክምና እና መሰል አገልግሎቶችም በአስተማማኝ ሁኔታ መስጠት እንደሚቻል ተናግረው፣ ይህ ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስኬት እንዲገኝ ማስቻሉን ነው ያመለከቱት።

ይህም በመሆኑ ከዚህ ቀደም ከአንድ ላም በቀን ይገኝ የነበረውን የወተት መጠን በከፍተኛ መጠን ማሳደግ እንዳስቻለ ጠቁመው፤ ይህን ተከትሎም አርሶ አደሩ የራሱን የተመጣጠነ ምግብ ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ ለገበያ አቅርቦ የገቢ አቅሙን ለማሳደግ እድል እንደፈጠረለት ይናገራሉ። ‹‹አሁን በትንሹ አንድ ላም ያለው ሰው ከዘጠኝ እስከ 12ሺ ብር በወር ገቢ ያገኛል›› ይላሉ። አርሶ አደሩ በተጓዳኝ ሌሎች የልማት ሥራዎችን እንደሚሰራ ጠቅሰው፣ ይህ ሁሉ የእንስሳሰት ሀብት ልማቱ ውጤታማነቱ አስተማማኝ በሚባል ደረጃ እንዲታይ እያደረገ ነው ባይ ናቸው። ከዚህም በላይ የሥነ-ምግብ ሥርዓቱም እንዲለወጥ እያደረገ ስለመሆኑም ይጠቁማሉ።

ዶክተር ኡልፍነህ አሁን ላይ እንደሀገር ስድስት ቢሊየን ሊትር ወተት ይመረታል፤ ይህ አሀዝ ከአራት ዓመት በፊት 3 ቢሊዮን እንኳን አይሞላም ነበር፤ ይህ ሊሆን የቻለው ከምርምር የወጡትን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀማችን ነው ይላሉ።

ዶክተር ኡልፍነህ ከዚያ በፊትም ቢሆን ሀገሪቱ ያላትን ሀብት አልተጠቀመችበትም በሚለው ሃሳብ ላይ ልዩነት እንዳላቸው ይገልፃሉ። ‹‹እኔ በመሠረቱ ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት አልተጠቀመችበትም የሚል እምነት የለኝም። ለምሳሌ እርሻ ብንወስድ 90 በመቶ የሚሆነው መሬት የሚታረሰው በእንስሳት ነው። በወተትም የሚገኘው ምርት እንደቀላል የሚታይ አይደለም›› ሲሉ ይገልፃሉ። ግን ደግሞ ከዚህ በላይ ተጠቃሚ መሆን ይገባ እንደነበር ያምናሉ።

ከእንስሳት ቁጥር ብዛት አንጻር ሕዝቡ ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ወተት፣ ሥጋ፣ እንቁላልና ማር የመሳሰሉ የእንስሳት ተዋጽኦዎችን እንዲያገኝ በማድረግ በኩል ሰፊ ክፍተት እንዳለ ያመለክታሉ። ለዚህ ደግሞ በቂና ጥራት ያለው የመኖ አቅርቦት ከማድረግ ጀምሮ ለእንስሳት ሀብቱ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑ እንደሆን ያስረዳሉ። አሁን በሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብሩ የተጀመረውን የተቀናጀ ሥራ ማስፋትና ማጠናከሩ ወሳኝ እንደሆነ ነው ያስገነዘቡት።

ማዕከሉ የኢትዮጵያ መንግሥት የጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር እንዲሳካ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸው፤ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሌማት ትሩፋት ያሳየው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን አስታውቀዋል። ይህም ሀገሪቱ ያላትን የእንስሳት ሀብት ምርታማነት ለማሳደግ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ያመለክታሉ። ለዚህም ምርምር ማዕከሉ በቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስና አዳዲስ አሠራሮችን ተደራሽ በማድረግ በኩል አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ሲሉ አስታውቀዋል።

የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር እንስሳት በቂ መኖ እንዲያገኙና የጤና እንክብካቤ እንዲደርግላቸው እንዲሁም የእንስሳት ዝርያ ማሻሻልን መሠረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዘርፉን ለማሳደግ የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው ይናገራሉ። በተጓዳኝም የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር የምርምር ተቋማት የተሻለ ቴክኖሎጂዎችን እንዲያፈልቁና እንዲያስተዋውቁ እድል እንደፈጠረላቸው ያስረዳሉ። መርሃ-ግብሩ የምርምር ማዕከላት የእንስሳት ሀብት ምርትና ማርታማነት ለማሳደግና የመኖ አቅርቦት እጥረትን ለማቃለል የበለጠ ምርምር እንዲደረግ የሚያበረታታ ነው ብለዋል።

ዶክተር ኡልፍነህ የሌማት ትሩፋት መርሀ-ግብሩ ለእንስሳት ሀብት ምርታማነት ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ ቀደም ሲል በስፋት ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮች እንዲቃለሉ ያግዛል ሲሉም ያመለክታሉ። በተጨማሪም በምርምር ማዕከሉ የፈለቁ ቴክኖሎጂዎችንና መረጃዎችን ለአርሶ አደሩ በማድረስ የዲቃላ ከብቶች የአያያዝ፣ የአመጋገብና የጤና እንክብካቤ ሥልጠና በመስጠት ልምድ እንዲያካብቱና ለሌሎች ምሳሌ እንዲሆኑ ከማድረግ አንፃር አመርቂ ውጤት እንዳስገኘም ይናገራሉ።

እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ በመርሃ ግብሩ የቴክኖሎጂ የማስተዋወቅ እና የቅድመ ማስፋፋት ሥራዎች በመካሄዳቸው የሚያበረታታ ገበያ በመፈጠሩ የቴክኖሎጂ ፍላጎት ጨምሯል። በወተት ላሞች ቴክኖሎጂ የተጠቀሙ አርሶ አደሮች ገቢያቸው በመጨመሩ ኑሯቸውን ከማሻሻል አልፈው እርባታቸውን ወደ ገበያ-ተኮር በማሸጋገር ላይ ይገኛሉ። በማሕበር ተደራጅተው ዘመናዊ የወተት ከብት ርባታ ለጀመሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ዲቃላ ጊደሮችን በተመጣጣኝ ዋጋ በመስጠት የምክር አገልግሎት ድጋፍ ተደርጓል። ለብሔራዊ ሰው ሠራሽ የእንስሳት ማራቢያ ማዕከል አባለዘር እንዲሰበስቡ ኮርማዎች ተሰጥተዋል።

አርሶ አደሮች ለእርሻ አገልግሎት እንዲጠቀሙባቸው ወይም እንደ ፍላጎታቸው አድልበው ለሥጋ ለመሸጥ እንዲችሉ ወይፈኖች ተኮላሽተው ተሰጥቷቸዋል። አካባቢው ለአርሶ አደሮች የወተት ምርት ግብይት የተመቻቸ ስለሆነ ከዘመናዊ የወተት ከብት ርባታ ጋር እንዲተዋወቁ ዲቃላ ጊደሮች ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።

ለዲቃላ ከብቶች የተሻሻለ አያያዝ ፣ አመጋገብና ጤና ክትትል ስለሚያስፈልግ በቅርብ ክትትል 75 በመቶ የውጭ ደም ያላቸው እርጉዝ ጊደሮችን ለሆለታ አካባቢ አርሶ አደሮች ተሰራጭተዋል ሲሉም ይናገራሉ። ማዕከሉ በቀጣይ መርሃ ግብሩ በመላው የሀገሪቱ አካባቢዎች በስኬታማ ሁኔታ እንዲተገበር የበኩሉን ኃላፊነት እንደሚወጣ ነው ያስገንዘቡት።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በሌማት ቱሩፋቱ ከአንድ የተሻሻለ ዝርያ ካላት ላም በቀን ከ35 እስከ 42 ሊትር ወተት ለማግኘት እየተሠራ ነው

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You