የጎበዞቹ ምክር ለልጆች

ሰላም እንዴት ናችሁ ልጆችዬ? ሳምንቱን በጥሩ አሳለፋችሁ?ጥናት እና ትምህርት እንዴት ነው? ወላጆቻችሁስ እያገዟችሁ ነው? እናተስ እገዛ እንዲያደርጉላችሁ ትጠይቃላችሁ? በጣም ጥሩ! እናንተ ጎበዞች ስለሆናችሁ ትምህርታችሁን በጥሩ ሁኔታ እያስኬዳችሁት እንደሆነ እገምታለሁ። የእናንተ ወላጆች ነገ ጥሩ ቦታ እንድትደርሱላቸው ስለሚፈልጉ በሚገባ እንደሚያግዟችሁም ተስፋ አደርጋለሁ።

ልጆችዬ ኢትዮ ሮቦ ሮቦቲክስ የትምህርትና የስልጠና ማዕከል ከአጋር ተቋማት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ‹‹ሁለተኛው የአፍሪካ ሮቦቲክስ ሻምፒዮንሽፕ ›› ውድድር በርካታ ተማሪዎች እና ወላጆች ተገኝተው ነበር። እኛም በዚህ ውድድር ላይ ተሳትፎ ካደረጉት ተማሪዎች መካከል ለእናንተ ልምዳቸውን እንዲያካፍሏችሁ በማሰብ አነጋግረናቸዋል። ከመልዕክታቸው ብዙ እንደምትማሩ እናምናለን። ያስተላለፉት መልዕክትም እንሆ..

ምስጋናው ታምራት ይባላል። የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ሬነሳንስ በተባለ ትምህርት ቤት ነው የሚማረው። እርሱና ጓደኞቹ የሰሩት ሮቦት እቃ ማንሻ ነው። ምስጋናው ለወደፊቱ አንጂነር መሆን ይፈልጋል።ታዲያ የነገ ምኞቱን ለማሳከት ዛሬን ትምህርቱን በጥሩ ሁኔታ እየተከታተለ ይገኛል። ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ትምህርቶችንም ከትምህርቱ ጎን ለጎን እየተማረ ነው። ወላጆቹም ድጋፍ እያደረጉለት ሲሆን ‹‹ልጆች አዳዲስ እውቀቶችን እንዲያገኙ ጠንክረው መማር አለባቸው›› ይላል።

ሌላኛው በውድድሩ ላይ ያገኘነው ተማሪ እዮብ በፍቃዱ ይባላል።እድሜው አስር ነው። የአራተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን በአቡነ ጎርጎሪዎስ ትምህርት ቤት ነው የሚማረው።በዘንድሮው የአንደኛ የትምህርት መንፈቅ ዓመት አንደኛ መውጣቷ። ሳይንቲስት ለመሆነ ፍላጎት ያለው ሲሆን በትርፍ ሰዓቱ በቤት ውስጥ የተለያየ የፈጠራ ሥራዎችን ለመሥራት ይጥራል። ሌሎች ተማሪዎች እንደ እርሱ አንደኛ እንዲወጡ በርትተው ማጥናት እንዳለባቸው ይመክራል።

ልጆችዬ! ተማሪ እዮብ ሌላም ምክር አለው። ምክሩ ምን መሰላችሁ ? ልጆች በፍጹም ጊዜያቸውን በስልክ በጌም (ጨዋታ) እና በማይጠቅማቸው ነገር ማሳለፍ የለባቸውም ይላል። በተጨማሪም ወላጆች ልጆቻቸው የሚፈልጉትን ነገር በመጠየቅ ለነገ ሕይወታቸው የሚጠቅማቸውን ነገር እንዲያደርጉም ምክሩን ይለግሳል።

ናታን በፍቃዱ ዕድሜው አስራ ሁለት ዓመት ነው። የሚማረው ደግሞ በአቡነ ጎርጎሪዎስ ትምህርት ቤት ነው።በውድድሩ ላይ ሮቦቶችን ከጓደኞቹ ጋራ በመሥራት በውድድሩ ላይ ተሳትፏል። እርሱና ጓደኞቹ ሮቦቱን ለመሥራት የሁለት ወራት ጊዜ እንደፈጀባቸው ይናገራል። የሮቦት ኢንጂነር የመሆን ህልም ያለው ተማሪ ናታን፤ በትምህርት የሚያገኘውን እውቀት በቤት ውስጥ በካርቶን ላይ በመሥራት እንደሚለማመድ ይናገራል።ቤተሰቦቹም እገዛ ያደርጉለታል። ናታን በመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ሁለተኛ መውጣት የቻለ ጎበዝ ተማሪ ነው።

በርትቶ ስላጠና ጥሩ ውጤት ማምጣት ችሏል። ሌሎች ተማሪዎች እንደርሱ ጎብዘው ትምህርታቸው ላይ መበርታት እንዳለባቸው ይመክራል። በተጨማሪም በራሳቸው ተነሳሽነት ማጥናት እና ወደፊት መሆን የሚፈልጉትን ነገር በመለየት ጠንክረው መማር እንዳለባቸው ይናገራል።

ሌላኛውን ተማሪ እናስተዋውቃችሁ አይደል ልጆችዬ? በጣም ጥሩ። በረከት ታምራት ይባላል። የአስራ ሶስት ዓመት ታዳጊ ነው። ለወደፊት የአውሮፕላን አብራሪ(ፓይለት) የመሆን ፍላጎት አለው። ታዲያ እርሱ ነገ ፓይለት ለመሆን ዛሬን ምን ማድረግ እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል። ከትምህርቱ ጎን ለጎን አውሮፕላን አብራሪ ለመሆን የሚረዱ ጽሁፎችን ያነባል። በተጨማሪም ቤት ውስጥ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት ሙከራዎችን ያደርጋል።

በዚህ ውድድር ከተሳተፉ ሴት ተማሪዎች መካከል ተማሪ የሁዳድ አብደላ አንዷ ናት። የአስራ አንድ ዓመት ተዳጊዋ በቀኝ አዝማች አንዳርጌ ትምህርት ቤት ትማራለች። የአራተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን በዘንደሮው የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት አንደኛ እንደወጣች ትናገራለች። ለወደፊት የሮቦት ኢንጂነር የመሆን ፍላጎት አላት። ዛሬ ላይ ከሮቦት ጋር የተያያዙ ትምህርቶችን ከትምህርቷ ጎን ለጎን እየተማረች ትገኛለች። ልጆች ወደፊት መሆን የሚፈልጉትን ለማሳካት በትጋት ትምህርታቸውን መከታተል እንዳለባቸው ትመክራለች። እርሷ ነገ ተምራ በቴክሎጂው ዘርፍ ሀገሯን ለማገልገል ጥረት እያደረገች ትገኛለች።

ናታን ፍቅሩን እናስተዋውቃችሁ አይደል? የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን የሮቦት ጎማዎችን በመሥራት ከጓደኞቹ ጋር በጋራ በመሆን በውድድሩ ላይ ተሳትፎ አድርጓል። በትምህርቱም የደረጃ ተማሪ ከሚባሉት መካከል ነው። በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በመነጋገርና በኅብረት በመሥራቱ ነገሮች እንደቀለሉት ይገልፃል። ሌሎች ተማሪዎችን በኅብረት በማጥናት እና በመተጋገዝ ብዙ እውቀቶችን ማግኘት እንደሚችሉ ይመክራል።

ልጆች በውድድሩ ላይ ተሳታፊ ከነበሩት ተማሪዎች መካከል ጎበዝ የሆኑ ልጆችን በማነጋገር ልምዳቸውን እና ምክራቸውን አጋርተናችኋል። በተለይም በትምህርታቸው እንዴት ጥሩ ውጤት ማምጣት እንደቻሉ ልምዳቸውን በሚገባ ተናግረዋል ብለን እናስባለን። ከእናንተ መካከል በትምህርቱ ደከም ያለ ተማሪ ካለ ትምህርቱ ላይ የበለጠ ማተኮር እንዳለበት ብሎም የወላጆቹን እገዛ መጠየቅ እና በኅብረት በመሥራት ውጤት ማሻሻል እንደሚቻል እንደተገነዘባችሁ ምንም ጥርጥር የለኝም። ልጆችዬ በሌላ ጊዜ ጥሩ ውጤት ስላመጡ ጎበዝ ልጆች የምንላችሁ ይኖረናል። ለዛሬው በዚሁ እንሰነባበት አይደል? እስከ ሳምንት በቸር እንዲያገናኘን በመመኘት ለዛሬው በዚሁ አበቃን።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን መጋቢት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You