የእናት ጡት ወተት ለሕፃናት ጤናማ እድገት

የሕፃኑ ሕይወት የመጀመሪያዎቹ አንድ ሺህ ቀናት በጣም አስፈላጊ መሆናቸውን ዓለም አቀፍ ጥናቶች ያመላክታሉ። ይህ ጊዜም ከመጀመሪያው የእርግዝና የመጀመሪያ ቀን ውስጥ የሚካተት ሲሆን፤ የልጆች የሁለት ዓመት ዕድሜ እስኪያበቃ ድረስ የሚቆጠር ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ የሕፃኑ አካል፤ አንጎል እና የወደፊቱ ጤንነት ይወሰናል። ይህንን እድገት የተሟላና ጤናማ ለማድረግም በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ ጤናማ አመጋገብ ነው። በተለይ የእናት ጡት ማጥባት ሕፃናቱን ጠንካራ እና ጤናማ ለማድረግ ወሳኝ እንደሆነ ጥናቶቹ ያሳያሉ።

ጡት ማጥባት ለእያንዳንዱ ሕፃን ምርጥ የአስተዳደግ ጅምር ነው። የእናት ጡት ወተት በተለይም የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ላሉ ሕፃናት የሚያስፈልጋቸውን ሁሉም ንጥረ ነገሮች እንዲያገኙ ያግዛቸዋል፤ እጅግ ጠቃሚ ነው። ሕፃናቱን ከበሽታ ለመጠበቅ፤ ኢንፌክሽኖችን ለመከላከልም ከፍተኛ ፋይዳ አለው።

እንደ የዓለም ጤና ድርጅት የጥናት ውጤት ከሆነ፤ ጡት በማጥባት ሕፃናትን ከተቅማጥ፣ ከሳንባ ምች እና ከሌሎች ከባድ ችግሮች መታደግ ይቻላል። ከሕፃናቱ ባሻገርም ጡት ማጥባት እናቱንም ከበሽታ ለመከላከል ሁነኛ መድኃኒት ነው። በተለይ እናት በጡት ካንሰር እንዳትያዝ ከማድረግ አንጻር ሚናው ከፍተኛ ነው። የእናቲቱን ሰውነት ከወሊድ በኋላ ወደ መደበኛው አቋም እንዲመለስም ያደርጋል።

ሕፃናቱ ጠንካራ ምግብ መብላት ሲጀምር፤ የተመጣጠነ እና ትክክለኛውን የምግብ ዓይነቶችን መስጠትም ሌላው የሕፃናትን ጤና የምንጠብቅበት መንገድ ነው። ምግቦቹ አብዛኛው አይረን፣ ፕሮቲን፣ ቫይታሚኖች እና ሌሎች ንጥረ ነገሮችን የያዙ ቢሆኑ ተመራጭነት እንዳላቸውም ዓለም አቀፍ ጥናቶች ያመላክታሉ። ምክንያቱም እነዚህን ምግቦች መመገብ የሕፃናቱን አካል እና አንጎል በጣም በፍጥነት እንዲያድግ ያግዘዋል።

የዩኒሴፍ ጥናት እንደሚያሳየው፤ በመጀመሪያዎቹ አንድ ሺህ ቀናት ውስጥ ሕፃናትን የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ልጆች በትምህርት ቤት ውስጥ ከሚተላለፉ በሽታዎች እንዲጠበቁ ያደርጋቸዋል፤ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑም ያግዛቸዋል፤ የተሻለ የአዕምሮ እድገት እንዲኖራቸውም ይረዳቸዋል። በተመሳሳይ ደካማ የአመጋገብ ሥርዓት ያላቸው ልጆች ደግሞ በበሽታ የመጠቃት እድላቸው ከፍ ያለ ነው። ለምሳሌ ትክክለኛውን የተመጣጠነ ምግብ የማያገኙ ሕፃናት የልብ በሽታ ወይም የስኳር በሽታ በቀላሉ ሊይዛቸው ይችላል። የዕድሜ ልክ ችግሮችን እስከማስከተል የሚደርስ ጉዳት ሊያጋጥማቸውም ይችላል።

ዓለም አቀፍ ጥናቶች አንደሚያሳዩት፤ በታዳጊ ሀገሮች ውስጥ ብዙ ልጆች የሚፈልጉትን የተመጣጠነ ምግብ አያገኙም። ይህ በልጆቹም ሆነ በሀገር እድገት ላይ ከፍተኛ ችግሮችን ይደቅናል። ይህንን ችግር ለመፍታት ደግሞ የእናት ጡት ማጥባት እና የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ወሳኝነት አለው። በዚህም አስፈላጊውን የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ለእናቶች እና ማኅበረሰቡ መስጠት ያስፈልጋል። የጤና ባለሙያዎችም ቢሆኑ ሕፃናት ከተወለዱ በኋላ እናቶችን ለመጀመሪያ ጊዜ ጡት ማጥባት እንዲጀምሩ እና ቢያንስ ለሁለት ዓመት እንዲቀጥሉ መደገፍ አለባቸው። በስድስት ወር ሕፃናት ጠንካራ ምግቦችን መብላት መጀመር እንዳለባቸውም ግንዛቤ መስጠት ይገባቸዋል።

ከምግቡ ጎን ለጎን ጡት ማጥባት መቀጠል እንዳለበት እናቶች ማወቅ አለባቸውም። ወላጆች ሕፃናት በጥሩ ሁኔታ እንዲያድጉ የሚያደርጉ የተመጣጠኑ ምግቦችን እንዴት ማዘጋጀት እንደሚችሉ ማወቅ እንዲችሉ የጤና ባለሙያዎች ምክር አስፈላጊ መሆኑንም ጥናታዊ ጽሑፎቹ ያመላክታሉ።

ጤናማና የተመጣጠነ የአመጋገብ ሥርዓት የሕፃናትን ሁለንተናዊ እድገት ያፋጥናል። በጥሩ ሁኔታ የተመጣጠነ ምግብ የሚመገብ ሕፃን ከእናቱ ወተት ጋር ተደምሮ ሲያገኝ አካላዊና አዕምሯዊ እድገቱን ጤናማ ማድረግ እንዲችል ያግዘዋል። ይህ ሁኔታ ደግሞ በቤት ውስጥ ደስተኛ ቤተሰብ እንዲፈጠር ይረዳል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ጥልቅ ምርምር ያደረገው የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ጥናት እንደሚያሳየው፤ ለልጆች የሚሰጠው እንክብካቤ፣ ፍቅር እና የተመጣጠነ ምግብ በአንድነት ታዳጊዎች ጠንካራ እንዲሆኑ፣ ጥሩ ባሕሪ ያላቸው ልጆች ሆነው እንዲያድጉ ልዩ አስተዋጽኦ አለው። በዚህም ጥናቱ አንድ ሺህ ቀናቶች ለእናትም ሆነ ለሕፃናቱ ወርቃማ ጊዜያት ናቸው ሲል ይበይናቸዋል።

መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚወለዱ ሕፃናት ጤናማና ሁለንተናዊ እድገታቸው የተሟላ እንዲሆን በፖሊሲ ደረጃ ቀርጾ ተከታታይ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ። በተለይ የሕፃናት እድገትን የሚያጎለብቱ የተመጣጠነ ምግብና የእናት ጡት አስፈላጊነት ላይ ልዩ ድጋፍና የግንዛቤ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ይህንን በሳይንሳዊ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግም በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመሆናቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።

ለሕፃናት ሁለንተናዊ እድገት ከእናት ጡት አንስቶ የተመጣጠነ ምግብ፣ የፀሐይ ብርሃን ጤናማ ማኅበረሰብን ከመፍጠር አንጻር የማይተካ ሚና አላቸው። እንደ ሀገር በተገቢው መልኩ የሚያስፈልገው መሟላትና አለመሟላቱን ለማወቅ ደግሞ ጥናት ያስፈልጋል። ይህን መመለስ የሚችል ጥናት በአዲስ አበባና በድሬዳዋ በሚገኙ ሕፃናት ላይ በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ተጠንቷል። ለጥናቱ በሁለቱ ከተሞች ከሚገኙ 4 ሺህ 442 ሕፃናት መረጃ ተወስዷል። 2ሺህ 745ቱ ሕፃናት ከአዲስ አበባ ሲሆኑ፤ የተቀሩት ሕፃናት የድሬዳዋ ነዋሪ ናቸው።

በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በሥርዓተ ጾታና የልጆች ልማት ዲፓርትመንት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ቃልአብ ከበደ እንደሚሉት፤ ጥናቱ ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር የተሠራ ሲሆን፤ በሁለቱ ከተሞች ለሚገኙ ሕፃናት እድገት እና ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች በምን ሁኔታ እንደሚገኝ የብዝሀ- ልኬት ሕፃናት ድህነት እና እጦት ሁኔታ በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ‹‹The State of Multidimensional Child Poverty and Deprivations In Addis Ababa and Dire Dawa›› በሚል ርዕስ ተዳሷል።

የልጆች ድህነት ሲባል በገንዘብ ከሚለካ ያለፈ ዘርፈ ብዙ ሁኔታዎች እንዳሉትና አንዱ ሳይሟላ ሲቀር በሌሎቹም ረገድ የመጉደል አዝማሚያ እንዳለው ጠቁመዋል። በመሆኑም በጥናቱ ለሕፃናቱ አስፈላጊ የሆኑ ዘጠኝ አመልካቾችን በመለየት ያሉበት ሁኔታ በጥልቀት አሳይቷል። እነሱም ጤና፣ ምግብ፣ ትምህርት፣ ደህንነት፣ ውሃ፣ ንጽህና፣ መኖሪያ ቤት፣ መረጃና ተሳትፎ፣ የመዝናኛ ሁኔታ ናቸው ብለዋል።

በሁለቱ ከተሞች ከሚገኙ ከ40 በመቶ በላይ ሕፃናት (በቁጥር ወደ ስምንት መቶ ሺህ የሚሆኑ) በዘርፈ ብዙ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ 97 በመቶዎቹ ለሁለትና ከዚያ በላይ ለሆኑ ችግሮች የተጋለጡ ናቸው። በጥናቱ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰብ ሕፃናት ለዘርፈ ብዙ የሕፃናት ድህነት ተጋላጭ የሚሆኑበትን እድል አይቷል። በዚህም ጥናቱ ገቢ ከመሠረታዊ ፍላጎት መሟላት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው አመላክቷል።

በጥናቱ ሴት ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኛ ሕፃናት፣ ወላጅ አልባ ሕፃናት፣ ካልተማረ ቤተሰብ የተገኙ ሕፃናት ለዘርፈ ብዙ ድህነት የመጋለጥ እድላቸው ከፍ ያለ መሆኑንም የተመላከተ ሲሆን፤ በከተሞቹ በተደረገው ጥናት ውሃ ከ89 በመቶ በላይ፣ መዝናኛ 77 በመቶ በላይ መኖሪያ 64 በመቶና ምግብ 55 በመቶ ሕፃናት ላይ እጥረት መኖሩ ተለይቷል። በሁለቱ ከተሞች ከሚኖሩ ሕፃናት 17 በመቶው ለመኖሪያ ቤት ለውሃና ለንጽህና እጥረት በጋራ ተጋላጭ መሆናቸው ተብራርቷል።

በጥናቱ ለሕፃናቱ ውሃና መኖሪያ ጥልቅ ቁርኝት እንዳላቸው የታየ ሲሆን፤ 40 በመቶዎቹ ሕፃናት መኖሪያና ውሃ እጥረት በጋራ ተጋላጭ ናቸው። በሁለቱ ከተሞች ከሚገኙ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት 20 በመቶው ለጤና፣ ለምግብና ለውሃ አቅርቦት እጥረት በጋራ የተዳረጉ መሆኑን ያሳያል። 30 በመቶው በቂ ያልሆነ የምግብና የውሃ አቅርቦት በጋራ ችግር ያለባቸው መሆኑንም ዳሷል።

ከ5 እስከ 17 የእድሜ ክልል ከሚገኙ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ ሕፃናት መካከል 22 በመቶው ከትምህርትና ጤና ጋር ተያይዞ መረጃ የማግኘት ሁኔታ ሲታይ ቢያንስ ከሦስቱ የሁለቱ እጥረት አለባቸው። ስለዚህም ሕፃናቱ ለበርካታ ችግሮች ተጋላጭ በመሆናቸው ችግሩን ለመቅረፍ የበርካታ ተቋማትን ቅንጅት ይሻል ሲል ጥናቱ ምክረ ሃሳቡን ያስቀምጣል።

እንደ ዶክተር ቃልአብ ገለጻ፤ ጥናቱ ለሕፃናቱ መሟላት የሚገባቸውን ዘጠኝ አስፈላጊ የሆኑ መስፈርቶች ዙሪያ በጥልቅ መመልከት በመቻሉ በየትኛው ረገድ ክፍተት እንዳለ ለማወቅ ያግዛል። ለልጆቹ አስፈላጊ ነገሮች ያልተሟሉት በየትኛው ረገድ ነው የሚለውና መስፈርቶቹ በተናጠልና አንዱ ሲጎድል አብሮ የሚመጣው ሌላ ጉድለት በጥልቀት ተዳሷል። ይህ መደረጉ ደግሞ ለቀጣይ የፖሊሲ አቅጣጫ ሲቀመጥም ሆነ በሕፃናት ዙሪያ የሚሠሩ ተቋማት ሲኖሩ የትኛው ላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው ሰፊ መረጃ ይሰጣል። የልጆች ድህነትን ለመቀነስ ምን ማድረግ እንዳለባቸውም እንዲያውቁ ያግዛል።

ሕፃናቱ አንዱ ፍላጎታቸው ላይ እጥረት ሲኖር በዚያ ከመወሰን ይልቅ በሌሎችም ረገድ ለእጥረት የመጋለጣቸው ሁኔታ የሰፋ መሆኑን ጥናቱ ማሳየቱን የሚናገሩት ተመራማሪው፤ ችግሩን ለመቅረፍ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅትና የጋራ ርብርብ የሚሻ መሆኑን ጠቁመዋል።

በጥናቱ የኢኮኖሚ አቅምና የሕፃናት ፍላጎት አለመሟላት ከፍ ያለ ቁርኝት መኖሩ ስለታየ የቤተሰብን የገቢ ሁኔታ የሚያሻሽሉ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ምክረ ሃሳብ ተሰጥቷል። በአንዴ ለሁሉም ችግሮች መመለስ ባይቻል እንኳን የውሃና የመኖሪያ ቤት አለመኖር እና የምግብ እጥረት ዋናዎቹ የሕፃናት ድህነት ምንጮች ስለሆኑ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ትኩረት ተደርጎ ቢሠራ ሌሎችን ለማሟላትም ድርሻው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ተመራማሪው አስተያየት፤ ኢንስቲትዩቱ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞችን ውጤት በተለያየ መድረኮች ለባለድርሻ አካላት አቅርቧል። በዚሁ ርዕስ ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ በተጨማሪ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ከአሜሪካን ኢንስቲትዩትስ ፎር ሪሰርች (American Institutes for Research) ጋር በመሆን ከዩኒሴፍ ኢትዮጵያ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ሀገር አቀፍ ጥናት አጠናቋል። በጥናቱ የተካተቱት ዘጠኙ ማሳያዎች በተለያየ ሴክተር የሚተገበሩ በመሆኑ ጥናቱ ይፋ ሲደረግ ሁሉም የድርሻውን በመውሰድ የሕፃናቱ ሁኔታ ለማሻሻል በተናጥል እና በቅንጅት መሥራት ይገባዋል ብለዋል።

ሁሉም በየዘርፉ የየራሱን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ያወሱት ዶክተር ቃልአብ፤ በሁለቱ ከተሞች የተሠራውን ጥናት ኢንስቲትዩቱ ቢሠራውም በዘጠኙ አመላካች ላይ ባለድርሻ አካላትን ጠርተው ማወያየታቸውን ያስታውሳሉ። በዚህም የትኞቹ አመላካቾች ይግቡ ለሚለው መግባባት ላይ መደረሱንና ባለድርሻዎቹ እንዲካተት የሚፈልጉትን አመላካች ሃሳብ እንዲሰጡ ተደርጎ ወደ ጥናቱ ተገብቷል። ጥናቱ ከጥንስሱ ጀምሮ የሚመለከታቸው አካላት ስለሚያውቁት ውጤቱን እንደሚጠብቁትና ምክረ ሃሳቡን ተግባራዊ እንደሚያደርጉት ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You