
አዲስ አበባ፡– በኢትዮጵያ በቲቢ ከተያዙ 156 ሺህ ታማሚዎች 20 ሺህ የሚሆኑት ወደ ሕክምና ማዕከላት አይሄዱም ሲል ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ እና የዓለም ጤና ድርጅት በመተባበር ያዘጋጁት የቲቢ በሽታ የግንዛቤ ማስጨበጫ የግማሽ ቀን ስልጠና ትናንት ለሚዲያ ባለሙያዎች ተሠጥቷል።
በስልጠናው ላይ የተገኙት በጤና ሚኒስቴር የቲቢ፣ የስጋ ደዌ እና ሌሎች የሳንባ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዴስክ ኃላፊ አቶ ታዬ ለታ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ በዓመት 156ሺ የቲቢ ታማሚዎች አሉ ተብሎ ይታሰባል። ከነዚህ ውስጥ 20 ሺህ የሚሆኑት ወደ ሕክምና ተቋም የማይመጡ እና በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ 16 ሺህ የሚሆኑት ታማሚዎች በበሽታው ምክንያት ለህልፈት ይዳረጋሉ።
ጤና ሚኒስቴር በሽታውን መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ በዋናነት ስለበሽታው መተላለፊያ መንገዶች ግንዛቤ በመፍጠር፣ የግል ተቋማትን ያማከለ ሕክምና እና ምርመራ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የበሽታው ተጋላጭ የሆኑት በተለይ በማዕድን ማውጫዎች፣ በካምፖች እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢዎች የሚገኙት ሰዎች መሆናቸውን አስረድተዋል። የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ በኢትዮጵያ አሁን ካለው የቲቢ በሽታ ታማሚ ቁጥር በእአአ 2030 ወደ 108 ሺ ለመቀነስ እንዲሁም በእአአ 2035 ቲቢ የማህበረሰቡ የጤና ችግር በማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ እየተሠራ ነው። የቲቢ በሽታን ለመመርመር የሚረዱ አዳዲስ መሳሪዎችም ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው።
በሽታውን ለመከላከል በሚደረገው ርብርብ የሚዲያ ባለሙያዎች ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ ኅብረተሰቡ ስለበሽታው መተላለፊያ መንገዶች እንዲያውቅ ግንዛቤ በመፍጠር የሚዲያ ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል። የሚዲያ ተቋማትም ማህበራዊ ኃላፊነታቸዉን እንዲወጡ አሳስበዋል።
አብዛኛው የቲቢ በሽታ ምልክት ደረቅ ሳል፣ ክብደት መቀነስ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስና የሌሊት ላብ መሆኑን የተናገሩት አቶ ታዬ፤ ኅብረተሰቡ እነዚህን ምልክቶች ሲያስተውል በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ የቲቢ ምርመራ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ዓለም አቀፍ የቲቢ ቀን መጋቢት 15 “የቲቢ በሽታን መግታት እንችላለን” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል። ስልጠናው የቲቢ በሽታ ምንነት፣ አይነቶች እና መከላከያ መንገዶች ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ ከተለያዩ ሚዲያ ተቋማት የመጡ ጋዜጠኞች ተሳትፈዋል።
መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም