ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ሠላም ቀዳሚ አጀንዳ ነው። በተለይም በሠላም እጦት ምክንያት ያሰቡትን ውጥን መፈፀም ላልቻሉ፤ በድህነትና በኋላቀርነት ብዙ ዋጋ እየከፈሉ ለሚገኙ ሀገራት ለድርድር የሚቀርብ አይደለም። ምክንያቱም የዛሬን ብቻ ሳይሆን የነገ ዕጣ ፈንታቸውን የሚወስንና ቅድሚያ የሚሰጡት ሀገራዊ አጀንዳቸው በመሆኑ ነው።
ድህነትና ኋላ ቀርነት የሀገር ነፃነትን እና ክብርን የሚገዳደር ነው። በያዝነው 21ኛው ክፍለ ዘመን ያለ ኢኮኖሚ ነፃነት ራስን ሆኖ መኖር ከባድ ፈተና ነው። እንደቀደሙት ዘመናት ከዓለም ተገልሎ መኖርም ፈፅሞ አይታሰብም። እንደ ሀገር ለመቀጠል፣ ብሔራዊ ጥቅምንና ክብርን አስጠብቆ ለመጓዝ ከድህነትን እና ኋላ ቀርነትን የመውጣት ጉዳይ አልፋ እና ኦሜጋ ነው።
አባቶቻችን በብዙ የሕይወት መስዋዕትነት ነፃነታችንንና ብሔራዊ ክብራችንን አስጠብቀው፤ ከእኛው አልፈው ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነፃነት ጮራ ፈንጥቀው አስረክበውናል። እኛ ደግሞ ይህንን በገንዘብ የማይተመን ሉዓላዊ ክብር ድህነትንና ኋላ ቀርነትን አሸንፈን በመውጣት ታፍሮና ተከብሮ የቆየውን ሉዓላዊነታችንን፣ ባሕልና እሴቶቻችንን ማስጠበቅ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ይጠበቅብናል።
በጭቃ በተለውሱ እሾሆች (ሴራዎች) ዓለም ሰብዓዊነት በጎደለው መልኩ ብዙ ዋጋ እየከፈለች ነው። በዚህ ደግሞ ከማንም በላይ በድህነት አረንቋ ውስጥ ያሉ ሕዝቦች ግንባር ቀደም ተጎጂ ናቸው። በዚህ ምክንያት የውስጥ ሠላማችንን መጠበቅ እና በሴራው ላለመጠለፍ ከምንም በላይ ቅድሚያ የምንሰጠው ብሔራዊ አጀንዳችን ልናደርገው ይገባል።
እኛ ኢትዮጵያውያን በድህነትና በኋላ ቀርነት በብዙ ተፈትነናል። ሠላም ማጣትም ትኩረታችንን በትኖት የገባንበት ማጥ ውስጥ እንድንዳክር አስገድዶናል። ከሠላም ማጣት የተነሳም እያጋጠመን ያለው ፈተና እንደ ሀገር የሕልውና አደጋ ውስጥ ከቶናል። በምላሹም ብዙ ያልተገባ ዋጋ እንድንከፍል አስገድዶናል። በዚህ የተነሳ የተፈጠረው ሀገራዊ ስብራት እና ጠባሳ ብዙ ነው።
የሀገርን ሕልውና አደጋ ውስጥ ከከተቱ ጉዳዮችና ከውስጥ ችግራችን ባልተናነሰ ደግሞ በዓለም አቀፍ መድረኮች ድምፃችን ጎልቶ እንዳይደመጥ የፈጠረው ተግዳሮት በቀላሉ የሚታይ አልነበረም። ነፃነታችንን እና ብሔራዊ ክብራችንን የቱን ያህል እንደተፈታተነው ለማስታወስ አይከብድም።
ሠላም ማጣት ብዙ ትናንቶችን አሳጥቶናል፤ ብዙ የለውጥ መነቃቃቶችን አክስሞብናል። የሴራ እና የኃይል የፖለቲካ ባሕላችን በለውጡ ማግስት አዲስ ትንሳኤ አግኝቶ ዳግም ሀገርን የግጭት አዙሪት ውስጥ ለመክተት እየተፈታተነን ነው። ለጀመርነው ልማት ስኬት ዋነኛ አቅም የሆነውን ሀገራዊ ሠላም ፈተና ውስጥ ለመጨመር እየታገለን ነው። በተለመደው መንገድ የለውጥ ሞቅታዎችን አቀዛቅዞ ብሔራዊ ድባቴ ከፈጠረም ውሎ አድሯል።
መንግሥት ለውጡ ሠላማዊ እንዲሆንና ሂደቱ እንዲቀጥል ከዋዜማው ጀምሮ የሄደበት መንገድ ተስፋ ሰጪ ነው። ይሁን እንጂ የመጣንበት ኋላቀር የፖለቲካ ባሕል በፈጠረው ትርምስ ሁኔታዎች መልካቸውን እየቀየሩ ወደ ቀደመው የግጭት አዙሪት የገባንበት አጋጣሚ ተፈጥሯል።
እንደሀገር ብዙ ያልተገቡ ዋጋዎችን ለመክፈል ተገደናል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ለሞትና ለአካል ጉድለት ተዳርገዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር የሀገር እና የሕዝብ ሀብት ለውድመት ተዳርጓል። ከጦርነቱና ከግጭቶች ጋር በተያያዘም እንደሀገር የተፈጠረው ስብራትና በዜጎች ላይ የደረሰው ስነ ልቦናዊ ጫናም መጠነ ሰፊ ነው።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የታየው የፖለቲካ ባሕላችን ተስፋ ለምናደርጋቸው ብሩህ ነገዎች የቱን ያህል ፈተና እንደሆነ በተጨባጭ ያሳየ ነው። በተለይም ድህነትን በልማት አሸንፎ ለመውጣት በትውልዶች መካከል የነበረውን እና ያለውን ተስፋ በማደብዘዝ፤ የሀገርን ሕልውና ጭምር አደጋ ውስጥ የመክተት አቅም እንዳለው ያስገነዘበን ነበር።
እዚህ ጋር አንድ ነገር ሊሰመርበት ይገባል። ዘመናትን የተሻገሩትና አሁንም የሚፈጠሩት ችግሮቻችን መገለጫቸው ቢለያይም መሠረታዊ ምንጫቸው ግን ድህነትና ኋላቀርነት መሆኑ መታወቅ አለበት። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያጋጥሙን ፈተናዎችም ድህነትን አሸንፈን ለመነሳት በምናደርገው ብሔራዊ መነቃቃት ምክንያት የሚፈጠሩ ናቸው። አሮጌው የፖለቲካ ባሕላችንም ቢሆን የዚህ እውነታ ነፀብራቅ ነው።
እንደ ጥላ የሚከተለንን የሠላም እጦትና እርሱ የሚፈጥረውን ድህነትና ኋላ ቀርነት በቃ ልንል ይገባል። ሴራውን በብልሃት መሻገር እና መንቃት ይጠበቅብናል። የሠላም እጦት ወደ ብሩህ ነገዎች እንዳንሻገር እየተገዳደረን ነው። በመሆኑም አሮጌ የፖለቲካ ባሕላችንን ዘመኑን በሚዋጅ የፖለቲካ አስተሳሰብ በመቀየር ሉዓላዊነታችንን፣ ብሔራዊ ጥቅማችንን እንዲሁም ሠላማችንን ማጽናት ይጠበቅብናል። ይህ ደግሞ ለመንግሥት ወይም ለተወሰኑ ቡድኖች የሚተው አይደለም፤ እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት አለበት።
በለውጡ ማግሥት የጀመርነው ድህነትን በልማት ታሪክ የማድረግ ትግል ስኬታማ ሊሆን የሚችለው ሠላማችንን መጠበቅ ስንችል ነው። በዓለም አቀፍ መድረክ ተሰሚነታችን ጎልቶ የሚወጣውና ከጫና መላቀቅ የምንችለው አስተሳሰባችን በዚህ እሳቤ ሲቀረፅ ነው። ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ ከአሮጌ የፖለቲካ ባሕላችን መላቀቅ ይኖርብናል። ያን ግዜ አባቶቻችን በብዙ የሕይወት መስዋዕትነት እና ተጋድሎ ያስጠበቁትን ነፃነታችን፣ ብሔራዊ ክብራችንን በተሻለ መልኩ አስጠብቅን እኛም ለትውልድ ማሻገር እንችላለን!
አዲስ ዘመን መጋቢት 15 ቀን 2016 ዓ.ም