
አዲስ አበባ፡– የኢትዮጵያ ምልዑነት ሊረጋገጥ የሚችለው ሁሉም እምነት፣ ባህልና ታሪክ በልክ ሲቀመጡ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ አካባቢዎች ከተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች ጋር ሰሞኑን ተወያይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስና ከተለያዩ አካባቢዎች ከተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች ጋር ባደረጉት ውይይት እንደገለጹት፤ መንግሥት ሁሉም ማህበራዊ እሴቶች የሀገር ህልውና መሰረት በመሆናቸው መጠናከር አለባቸው ብሎ ያምናል።
የኢትዮጵያ ምልዑነት ሊረጋገጥ የሚችለው ሁሉም እምነት፣ ባህልና ታሪክ በልክ ሲቀመጥ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ኦርቶዶክስን በሚመለከት ምንም የተናወጠ አቋም የለኝም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለኢትዮጵያ መሠረት፣ ጽኑ ምሰሶና የማይፈርስ አስፈላጊ ተቋም ነው ሲሉ አብራርተዋል።
ክርስትና፣ እስልምና፣ ቅዳሴና አዛን የኢትዮጵያ መገለጫዎች መሆናቸውንም አንስተዋል።
እኛ የምንፈልገው እምነትም መንግሥትም በራሳቸው ሕግ፣ ሥርዓትና መርህ እንዲመሩ፤ እንዲሁም አንዱ ለአንዱ ጋሻ በመሆኑ አስፈላጊ በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ አብረው እንዲሠሩ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የእምነት ተቋማትን በሚመለከት በቅርቡ አዋጅ ስለሚወጣ የእምነት ተቋማት በአዋጁ ላይ በመወያየት ሃሳባቸውን ሊያስቀምጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ሀገር የማስተዳደሩ ሥራ መቶ በመቶ የመንግሥት ሥራ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ወንጌል እንዴት ይስፋፋል የሚለው ደግሞ የሃይማኖት አባቶች ሥራ መሆኑን አብራርተዋል። በዚህም መሠረት መተጋገዙ ተገቢ ቢሆንም አንዱ በሌላው ጣልቃ ሳይገባ መሥራት የሚገባው መሆኑን ተናግረዋል።
ወንጌል የሚስፋፋው ሀገር ለመጠበቅ፣ ትውልድ ለማነጽ፣ የሰላምን አውድ ለመፍጠር በሚችል መልኩ መሆኑን ጠቅሰው፤ በመሰል ጉዳዮች ላይ መንግሥት እገዛ ሊያደርግልን ይገባል ብሎ ጥያቄ ማቅረብ አግባብ መሆኑን አስረድተዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት እምነትና መንግሥት ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንዲሠሩ፣ ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኙ፣ ችግሮች ሲያጋጥሙ በውይይት እንዲፈቱ ተደርጓል ብለዋል።
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት በአዲስ አበባ ብቻ የአምልኮ ቦታ 68፣ ለታቦታት ማደሪያ 40፣ ለመንበረ ጵጵስና አንድ፣ ለማዕከል ሁለት በጥቅሉ 111 ቦታዎች ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ካሬ መሬት በላይ መሰጠቱን አስታውቀዋል።
ቋንቋና ባህልን በሚመለከት ለመስፋፋት በሚያስችል መልኩ መሥራት እንደሚገባ ገልጸው፤ ቋንቋን በሚመለከት ቅሬታ ስታዩ በመወያየትና በንግግር መፍታት ይገባል ብለዋል።
ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮችና ከተለያዩ ክልሎች ከተውጣጡ አባቶች ጋር ባደረጉት ውይይት፤ በ1966 ዓ.ም ሙስሊሞች 13 ጥያቄዎችን የያዘ ከፍተኛ ንቅንቄ ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰዋል።
በኢትዮጵያ መንግሥት በሚቀያየርበት ዘመን የሙስሊሞች እንቅስቃሴና ጥያቄ እንደነበርም አንስተዋል።
የሙስሊም ሕጋዊ እውቅና ማግኘት፤ የመደራጀት መብት፤ የመስጊድ ግንባታ ፈቃድ እንዲሁም ሸሪዓን በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎች ሲነሱ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከሚነሱት ጥያቄዎች የተመለሱ ቢኖሩም አሁንም ብዙ ይቀራል ሲሉ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የሙስሊሙም የክርስቲያኑም ሀገር በመሆኗ በተለይ ሙስሊም ወጣቶች እኛ ሁለተኛ ዜጋ ነን እየተገፋን ነው የሚለውን እሳቤ ሊያስተካክሉ እንደሚገባ ገልጸው፤ በሀገራቸው ከሌሎች ወንድሞች ጋር በእኩል የመኖርና የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት በአዲስ አበባ 124 ቦታዎች ለመስጂድ መሥሪያ፣ ሦስት የቀብር ቦታ፣ ለማዕከል አንድ ቦታ መሰጠቱን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ አቅም በፈቀደ መልኩ የእምነት ተቋማትን ጥያቄ ለመመለስ ወደፊትም በተጠናከረ ሁኔታ ይሠራል ብለዋል።
የወሰዱትን ቦታ አጥረው ያስቀመጡ የእምነት ተቋማት ለታለመለት ዓላማ ሊያውሉት ይገባል ሲሉም ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
ኢስላሚክ ዩኒቨርሲቲ፣ ኢስላሚክ ትምህርት እና አረብኛ ቋንቋን ለመጀመር እውቅና ይሰጠን የተባለውን ጥያቄ አስመልክተውም፤ ለሌሎች የእምነት ተቋማትም እውቅና ለመስጠት አቅጣጫ የተቀመጠ ስለሆነ ጥናት ተጠንቶ በጋራ ይመለሳል ብለዋል።
አረብኛ ቋንቋ ትምህርት ለሚለው ግን ኢትዮጵያውያን አረብኛ ቋንቋ አለማወቃችን ጉዳት በመሆኑ ለቢዝነስ ዲፕሎማሲ ሲባል ቢጠናከር ጥሩ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የአለባበስ ሥርዓትን በተመለከተ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመመሪያው ዙሪያ እንነጋገራለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በእኔ በኩል ግን በትምህርት ቤት አካባቢ ሲቪክ የሆነ አቀራረብ ቢኖር መልካም ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ተቋማት አባል አለመሆኗ ጉዳት አድርሶባታል። በአረብ ሊግ የአባልነት እንኳን ባይሆን የታዛቢነት ወንበር ባለማግኘታችን ስለኢትዮጵያ የፈለጉትን እንዲናገሩ ፈቅደናል። የታዛቢነት ወንበር ማግኘት ጠቃሚ በመሆኑ የኢትዮጵያ ሙስሊምና መንግሥት በትብብር ልንሠራባቸው ይገባል።
በአፋርና በሶማሌ ክልሎች አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር የተጀመረው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፤ ለስኬታማነቱ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
ከአፍሪካና ሌሎች ሀገራት ጋር ከሀገሪቱ እምነት፣ ባህልና እሴት የሚጣረሱ ስምምነቶች ተፈራርመዋል ለተባለውም ለኢትዮጵያ የማይመች አንቀጽ ካለው አይፈጸምም ብለዋል።
ከኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ካውንስልና አባል አብያተክርስቲያናት ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት፤ ፕሮቴስታንቶች እንደዜጋ የቀብርና የማምለኪያ ቦታ ማግኘት ይገባቸዋል ብለዋል።
ጥያቄአቸው እስካሁን በተወሰነ ደረጃ የተመለሰ ሲሆን፤ ወደፊት ደረጃ በደረጃ ሁሉንም የማስተናገድ ሥራ የሚሠራ መሆኑን ገልጸው፤ የተጀመሩትን ሥራዎች ለማጠናቀቅ መተጋገዝ ወሳኝ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ጴንጤ፣ ፕሮቴስታንትና ወንጌላውያን የሚገባችሁን ቦታ አግኝታችኋል ወይ ከተባለ ቢበዛ ሁለት በመቶ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቤተ አምልኮ ግንባታን በተመለከተ የተነሱ ችግሮችን ከሌሎች ሃይማኖቶች ልምድ በመውሰድ መፍታት እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ያለው መንግሥት የፕሮቴስታንት ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግሥት በመሆኑ የተለየ ባለቤት ለመሆንና ደጋፊ ለመሆን አትሞክሩ ብለዋል።
ይሄንን እውነት ከዘነጋን ከመቀራረብ ይልቅ መራራቅን እናስፋፋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለመከፋፈል ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በሰከነ መንፈስ በመወያየት ጠንካራ ተቋም በመገንባት ለኢትዮጵያ ኩራት መሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና አንድነትን ማረጋገጥ ብንችል የክፋት ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ሀገር ለመውረር እንደማይነሳሱ ገልጸው፤ መንግሥት ካለው የሰላም ፍላጎት የተነሳ እስረኛ መፍታቱን፣ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዜጎችን ወደሀገር ውስጥ ማስገባቱን እና ለተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ስልጣን ማጋራቱን ተናግረዋል።
አንዳንድ ሰዎች በራሳቸው እሳቤና መመዘኛ ለእነርሱ ሰላም ብለው የሚያስቡት አሁን ያለው መንግሥት ከሌለ ብቻ መሆኑን ጠቁመው፤ ሰላም ሊፈጠር የሚችለው ልዩነትን ማክበር እና አብሮ የመኖር ሥርዓትን ማዳበር ሲቻል መሆኑን አስገንዝበዋል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም