ትውልዱ በስክነት እና በአርቆ አሳቢነት የተሻለች ሀገር የመገንባት ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል!

እያንዳንዱ ትውልድ በታሪክ ፍሰት ውስጥ ዘመኑን /ወቅቱን በገዛው አስተሳሰብ እና አስተሳሰቡ በወለደው ተግባር የራሱ የሆኑ በመጥፎም ሆነ በበጎ የሚጠቀሱ ዐሻራዎችን ጥሎ ያልፋል። ይህ በየትኛውም የዓለም አካባቢ እና ዘመን የሚገኝ ትውልድ የተጓዘበትና እየተጓዘበት ያለ የሕይወት ጎዳና ነው።

በዚህ የሕይወት መንገድ አንዳንድ ትውልዶች፣ ዘመናቸውን በተሻለ መንገድ በመገንዘብ ዘመኑን በሚዋጅ አስተሳሰብ ተገርተው፤ ለራሳቸው፣ ለሀገራቸው፤ ከዚያም አልፈው ለመላው የሰው ልጆች የሚሆኑ በበጎነት የሚጠቀሱ ተግባራትን አከናውነዋል፣ በዚህ ታሪካቸውም ሁሌም ከመቃብር በላይ ቆሞ የሚሄድ ሆኗል።

ሌሎች ደግሞ ባልተገባ መንገድ በተገሩበት የተዛባ አስተሳሰብ፤ በስሜትና በእልህ፣ በራስ ወዳድነትና በማንአለብኝነት፤ በጥላቻና በከፋ ዘረኝነት መንፈስ ተለክፈው ዓለምን የመከራና የስቃይ ፤ የጥፋትና የእልቂት አውድማ አድርገዋት አልፈዋል ፣ በዚህ እኩይ ተግባራቸውም በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ሁሌም ሲኮነኑ ውለው ያድራሉ።

ዓለም እነዚህን ሁለት ጽንፍ የረገጡ አስተሳሰቦች እና አስተሳሰቦቹ የወለዷቸውን ክፉና ደግ ተግባራት በማስተናገድ ዛሬ ላይ ደርሳለች፤ ከመጣችባቸው ከነዚህ መንገዶች በመማር የሄደችባቸው የመታረም መንገዶችም የአሁኑ ትውልድ የተረጋጋ ሕይወት እንዲመራ መልካም እድል ፈጥሮለታል።

ከዛም በላይ አሁን ላይ ዓለም ለደረሰችበት ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያው እድገት፤ የቴክኖሎጂ ልቀትና የአስተሳሰብ ከፍታ ይህ ከትናንት እየተማሩ የመምጣቱ እውነታ ትልቅ ስፍራ እንደሚኖረው ፤ ነገ ላይም ለሚታሰበው የተሻለች ዓለም ግንባታ ከፍ ያለ አቅም እንደሚሆን ይታመናል።

ከትናንት ስህተቶች ተምሮ ቢያንስ ቢያንስ ፤ ዛሬዎች የትናንት ስህተቶች ጥላ ሰለባ እንዳይሆኑ ማድረግ፤ የትናንት ስህተቶችን በመድገም ከሚከፈል ያልተፈለገ ዋጋ ራስን መታደግ የአንድ ጤነኛ ትውልድ መገለጫ ፤ ዋነኛ ኃላፊነት ነው። ራስን ሆኖ የማለፍ ተፈጥሯዊ ማንነቱ መገለጫ ጭምር ነው።

ይህንን እውነታ በአግባቡ አለማጤን ፤ ቆም ብሎ ከትናንት ክፉና ደግ ታሪኮች ተገቢውን አስተምሮ ለመውሰድ የተከፈተ ልብ እና አእምሮ የማጣት እውነታ እንደ ሀገር እኛ ኢትዮጵያውያንን ብዙ ያልተገባ ዋጋ እንድንከፍል እያስገደደን ያለ እውነታ ነው። ችግሩ ዛሬ ላይ በብዙ ተስፋ የጀመርነው የለውጥ ጉዞ ሳይቀር በፈተናዎች እንዲንገጫገጭ አድርጎታል።

በርግጥ እኛ ኢትዮጵያውያን ካለን የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ግንባታ አኳያ ፤ ዛሬዎቻችንን በተሻለ መንገድ መምራት የሚያስችሉ ሰፊ ተሞክሮዎች/ታሪኮች ባለቤት ነን። እንደ ሀገር ስለ ነፃነት፣ ፍትህ የከፈልናቸው ዋጋዎችና ያጎናጸፉን ልዕልና ከእኛ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያተረፉልን ናቸው።

ከእነዚህ እውቅናዎች በስተጀርባ ያሉ መንፈሳዊ፣ ማህበራዊና ባሕላዊ እሴቶቻችንን ለይተን፣ ለዛሬ ብሔራዊ ማንነታችን ግንባታ አቅም አድርገን በመጠቀም አለመቻላችን፤ ከዛም በላይ እንደ ሀገር ካለንበት የግጭት አዙሪት የዳረጉንን የተዛቡ እሳቤዎች እና ምንጮቻቸውን ቆም ብለን ለማየት ፈቃደኝነት ማጣታችን በትናንት ችግሮቻችን ዛሬ ላይ እንድንዳክር አድርገውናል።

ትናንት ላይ በብዙ ምጥ የጀመርናቸው የለውጥ መነሳሳቶች የየትውልዱን ስክነት አጥተው ፤ ከተስፋ መፈክሮች ሳይዘሉ፤ የቁም ቅዠት ያህል ተጨናግፈው ሲቀሩ፤ ለለውጥ የሚከፈሉ መስዋዕትነቶች ሳይቀሩ የታሪካችን ጥቁር ድሪቶ ሆነው፤ ዛሬዎቻችን እየተናጠቁን ዘመናትን ለመቁጠር ተገደናል።

በተለይም በኃይልና በሴራ ላይ የተገነባው የፖለቲካ እሳቤያችን በየዘመኑ የሚገራው ትውልድ አጥቶ፣ እንደ ሀገር እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ፣ በግጭት አዙሪት ውስጥ እንድንዳክር አድርጎናል። በዚህም ተፈጥሮ የቸረችንን ሀብት ሳይቀር አውቀን በመገልገል፤ ካለንበት ድህነትና ኋላቀርነት መገላገል የሚያስችለንን ዕድል መጠቀም ሳንችል ቀርተናል።

ከዚህ ይልቅ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ጨምሮ በየወቅቱ መነሳታችን የሚያሳስባቸው የውጭ ኃይሎች እኩይ ዓላማ ተጋላጭ አድርገውናል፤ እርስ በርሳችን ላልተገባ መገፋፋት ዳርገውናል፣ የብዙ ጥቁር ታሪኮች ትርክት ባለቤት በማድረግ አንገታችንን አስደፍተውናል። በታሪክ ስብራቶች እንድናነክስ አስገድደውናል።

ይህ ከትናንት ያለመማር ፣ ለዚህ የሚሆን ስክነት የማጣታችን እውነታ ዛሬም በብዙ ተስፋና እልህ የጀመርነውን ለውጥ እየተፍታተ ይገኛል። ባለፉት ትናንቶች በሴራና በኃይል /በእንሞካከር ከመከኑ ትላልቅ የለውጥ ተስፋዎቻችን መማር አለመቻላችን የጀመርነው ለውጥ ፍሬ አፍርቶ ለመጪዎቹ ትውልዶች የመነሳት ጅማሪ እንዲሆን፤ ከሁሉም በላይ ስክነት ፤ እንደ ጤናማ ትውልድ ከትናንት ስህተቶቻችን መማር የሚያስችል የልብና የአእምሮ ዝግጁነት ያስፈልገናል። ዘመኑን የሚመጥን የሚዋጅ የአስተሳሰብ መሠረት መጣልም ይጠበቅብናል።

ችግሮቻችንን በአግባቡ ተረድተን፤ ሁላችንም በንግግር እና በውይይት የመፍትሔ አካል የምንሆንበት አዲስ የአስተሳሰብ ጅማሪ ውስጥ መግባት አለብን። በችግሮች ዙሪያ ጣት ከመቀሰር ወጥተን፤ ከችግሮች ይልቅ ለመፍትሔዎች ትኩረት የምናደርግበትን የትውልድ የአእምሮ ውቅር መፍጠር ይኖርብናል።

ከዚህ ውጭ በየትኛውም መንገድ እና መልኩ ፍላጎቶችን በሴራ እና በኃይል በሀገር እና በሕዝብ ላይ ለመጫን፤ በሁከት እና በጠመንጃ የመንግስት ስልጣን ለመያዝ የሚደረጉ ጥረቶች ከጥፋት ውጪ የሚያመጡት ትርፍ አይኖርም። ይህ ደግሞ ለታሪካዊ ጠላቶቻችን እና በየወቅቱ መነሳታችን ለሚያሳስባቸው የውጭ ኃይሎች እኩይ አላማ ተጋላጭ ከማድረግ ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም።

ትውልዱ ይህንን እውነታ ከትናንት ተጨባጭ ታሪኮቹ በአግባቡ በመረዳት፤ እራሱን ከጥፋት መንገድ መቆጠብ፤ ነገሮችን በሰከነ መንገድ ፤ በአርቆ አሳቢነት እና በኃላፊነት መንፈስ ሊመለከት ይገባል። ይህንን በማድረግ ሀገርን እንደ ሀገር ከማስቀጠል ባለፈ የተሻለች ሀገር የመገንባት ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል!

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You