በሕይወታችን ውስጥ ‹‹እኔ እኮ ሰነፍ ነኝ! ምንም አልችልም! በቃ እኔ እኮ የተፈጠርኩት ለስንፍና ነው! አልረባም!›› ልንል እንችላለን። ግን ክፍተታችን በጣም ቀላልና ትንሽ ብቻ መድኃኒት የሚያስፈልጋት ልትሆን ትችላለች። ስለዚህ ከታች ከተዘረዘሩት ስድስት ነጥቦች ውስጥ አንዱ የእኛ ክፍተት ሊሆን ይችላል። ልክ እርሱን ስናስተካክል ‹‹ለካ ሰነፍ አልነበርኩም፤ መጀመሪያውኑ አቅም አለኝ›› እንድንል ያደርገናል።
በርግጠኝነት ከነዚህ ስድስት ነጥቦች መካከል አንዱ ክፍተታችን ሊሆን ይችላል። እርሱን ስታስተካክሉ ስንፍናችሁ ይጠፋል። በትምህርት፣ በሥራ ወዘተ ሊሆን ይችላል ስንፍናችሁ! ‹‹እኔ ሰነፍ ነኝ!›› ብላችሁ የምታምኑ ከሆነ ከዛሬ ጀምሮ እንዳልሆናችሁ ታረጋግጣላችሁ። እነሆ ስድስቱ ነጥቦች…
1ኛ. ኃላፊነት እንውሰድ
አንዳንድ ጊዜ እድሌ እኮ ነው! እኔ የሚያስጠናኝ ሰው የለም እንጂ ሰነፍ ለመሆን ተፈጥሬ አይደለም! ማን ይርዳኝ እኔን! ቤተሰቦቼ ጥሩ አቅም የላቸውም! አያስተምሩኝም! ጥሩ ትምህርት ቤት አላኩኝም! ደሞም ገንዘብ የላቸውም! የሆነች ነገር እኮ ቢያስጀምሩኝ ጥሩ ቦታ እደርሳለሁ›› እንላለን። የብዙዎቻችን ምክንያት ነው። እኔ በቤተሰቤ ምክንያት ነው፣ በተወለድኩበት ሀገር ነው፣ በምሠራው ሥራ ነው፣ በምውላቸው ሰዎች ነው፣ በተፈጥሮዬ ነው እያልን ሰበብ እንደረድራለን።
ከዛሬ ጀምሮ ግን ኃላፊነት መውሰድ አለብን። ለምን መሰላችሁ? ስንፍና በሆነ ነገር ይደበቃል። ኃላፊነት የማንወስድ ከሆነ ለስንፍናችን ጥሩ ምክንያት አለን። ‹‹እኔ እኮ ጥሩ ነገር ላይ እደርስ ነበር፤ ቤተሰቦቼ እንዲህ ስለሆኑ ነው፣ የሚያስጠናኝ የሚያስረዳኝ ሰው ስለሌለ ነው፣ መጽሐፍ የሚያውሰኝ የለም፣ መጽሐፍ የሚገዛልኝ የለም›› እያልን ምክንያት ልንደረድር እንችላለን። ግን ኃላፊነት ብንወስድስ? በራሴ ምክንያት ነው የሰነፍኩት፣ ስለማልጥር ነው፣ ሥራዬ ላይ ጥሩ ስላልሆንኩ ነው፣ ማንበብ ስለማልወድ ነው፣ ኃላፊነቱ ራሴ እወስዳለሁ ስንል በህይወታችን በርካታ ነገር ይቀየራል።
ምክንያት ማብዛትም ቀላል ነው። ሰውዬው ቁልፍ ይጠፋበታል። ምሽት ነው። እየፈለገ ነው። ኧረ ! ዛሬ የት ነው የማገኘው እያለ እየተተራመሰ ነው። በመንገድ የሚያልፉ ሰዎች ደግሞ አያግዙትም። የሚፈልገው ብርሃን ላይ ነው። እንዴት ቁልፉ እንደጠፋበት አያውቅም ይሁን ብቻ ይፈልጋል። አንድ ጠጋ ብሎ ‹‹ምን አጥተህ ነው?›› አለው። ቁልፍ ጠፋብኝ አለ። እሺ ላፋልግህ ብሎ ማፋለግ ጀመረ። ደቂቃዎች ነጎዱ። ‹‹ይሄ ነገር እዚህ እንደጠፋብህ ርግጠኛ ነህ›› አለው ሰውዬው።
‹‹አይ እሱማ የጠፋብኝ እዛ ጨለማ ጋር ነው፤ ነገር ግን ለመፈለግ የሚመቸው እዚህ ብርሃኑ ጋር ነው›› አለው። አያችሁ! በሕይወታችሁ ውስጥ አንዳንድ ጊዜ ምክንያት ለመፍጠር በጣም ቀላል ነው። ያጠፋነው እኛ ሆነን ጨለማው እኛ ውስጥ ሆኖ ብርሃኑ ግን ቀላል የሆነውን መንገድ ለምክንያት እንጠቀማለን። በቤተሰቤ ነው፣ ትምህርቴ ነው፣ ጓደኛ የለኝም፣ የሚያስረዳኝ ሰው የለም እንላለን። ስለዚህ ምክንያቶች ብቻ ስንፍናችንን ወስደውብናል። ከዛሬ ጀምሮ ኃላፊነት መውሰድ እንጀምራለን።
2ኛ. የምንመኘውን ማወቅ አለብን
አንዳንድ ጊዜ ‹‹እኔ እኮ ያው ኑሮ እየከበደ መጣ እንጂ አቅሙ ነበረኝ፤ አሁን ግን ኑሮ ተወደደ›› እንላለን። ነገሮች ቀላልና አልጋ በአልጋ እንዲሆኑ መመኘት የለብንም። እኛ ነን መክበድ ያለብን። ኑሮ እንዲቀል የምንፈልግ ከሆነ መቼም አይቀልም። በሃምሳ ዓመት ልምድ ውስጥ ኑሮ እየተወደደ እንጂ እየረከሰ አልመጣም። ከንጉሡም ዘመን፤ ከደርግም፤ ከኢህአዴግም ጀምሮ እያንዳንዱ ነገር እየጨመረና እየተወደደ መጣ እንጂ አንድም የቀነሰ ነገር የለም።
ስለዚህ ማሰብ ያለብን የእኛን የመግዛት ወይም የገንዘብ አቅማችንን ማሳደግ ነው እንጂ ነገሮች ለምን አይረክሱም፤ ለምን ኑሮ ተወደደ ብለን ምክንያት ማብዛት የለብንም። ከዚህ አንፃር የምንመኘውን ነገር ማወቅ አለብን። በትምህርትም እያደግን ስንመጣ እየከበደ እንጂ እየቀለለ አይመጣም። ‹‹እኔ እኮ በልጅነቴ ጎበዝ ነበርኩ አሁን ነው የሰነፍኩት›› የምንል ከሆነ ራሳችንን እያታለልን ነው።
ስለዚህ ትምህርቱ እስከ ከበደ ድረስ እኛም ትምህርቱን ልናከብደው ይገባል። ለትምህርቱ የሚመጥን አቅም ማዘጋጀት አለብን። ከትምህርቱ ጋር አብረን ማደግ አለብን። ምኞታችንም አብሮ ማደግ አለበት። ኑሮ ሲወደድ እኔ ገቢዬን እጨምራለሁ እንጂ ኑሮ መወደዱ ሊያበሳጨኝ አይገባም ማለት አለብን።
3ኛ. ራሳችንን ስላላወቅን ነው
አይታችሁ ከሆነ አንዳንዴ ለራሳችን የምንሰጠው ቦታ ወይም ደግሞ ራሳችን እየሠራነው ያለውን ነገር ካላወቅን ሰነፍ እንደሆንን ልናምን እንችላለን። ስለዚህ መፍትሔው ራስን ማወቅ ነው። ዶክተር ኤለን ላገር የተሰኘች ተመራማሪ ባጠናችው ጥናት በሆቴል ውስጥ 84 ሠራተኞች አሉ። እነዚህ ሠራተኞች አልጋ አንጣፊዎች ናቸው። አንዷ ሠራተኛ በቀን 15 አልጋ ታነጥፋለች። ወይም አስራ አምስት ክፍሎችን ታፀዳለች። እነዚህ 84 ሠራተኞች ተጠየቁ..
‹‹ስፖርት ትሠራላችሁ ወይ? ተባሉ። ሃያዎቹ ‹‹አይ! በፍፁም ሠርተን አናውቅም›› አሉ። የተቀሩት ደግሞ ‹‹ብዙ ጊዜ አንሠራም አንዳንዴ ሲመቸን እንሠራለን›› አሉ። አጥኚዎቹ ምን ብለው መለሱ..‹‹ የሥራ መደቡ መስፈርት እኮ የእናንተን ሥራ ያሟላል። የምትሠሩት ሥራ በሙሉ ቅልጥ ያለ ስፖርት ነው›› አሏቸው። ሠራተኞቹ በጣም ተገረሙ። እነዚህ አጥኚዎች ከወር በኋላ ሲመለሱ አብዛኛዎቹ ሠራተኞች ሁለትና ከዚያ በላይ ኪሎ ግራም ቀንሰዋል። የሚገርም የሰውነት አቋም ይዘዋል።
ከዚያ አጥኚዎቹ ጠየቋቸው ‹‹እንዴት ነው ስፖርት ጀመራችሁ ወይ? የዛሬ ወር መጥተን ካናገርናችሁ በኋላ ስፖርት ጀመራችሁ እንዴ›› ሲሏቸው ኧረ! አልጀመርንም ግን ምንሠራው ሥራ ስፖርት እንደሆነ ስናውቅ ይኸው ይሄ ነገር ተፈጠረ አሉ። አያችሁ! አንዳንድ ጊዜ በሕይወታችን ገቢያችን ጥሩ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ምን ያህል እያስገባን እንደሆነ ካላወቅን ወጪ ላይ ብዙ እያፈሰስን ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ገቢያችንን ስናውቅ ‹‹አሃ! እኔ እኮ ጥሩ ገቢ አለኝ፤ የጨረሰብኝ እኮ እንዲህ ማውጣቴ ነው፣ እንዲህ ማድረጌ ነው ስንል ያለንበትን እናውቃለን። ‹‹እኔ ሰነፍ ስለሆንኩ አይደለም፤ የሆነች ትንሽ ክፍተት ናት፣ ራሴን ስላላወኩ ነው›› ስንል ሕይወታችን መስተካከል ይጀምራል። ስለዚህ ሰነፍ ስለሆንን አይደለም ራሳችንን ስላላወቅን ነው።
4ኛ. ሥነ ምግባር ማዳበር
ሥነ ምግባር(ዲስፕሊን) ከሌለን አቅም ቢኖረንም ጥረታችን ሁሉ ያለ ዲስፕሊን ከሆኑ ይበላሻል። ወጥ አይሆኑም። እንደውም ኬንያዊው የማራቶን ሯጭ ኢሉድ ኪፕቾጌ ‹‹ዲስፕሊን ያለው ሰው በጣም ነፃነት አለው። ምክንያቱም ማድረግ ያለበትን ካደረገ በኋላ አይምሮው ነፃ ይሆናል። ግን ዲስፕሊን የሌለው ሰው የስሜቱ ባሪያ ነው። አሁን እኮ ባታጠናስ፣ ባትሰራስ ስለሚለው ያንን ያደርጋል። ተዝናና ሲለው ስሜቱን ይከተልና ይዝናናል። ስለዚህ ስሜቱ ባሪያው አድርጎታል። ዲስፕሊን ያለው ሰው ግን ነፃነት አለው›› ይለናል። ስለዚህ ዲስፕሊን እንዲኖረን ማድረግ ያለብኝን ሳልጨርስ አልዝናናም። ሶሻል ሚዲያ አልጠቀምም፣ እንዲህ አላደርግም… ወዘተ ማለት አለብን።
5ኛ. ደካማ ጎናችን ላይ ስለምናተኩር
ደካማ ጎናችን ላይ ስለምናተኩር ይሆናል ሰነፍ እንደሆንን የሚሰማን። ያተኩርንባቸው ነገሮች ጎልተው መውጣት ይጀምራሉ። ድክመታችን ላይ የምናተኩር ከሆነ በቃ! ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠረናል። ዛፉን ብቻ የምናይ ከሆነ መኪና እየነዳን ከዛፉ ጋር መጋጨታችን አይቀርም።
ስለዚህ በአንድ ትምህርት ደከም ካልን አይ እኔ እኮ በሁሉም ትምህርት ነው ልንል እንችላለን። በፍቅር ግንኙነታችን፣ ወይ በሥራ አልያም ደግሞ በትምህርት በሆነ አጋጣሚ ድክመት ካለብን እኔ እኮ አልረባም ልንል እንችላለን። ግን ጠንካራ ጎናችን ላይ ብናተኩርስ? ለምሳሌ ትምህርት ካላዋጣን ለምን ቢዝነስ ላይ አናተኩርም። ተግባቢ ከሆንን ከመግባባት ጋር የተገናኘ ሥራ አንሠራም።
ለምሳሌ ኃይሌና ዩዜን ቦልት በመቶ ሜትር ርቀት ሩጫ ሊፋለሙ አይችሉም። ዩዜን ቦልት በርቀቱ አንበሳ ነው። ኃይሌ ደግሞ በ10 ሺ ሜትር አንበሳ ነው። ስለዚህ እናንተም ለምን ጠንካራ ጎናችን አልጎላም ብላችሁ መጨነቅ እንጂ ደካማ ጎናችሁ ላይ በፍጹም አታተኩሩ። የስንፍናህ መነሻው ደካማ ጎንህ ላይ ማተኮርህ ነው። ስለዚህ የስንፍና መድኃኒቱ ጠንካራ ጎንህ ላይ ማተኮር ነው።
6ኛ. በትናንሽ ስኬቶቻችን እንደሰት
ትንሽ ነገር ስታሳኩ ‹‹እኔ እኮ ምን ዓይነት ጭንቅላት ነው ያለኝ፣ እንዴት ጎበዝ ነኝ›› እያልን ራሳችንን እናድንቅ፤ ለራሳችን እንጎርር። በራሳችን ፊት ራሳችን ግዙፍ እንደሆንን እንዲሰማን እናድርግ። አንዳንዴ በጣም የምናደንቃቸው ሰዎች አሉ። በስፖርት፣ በሙዚቃ ወይ ደግሞ በፖለቲካና በኪነጥበብ ሊሆን ይችላል። አንድ ነገር ግን ይወቁ! እዛ ሰው ውስጥ ያለው ማንነት ወይም ችሎታ እኛም ውስጥ አለ። ማመን ብቻ ነው የሚጠበቅብን።
እንደዚህ ዓይነት እምነት ግን የምናዳብረው በትናንሽ ልፋቶች ነው። በትናንሽ ጥረቶች ነው። ወይም በትናንሽ እምነቶች ነው። ስለዚህ ትናንሽ ነገሮችን ስናሳካ ‹‹አዬ! ቀላል ሰው አድርጋችሁኛል! በጣም ጀግና ሰው ነኝ፣ በጣም ጎበዝ ነኝ›› ስንል ሌሎች ነገሮችንም እንድንሞክር ማንነታችን ይገፋፋናል። ‹‹እንዴ! ባለፈው የሰራኸው ነገር እኮ የሚገርም ነው ይችን ብትሞክራትስ›› ይልሃል። አያችሁ ስንፍና ወደኋላ ያስቀራችሁ ለራሳችሁ የምትሰጡት አድናቆት በማነሱ ነው። ራሳችሁን አድንቁ።
በነገራችን ላይ በጣም ጉረኛ ሰዎች ሕይወታቸው በጣም የተስተካከለ ነው። ያው ጉረኛ ስለሆኑ እኛ ላንወዳቸው እንችላለን። እነርሱ ግን በጎረሩ ቁጥር ‹‹እንዲህ አለኝ እኮ፣ ቀላል ሰው አድርገኸኛል›› እያሉ በባዶ ሜዳ ጎርረው የሆነ ሰዓት ላይ ያ ነገር ወደ ሕይወታቸው ይመጣል። አያችሁ! በራሳቸው ገዝፈው ይታያሉ። ስለዚህ እኛስ? ሰው ፊት ባንጎርር ለራሳችን ለምን አንጎርርም? ራሳችንን ለምን አናደንቅም? እንደምንችል ለራሳችን እየደጋገምን ለምን አንነግረውም ?ትንሽ ነገር ስናሳካ ‹‹ቀላል ሰው አይደለሁም እኔ! ጀግና ነኝ›› እንበል። ከዛ ለውጡ ታዩታላችሁ። ስለዚህ ወዳጆች! ከላይ በተዘረዘሩት ስድስት ነጥቦች መሠረት ሰነፍ ስለሆናችሁ አይደለም፤ ከነዚህ ክፍተቶች መካከል አንዱ በውስጣችሁ ስላለ ነው። እነዚህ ነገሮች የሏችሁም ማለት ግን ሰነፍ ናችሁ ማለት አይደለም። ለምን? ማስተካከል ትችላላችሁ። ስለዚህ ከነመፍትሔው ሕይወታችሁ ላይ መተግበር እንዳትረሱ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም