ዝነኛው የእግር ኳስ ስፖርት ክለብ ኢትዮጵያ ቡና በየዓመቱ የሚያዘጋጀው የቤተሰብ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ዘንድሮ ለ7ኛ ጊዜ ይካሄዳል። ሩጫው በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የሚካሄድ ሲሆን የመወዳደርያ ቲሸርት ህትመት መጀመሩም ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ህዝባዊ ክለብ እንደመሆኑ በተለያዩ መንገዶች በሚያገኛቸው የገቢ ምንጮች የክለቡን ፋይናንስ ይደጉማል። ከእነዚህም መካከል የክለቡን ደጋፊዎች በአንድነት የሚያሰባስበው የቤተሰብ ሩጫ የሚገኝበት ሲሆን ውድድሩ ዘንድሮ ለ7ኛ ጊዜ ይካሄዳል። ውድድሩን ለማካሄድ የሚያስፈልገው ቅድመ ዝግጅትም መጠናቀቁን የሩጫው አዘጋጅ ኮሚቴ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።
የዘንድሮው የሩጫ ውድድር ግንቦት 11/2016 ዓም ‹‹ቡንዬ የኔ›› በሚል መሪ ሃሳብ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተደረጉ ሲሆን፣ እስከ 35 ሺ ሰው ለማሳተፍ እንደታቀደም ተጠቅሷል። አስገዳጅ የሆኑ ሁኔታዎች ካላጋጠሙ በስተቀር ውድድሩ በተያዘለት ጊዜም ይካሄዳል። በዚህም መሰረት በተጠቀሰው ዕለት ጠዋት ሩጫው መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ ይካሄዳል። ለዚህም ፍቃድ ለማግኘት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤትና ለሚመለከታቸው አካላት በደብዳቤ ማሳወቁን ኮሚቴው ጠቁሟል።
7ኛውን የቤተሰብ ሩጫ ለማካሄድ በክለብ ስራ አመራር ቦርድ አማካኝነት አባላት፣ ከደጋፊ ማህበርና ከጽህፈት ቤት የተውጣጣ ኮሚቴ ተዋቅሮ ለሶስት ወራት የቅድመ ዝግጀት ስራን ሲያከናውን መቆየቱ ተገልጿል። በ2017 ዓ.ም የክለቡን ጠንካራነትና ተፎካካሪነት ለማስቀጠል፤ የፋይናንስ አቅም ማሳደግ ስለሚገባ የመሮጫ ቲሸርቱን የመሸጫ ዋጋን፣ በስራ አመራር ቦርዱና በኮሚቴው 800 መቶ ብር እንዲሆን እንደተወሰነ ለማወቅ ተችሏል። ከዚህ ቀደም የነበሩ እጥረቶችና መሰል ችግሮች እንዳይገጥሙም ህትመቱን በፍጥነት ለማስጀመር መታቀዱም ተጠቅሷል።
የመሮጫ ቲሸርቱን ለማቅረብ በቡና ባንክ ቅርንጫፎች፣ በክለቡ ስም በተደራጁ እድሮችና በደጋፊ ማህበሩ በተመረጡ እና በተለያዩ አካባቢ በሚገኙ ደጋፊዎች አማካኝነት ይሆናል። የመሮጫ ቲሸርት ሽያጩም እንደ ከዚህ ቀደሙ እስከ ውድድሩ ቀን እንደማይሆንና ቀኑ የተገደበ መሆኑም ታውቋል። በዚህም የቲሸርት ህትመቱ ከወዲሁ የሚጠናቀቅ በመሆኑ በሩጫው መዳረሻ ጊዜና በዕለቱ ሽያጭ አይኖርም። የትኬት ሽያጩ ከመጋቢት 13 እስከ ሚያዝያ 13/2016 ዓም ድረስ ይሆናል።
የቤተሰብ ሩጫው በ2007 ዓ.ም መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሳይቋረጥ ለ 5 ጊዜ በጎዳና ላይ እና አንድ ጊዜ ደግሞ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት ደጋፊዎች በያሉበት በመሆን በማህበራዊ ድረ ገጽ ማካሄድ ችሏል። ከስድስቱ ውድድሮች የተወሰዱትን መልካም ተሞክሮዎች በማስቀጠል፣ በሰባተኛው ውድድር የተሻሻሉ ነገሮችን በማካተት ሙሉ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል። በተጨማሪም ከሩጫው በኋላ የደጋፊዎቹን አብሮነት ለማስቀጠል የሙዚቃ ድግስን ለማድረግ ታቅዷል።
ሩጫው ዓላማ አድርጎ የተነሳው ክለቡ የካምፕ መስሪያ ቦታን በማግኘቱና እሱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማሰባሰብ ነው። ለዚህም በተለያየ መንገድ ገቢን ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበረ ሲሆን፣ ከእነዚህም ወስጥ የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ፕሮግራም፣ የሙዚቃ ኮንሰርትና የሩጫ ውድድር በዋናነት ለገቢ ማሰባሰቢያ ታስበው የነበሩ የክለቡ የገቢ ማግኛ መንገዶች ውስጥ ናቸው። በሩጫውና በተጠቀሱት የገቢ ማግኛ መንገዶች የታቀደው የተጫዋቾች ካምፕ እውን መሆኑንም የክለቡ ስራ ስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ገልጸዋል።
የዘንድሮውም ውድድር በዋናነት ሁለት ዓላማዎችን አንግቦ የሚካሄድ ሲሆን፣ እነዚህም የክለቡን የገቢ አቅም ማጠናከርና በክለቡ በደጋፊዎች መካከል ቤተሰባዊ ትስስርን ማጠናከር መሆኑም ተገልጿል። አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ክለቡ ህዝባዊ መሰረት ያለው ትልቅ ክለብ መሆኑን ተናግረው፣ የገቢ ምንጩን በተለያየ መንገድ ከህዝቡ በሚያገኘው ገንዘብ የሚደጉም መሆኑን ገልፀዋል። ክለቡ በዋናነት ገቢ የሚያገኘው ከቡና ሴክተር፣ ከስፖንሰር እና ከደጋፊዎች ሲሆን፤ በተጨማሪም ክለቡ ለሽያጭ ከሚያቀርባቸው የተለያዩ ቁሳቁሶች፣ ከስታዲየም መግቢያ ትኬቶችና ከሩጫው በሚያገኘው ገቢ የዓመቱን በጀት እንደሚሸፍን አስረድተዋል። በዚህም ክለቡ በዋናነት የፋይናንስ ገቢውን ከህዝቡ በተለያየ መንገድ በመሰብሰብ ጠንካራ ክለብ ለመገንባት ጥረት እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም