መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ከፍ ያለ ስፍራ ከሚሰጣቸው ዕለታት አንዱ ነው። ምክንያቱም ቀኑ
ኢትዮጵያውያን አስበው የሚቀሩ ሳይሆን ያሰቡትንም ማድረግ እንደሚችሉ የገለጡበት፤ ማድረግ መቻላቸውም በሰው ትከሻ ሳይሆን
በራሳቸው አቅም መሆኑን ያረጋገጡበት ክስተት የተፈጸመባት በመሆኑ ነው።
ይሄውም ዓባይን ከስደተኝነት ወደ ቤተኝነት የለወጠ፤ ለሀገሩ ልጆች ብርሃንን እንዲያበረክት ያስገደደ፤ የቀደሙት መሪዎች
ሕልምና ምኞትን ወደ ተጨባጭ እውነት እንዲቀየር ያደረገው – የዓባይ ግድብ ግንባታ የመሠረተ ድንጋይ ተቀምጦ ሥራው
የተጀመረበት ዕለት በመሆኑ ነው።
ዓባይ ከወንዝነት ወደ መብራትነት እንዲቀየር ታስቦም፣ ታቅዶም፣ ለሥራው የሚሆን በርካታ ዝግጅት ተደርጎም የነበረው
በቀደመው ጊዜ ነበር። በተለይ አፄ ኃይለሥላሴ በአሜሪካ ባለሙያዎች አስጠንተውና ዲዛይን አሠርተው ወደ ተግባር ለመግባት
ባቀዱበት ወቅት፤ አጋዥና ደጋፊ የሚሆን የውጪ አጋር በመጥፋቱ ሀሳባቸው ሳይሰምር ቀረ።
በኋላም በራስ አቅም ለመገንባት ሕዝቡን አስተባብሮ አቅም ለመፍጠር ሞክረውም ነበር። ይሄም በወቅቱ በነበረው የኢኮኖሚ
አቅም የሚሞከር ባለመሆኑ አልተሳካም። እናም ሀሳብና ንድፋቸው እንዳይባክን፣ ከፍ ያለ መሻታቸውን ትውልድ በጊዜው ጊዜ
እንዲፈጽም በጥንቃቄ እንዲቀመጥ አዘዙ።
በኋላም በደርግ ዘመን ይሄው ታስቦ የነበረ ቢሆንም በወቅቱ ዘርፈ ብዙ ችግር ምክንያት ሳይሳካ ቀረ። በዘመነ ኢሕአዴግም
ከብዙ ቆይታ በኋላ ጉዳዩን መተግበር ወደሚያስችል ዝግጅት ተገባ። እናም የአባቶች አደራ፣ የመሪዎች የዘመናት መሻት ወደ
ተጨባጭ እውነት ተቀየረ።እናም በዓባይ ወንዝ ላይ የዓባይ ግድብን ገንብቶ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚደረገው ጉዞ
ጅማሮውን አደረገ።
ይሄ የመጀመር ወቅት ነው። ሃሳብንና ንድፍን ወደ ተግባር የመለወጥ ጊዜ። በኋላም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ፕሮጀክቱ በልዩ
ትኩረት እንዲከናወን አቅጣጫ (በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አማካኝነት) ተቀመጠ። በዚህ ወቅት ታዲያ ግድቡ በተጀመረበትና
ከግማሽ በላይ ግንባታው በተከናወነባቸው ከለውጥ በፊት ዓመታት የነበሩ መልካም ነገሮች እንዲቀጥሉ የተደረገበት ብቻ አልነበረም።
ይልቁንም የነበሩ ችግሮች በተለይም የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ላይ ከፍ ያለ ጫና ሲያሳደሩ የነበሩ አካሄድና አሠራሮችን አርሞ
የማስተካከል እርምጃም የተወሰደበት ነበር። በዚህም ፕሮጀክቱን የነበሩበት ችግሮች ተፈትተው ወደተሟላ መስመር እንዲገባ
ማድረግ ተችሏል።
ከዛም በላይ ለዘመናት ይናፈቅ የነበረው የውሃ ሙሌት፤ እንዲሁም የተርባይኖች ገጠማና ኤሌክትሪክ የማመንጨት ሥራዎች
በተከታታይ ተሠሩ። በዚህም ዛሬ ላይ የግንባታው አጠቃላይ አፈጻጸም 94 በመቶ መድረስ ከመቻሉም በላይ፤ በቀጣይ ሰባት ወራት
ውስጥ ግንባታው የሚጠናቀቅ ስለመሆኑም ነው የተገለጸው። በመሆኑም ይሄኛው ዘመን የመጨረስ/የማጠናቀቅ ዘመን ነው ማለት
እንችላለን።
በዚህ ሁሉ ሂደት ሁለት ነገሮችን በልዩነት ማንሳት ይገባል። አንዱ የማድረግ አቅምና ስኬታማነት የተገለጠበት እውነት ሲሆን፤
ሁለተኛው ደግሞ ለስኬታማነቱ ዋጋ የከፈሉ አካላት በመኖራቸው እነዚህን አካላት ስለ ሁሉም አበርክቷቸው ክብርም፣ ዕውቅናና
ምስጋና መስጠት የተገባ መሆኑን ነው።
ከማድረግ አቅምና ስኬታማነት አኳያ፣ ኢትዮጵያ በዘመናት ጉዞ ውስጥ ያላትን ነፃነትና ሉዓላዊነት የሚመጥን የኢኮኖሚ
አቅም በእጅጉ ያስፈልጋት ነበር። ከዚህ አኳያ የዓባይ ግድብ ከፍ ያለ ትርጉም ያለው ነው። ምክንያቱም አይችሉም ሲባል መቻልን፤
አይፈጽሙም ሲባል ፈጽሞ ማሳየትን፤ አይጨርሱም ሲባል ጨርሶ ማሳፈርን፤… ለወዳጅም ለጠላትም በሚታይ መልኩ መግለጥ
ችለናል።
በዚህም ኢትዮጵያውያን ለነፃነታቸው ምሉዕነት ያላቸውን ቁርጠኝነት፤ ያላቸውን አቅምና የማድረግ ልክ በዓባይ ግድብ
አማካኝነት አሳክተው አሳይተዋል። እናም የዓባይ ግድብ የኢትዮጵያውያን የማድረግ አቅም መለኪያ፤ ሀሳብን ለተግባር፣ ተግባርንም
ለፍጻሜ የማብቃት የውጤት ሰገነት ሆኖ የሚነገር ነው። በመሆኑም ይሄንን ውጤት በልኩ መግለጥም፤ በሌሎች ላይ አልቆ መድገምም
የቀጣይ የቤት ሥራ አድርጎ መውሰድ ይገባል።
በሌላ በኩል ለግድቡ ለዚህ ስኬት መብቃት በርካታ አካላት የበኩላቸውን አበርክተዋል። መሪዎች ሀሳብ አመንጭቶ እስከ
ማስፈጸም የደረሰን ተግባር በየዘመናቸው ከውነዋል። ሕዝቦች ያላቸውን ሳይሰስቱ ሰጥተዋል። ዲፕሎማቶች ከፍ ያለ የዲፕሎማሲ
ሥራን ከውነዋል። ተደራዳሪዎች በሀገር ፍቅርና እውቀት ታግዘው የኢትዮጵያን ጥቅም ያስከበረ ተግባርን ፈጽመዋል። ምሑራን፣
ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ዜጎች ስለ ሀገራቸው ድንበርና የፖለቲካ እሳቤ ሳይበግራቸው ተሟግተዋል። ባለሃብቶች ያለ ስስት ካዝናቸውን
ከፍተዋል። ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖችን የቦታው ሀሩር ሳይበግራቸው ላብና ደማቸውን ጭምር ሰጥተው ግድቡን ገንብተዋል።
በዚህ ሁሉ ሂደት ሃሳብና ድካማቸው ለሀገርና ሕዝብ ከፍታ እንደመሆኑ፤ ሀሳብና ንድፍ አኑረው ላለፉም፣ ሃሳብና ንድፉን
ተቀብለው ላስጀመሩም፣ ጅምሩን አርመውና አልቀው ወደ ፍጻሜው ጫፍ ላደረሱም መሪዎች ምስጋና መቸር የተገባ ነው። ከዚህ
ባለፈ፣ በሃብት ማዋጣት፣ በዲፕሎማሲው፣ በድርድሩም፣ በሚዲያና ኮሙኒኬሽኑም፣ እንዲሁም በብዙ ፈተና ውስጥ ሆነው በቀጥታ
በግንባታው ሂደት ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋና የተገባ ነው።
ምክንያቱም ውጤታማነትን መግለጽና አልቆ ማስቀጠል አንድ ተግባር ሆኖ፤ ይሄንን ማስቀጠል የሚቻለው ውጤት ለመገኘቱ
ምክንያት የሆኑትን ሁሉ ማክበር፣ ማመስገንና እውቅና መስጠት ሲቻል ነው። በመሆኑም ስለ ዓባይ ግድብ ስናነሳም፣ 13ኛ ዓመቱን
ለማክበር ስንሰናዳም፣ በዘመናት ሂደት ውስጥ ለግድቡ ከሃሳብ እስከ መፈጸም አበርክቶ የነበራቸውን አካላት እያመሰገንን፤ ለላቀ
ኃላፊነትም እያበቃን ሊሆን ይገባል!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም