የኦሮሚያ ክልል በተፈጥሮ ሀብት የታደለ ነው። ከእነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች መካከልም ማዕድናት ይጠቀሳሉ፡፡ በክልሉ የወርቅ፣ የከበሩ ማዕድናት፣ የድንጋይ ከሰል፣ የኢንዱስትሪ፣ የኮንስትራክሽንና ሌሎች ማዕድናት በስፋት ይገኛሉ፡፡ እነዚህን የማዕድን ሀብቶች በማልማት በኩልም አነስተኛና ከፍተኛ አምራቾች እንዲሁም ኩባንያዎች ተሰማርተው ለራሳቸውም ለሀገራቸውም ገቢ እያስገኙ ናቸው፡፡
የክልሉ ማዕድን ልማት ባለሥልጣን መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ በክልሉ በማዕድን ልማት 804 አነስተኛ አምራቾች እና ከፍተኛ አምራቾች ተሰማርተዋል፡፡ በዘርፉ በተያዘው በጀት ዓመት ግማሽ ዓመት ብቻ በማዕድን ዘርፉ ከአንድ ሺ 314 በላይ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል አግኝተዋል፡፡
የኦሮሚያ ማዕድን ልማት ባለሥልጣን ዋና ኃላፊ አቶ በዙ ዋቅቤካ በክልሉ እምቅ የማዕድናት ሀብት መኖሩን ጠቅሰው፣ የወርቅ፣ የከበሩ ማዕድናት፣ የድንጋይ ከሰል፣ የኢንዱስትሪ እና የኮንስትራክሽን ማዕድናትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ማዕድናት እንደሚገኙ ያመላክታሉ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ ክልሉ ካሉት በርካታ ማዕድናት መካከል ከ60 በላይ ማዕድናት በጥናት ተለይተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል እስካሁን 40 የሚደርሱትን ለማልማት ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ እነዚህን ማዕድናት በሙሉ ለማምረት የሚያስችል ፈቃድ ወስደው የተሰማሩ ባለሀብቶች የሉም፤ ይህም በአካባቢው ያለውን ዕምቅ የማዕድን ሀብት አልምቶ ሀገርን ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር እምብዛም ያልተሰራበት መሆኑን ያመለክታል፡፡
በማዕድን ልማቱ በኩል አሁን ላይ መሻሻልና ለውጦች እየታዩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በልማቱ ብዙ ርቀት ለመጓዝ ብዙ መሥራት ይጠይቃል ሲሉ ያመላክታሉ፡፡ በተያዘው በጀት ዓመትም ክልሉ የተለያዩ ማዕድናትን ለማምረት አቅዶ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ማዕድናት በማልማት ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡትን ምርቶች በሀገር ውስጥ በመተካት እንዲሁም ወደ ውጭ በመላክ ማዕድናቱ የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኙ እየተሠራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
በማዕድን ዘርፉ ለማሳካት ከታቀዱት አራት ግቦች መካከል፤ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት እና የውጭ ምንዛሪን ግኝትን ማሳደግ በሚሉት ላይ ያተኮሩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በማዕድን ዘርፉ በርካታ ቁጥር ያላቸው አምራቾች የተሰማሩ ሲሆን ውጤታማ የሆኑት ግን ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በክልል ደረጃ ፈቃድ የወሰዱት አነስተኛ አምራቾች 781 ሲሆኑ፤ በፌዴራል ደረጃ ፈቃድ ወሰደው በክልሉ ማዕድን ልማት ላይ የተሰማሩ ደግሞ 23 ከፍተኛ አምራቾች ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል በአነስተኛም ሆነ በከፍተኛ ፍቃድ ካገኙ አልሚዎች ውስጥ ውጤታማ የሆኑት ጥቂቶች ሲሆኑ፣ አብዛኞቹ ብዙ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
አቶ በዙ እንዳሉት፤ በክልሉ ሜድሮክ ኩባንያ ወርቅ በማምረት ውጤታማ ነው፡፡ ሜድሮክም ቢሆን ግን ክልሉ ካለው ሀብትና አቅም አንጻር ከዚህ በላይ መሥራት እንዳለበት ይጠበቃል። በዘርፉ ምን ያህል አምራቾች ተሰማሩ ማለት ሳይሆን ምን ያህሉ ናቸው ውጤታማ የሆኑት የሚለው በደንብ ተፈትሾ መሥራት ይኖርበታል፡፡
በክልሉ በ2016 በጀት ዓመት በማዕድን ዘርፍ በርካታ ሥራዎች መሥራታቸውን የገለጹት ዋና ኃላፊው፤ በማዕድን ዘርፉ ከአንድ ሺ 314 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፈጠሩንም ተናግረዋል፡፡ በጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት መሠራቱን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ወራት ደግሞ የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል ትልቅ ለውጥ እንደሚመጣ ይታመናል ብለዋል፡፡
በክልሉ ለማዕድን ዘርፉ የልማት ጋሬጣ ከሆኑ ችግሮች መካከል የኮንትሮባንድ ንግድና ሕገ ወጥ የማዕድን ዝውውር፤ አለመረጋጋትና የሰላም እጦት እንዲሁም ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ማምረት አለመቻል ዋና ዋናዎቹ ናቸው ያሉት ዋና ኃላፊው፣ በዘርፉ ያጋጠሙትን እነዚህን ሦስት ጋሬጣዎች ለመፍታት ብዙ መሠራቱንም ገልጸዋል፡፡ ለአብነት ኮንትሮባንድ /ሕገ ወጥነት/ ለመከላከል ኅብረተሰቡን ያሳተፉ የተለያዩ አሠራሮች በመዘርጋት እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ሕገ ወጥነትን ከመከላከል አንጻር ሕገ ወጥ አካላትን በመለየትም ርምጃ ተወስዷል፡፡ ማዕድን በማምረት ሥራ ላይ በባሕላዊ መንገድ ብቻ ሁለት ሺ463 ፈቃድ አውጥተው እየሠሩ ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ሕጋዊውን መስመር ተከትለው እንዲሰሩ ለማስቻል በተደረገው የማጣራት ሥራ ፈቃድ ወስደው ሕጋዊ በሆነ መንገድ እየሠሩ ያሉት 781 ብቻ ናቸው፡፡ በመሆኑም ከአንድ ሺ 600 በላይ አምራቾች ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ ማዕድን እያመረቱ በመገኘታቸው ርምጃ እንደተወሰደባቸው አስታ ውቀዋል፡፡
በተጨማሪም ሕገ ወጥነትና ኮንትሮባንድ ሊከላከል የሚችል ከተለያዩ አካላት የተወጣጣ የማዕድን ኮሚቴ በቦርድ ደረጃ ተቋቁሟል። ኮሚቴው ከክልል ጀምሮ እየሠራ ይገኛል። በዚህም ለውጦች እየመጡ ናቸው፡፡ በዚህ ሥራ ኅብረተሰቡንም በደንብ ማሳተፍ ይገባል። እነዚህን ማነቆዎች ለመፍታት በተደራጀ መልኩ በመሥራት ኮንትሮባንድና ሕገ ወጥነትን መከላከል ለውጦች ማምጣት ይቻላል ብለው እንደሚያመኑም ዋና ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
ማዕድን ማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ አምራቾች ቴክኖሎጂ እንዲያገኙና አቅማቸው እንዲዳብር መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ዋና ኃላፊው፤ ይህም በአሠራር፣ በመመሪያ፣ በደንብና በአዋጆች እንዲደገፍ ብዙ መሥራትን እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡ በሰላም ጉዳይ ላይም የሚመለከታቸው የፀጥታ ኃይሎች ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
እንደዋና ኃላፊው ማብራሪያ፤ መንግሥት በተለይ ለማዕድን ዘርፉ በሰጠው ትኩረት ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝና ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት እንዲቻል የሚረዱ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው፡፡ የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ያሉት ማዕድናትን ለማምረት ሰላም በማስጠበቅ ረገድ የፀጥታ አካላት የሚሰሩት ሥራ እንዳለ ሆኖ ኅብረተሰቡን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ የድርሻውን መወጣት አለበት። በሰላም ረገድም ቢሆን መሻሻሎች ታይተው ለውጦች እንደሚመጡ ይታመናል ብለዋል፡፡
‹‹ክልሉ በማዕድን ሀብት የበለጸገ ቢሆንም፣ ከዚህ ሀብት የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ አይደለም›› ያሉት ዋና ኃላፊው፤ ለዚህ ምክንያቱ ቀደም ሲል የማዕድን ዘርፍ እምብዛም ትኩረት ተሰጥቶት ባለመሥራቱ ነው ይላሉ፡፡ ዘርፉ በመንግሥት ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ተደርጎ መሠራት ከተጀመረ ቅርብ ጊዜ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዘርፉን በቴክኖሎጂ መደገፍ የመጀመሪያው ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራበት የሚገባው ጉዳይ እንደሆነ ያመላክታሉ። ዘርፉን ለማጠናከር አመለካከትን ጭምር መቀየር እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾች እውቀትና ብቃት እንዲኖራቸው በቴክኖሎጂ የዳበረ ልምድ እንዲያገኙ መሠራት አለበት ሲሉም ገልጸዋል፡፡
‹‹ማዕድንን ማልማት በባሕሪው ከፍተኛ ካፒታል ይጠይቃል›› ያሉት ዋና ኃላፊው፤ አሁን እየተሠራ ባለበት መንገድ በማዕድን (በባሕላዊ እና በተበታተነ መልኩ) የማምረት ሥራ ላይ ውጤት ማምጣት እንደማይቻልም ያመናሉ፡፡ እነዚህን አምራቾች ወደ አንድ በማምጣትና በማቀናጀት በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ ማድረግ ከተቻለ ለውጦች ማምጣት እንደሚቻል ጠቅሰው፤ አሁን መንግሥት በሰጠው ትኩረት ልክ ልማቱ የሚቀጥል ከሆነ ውጤቶች ማምጣት ይቻላል ብለዋል፡፡
አቶ በዙ እንዳስታወቁት፤ የማዕድን ዘርፉን ሥራ ከፖሊሲ፣ ከአዋጆች እና ከሕግ ጋር አቀናጅቶ መሥራት በፋይናንስና በሎጀስቲክ መደገፍ መቻልን እስከ ታችኛው እርከን ድረስ በደንብ መሬት ይዞ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ ‹‹ማዕድን ስለተፈለገ ብቻ አይገኝም፤ በማዕድን ላይ ድርሻ ያላቸው አካላት ሁሉ ኃላፊነታቸውን መወጣት ሲችሉ ነው ውጤት ማምጣት የሚቻለው፡፡ መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት ብዙ ለውጦች እየታዩ ናቸው፤ ልማቱ እነዚህን አጠናክሮ ማስቀጠልን ይጠይቃል፡፡ በማዕድኑ ዘርፍ የተሰማሩ አካላት በእውቀት ላይ የተመሠረተ ሥራ እንዲሰሩ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ሀብት አውቆና ተረድቶ በእውቀት መመራት ይገባል፡፡
በባለሥልጣኑ በኩል የዘርፉን ችግሮች በመፍታት የማዕድን ልማቱን ለማፋጠን እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ አሁን በማዕድን ዘርፉ የተመዘገቡትን ውጤቶች በማስቀጠል በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ብዙ ጥረቶችን ማድረግ እንደሚያስፈልግም ዋና ኃላፊው አስገንዝበዋል፡፡
የክልሉ የማዕድን ልማት ባለሥልጣን ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ትዕግስት ተረፈ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ሰባት ወራት ውስጥ በርካታ ማዕድናት ወደ ውጭ ተልከዋል፡፡ በክልሉ በሰባት ወራት ውስጥ የማዕድን ዘርፍ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ 306 ሚሊዮን 810 ሺህ 980 ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ፤ 163 ሚሊዮን 741 ሺህ 599 ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ከማዕድን ዘርፉ ከሀገር ውስጥ ገቢ አንድ ቢሊዮን 368 ሚሊዮን 338 ሺህ 721 ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ፤ አንድ ቢሊዮን 36 ሚሊዮን 545 ሺህ 436 ብር ገቢ ማግኘት ተችሏል፡፡
በክልሉ የግንባታና የኢንዱስትሪ ማዕድናት በስፋት ገቢ የሚያስገኙ ምርቶች ናቸው ያሉት ምክትል ኃላፊዋ፤ የወርቅና የጌጣጌጥ ማዕድናት የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘታቸው በተጨማሪም ከፍተኛ የሆነ የ“ሮያሊቲ” ገቢ እንዲገኝ ማድረ ጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ባዛሌት፣ አሸዋ፣ ኢግኒምብራይት የግንባታ ማዕድናትን ጨምሮ በክልሉ የተለያዩ ማዕድናት እንደሚመረቱ ጠቅሰዋል። እንደ ላይምስቶን፣ ጂፕሰም፣ የድንጋይ ከሰልና የመሳሰሉት የኢንዱስትሪ ማዕድናትን እንደሚ መረቱ ጠቅሰው፣ ከዚህም ስድስት ሚሊዮን 112 ሺህ 268 ቶን ማምረት መቻሉን አስታወቀዋል፡፡
በክልሉ በሰባት ወራት የማህበራትንና የኩባንያዎችን ምርት ጨምሮ አንድ ሺህ 817 ነጥብ 76 ኪሎ ግራም ወርቅ መመረቱን ጠቁመው፣ 16 ሺህ 730 ኪሎ ግራም የጌጣጌጥ ማዕድናት ማምረት ተችሏል ብለዋል፡፡
ለዘርፉ ዋና ተግዳሮት ተብለው ከሚጠቀሱ ጉዳዮች መካከል ሕገ-ወጥ የማዕድናት ምርት ግብይትና አቅርቦት ዋነኛው መሆኑን ምክትል ኃላፊዋ ያመላክታሉ፡፡ በሰባት ወራቱም ከድንጋይ ከሰል ምርት ጋር ተያይዞ ያለው የገበያ ችግር ፈታኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም በክልሉ ያሉትን የማዕድን ምርት ፈቃዶች በሙሉ በአዲስ መልክ ለማድረግ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ ከፍተኛ እንቅስቃሴ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም አምራቾቹ ሕጋዊ መስመርን ብቻ ተከትለው እንዲሰሩ ከፍተኛ ሥራ መሥራቱን አመላክተዋል፡፡ ሕጋዊ አሠራር የማይከተሉ አምራቾችንም በመለየት ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድባቸው መደረጉንም ጠቅሰው፣ በዚህም መሠረት የግንባታና የኢንዱስትሪ ማዕድናት ምርት ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም