ትኩረት ያላገኘው የአዕምሮ እድገት ውስንነት

የሰው እድገት ተለዋዋጭና ከፅንሰት እስከሞት የሚኖሩትን አካላዊ፣ አዕምሯዊ፣ ማህበራዊና ሥነ ልቦና ለውጦችን ያካትታል። ስለዚህ የሰዎች ዕድገት የለውጥ ሂደት ነው ማለት ይቻላል። ይህ የለውጥ ሂደት ደግሞ በተፈጥሮና በአካባቢ መስተጋብር ላይ የተመሠረተ ነው።
የአንድ ሰው የሕይወት ቆይታ ተለዋዋጭ ነው ተብሎ ይታሰባል። በዚህም የአዕምሮ ግንዛቤ አቅሙ ትርጓሜው በብዙ መልኩ ሊገለፅ ይችላል። በዋናነት ግን የሰዎች የአዕምሮ ግንዛቤ ሲባል የመማር፣ የማሰብ፣ የማመዛዘን፣ ችግር የመፍታት፣ የማቀድ፣ የመወሰን፣ የማይዳሰሱ ነገሮችን የማሰብና የተማሩትን ነገር የማስተላለፍ፣ ይዞ የማቆየት፣ መረጃዎችን የመተንተን፣ እውቀቶችን መፍጠርና ኑሮን የመቋቋም ወዘተ የመሳሰሉትን ነገሮች ያጠቃልላል።
በዚህ የአዕምሮ ግንዛቤ አቅም ውስጥ ራስን የማስማማትና የማለማመድ ክህሎቶች ይኖራሉ። ይህም ራስን ችሎ ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ ችሎታዎች ወይም ክህሎቶችን ለምሳሌ የነገሮችን ፅንሰ ሃሳብ የመለየት አቅም/conceptual skill/፣ ማህበራዊ ክህሎት /social skill/ እና ተግባራዊ ክህሎት /practical skill/ በስሩ ያካትታል። ለሰው እድገት አስፈላጊ የሆኑ አካባቢያዊና ግብዓቶች በመጓደላቸው ምክንያት በግላዊና ማህበራዊ ክዋኔዎች ረገድ መዘግየት ሲፈጠር የአዕምሮ እድገት ውስንነት/intellectual disability/ ይከሰታል።
በኢትዮጵያ በቂ ጥናት ባለመደረጉ ከአዕምሮ እድገት ውስንነት ጋር የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ በትክክል አይታወቅም። ነገር ግን የዓለም ጤና ድርጅት በአዕምሮ እድገት ውስንነት ላይ ባወጡት መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ ካለው 110 ሚሊዮን በላይ ከሚሆን ሕዝብ ውስጥ ከሰባት ሰዎች ውስጥ አንዱ የአዕምሮ እድገት ውስንነት እንዳለበት አመልክቷል። ዩኒሴፍ እ.ኤ.አ በ2018 ባወጣው ሪፖርት መሠረት ደግሞ 7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች በተለያዩ የአዕምሮ እድገት ውስንነት እንደተጠበቁ አሳይቷል። ይህም ኢትዮጵያ ካላት ሕዝብ ወደ 9 ነጥብ 3 ከመቶ ያህሉ በዚህ ሕመም ውስጥ እንዳለ ያሳያል።
የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሰዎች በህብረተሰቡ በኩል የሚደርስባቸው መገለልና መድልኦም ቀላል የሚባል አይደለም። ይህንን ተከትሎም በርካታ ወላጆችም ታማሚ ልጆቻቸውን በቤት ለመደበቅ ተገደዋል። ጥቂት ወላጆች ናቸው ዛሬ ላይ ደፍረው ልጆቻቸውን በአደባባይ አውጥተው ከአዕምሮ እድገት ውስንነት ጋር የሚኖሩ ልጆች እንደሌሎች ጤናማ ልጆች መማር፣ መሥራትና አዲስ ነገር መፍጠር እንደሚችሉ ያሳዩት። ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ከአዕምሮ እድገት ውስንነት ጋር ለሚኖሩ ልጆችና ወላጆቻቸው ብርሃን የሆኑት። እነዚህ ወላጆች ናቸው ዛሬም ድረስ የአዕምሮ እድገት ውስንነት በመንግሥት በኩል ትኩረት እንዲያገኝ ግፊት እያደረጉ ያሉት። እነዚህ ወላጆች ናቸው በአዕምሮ እድገት ውስንነት ዙሪያ ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየሰሩ ያሉት።
ከነዚህ ወላጆች ውስጥ ወይዘሮ ምህረት ንጉሴ አንዷ ናቸው። እርሳቸው የፍቅር ኢትዮጵያ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ብሔራዊ ማህበር ፕሬዚዳንት ናቸው። ማህበሩን የመሠረቱት ከሌሎች ልጆቻቸው የአዕምሮ እድገት ውስንነት ካለባቸው ወላጆች ጋር በመሆን ነው። የእርሳቸውም ታናሽ ወንድም ከአእምሮ እድገት ውስንነት ጋር ይኖራል።
እርሳቸው እንደሚሉት፣ ማህበሩ ከዛሬ 29 ዓመት በፊት በ1987 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን አላማውም በአዕምሮ እድገት ውስንነት ዙሪያ ለወላጆች፣ ለመንግሥት አካላት፣ መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ አካቶ ትምህርትን ማስፋፋት፣ በተለያዩ ሙያዎች ማሰልጠን፣ የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት መስጠት፣ በኢኮኖሚ ለማብቃት የወላጆችን አቅም ማሳደግ፣ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ ነው።
ሥራውን በአዲስ አበባ የጀመረው ማህበሩ በስምንት ክልሎች ከ17 በላይ ቅርንጫፎች ከፍቶ ከ15 ሺ በላይ አባላትን በማፍራት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ከአካቶ ትምህርት ጋር በተያያዘም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት ይሠራል። ቀደም ሲል በአዲስ አበባ አንድ ብቻ የነበረውን የአካቶ ትምህርት በአሁኑ ጊዜ ከ15 በላይ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል። ከ150 በላይ ልጆች በተለያዩ ሙያዎች አሰልጥኗል።
ከዚህ ባሻገር ማህበሩ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሠራ የሚገኝ ሲሆን በርካታ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ከቤት እንዲወጡ የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል። ከአዕምሮ እድገት ውስንነት ጋር በተያያዘ ለመምህራን ተከታታይ ሥልጠናዎችን ከመሰጠቱም በላይ ለሃይማኖት አባቶች፣ ለፍትህ አካላትና ለሚዲያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሰርቷል።
ፕሬዚዳንቷ እንደሚያብራሩት የማህበሩ ሃያ ዘጠኝ ዓመታት ጉዞው አልጋ በአልጋ አልነበረም። በተለያዩ ችግሮች ውስጥ አልፏል። በተለይ ከአዕምሮ እድገት ውስንነት ጋር የሚኖሩ ልጆችን ከተደበቁበት የማውጣት ሥራ ላይ አተኩሮ ሲሰራ ስለቆየ ውጣውረዶቹ ቀላል አልነበሩም። ነገር ግን በነዚህ ውጣውረዶች ውስጥ ማህበሩ ያከናወናቸው ሥራዎች ዛሬ ላይ ፍሬ አፍርተዋል። ዛሬ ላይ በማህበሩ ውስጥ ገብተው ትምህርት ያገኙ ከአእምሮ እድገት ውስንነት ጋር የሚኖሩ ልጆች ትልቅ ለውጥ አምጥተዋል። ከዚህም በላይ እገዛ ቢደረግላቸው ደግሞ ትልቅ ቦታ ሊደርሱ ይችላሉ።
የዚህ ዓመት የአዕምሮ እድገት ውስንነት ቀን መሪ ቃል ‹‹ፍረጃ ይቁም›› የሚል ነው። ይህ መሪ ቃል የመረጠውም ያለ ምክንያት አይደለም። ይህ ጭፍን ፍረጃ ነው በርካታ ከአዕምሮ እድገት ውስንነት ጋር የሚኖሩ ልጆችን እንዲደበቁና ወደኋላ እንዲቀሩ ያደረገው። ፍረጃው ከቤተሰብ፣ አካባቢና ከማህበረሰብ ነው የሚጀምረው። ይሁንና ፍረጃው ሲቀርና አስፈላጊው ድጋፍ ሲደረግላቸው የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎች ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ሊያደርገው የሚችለውን ነገር ሁሉ ማድረግ ይችላሉ።
የአዕምሮ እድገት ውስንነት በመንግሥትም ሆነ በተቀረው የህብረተሰብ ክፍል በኩል ትኩረት ሲያገኝ እነዚህ ልጆች ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ይችላሉ። ማህበረሰቡ የሚቀበላቸውና የእኛ ልጆች ናቸው ብሎ ከአዕምሮ እድገት ውስንነት ጋር አብረው የሚኖሩ ልጆችን እንዲቀበላቸው ልጆቹ ወደፊት ከፍ ያለ ቦታ እንዲደርሱ የሁሉም ሰው ድጋፍ ያስፈልጋል።
ወይዘሮ ናርዶስ አሰፋ የብሩህ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ማዕከል መሥራችና ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት በልጅነት ጊዜ ልጆች የተለያዩ ራሳቸውን የመቻል እንቅስቃሴዎችን ይጀምራሉ። ከነዚህም መካከል በራሳቸው መመገብ፣ መልበስ፣ መፀዳዳት፣ መሄድና የመሳሰሉት ይገኛሉ። ሆኖም እድሜያቸው ከፍ ሲልና በታዳጊነት የእድሜ ክልል ላይ ሲደርሱ ከጥገኝነት ለመላቀቅ በልጅነት ጊዜ ካገኙት ክህሎት በመነሳት የተለያዩ ክህሎቶችን ያዳብራሉ። እነዚህን ከጥገኝነት የሚያላቅቁ ክህሎቶችና የግል እንክብካቤ ያተኮሩ ተግባራትን የሚፈጥሩበትን እድል ማመቻቸት ያስፈልጋል።
ይህም ለአንድ ግለሰብ በራስ መተማመንና በማህበረሰብ ተሳትፎ የዳበረና ኃላፊነት የሚሰማው ቤተሰብ ለመፍጠር እጅግ የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል። የሰብዓዊ መብት በዋናነት ሕፃናትን መንከባከብና በክህሎት አበልፅጎ ማሳደግ ድህነትን የመቅረፍና ማህበረሰቡን ኢኮኖሚ ዋነኛ ቁልፍ ተግባር ነው።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ፣ ማዕከሉ ከአዕምሮ እድገት ውስንነት ጋር የሚኖሩ ልጆችን ለመርዳት የተቋቋመ ሲሆን ሥራ ከጀመረ አስራ ስድስተኛ ዓመቱን ይዟል። በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች በእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸው ከጥገኝነት እንዲላቀቁ ለማድረግ ከስድስት በማይበልጡ ልጆች ሥራውን ጀምሮ ለአስራ አምስት ዓመታት ዘልቋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ እድሜያቸው ከስድስት እስከ ሃያ ዓመት ያሉ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው 39 ልጆችን በስሩ ይዞ እንክብካቤና የክህሎት ማሳደጊያ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
የሚንከባከባቸው ልጆች በራሳቸው እንዲመገቡ፣ እንዲለብሱ፣ ጫማቸውን እንዲያደርጉ፣ እንዲፀዳዱና ቀለል ያሉ የቀለም ትምህርቶችንና የሙያ ሥልጠናዎችን እንዲከታተሉ እያደረገ ነው። ከዚህ ባለፈ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ወላጆች ምርታማ እንዲሆኑ በእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸው ልጆቻቸውን በቤት ውስጥ በመንከባከብ ከሚያወጡት ጊዜና ድካም እንዲያርፉና በአዕምሯቸው ላይ የሚፈጠረውን ጫና ለመቀነስ በማሰብ ብሎም የማህበረሰብ አሉታዊ ተፅእኖ በመፍራት ሸሽገው ያስቀመጧቸውን ልጆች ግንዛቤ በማስጨበጥ እንዲያወጡ የማድረግ ሥራዎች ይሠራሉ። ከጭንቀትና ከመከራ ስሜት በማውጣት ራሳቸውን እንዲችሉና የገቢ ምንጭ እንዲያገኙ ሥልጠና በመስጠት ረገድም ማዕከሉ ከፍተኛ ሥራ ሰርቷል።
ማዕከሉ እስካሁን ባደረገው ጥረት ህብረተሰቡን በማንቃትና ግንዛቤ በማስጨበጥ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ከቤት ወጥተው እንደ ትምህርትና የጤና አገልግሎቶችን ቀርበው እንዲያገኙና እንዲታገዙ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል። መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የዚህ ችግር ተጠቂ የሆኑ ሕፃናት ተገቢውንና አቅም የፈቀደውን ትምህርትና ሥልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ባለሙያዎችን በማሳተፍ የህብረተሰቡን አቅም በማስተባበርና ድርጅቶችን በማሳተፍ ረገድም የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል።
የዚህ ችግር ዋነኛ ገፈት ቀማሽ የሆኑትን እናቶችን የእለት ከእለት እንቅስቃሴያቸውንና ማህበራዊ ሕይወታቸውን እንዲመሩና እንዲያስተካክሉ ከማድረግ አንፃርም ማዕከሉ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል። በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠርና የልምድ ልውውጦችን በማድረግ ጠቃሚና ገንቢ የሥራ እንቅስቃሴዎች እያደረገም ይገኛል።
ይሁንና ማዕከሉ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆችን ተቀብሎ ለማስተናገድ የሚያስችል ሀብት ያለመኖር፣ ቋሚ የማሰልጠኛና የማስተማሪያ ቦታ ያለመኖር፣ በሙያው የሰለጠኑ ባለሙያዎች እጥረት፣ ለመማር ማስተማርና ማሰልጠኛ ሊሆን የሚችል በቂ የግብዓት አቅርቦት አለመኖር፣ ንቁ የወላጆች ተሳትፎ አለመኖር የመሳሰሉ ችግሮች አሉበት።
ከዚህ አንፃር ማዕከሉ የአዕምሮ እድገት ውስንነት በመንግሥትም ሆነ በህብረተሰቡ ዘንድ በቂ ትኩረት እንዲያገኝ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በግልና በመንግሥት ሚዲያዎች በኩል እየተሠሩ ይገኛሉ። የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ የማሳደግ፣ የወጡ የመንግሥት ፖሊሲዎችንና ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየተሠራ ነው።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ተወካይ አቶ መሰለ ተስፋ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፣ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ሶስት አካላት ወሳኝ ሚና አላቸው። አንደኛው መንግሥት ሲሆን በመንግሥት ደረጃ መሥራት የሚገባውን የሕግ ማዕቀፎች ከማውጣት፣ የአሠራር ሥርዓት ከመዘርጋት፣ አደረጃጀቶች ከመፍጠር አንፃር የድርሻውን መወጣት አለበት።
ሁለተኛው ማህበረሰቡ ሲሆን የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ዜጎች ከሌሎች ዜጎች ባልተለየ ሁኔታ ሊንከባከባቸውና ሊደግፋቸው ይገባል። ግንዛቤውም በዛው ልክ ማደግ ይኖርበታል። ግንዛቤውን ለማሳደግ ደግሞ በተለይ የሚዲያ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው። በሶስተኛ ደረጃ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ወገኖችን የሚረዱ ማዕከላትን በማገዝና ከጎናቸው በመቆም፤ ለሚሠሩት ሥራም ድጋፍና እውቅና በመስጠት አጋርነታቸውን ማሳየት አለባቸው። እስካሁን ድረስ በዚህ ጉዳይ ላይ ያልሰሩ ድርጅቶችም ካሉ ተቀላቅለው ሥራውን ሊደግፉ ይገባል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮንቬንሽን በአዋጅ ቁጥር 676 በማፅደቅ ወደ ሥራ ተገብቷል። ነገር ግን ሥራው በአጥጋቢ ሁኔታ መሬት ላይ ውርዷል ማለት አይቻልም። የወጡ አካታች ፖሊሲዎች አሉ። ሆኖም አተገባበራቸው በሚፈለገውና ለውጥ ሊያመጣ በሚችል መልኩ ተተግብሯል ለማለት አይቻልም።
ስለዚህ በመንግሥት በኩል የወጡ አዋጆችን ተግባራዊ በማድረግ፣ የወጡ ፖሊሲዎችን ወደ መሬት በማውረድ ከዜጎች ጋር በመሆን ወደፊት የሚሰራበት እድል አለ። ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ግን ከአዕምሮ እድገት ውስንነት ካለባቸው ዜጎች ጋር አብሮ መሆንና መደገፍና መንከባከብ አለበት።
‹‹ የዓለም ጤና ድርጅት በአዕምሮ እድገት ውስንነት ላይ ባወጡት መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ ካለው 110 ሚሊዮን በላይ ከሚሆን ሕዝብ ውስጥ ከሰባት ሰዎች ውስጥ አንዱ የአዕምሮ እድገት ውስንነት እንዳለበት አመልክቷል። ዩኒሴፍ እ.ኤ.አ በ2018 ባወጣው ሪፖርት መሠረት ደግሞ 7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች በተለያዩ የአዕምሮ እድገት ውስንነት እንደተጠቁ አሳይቷል። ››

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You