ለጥያቄዎቻችን መልስ መስጠት የተገባን እኛው ነን!

የዛሬው ጽሑፉ ዋና ዓላማ፤ ጥቂት ጥያቄዎች አንስቼ አንባቢ የመፍትሔ መልስ ጥቁምታውን እንዲሰነዝር፤ የሚመለከተው አካልም ጥያቄዎቹ ተገቢ ናቸው ብሎ ካመነባቸው ተግባራዊ ምላሽ እንዲሰጥባቸው ነው፡፡

ልዩነት

* የፖለቲካ እሳቤ በአመለካከትና በፍላጎት ልዩነት መዋገን እንጂ፤

* እንደቃየል የሚሰደዱበትና የሚቅበዘበዙበት መሆን አለበት እንዴ?

ፖለቲካዊ ጥያቄዎች

* ዛሬ ሁሉም ሰው ለምን ፖለቲከኛ ሆነ?

* ፖለቲካ ሙያ ከመሆን ወጥቶ ለምን ማጀት ድረስ ገባ? ለዚህ ተጠያቂው ማን ነው?

* ፖለቲካ በእኛ ሀገር ሲሆን በሴራ መተባተብ፣ በሸውራራ ትርክት መናቆር፣ በክብረ ሕሊናና በሥጋ መበቃቀልና መገዳደል ለምን ሆነ? ለምን ይህንን መሰናከል ማለፍ ተሳነን?

* የሀገራችን ፖለቲካ ባሕል የጎደለው ምን ይሆን?

  • መተማመን መጥፋቱ ነው?
  • የሥልጣን ጥመኝነቱ ነው?
  • የዕውቀትና የአመራር ብቃት ማነስ ነው?
  • ፖለቲካ ስለማይገባንና ስለማይገባን ነው?
  • ፖለቲካ በራሱ ፖለቲካ ስለሆነብን ነው?

* ችግሩ ምንድን ነው? ማን ነው ለእነዚህ ጥያቄዎች ብዙኃኑን በአብላጫ የሚያስማማ መልስ የሚመልሰውና የሀገሪቱን አውራ ችግር የሚቀርፈው?

አርነት የሚሻ

እኛ የመኖር ሕልውናችን ተናጥቦ፤ የሥጋና የመንፈስ ምቾት ርቆን፤ ጦርነት፣ ስደት፣ መፈናቀል፣ ረኃብ፣ ሙስና፣ ዘረኝነት፣ በጎጥ ውስጥ ተሸሽጎ መኖር፣ በመንጋ ማሰብ…. እንደ ምርጥ ዘር በዙ፡፡ እነዚህና መሰል ክፉ ድርጊቶች በሀገራችን ውስጥ እኩይ መናፍስት መስለው ልቦናቸው በቆሸሹ ሰዎች እያደሩ ሕዝብን ለመከራ፤ ፤ለችግርና ለሞት ይዳርጋሉ፡፡ ታዲያ እነዚህ እንደመናፍስት እየተጣቡን እስከመቼ ድረስ በሀገራችን ውስጥ ዘና ባለ ስሜት ይኖራሉ?

ምን ነካን

ብዙ ብዙ አርዓያ የሚሆኑን የሀገር መሪዎች አሉን፡፡ ቢያንስ ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ እንኳ ጥለውልን ያለፉት አርዓያነትን ብናጤነው፤ እጃቸውን ያልሰጡት በሥጋቸው ብቻ ሳይሆን በሐሳብና በመንፈሳቸው ጭምር ነበር፡፡ ዛሬ እኛ በመንፈስ አርዓያነታቸውን ስላልተከተልን ይሆን የውስጥ ጥንካሬአችን፣ ችግርን የማሸነፍ ወኔ፣ ከአቀረቀርንበት ቀና ብሎ የመሄድ ድፍረት፣ ሀገርን ወዶ ማገልገልና በሀገር የመኖር ስሜት እንዲሁም ራስን ከድኅነት የማላቀቅ ሐሞት የነጠበብን፡፡ እንዲህ የመከንነውና እያደር የኮሰመነው ለምን ይሆን?

ድርሻ

ከዚህች ሀገር ጥቁር አፈር የበቀሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ከድርቅ፣ ከመፈናቀልና ከስደት ያልተፈረጁ ብዙኃን ዜጎች አሉ፡፡ ከማኅፀን ጀምሮ እስከ ሽምግልናም ድረስ መራር የሕይወት ጽዋን የሚጎነጩ አያሌ ናቸው፡፡ እነዚህ ከዓይንና ከምጽዋት የተሰወሩ ፍጹም ድኆች፤ ከርጥብ አራስ እስከ አረጋውያን የጎዳና ተዳዳሪዎችና ነዳያን የዜግነት ድርሻቸው የት ነው ያለው?

በዚህ ሀገር ላይ

* ዛሬ ላይ የተማረ ሰው የኑሮ ልኩን ማን ነው የሚያስተካክለው?

* የመለያየታችንን የገደል አፍ ስፋት ማን ነው የሚያጠበው?

* ነጋዴ ላይ ጣልቃ የሚገባ ሥርዓት መች ይፈጠራል?

* ፖለቲከኞቻችን እንዲህ የገነነ የንዋይና የሥልጣንን ፍቅር ከየት አመጡት?

እውነቱ የቱ ይሆን?

መጫኛ ያዥ፣ መሬት ገፊ፣ ገረድ፣ ባሪያ፣ ፉጋ፣ ፋቂ፣ ቀጥቃጭ፣ አንጥረኛ፣ ቡዳ፣ ጭሰኛ፣ ጨዋ፣ ነፍጠኛ፣ ሸማኔ፣ አዝማሪ፣ … መኳንንት፣ መሳፍንት፣ ልዕልት፣ ልዑል፣… ብሎ ጥንቱን የሰው ሰውነቱ ተክዶ በተኖረበት ሀገር፤ እንደሰው፣ እንደኅብረተሰብና እንደ ሕዝብ ከአንድነትና ከእኩልነት፤ ይልቅ ተከፋፍሎና ተበላልጦ ለኖረ ሕዝብ፤ ዛሬ በብሔር ተከፋፈልንና ብሔርተኝነት በሀገር ላይ መጣ ተብሎ እዬዬ መባሉ እውነት ይሆን?

መበቃቀል

በድሮ ግብር መበቃቀል ካለ ዘረ አዳም አይተርፍም፡፡ ለምሳሌ ቴዎድሮስ ባጠፋ ቋራ የሚቀጣ፤ ዮሐንስ ባጠፋ ትግሬ የሚቀጣ፤ ምኒሊክ ባጠፋ ሸዋ የሚቀጣ፤… መሆን የለበትም፡፡ ኢ- ምክንያታዊ ነውና፡፡ ግብፅን፣ ኑቢያን/ ሱዳንን/፣ የመንን እና ሕንድ ድረስ ዘልቀን… ማስገበርና ማስተዳደራችን ታሪክ ዘግቦታል፡፡ እነርሱ ግን ዛሬ በትናንት ታሪካችን መጣንባችሁ አላሉንም፡፡ እንዲሁም ኢጣሊያንም ከትናንቱ እጅግ ብታይልም የመሪዎቿን ስህተት አረመች እንጂ ወዮውላችሁ አላለችም፡፡

እኛም በዛሬ ፖለቲካችን ትናንት ባልኖርንበት ዘመን በተሠሩ ስህተቶች ቂም ተቆጣጥረን ታሪክ ለማወራረድ ወደመበቃቀሉ ከኼድን ከዚህ ወደባሰና ወደከፋ አዘቅት ይወስደናል፡፡ ከሰውነት በታችም ያወርደናል፡፡ በዚህች ጥንታዊትና ትልቅ ሕዝብ፣ ነባርና ታሪካዊት ሀገር እንዲሁም አንዱ ከአንዱ ጋር ፍጹም በሆነ መንገድ በጋብቻና በሌላም የተጋመደና የተዋሐደ ሰፊ ሀገር ልንኖር ነው ተፈጥሮ የጠራችን፡፡

እኛ የዛሬ ነን ከእኛ የሚጠበቀው ለዚህች ዓለም በጊዜያችንን በሠላም፣ በደስታና በተስፋ በመኖር የዛሬ ዘመናችንን በረከት ማጣጣም ነው፡፡ በትናንት የኑሮ ዘይቤው የዛሬ ሕልውናችንን ማናጠብ፣ ማጠየም አይገባም፡፡ ይህም ለነገው ትውልድ ጥሩ መሠረት እንድንጥል አያደርገንም፡፡ ሕይወትን በቀላል ለመኖር ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም የተባለውን ሐሳብ ገንዘብ ማድረግ አይበጅም ?

ሕገ መንግሥት

የዛሬን ሕገ መንግሥት የፈጠሩት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የቀደሙ ሕገ መንግሥታት ናቸው፡፡ ዛሬ ሀገር ለመታደግ አንድ መንገድ ብቻ ያለ አስመስሏል፡ ፡ ርሱም አዲስ ሕገ መንግስት መቅረጽ የብዙኃን እሳቤ ይመስላል፡፡ ቢያንስ የተወሰኑ አንቀጾችን ለማሻሻል ጥሩ የሚባል ግንዛቤ ያለ አልመስል ብሏል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን በምንም መልክ ይቀረጽ ሕገ መንግሥት ብቻውን ፋይዳቢስ ነው፡፡ በሰነድ ብቻ የሀገር ችግር አይፈታም፡፡ ሌላው ቢቀር ባለው ሕገ መንግሥት ላይ የሰፈሩ ምርጥ ምርጥ አንቀጾች/ሐሳቦች እንኳ በቅጡ አልተተገበሩም፡፡

በሕገ መንግሥት ፈንታ እግዚአብሔር በጣቶቹ ጽላት ላይ ጽፎ ለሙሴ የሰጠው አሥርቱ ሕግ ለሀገር መተዳደሪያነት ብንጠቀምበት ተግባራዊ አይሆንም፡፡ መጀመሪያ ሰው በሰውነቱ የሚከበርና የሚኖር፤ ሥርዓትና ሕግ የሚያከብር፤ በፍትሕ የሚተዳደርና ርትሕንም የሚያውቅ መሆን አለበት፡፡ ሕግ ፍትሐዊነትን ተግባራዊ በማድረግ የሚጸና እንጂ የነጠረ ሕግ ብቻውን ሥርዓትና ፍትሕን አያመጣም፡፡

ሕግ በቁሙ ብቻውን አይጠቅመንም፣ ውጤታማም አንሆንበትም፣ አይታደገንም፡፡ ለምሳሌ ሙስናን በሀገር ላይ ለመዋጋት አትስረቅ ከሚለው የታላቁ መጽሐፍ ሕግ በላይ ምን ሊመጣ ችላል? ይህ ሕግ በየቤተ እምነቱ አለ፤ ግን ሌብነቱ በየቤተ እምነቶችና በየመንግሥት ተቋማት የፀና ነው፡፡ የጽሑፍ ሕግ ብቻውን የትኛውንም ግለሰብ ሆነ ተቋም አይገዛም፤ ለዚህ ቢያንስ ነጻና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሕግ አስፈጻሚን ይሻል፡፡

የነጠረ ርዕዮተ ዓለም ብቻውን አርነት አያወጣም፡፡ ሰብዓዊነት፣ ንጹሕ ልቦና፣ ፍትሕና ርትሕን መያዝ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ደግሞ በዛሬ ልቦናችን አስርቱን የሙሴ ሕግ ለሀገር መተዳደሪያ ብንጠቀምበት ከመበደልና ሕግን ከመተላለፍ አናመልጥም፡፡ ኃይለ ስሜት፣ አዕምሮ፣ ሕሊና፣ ልቡና የነፍስ ዕውቀት፣ ሕግ፣ ፍትሕ፣ ርትሕ… ታድሎን ሰው መሆን ተስኖናል፡፡

የሰው ልጅ ከሕግ በላይ ነው፡፡ ሰውን የሚገዛው ሕግ ሳይሆን ሕሊናው ነው፡፡ ሰውነትን ማክበርና መቀበል፤ በሰው ሞራላዊ ሕግና ፍትሕ መገዛት ቀዳሚ ተግባር አይመስላችሁም ? ምክንያቱም ሰው በልቦናው ሰሌዳው ላይ የታተመለት የሞራልና የተፈጥሮ ሕጉ ሲሳሳና ሲጠፋ የጽሑፍ ሕግ እያጠነከረ ያመጣል፡፡

ለዚህ ሀገር ሕግ በየጊዜው መቅረጽ ነው ወይንስ በሃይማኖት፣ በባሕል፣ በሀገር መልካም ዕሴቶች እየተገነባ በተፈጥሮ የሰውነት ልክ ሕዝቡን አድርሶ እንደሰው የተወሰነ ሕግ ለስሁትነቱ ማስቀመጥ አይሻልም?

መልስ መስጫ

ከላይ ለቀረቡ ጥያቄዎች በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በነፃ ሐሳብ ዓምድ ስር መልሶቻቸውን ብትሰጡ በቀላሉ ይደርሰኛል፡፡ ሌላ አማራጭ ብትጠቀሙም በተዘዋዋሪ አገኘዋለሁ፡

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You