ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖቶች መገኛ ሀገር ናት። ከሕዝቦቿም ከ90 ከመቶ በላይ የሚሆነው ሃይማኖተኛ እንደሆነ ይታመናል። ከዚህ የተነሳም እንደ ሀገር የብዙ ሃይማኖታዊ እሴቶች መገኛ ብቻ ሳይሆን፤ በነዚህ እሴቶች የተገሩ ብዙ ትውልዶችን ማስተናገድ የቻለች የረጅም ዘመን ዕድሜ ባለፀጋም ናት።
የሃይማኖቶቹ እሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፈጠሩት ፈሪሀ እግዚአብሔር / ፈጣሪን የመፍራት እሴት አንጻርም በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች ፣ በፍቅር እና በመተሳሰብ ከፍያለ ማኅበራዊ መስተጋብሮችን ፈጥረው አብረው መኖር የቻሉበትን የታሪክ ገጾች ጽፈው ማለፍ ችለዋል። ይህም ለዘመናት ሀገራዊ መለያችን ሆኖ አገልግሎናል።
ፍቅር ከዚህ የሚመነጭ ወንድማማችነት ፣ ትህትና ከዚህ የሚመነጭ ወንድምን እስከ ጉድለቱ መቀበል ፣ ይቅር ባይነት ከዚህ የሚመነጭ ሆደ ሰፊነት ፣ ልግስና ከዚህ የሚመነጭ በክፉ ቀናት የሚገለጥ ቅንነት …ወዘተ የቀደሙት ትውልዶች /አባቶቻችን የጋራ ስብዕናዎች ዋነኛ መገለጫ ነበሩ።
ልዩነቶችን በመቻቻል ፣ ከዛም ባለፈ ውበት አድርጎ ከማየት የተቀዱት ፣በዚህም ዘመናት ያስቆጠሩት ማኅበራዊ እሴቶቻችን ፣ እንደ ሀገር ለመጣንባቸው ረጅም ዘመናት ሆነ፣ በጠንካራ መሠረት ላይ ለተዋቀረው የሀገረ መንግሥት መንግሥት ታሪካችን አልፋና ኦሜጋ እንደነበሩም ይታመናል።
ይህም ከራሱ ይልቅ ለጎረቤቱ የሚያስብና ፣ መንገደኛ በፍቅር ተቀብሎ፣ አብልቶ፣ አጠጥቶ ፣ እግር አጥቦ መኝታውን ለቆ መሬት የሚተኛ ከፍ ያለ የሞራል ልእልና የተላበሰ ትውልድ በዘመናት መካከል መፍጠር አስችሏል። የማይቻሉ የሚመስሉ መንፈሳዊ /ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችን መሬት አውርዶ በሕይወቱ መግለጽ የቻለ ትውልድ ተፈጥሮ በተጨባጭ ታይቷል።
ለቀጣይ ትውልዶች የሕይወት ስንቅ የሚሆኑ የሕይወት ልምምዶች ፤ለተሻለ አስተሳሰብ መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ እሴቶች ፣ በነዚህ እሴቶች የተገሩ ማኅበራዊ ማንነቶች ተፈጥረው ፣ በነዚህም እንደ ሕዝብ ከፍ ያለ የሞራል ልዕልና ተላብሰናል። የታላላቅ ታሪክ ባለቤቶች መሆን የቻልንበትን አቅም ገንብተውልናል።
ክፉ በሚባሉ ቀናቶች ሳይቀር፤ በነዚህ ከፍ ባሉ የሞራል እሴቶች ተደግፈን ማኅበራዊ ማንነታችንን ሳናዛንፍ ዘመናትን መጓዝ ችለናል። በዚህም ለዓለም እንቆቅልሽ የሆንባቸው ክስተቶች በየዘመኑ ተፈጥረዋል። በእነዚህ የዘመኑን ተግዳሮቶች ተሻግረን ዛሬ ላይ መድረስ ፤ነገዎቻችንንም ተስፋ ማድረግ ችለናል።
የዛሬ ፈተናዎቻችን ምንጭ ይህንኑ እውነታ ተረድተን ማስቀጠል አለመቻላችን እንደሆነ የብዙዎች እምነት ነው። ከነዚህ ዘመን ተሻጋሪና አሻጋሪ እሴቶቻችን ጋር ያደረግነው ያልተጋባ ፍች እንደሆነም እንዲሁ ብዙዎች ይስማማሉ። የነገ ተስፋችን ተግዳሮትም ይሄው እውነት እንደሚሆን ለብዙዎች ጥያቄ አይደለም።
ከዚህ የተነሳ አሁን ላይ ይህንን እውነታ ቆም ብለን በሰከነ መንፈስና በጠራ አዕምሮ ልናጤነው፣ ደግመን ደጋግመን ልናስበው ፣ በተለይም ያለንበት ወቅት የታላላቅ ጾሞች ወቅት ከመሆኑ አንጻር አጋጣሚውን በአግባቡ ልንጠቀምበት ፣ ውስጣችንን በአግባቡ ተመልክተን ከራሳችን ጋር እርቅ ልንፈጥርበት ይገባል።
ካልተገባ ጥላቻ እና ጠብ ወጥተን ፤ከጠባችን እና ከተዘራብን ጥላቻ በስተጀርባ ያሉ ትርክቶችን በቀደሙት መንፈሳዊና ማኅበራዊ እሴቶቻችን መርምረን የጥላቻ እና የጥፋት ባርነት ራሳችን እና ማኅበረሰባዊ ማንነታችንን ነጻ ማውጣት ይጠበቅብናል።
ያለንበት የጾም ጸሎት ወር የትናንት ወንድማማችነታችንን ፣ ”አንተ ትብስ እኔ … ” ለሚለውን የቀደመ የማንነት ሥሪታችን ትንሳኤ፣ ከተጣባን ራስ ወዳድነት እና ደንታ ቢስነት ወጥተን ከፍ ባለ የሞራል እሴት እንደ ሀገር በኃላፊነት መንፈስ የዕለት ተዕለት ሕይወታችንን የምንመራበትን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መፍጠር የሚያስችል ሊሆን ይገባል። ለዚህ የሚሆን መንፈሳዊ ዝግጁነትም ከሁሉም የሚጠበቅ ይሆናል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2016 ዓ.ም