የሁቲዎች ጥቃት በሀገራችን የኤክስፖርት ንግድ ላይ ይዞት የመጣው ስጋት

በቀይ ባሕር በተቀሰቀሰው ጅኦፖለቲካዊ ቀውስ ሳቢያ እንደ ቡና ያሉ የውጭ ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ አዳጋች በመሆኑ ላኪዎችና በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቡና አምራቾች ላይ አደጋ ደቅኗል። የአዲስ ፎርቹን ጸሐፊ አክሳህ ኢታሎ በዚያ ሰሞኑ ባስነበበን መጣጥፍ ለኢኮኖሚው ከመርግ የከበደ መርዶ አርድቶናል። ወደብና ባሕር አልባ መሆናችን ሳያንስ በቀይ ባሕር ኮሽ ባለ ቁጥር ህልውናችንና ኢኮኖሚያችን ምን ያህል ለአደጋ እንደሚያጋልጥ ያመላከተ ነው። የሁቲ አማጽያን በቀይ ባሕር ላይ በሚፈጽሙት ተደጋጋሚ ጥቃት የተነሳ የጭነት መርከቦች በዚህ መስመር መቅዘፍ ቀንሰዋል አልያም ከእነ አካቴው አቁመዋል።

የሁቲዎችን ጥቃት በመሸሽ በደቡባዊ አፍሪካ ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ ዙሪያ ጥምጥም ለመጓዝ በመገደዳቸው የጭነትና የዋስትና ዋጋ እጅግ አሻቅቧል። ንሯል። በዚህ የተነሳ ቡና ተቀባይ ሀገራት ፊታቸውን ወደ ብራዚል በማዞራቸው ከ3ሚሊዮን ኪ.ግ በላይ ቡና በጅቡቲ ወደብ ተከማችቶ ይገኛል።የቀይ ባሕር ጉዳይ በቅርቡ መፍትሔ አግኝቶ መውጣት ካልቻለ የቡና ላኪዎችና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቡና አምራች ገበሬዎች ህይወት ላይ የከፋ ችግር ያስከትላል። በጦርነት፣ በማዕቀብና በብድር እጦት ክፉኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ገጥሞት እየተፍገመገመ ላለ ኢኮኖሚ አንደኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኛ የሆነው የቡና ኤክስፖርት ላይ የገጠመው ከባድ ፈተና ኢኮኖሚውን ከድጡ ወደ ማጡ ይከተዋል።

ኢኮኖሚው በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተቀሰቀሰው ጦርነት ሀገራችን ከአግዋ ተጠቃሚነት በመውጣቷ፤ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመቀዛቀዙ እና ቱሪዝም በብርቱ መዳከሙ ሳያንስ በአማራና ኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ጦርነት ደግሞ በእንቅርት ላይ ቆረቆር እንዲሉ ሆኗል።የኑሮ ውድነቱም በሰዓታት ጣራ እየነካ ዜጎችን በእጅጉ እያማረረ ባለበት ነው እንግዲህ የኤክስፖርት ንግዳችን ቅርቃር ውስጥ የገባው። በዋጋ ግሽበቱና እሱን ተከትሎ በመጣው የኑሮ ውድነት የዜጎች የሸመታ አቅም መዳከሙና መቀዛቀዙ ኢኮኖሚውን ታማሚ አድርጎታል። በአራዶች ቋንቋ አየሩ ተመቷል።ገቢ ቀንሷል።ሀገራዊ ቁጠባው እጅ አጥሮታል። በዚህ ቀውጢ ሰዓት ነው ኤክስፖርታችን ደግሞ ያልተጠበቀ ፈተና ውስጥ የገባው።

ወሳኝ የሆነውና ከዓለም ንግድ እስከ 15 በመቶ ይተላለፍበት የነበረው ቀይ ባሕር በሁቲ አማጽያን ተደጋጋሚ ጥቃትና እገታ የተነሳ በመስተጓጎሉ የኢትዮጵያን የውጭ ንግድ አደጋ ላይ ጥሎታል። ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች በወደቦች ለወራት መቆማቸው ሳያንስ ግዙፍ የጭነት መርከቦች በቀይ ባሕር መቅዘፍ ማቆማቸው በሀገራችን የወጭም ሆነ የገቢ ንግድ ላይ ከባድ ሳንካ ፈጥሯል።ግዙፉን የጭነት መርከብ ኩባንያ ሜርስክን እንኳ በአብነት ብንወስድ 600 የጭነት መርከቦቹ በቀይ ባሕር መቅዘፍ በማቆማቸው ከ30ሺህ በላይ ኮንቴነሮች በወደቦች እንዲከማቹ አስገድዷል።

ለዚህ ነው በሜርስክ የኢትዮጵያ ወኪል ዳኔል ዘሚካኤል መርከቦቻችን ለአደጋ በመጋለጣቸው በቀይ ባሕር በኩል የምናደርገውን ጉዞ ለማቆም ተገደናል።የሀገራችን ላኪዎችና የሎጅስቲክስ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን በሕንድ ውቅያኖስ አድርገው ወደ አውሮፓ ለመላክ የሞምባሳንና የላሙ ወደቦችን ለመጠቀም ተገደዋል።ይህ ደግሞ በቀይ ባሕር በጥቂት ሳምንታት ይጓጓዝ የነበረን ምርት ቢያንስ ወር ስለሚፈጅበት የማጓጓዣ ወጪውን ስለሚያንረው ከሌሎች ጋር ለመወዳደር አዳጋች አድርጎታል። ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚላኩ ምርቶችንም በአረቢያን ወሽመጥ በኩል ማጓጓዝ ግድ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ የተከሰተው ችግር የሀገራችንን የቡና ዘርፍ ክፉኛ ይጎዳዋል ብለውሰግተዋል።የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር በበኩላቸው፤ የኬንያን ወደቦች በአማራጭነት ለመጠቀም የዳሰሳ ጥናት እየተካሄደ ቢሆንም የወደቦቹ አቅም ውስን መሆኑና ተጨማሪ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑ ሌላው ፈተና ነው ይላሉ። የኬንያ ወደቦች የጭነት አቅም በኮንቴነር 28 ቶን ወይም 280 ኩንታል መሆኑ ቡናን ለመጫን የሚያስፈልገው፤ የጭነት መስፈርት የሚያሟላ አለመሆናቸው ሌላው ፈተና ነው። ስለሆነም አዋጭነታቸው ገና አለመረጋገጡ ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል።

የተከሰተው የሎጂስቲክስ ችግር የሀገራችንን ዋና የኤክስፖርት ምርት ቡናን ወደ አውሮፓና መካከለኛው ምሥራቅ እንዳንልክ አድርጎናል። ተቀባይ ኩባንያዎች ፊታቸውን ወደ ብራዚል ካዞሩ ደግሞ ደንበኞቻችንን ልናጣ ነው። ደንበኞች አንዴ ከእጅ ከወጡ ደግሞ መልሶ ማግኘት ፈተና ነው። ቡናን ወደ ውጭ የሚልኩት አቶ ዘላለም እሸቱ ከዚህ በፊት በአማካኝ እስከ 26 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቡና ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ይልኩ እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን የገዙትን ቡና ለመላክ መቸገራቸውን ለ”አዲስ ፎርቹን” ይናገራሉ።10ሺህ አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ቡና ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰይድ ሁሴን፤መንግሥት በቡና ኤክስፖርት ላይ ላጋጠመው ችግር አፋጣኝ መፍትሔ የማይሰጥ ከሆነ ሌላ መላ ይገኝለታል ብለው ተስፋ እንደማያደርጉ ለጋዜጣው ገልጸዋል።

ዘጠኝ እቃ ጫኝ መርከቦች እንዳሉት የሚታወቀው የኢትዮጵያ የመርከብና የሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሪሶ አማሎ በበኩላቸው፤ አጋር የጭነት መርከብ ኩባንያዎች በቀይ ባህር መቅዘፍ በማቆማቸው የድርጅታቸው አገልግሎት መስተጓጎሉን አስታውሰው፤ ችግሩን ለማቃለል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። 70ሺህ ቡና አምራች ገበሬዎችን በአባልነት ያቀፈው የሲዳማ የኅብረት ሥራ ዩኒየን ዋና ሥራ አስኪያጅ ጸጋዬ አኔቦ፤ላለፉት ሁለት ወራት ወደ ውጭ ለመላክ ጅቡቲ ወደብ ያደረስነው 3800 ኩንታል ቡና በዚያ እንደተቀመጠ ነው። በአየር እንዳናጓጉዝ የጭነት ዋጋው ከመርከብ 25 እጥፍ ይበልጣል። ይወደዳል። የምናደርገው ግራ ገብቶን ተቀምጠናል ይሉናል።

የቀድሞው የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳኒ ረዲ በዚህ ፈታኝ ወቅት ከትርፍ ይልቅ ደንበኞችን ላለማጣት ጥረት ሊደረግ ይገባል ሲሉ ያሳስባሉ።የቡና ኤክስፖርት ስትራቴጂንም እንደነባራዊ ሁኔታው መከለስና መቃኘት ያሻል። ደንበኛ አንዴ ከእጅ ካመለጠ መልሶ ማግኘት ያዳግታል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ የሶስት በመቶ ድርሻ ብቻ ያለው ሲሆን፤ የቬትናምና የብራዚል ድርሻ ግን እጅግ ከፍ ያለነው። ድርሻችን ከፍ እንዲል ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።

በሌላ በኩል የቡና ባለሙያዎችና የዘርፉ አንቀሳቃሾች እንደገለጹት፤ በ1980ዎቹ መጨረሻ የቡና ምርትና ግብይት ሒደት ለቀቅ ቢደረግም ከፖሊሲ አንጻር ግን ይህ ነው የሚባል መሠረታዊ ለውጥ ስላልታየበት በዓለም ገበያ ለሚከሰቱ አሉታዊ ተጽዕኖዎች በተደጋጋሚ ተጋላጭ መሆኑን ይናገራሉ። በዚህ ሁሉ ተግዳሮት ውስጥ ሆኖም የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምርታማነትን ለማሳደግና ተጨማሪ መዳረሻ ገበያን ለማግኘት እየሰራ ሲሆን በዓለም ገበያ ተፈላጊ የሆነውን ቡና በምታመርተው ይርጋ ጨፌም የምርምርና የልማት ኢንስቲትዩት ተከፍቷል።

በሀገራችን ቡና ወደ 6 ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ ዕድል ሲፈጥር፤ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች ደግም ሲሶውን ይይዛል። ባለፈው ዓመት 1.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አስገኝቷል። ቡና በብዛት የሚመረተው በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ መሆኑ ምርታማነቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሯል። ኦሮሚያ 59፣የደቡብ ምእራብ 15፣ሲዳማ ክልል 7 በመቶ ቀሪው ድርሻ የተለያዩ ክልሎች ነው።

አቶ ዳዊት ባደግ የዘላለም እሸቱ ቡና ላኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ከጊዜ ወደ ጊዜ የገበያ ውድድሩ እየከበደ ዓለም አቀፍ ዋጋው ደግሞ እየቀነሰ መሆኑ ሳያንስ ፍላጎቱም እየተቀዛቀዘ መሆኑ በአምራቾችና በላኪዎች ዘንድ ስጋት እየጎነቆለ ይገኛል ይሉናል። በዚህ ላይ የአውሮፓ የመድን ኩባንያዎች በቀይ ባሕር በተፈጠረው ቀውስ የተነሳ ይሰጡት የነበረውን ዋስትና በመቀነሳቸው ቡና ላኪዎችና ተቀባዮች ግራ ተጋብተዋል።

የሆነው ሆነና ሁቲዎች እነማን ናቸው?ሁቲዎች የየመን ታጣቂ ቡድን ሲሆኑ፤ መሰረታቸውም ዛይዲስ በመባል የሚታወቅ የሀገሪቱ የሺዓ ሙስሊም ነው። በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ሲቋቋሙ የወቅቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት አሊ አብደላህ ሳሌህ አገዛዝ የተንሰራፋውን ሙስና ለመዋጋት በሚል ነበር። ስማቸውንም የወሰዱት ከንቅናቄው መስራች ከሆኑት ሁሴን አል ሁቲ ነው። ራሳቸውንም ‘አንሳር አላህ’ ወይም “የአምላክ ደጋፊዎች” ብለው ይጠራሉ። በአሜሪካ መሪነት ምዕራባውያኑ ኢራቅን መውረራቸውንም ተከትሎ ሁቲዎች “አምላክ ታላቅ ነው፣ ሞት ለአሜሪካ፣ ሞት ለእስራኤል። እርግማን ለአይሁዶች፣ ድል ለእስልምና’ የሚል መፈክርን ማሰማት ጀመሩ።

እስራኤል፣ አሜሪካ እና ሰፊውን ምዕራባዊ ክፍል የሚቃወም እና በኢራን የሚመራው ‘አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ ጥምረት’ መሆናቸውንም አስታወቁ። ከሁቲ በተጨማሪ ሐማስ እና ሂዝቦላህ የዚህ ጥምረት አካል ናቸው።ሁቲዎች በአሁኑ ወቅት በባህረ ሰላጤው ወደ እስራኤል የሚያቀኑትን መርከቦች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ ያሉበትንም ምክንያት በአውሮፓ የሰላም ኢንስቲትዩት የየመን ተንታኝ ሂሻም አል ኦምሴ ያስረዳሉ።“በአሁኑ ወቅት ከኢምፔሪያሊስቶች ጋር እየተዋጉ ነው፤ የእስላም ሀገራት ጠላቶች ጋር እየተዋጉ ነው” የሚሉት ምሁሩ “ይህም ከመሰረታቸው ጋር የሚጣጣም” እንደሆነም ያስረዳሉ።

ሁቲዎች በመጀመሪያ ላይ ከፍተኛ የፖለቲካ ጥንካሬ ማግኘት የቻሉት ፕሬዚዳንት አሊ አብደላህ ሳሌህን በተኩት በፕሬዚዳንት አብድራቡህ ማንሱር ሃዲ ላይ በተነሱበት ወቅት ነው። ይህም በአውሮፓውያኑ 2014 ነው። ከቀድሞው ጠላታቸው እና ከስልጣን ከተነሱት ፕሬዚዳንት ሳሌህ ጋር ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላም እሳቸውን ወደ ስልጣን ለመመለስ አስበው ነበር። በቀጣዩ ዓመትም በየመን ሰሜናዊ ክፍል የሚገኘውን የሳዓዳ ግዛትን ተቆጣጠሩ። ይህም ዋና ከተማዋን ሰንዓን መቆጣጠር ያስቻላቸው ሲሆን ፕሬዚዳንት ሃዲንም ወደ ውጭ እንዲሰደዱ አስገደዷቸው።የየመን ጎረቤት የሆነችው ሳዑዲ አረቢያ ወታደራዊ ጣልቃ በመግባት ፕሬዚዳንት ሃዲን ወደ ስልጣን መለሰች እንዲሁም የሁቲዎችን ኃይልም ለማሸነፍ ሞከረች።ሳዑዲ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ባህሬንም ትደገፍ ነበር።ሆኖም ሁቲዎች የተሰነዘረባቸውን ጥቃት በመመከት ይዞታቸውን ማስፋት ቀጠሉ።

በአውሮፓውያኑ 2017 የቀድሞው ፕሬዚዳንት አሊ አብዱላህ ሳሌህ ወደ ሳዑዲ ጎራ ለመቀላቀል ሲሞክሩም በሁቲ ታጣቂዎች ተገደሉ። የሁቲ አማጺያን በሊባኖስ ውስጥ የሚገኘው የሺአው ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው። ሄዝቦላህም ለሁቲ አማጽያን ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮም ሰፊ ወታደራዊ ስልጠናዎችን እየሰጣቸው መሆኑን ሽብርተኝነትን የሚዋጋው ‘ዘ ኮምባቲንግ ቴሬሬዚም ሴንተር’ የተሰኘው የአሜሪካው የምርምር ተቋም አስታውቋል። ሁቲዎች ኢራንን በአጋርነት የሚያይዋት ሲሆን ሳዑዲ አረቢያም ደግሞ የጋራ ጠላታቸው ናት። ኢራን ለሁቲ አማጺያን የጦር መሳሪያ ታቀርባለች በሚል በተደጋጋሚ ብትከሰስም ታስተባብላለች።

ሁቲዎች በአውሮፓውያኑ 2017 በሳዑዲ መዲና ሪያድ ላይ ያስወነጨፉትን ባለስቲክ ሚሳኤል ያቀረበችው ኢራን ናት በማለት አሜሪካ እና ሳዑዲያ አረቢያ ይከሳሉ። በተጨማሪም በአውሮፓውያኑ 2019 ሁቲዎች የሳዑዲ ነዳጅ ማምረቻዎችን ለማጥቃት የተጠቀሙባቸውን የክሩዝ ሚሳኤሎች እና ድሮኖችን (ሰው አልባ አውሮፕላኖችን) የሰጠችው ኢራን እንደሆነች ይወሳል።ሁቲዎች መቼ በዚህ ሊቆሙ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአጭር ርቀት ሚሳኤሎችን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያስወነጨፉ ሲሆን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኢላማዎችም ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። እነዚህን መሳሪያዎች ለሁቲ አማጽያን ማቅረብ የተባበሩት መንግሥታት በኢራን ላይ የጣለውን የጦር መሳሪያ እገዳን የሚጥስ ቢሆንም ኢራን በጭራሽ ክሱን አትቀበለውም።

በዓለም አቀፍ ዕውቅና የተሰጠው መንግሥት የፕሬዚዳንቱ አመራር ምክር ቤት ነው። ፕሬዚዳንት አብዱራቡህ ማንሱር ሃዲ በአውሮፓውያኑ 2022 ስልጣናቸውን ለምክር ቤቱ አስተላልፈውለታል። ምክር ቤቱ መቀመጫውም በሳዑዲ መዲና ሪያድ ነው። ሆኖም አብዛኛው የየመን ህዝብ የሚኖረው በሁቲ አማጽያን ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች ነው። በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል ግብር የሚሰበስቡ ሲሆን የሀገሪቱንም መገበያያ ገንዘብም ያትማሉ።

የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሁቲዎች በአውሮፓውያኑ 2010፣ ከ100 ሺህ- 200 ሺህ የታጠቁ ወታደሮች እና ያልታጠቁ ደጋፊዎች እንዳላቸው ገልጿል።የሁቲ አማጽያን ሰፊውን የቀይ ባህር ጠረፍ ይቆጣጠራሉ። ከነዚህም አካባቢዎች ነው ጥቃቶቹን እየፈጸሙ የሚገኙት። እነዚህ ጥቃቶች ከሳዑዲ አረቢያ ጋር እያደረጉት ላለው የሰላም ድርድር አግዟቸዋል።“ለሳዑዲዎች የቀይ ባህር መተላለፊያ የሆነው ባብ አል ማንዳብ መዝጋት እንደሚችሉ በማሳየት በስምምነቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳረፍ ችለዋል” ይለናል ቢቢሲ።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You