የፖለቲካ ባሕላችን የሚዘምነው በውይይትና በውይይት ብቻ ነው!

 

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በግጭት ምክንያት ብዙ ጉዳት አስተናግዳለች፣ አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ችግሮች መኖራቸውን መሸሸግ አይቻልም። እነዚህ ሀገርና ሕዝብ ላይ የተጋረጡ ችግሮች አሳሳቢ ደረጃ የደረሱት የፖለቲካ ልዩነቶችን በማጥበብ ውይይትና በንግግር በእንጭጩ ባለመቅጨታችን ነው፡፡

አሁን ላይ በሀገሪቱ እየታዩ ያሉ ችግሮች ምንጫቸው ሕዝብ ሳይሆን የልዩነት ሀሳቦች አራማጆች በመሆናቸው ይህን አስተሳሰብ ለመቀየር እና ለሀገር አንድነት እና ብልጽግና በጋራ ለመሥራት ውይይቶች ይበልጥ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል። ኢትዮጵያውያን ጠንካራ መተማመንን በመገንባት የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች በጋራ መከላከል ይችሉ ዘንድ በችግሮቻቸው ዙሪያ በግልፅ የመነጋገር ባሕልን ማዳበር ግድ ነው። መወያየት ሕዝቡ በሚገጥሙት ፈተናዎችና የወደፊት ተስፋዎቹ ላይ ተነጋግሮ መፍትሔ ሊያመነጭበት የሚችል ባሕል ሆኖ ሊቀጥል ይገባዋል።

ሰሞኑን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጀምሮ በሀገር ጉዳይ ላይ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር የተካሄዱትን አይነት ውይይቶች እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ሊወርዱ ይገባል።

በምሑራንንና ፖለቲከኞችን ጨምሮ በዜጎች መካከል ገንቢ ውይይቶችን መልመድ በተለያየ መንገድ በሕዝቡ ውስጥ የሚነሱ ሃሳቦችን፣ ጥያቄዎችንና ግርታዎችን ወደአዳራሽ በማምጣት ለችግሮች መፍትሔ በጋራ ለማፈላለግ ዓይነተኛ ሚና አለው። ሀገራዊ መግባባት ተቀራርቦ ከመነጋገር ነው የሚጀምረው። መነጋገር፣ መቀራረብ እርስ በእርስ ለመተማመን ትልቁ ርምጃ ነው።

መጠራጠሮችን በማስወገድ ለሀገራችን እና ለሕዝባችን ሀገር ከሚከፋፍል ነገሮች ወጥተን በሀገር ጉዳይ አንድ እንድንሆን ይጠቅመናል። የተጀመሩ የሠላም ስምምነቶች እንዲሁም ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች የበለጠ መጽናት ይኖርባቸዋል።

በተለያየ መንገድ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ አካላትም በሀገራዊ የምክክር መርሐ ግብሩ ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ግቡን እስኪመታ ድረስ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

በዚህ ወቅት ስለ ሠላም መወያየትና መነጋገር እንዲሁም ሀገራዊ መግባባትን መፍጠር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባና ከምንግዜውም በላይ አስፈላጊ ጉዳይ ነው።

በቀጣይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሠላም መሥራት፣ ስለ ሠላም መወያየትና ችግሮችን በንግግር የመፍታት ልምድ የበለጠ መዳበር አለበት። በሀገራችን የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ ሠላምና መረጋጋት እንዲመጣ፣ የሰዎች ሰብዓዊ መብት ተከብሮ እንዲኖር ምሑራን፣ የሲቪክ ማኅበራትና ፖለ ቲከኞች ደግሞ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት አለ ባቸውም።

መንግሥትም ዘላቂ ሠላም መገንባት የሚያስችሉ ውይይቶች በተከታታይነት በማካሄድ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል ሚናውን ሊወጣ ይገባል።

የሀገራችንን ሠላም ዘላቂነት የምናረጋግጥበትን መንገድ ችግሮቻችንን በውይይትና በንግግር መፍታት ስንችል ነው። በመሆኑ ምሑራን፣ ፖለቲከኞችና የሃይማኖት መሪዎች የተጀመሩ ውይይቶችን በመደ ገፍ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ።

የሠላም ጉዳይ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ግድ ይላል። ከመገፋፋት ይልቅ መፎካከርን፣ ከመጓተት ይልቅ መተባበርን በማጎልበት የጥላቻ እና የሴራ ፖለቲካ በወንድማማችነት እና በእህትማማችነት የትብብር ፖለቲካ እንዲተካ ያላሰለሰ ጥረት ያስፈልጋል።

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን ስር እንዲሰድ በተለይም ከለውጡ ጀምሮ ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል ነፃና ገለልተኛ ተቋማትን መፍጠር ዛሬም ዋና ተግባር መሆን አለበት። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የመሳሰሉ በሕዝባችን ዘንድ አመኔታን ያተረፉ ሀገራዊ ተቋማት ዴሞክራሲያዊነትን አሳድገዋል።

በሀሳብ የተሸነፈ ሁሉ ጦር የሚመዝበት የተዋጊነት ባሕል ተወግዶ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት የፖለቲካ ባሕላችን እንዲሆን ሁሉንም ወገኖች አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን ለማፅናት ፅኑ መሠረት ናቸው።

አካታች በሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ከላይ እስከ ታች በሚገኙ የአስፈፃሚ እርከኖች ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ተካተው ለሀገራቸው የድርሻቸውን እንዲወጡ በማድረግ የሀሳብ ብዝኃነትን ለማስተናገድ ያለው ዋጋ ቀላል አይደለም።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የጀማመራቸው እንቅስቃሴዎችም ሁሉም ሀሳቦች ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት እንዲመጡ በማድረግ ከትውልድ ትውልድ እየተንከባለሉ ከእኛ ላይ የደረሱ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ የጎላ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው እምነት ተጥሎበታል። ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለኮሚሽኑ ሥራ መሳካት ከሚያደርጉት መልካም ትብብር ባሻገር ሀገር የመምራት ዕድል የተረከበው መንግሥትም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት የተጀማመሩ ጥረቶችን ማጠናከር ይገባዋል።

ሁሉም ችግሮች በውይይትና በድርድር መፍትሔ እንደሚያገኙ በማመን መቀራረብ፣ መሰማማት፣ መደማመጥ እንዲሁም ግትርነትን ማስወገድ ያልተግባባንባቸውን ሀገራዊ ጉዳዮች ወደ መፍትሔ ይወስዳሉ።

በሀገራችን የሚስተዋሉ የፖለቲካ ልዩነቶችን ለመፍታት ግጭት ምርጫ ሊሆን አይገባም። የትኛውም የፖለቲካ ልዩነት በግጭት መፍትሔ አግኝቶ አያውቅም። በኢትዮጵያም የፖለቲካ ልዩነቶችን ለመፍታት መወያየትና ተነጋግሮ መግባባት ብቸኛው አማራጭ ነው።

ተወዳዳሪ ሀሳብ በመያዝ እና የውይይትን ባሕልን በማዳበር ለፖለቲካችን መዘመን የድርሻችንን በመወጣት ሁለንተናዊ ብልፅግናችንን እናረጋግጥ!

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You