በአጼ ቴዎድሮስ የተፈሩት ራስ ዳርጌ

የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ አጎት የሆኑትና በጀግንነታቸው ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስን ጭምር ያስጨነቁትና ያስደነቁት ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ ያረፉት ከ124 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 15 ቀን 1892 ዓ.ም ነበር።

ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ የሸዋው ንጉሥ የንጉሥ ሳህለሥላሴ ወሰን ሰገድ ልጅ ናቸው። ራስ ዳርጌ የደጃዝማች አስፋው፣ የደጃዝማች ደስታ፣ የፊታውራሪ ሸዋረገድ፣ የወይዘሮ ትሰሜ፣ የወይዘሮ አስካለ፣ የወይዘሮ ፀሐየወርቅ እና የልጅ ጉግሳ አባት ናቸው። ወይዘሮ ትሰሜ ዳርጌ የልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ እናት ናቸው።

ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ የንጉሥ ኃይለመለኮት ሳህለሥላሴ (የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ አባት ማለት ነው) ወንድም ናቸው። በ1822 ዓ.ም ሸዋ ውስጥ የተወለዱት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ፣ የልጅነት ጊዜያቸውን በአንኮበርና በአንጎለላ አሳልፈው ወደ ጎንደር ተጉዘው በነበሩበት ወቅት በሰላይነት ተጠርጥረው ታስረው ነበር።

ይሁን እንጂ ራስ ዳርጌ ንፁህነታቸው ታውቆ ነፃ ከወጡ በኋላ በመልካም ጠባያቸውና በጦር ሜዳ ጀግንነታቸው በንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ ዘንድ ተወዳጅነትን አተረፉ። በዚህም ምክንያት ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ ራስ ዳርጌን ‹‹ዳሩ››፣ ‹‹ዳርዬ›› እያሉ ይጠሯቸው ነበር።

የርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ ጀግንነት ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስን ጭምር ያስጨነቀ ነበር። በንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ ጊዜ ሸዋን ይገዙ የነበሩት መርዕድ አዝማች ኃይሌ ንጉሰ ነገሥቱን በመክዳት ተጠርጥረው ታስረው ነበር።

ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስም አቤቶ ዳርጌን የሸዋ ገዢ አድርገው እንደሾሙ ተናገሩ፤ ነገር ግን ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ የራስ ዳርጌን የጦር ሰፈር ሲመለከቱት በጣም የደመቀና የተደራጀ ስለነበር በጣም ተጨነቁ። ንጉሰ ነገሥቱም አቤቶ ዳርጌን አስጠርተው ‹‹ዳሩዬ ፈራሁህ! በጥንድ ጦር የሚስተውን ኃይሌን ሽሬ በነጠላ ጦር ደርበህ ሁለት ሰው የምትገለውን አንተን በሸዋ ላይ አልሾምም›› ብለው

በግልጽ ነገሯቸው። ራስ ዳርጌም የመከፋትና የቅሬታ ምልክት ሳያሳዩና ሳይከፉ ‹‹እሺ›› ብለው ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስን በትህትና እጅ ነሱ።

ልጅ ምኒልክ (በኋላ ንጉሥ ምኒልክ፣ ከዚያም ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ) ከመቅደላ አምልጠው ሸዋ በገቡና በአባታቸው ዙፋን በተቀመጡ ጊዜም፣ ራስ ዳርጌ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ወደ ሸዋ ተመልሰው ከምኒልክ ጋር ተገናኙ። ምኒልክም ሸዋ ገብተው በአባቶቻቸው አልጋ ተተክተው የሸዋ ንጉሥ ሆነው ነበርና ራስ ዳርጌ እንደመጡ ‹‹እርስዎ ቀጥታ የንጉሥ ሳህለሥላሴ ልጅ ስለሆኑ ንጉሥነቴን ልተውልዎ›› ብለው ጠየቋቸው።

ራስ ዳርጌም ‹‹አይሆንም! አባታችን ሳህለሥላሴ አልጋቸውን አውርሰው የሞቱት በቀጥታ ለአንተ አባት ለንጉሥ ኃይለመለኮት ነው፤ አሁንም የነጋሲነት መስመሩ በዚያው ባንተ በኩል ነው መቀጠል ያለበት›› ብለው ንግሥናውን እንደማይፈልጉ ተናገሩ። ከዚያ በኋላም ራስ ዳርጌና ንጉሰ ነገሥት ምኒልክ እንደአባትና ልጅ ሆነው ከ30 ዓመታት በላይ ዓመታት ኖሩ።

ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ የተለያዩ አካባቢዎችን በማቅናትና በማስተዳደር ስራ ውስጥ የላቀ ድርሻ ነበራቸው። ከእነዚህ አካባቢዎች መካከል አርሲ እና ሰላሌና አካባቢው ይጠቀሳሉ። ንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ 4ኛ እና ንጉሥ ምኒልክ በተቀያየሙ ጊዜም አስታራቂ ሽማግሌ ሆነው ያገለገሉት ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ ነበሩ። ንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ 4ኛ እና ንጉሥ ምኒልክ ደብዳቤ የሚጻጻፉት በርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ በኩል ነበር። ደጃዝማች መሸሻ ሰይፉ በሸፈቱ ጊዜም ተቆጭው፣ አስማሚውና መካሪው ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ ነበሩ።

በዓድዋ ጦርነት ወቅትም ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ለጦርነቱ ወደ ዓድዋ በተጓዙበት ወቅት የንጉሰ ነገሥቱን ቦታ ተክተው ዙፋን የጠበቁትና አገር ያስተዳደሩት ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ ነበሩ።

በመልካም ጠባያቸው፣ በታማኝነታቸው፣ በበጎ አሳቢነታቸውና በጦር ጀግንነታቸው የሚታወቁት ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ መጋቢት 15 ቀን 1892 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው ሥርዓተ ቀብራቸውም በደብረ ሊባኖስ ገዳም ተፈጽሟል።

ከላይ ያየናቸው ሁለቱ ራሶች (ራስ መኮንን እና ራስ ዳርጌ) ሁለቱም የዚህ ሳምንት ተዘካሪ ናቸው። እንደመገጣጠም ሆኖ ሁለቱም የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ቤተሰቦች ናቸው። ሁለቱም በአንድ ወር ውስጥ ለዚያውም በአንድ ሳምንት ውስጥ ነው ያረፉት። እነሆ ይህንንም ታሪክ ያስታውሰዋል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን መጋቢት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You