“ወደ 71 የሚሆኑ የእንሰት ዝርያዎች እንዳይጠፉ አድርገናል” ዶክተር ዮሐንስ ገብሩ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት

ዩኒቨርሲቲዎች ከሚኖራቸው ዓለም አቀፋዊ፣ ሀገራዊና ክልላዊ ጠቀሜታ አኳያ በሶስት ዋና ዋና ተልዕኮዎች የተለዩ መሆናቸው ይታወቃል። ይኸውም የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች፣ አፕላይድ (የትግበራ) ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች እና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች በሚል ነው። በአራተኝነት የተቀመጡት ደግሞ አጠቃላይ ዩኒቨርሲቲዎች ሲሆኑ፣ አንድ ተጨማሪ ልዩ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ (ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ) መለየቱን የትምህርት ሚኒስቴር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች ከተካተቱ 15 ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ አፕላይድ ሳይንስ ሲባልም በተጨባጭ ጥናታዊ ትግበራ ላይ በመመሥረት የተጠቃለሉ ትምህርቶችን የሚያቀርብ ዘርፍ መሆኑ ይነገራል። ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ሬስ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድን በመስክ ሥራው ወደ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት ከዩኒቨርሲቲው የምርምር፣ የማኅበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ትራንስፈር ምክትል ፕሬዚዳንት ከሆኑት ከዶክተር ዮሐንስ ገብሩ ጋር በዩኒቨርሲቲው እየተካሔዱ ስላሉ የማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት እና የምርምር ሥራዎችን እንዲሁም ስለ አፕላይድ ሳይንሱ ሁኔታ ላይና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት አድርጎ ተከታዩን ዘገባ አጠናቅሯል።

ዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት እና በምርምር ሥራዎች ትኩረት አድርጎ የሚሰራው በየትኞቹ ላይ ነው?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡- ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በምርምር የማኅበረሰብ አገልግሎት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። ከምንሠራቸው በርካታ ምርምሮች ለምሳሌ ያህል እኤአ ከ2021 እስከ 2022 ድረስ ወደ 50 ፕሮጀክቶች ነበሩ። ሶስት ደግሞ ሜጋ ፕሮጀክቶች ነበሩ። እኤአ በ2023 ደግሞ ወደ 48 ፕሮጀክቶች ነበሩ። እነዚህን ፕሮጀክቶች የምንሰራው ከምርምር ጎን ነው።

ፕሮጀክቶቹን የምናስኬዳቸው ከመንግሥት ከሚመደብልን በጀት በተጨማሪ ከተለያዩ ድርጅቶች ከምናገኘው በጀት ነው። በዘንድሮ ዓመትም ይህን እየከለስን ነው። ሰሞኑን ለመምህራን በተመረጡ የምርምር መስኮች ላይ ድጋፍ መስጠት እንጀምራለን።

ወደ ማኅበረሰብ አገልግሎት ስንሄድ በዚህ አገልግሎት የምንሰራው በተለያዩ ዘርፎች ነው። በዋነኝነት በትምህርት፣ በጤና እና በኢነርጂ ላይ ትኩረት አድርገን እየሠራን እንገኛለን። ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በተለይ የትምህርት ሥርዓቱ ያጋጠመውን ችግር ለመቅረፍ መምህራኑ በ20 ትምህርት ቤቶች በምስራቅ ጉራጌ ዞንና በሁለት ልዩ ወረዳዎች በመጓዝ ቅዳሜ ቅዳሜ የማጠናከሪያ ትምህርት እየሰጡ ነው። በተጨማሪም በጤና ዘርፉ ላይ ደግሞ በአካባቢያችን የሚገኙ የሕክምና ተቋማትን የማጠናከር ሥራ እንሠራለን። በቅርቡም በዩኒቨርሲቲያችን አጠገብ ሐዋሪያት የሚባል ሆስፒታል የማስጀመር እንቅስቃሴ እያደረግን ነው።

በግብርናው ዘርፍ ሰርቶ ማሳያዎች አሉን። የፈርዝዬ የእንሰት ምርምር ማዕከል አለን። ይህ ማዕከል በእንሰት ዙሪያ የሚሰራ ነው ሲሆን፣ ይህ የምርምር ጣቢያ ከዩኒቨርሲቲያችን 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው። ምቄ የሚባል ጣቢያ አለን፤ እዛ ደግሞ የቡና እና የፍራፍሬ ምርምር የሚካሔድበት ጣቢያ ነው። ሌሎችም የምርምር ጣቢያዎች ያሉን ሲሆን፣ በዋነኝነት ግን ሁለቱ ጣቢያዎች በርካታ ሥራዎች የሚሰሩባቸው ናቸው። ከቴክኖሎጂ ሽግግር ጋር ተያይዞም ተመሳሳይ ሥራዎችን እንሰራለን። የአይ.ሲ.ቲ ኢንኩቬሽን ማዕከል አለን። ከኢንጂነሪንግ መምህራን ጋር የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን እንሠራለን። ለሀገር መትረፍ የሚችሉ ወጣት ልጆች ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መጥተው የሚሰልጥኑበት እና አቅማቸውን የሚያሳድጉበትን ሁኔታ እየፈጠርን ነው።

አዲስ ዘመን፡- የዩኒቨርሲቲው መምህራን በሃያ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን እየረዱ ነው ብለዋልና እየተረዱ ያሉት ምን ያህል ተማሪዎች ናቸው? አጋዥ ናቸው የሚባሉትስ መምህራን ቁጥር ምን ያህል ነው?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡– ዘንድሮ እየጀመርን ስለሆነ ልገልጽ የምችለው የአምናውን ነው። በዚህ ሲሳተፉ የነበሩት እስከ ስድስት ሺ የሚደርሱ ማለትም አምስት ሺ 885 አካባቢ ተማሪዎች ናቸው። ለማብቃት ጥረት እያደረግን ያለው ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉትን ተማሪዎች ነው።

እንደሚታወቀው የትምህርት ጥራት ለውጡን በአንድ ጊዜ ማምጣት የሚቻል አይደለም። ይሁንና ባገኘነው ግብረመልስ ብዙዎች እየተጠቀሙበት ነው። ወደ ሃያ ትምህርት ቤቶች እንሂድ እንጂ ሥልጠናውን የሚሰጡት የእኛ መምህራን ብቻ አይደሉም። በጣም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ እኛ መድረስ የምንችልበት አይደለም። በጠዋት መድረስ የሚችሉትን ከእኛ ወደ 50 መምህራንን እንጠቀማለን። አገልግሎቱን ስንሰጥ የቆየነው 50 መምህራን ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪና ከዚያ በላይ ያላቸውን ከዞኑ የተመረጡ መምህራንን እየተጠቀምን ነው። ከዚህ የተነሳ ተሳታፊ የሆነው ወደ መቶ መምህር ነው ማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- ከመምህራኑ የሚጠበቀው ምን ዓይነት አሰራር ነው? ቀጥታ ሔደው ማስተማር ብቻ ነው? ወይስ ሌላ ተጨማሪ የሚያደርጉት ሥራ አለ?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡- መምህራኑ የሚያስተምሩት የማጠናከሪያ ትምህርት ነው። በተለይ ደግሞ ወደ ገጠር ወጣ ሲባል አንዳንዶቹ ትምህርት ቤቶች በቂ መምህራን የሌላቸው ናቸው። ወይም ደግሞ አንዱን የትምህርት ዓይነት በትክክል ለዛ ተብሎ የዘርፉ መምህር ሳይሆን የሚያስተምረው ሌላ የትምህርት ዘርፍ ላይ ያለ መምህር ነው። እንደዚህ ዓይነቱን ክፍተት ለመሙላት ሙከራ እናደርጋለን። እንዲያም ሆኖ ትክክለኛውም መምህር ቢኖርም ተጨማሪ እውቀት ለመስጠት እናስተምራለን።

ከዚህ ጋር አያይዤ መጥቀስ የምፈልገው ነገር ቢኖር የመምህራን አቅም ከማጎልበት አንጻር ሰሞኑን የጨረስነው ከአንድ ሺ አንድ መቶ በላይ መምህራንን የዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ድረስ በመጥራት የአምስት ቀን ሥልጠና ሰጥተናል። ይህንን ሥልጠና የሰጠነው በቅርቡ ከተዋቀረው አዲሱ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጋር በመተባበር ሶስት የኒቨርሲቲዎች ነን። ይህ ማለት ጉራጌ ዞን ላይ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ዞኖች ላይም የተካሔደ ነው። ለምሳሌ የም ዞን የሚባል አለ። የሰጠነው እርሱንም ዞን ጨምረን ነው። ወራቤም ዋቸሞም ዩኒቨርሲቲ በተመሳሳይ ሰጥቷል። በዚህ መልኩ ሶስት የኒቨርሲቲዎች ተቀናጅተን ክልሉ ላይ ያሉ መምህራንን የአዲሱ የሥርዓተ ትምህርት የመጽሐፍ ማስተዋወቂያ ባለፈው ወር አጠናቅቀናል።

አዲስ ዘመን፡- ከእንሰት ምርት ምርምር ጋር ተያይዞ ምን የተሠራ ነገር አለ? የአካባቢው ኅብረተሰብ ከምርቱ በአግባቡ እንዲጠቀምስ ምን ታስቧል።

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡- ከእንሰት ጋር ተያይዞ እየሠራን ያለነው በሶስት ጉዳዮች ላይ አተኩረን ነው። አንደኛ ምርቱ እንዳይጠፋ ማድረግ ነው፤ ምክንያቱም እንሰት የተለያየ ዝርያ ያለው እንጂ ዝርያው አንድ ዓይነት አይደለም። እኛ ባለን የፈርዝዬ ማዕከል ያሉን የእንሰት ዝርያዎች ወደ 71 ያህል ናቸው። እያንዳንዱ ዝርያ የራሱ ጥቅም አለው። የሚያድግበት የአየር ጸባይም አለ። ስለዚህ ወደ 71 የሚሆኑ የእንሰት ዝርያዎችን እንዳይጠፉ ማድረግ ችለናል።

አንዳንዶቹ ዝርያዎቹ ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉ ስለነበሩ ከአርሶ አደሩ ማሳ ቀስ በቀስ እየተመናመኑና እየጠፉ የመጡ ስለሆነ እኛ እንዳይጠፉ በማድረግ ባለፈው ዓመት መልሰን በባዮ ቴክኖሎጂ ደግሞ በቲሹ ካልቸር አባዝተን ስንሰራ ቆይተናል። ስለዚህ ወደ ፈርዝዬ የእንሰት ምርምር ማዕከል የሄደ አንድ ሰው የሚያየው ነገር እንዳይጠፋ የምናደርግበት በብሎክ የተከፋፈለ ለእይታ አንድ ዓይነት የሚመስል ሊሆን ይችላል እንጂ በዝርያ ሲጤን ወደ 71 አንድ ዓይነት ዝርያን ማየት ይቻላል።

ሌላው ከእንሰት ጋር ተያይዞ ሁለተኛው ሥራችን በሽታን የመከላከል ሒደት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ በጣም ደስ የሚል ዜና ተገኝቷል። እንሰት ላይ ከተጋረጡ በርካታ ጉዳቶች አንዱ በሽታ ነው። ባክቴሪያ ዊልት የሚባለው በአማርኛ ደግሞ “እንሰት አጠውልግ” የሚባል የበሽታ ዓይነት አለ። ይህ የበሽታ ዓይነት እንሰትን ከማሳ እያስወገደ ያስቸገረ ነው። ለአርሶ አደሩም ከባድ የሆነ ፈተና ነበር። ዩኒቨርሲቲያችን ከተቋቋመ 11 ዓመቱ ነውና እዛ ላይ በርካታ ምርምሮች ሲካሔድ ቆይቷል። ነገር ግን መጨረሻው ላይ ሳይደርስ ሌላ ዩኒቨርሲቲ አግኝቷል። እሱ ደግሞ ድካማችንን የሚያቀል ነገር ነው። ስለዚህ ምርምሩ አንዱ የሚያተኩረው እሱ ላይ ነው ማለት ነው።

ሌላው ደግሞ በዋነኝነትና በጣም ወሳኝ የሆነው ሒደቱ ነው። እንሰት በእናቶች አቅም የሚሰራ በመሆኑ በጣም አድካሚ ነው። እናቶች በዚህ ሥራ በጣም ይደክማሉ። ስለዚህ እሱን ለመቅረፍ አሁንም በተለያዩ ተቋማት የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ይታያል፤ በተለይ ማሽነሪ ለማምረት ጥረት ተደርጓል። በእኛም ተቋም ሁለት ማሽኖች ፈጥረን እና ድጋፍ አግኝተን በቅርቡ ሰርቶ ማሳያ ላይ ሙከራ አድርገናል።

የባዮ ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ባለበት መድረክ ወልቂጤ ላይ ማሽኖች ተሻሽለውና ያሉባቸው ጥቃቅን ችግሮች ከተፈቱ ያቀድነው ለእያንዳንዱ አርሶ አደር እንኳ ማድረስ ባንችል በጋራ የተደራጁ ወጣቶችን በማዋቀር ልክ እንደ እንሰት ወፍጮ ቤት ዓይነት ነገር በወረዳው ላይ ለማቋቋም ነው። ይህን አስፍቶ ከመሥራት አንጻር አሁንም ድጋፍ እየፈለግን ነው። ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሰናል። የተወሰነ ድጋፍ ካገኘን የምናሰፋበት ሁኔታ ይፈጠራል።

ሌላው ከምርምር ጋር ወደ አራት ፕሮጀክቶች አሉ። አንዱ ሜጋ ፕሮጀክት ነው። ባዮ ስለሪ (ከባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ የሚገኝ የተፈጥሮ ማዳበሪያ) ወይም ከከብቶች የሚገኝ ፈሳሽ ሲሆን፣ እሱ በእንሰት ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ ምንድን ነው? የሚል ግምገማ እየተሠራ ነው። ከዚህ አንጻር የተፈጥሮ ማዳበሪያን ከመተካት አኳያ ትልቅ ፋይዳ ያለውን ተግባር እያከናወንን እንገኛለን።

ከሙዝ ጁስ ጋር በተያያዘ እንሰት ምን ያህል ጠቀሜታ አለው የሚለውን በማየቱ በኩል የምግብ ሳይንስ ኢንጂነሪንግ በኩል አንድ ፕሮጀክት እየተሠራ ነው። ሌላው የእንሰት ተረፈ ምርት ከአሸዋ እና ከጠጠር ጋር ተደበላልቆ ለአስፓልት ጥሩ ጥንካሬ ይሰጣል የሚል ጉዳይ ስላለ በሲቪል ኢንጂነሪንግ በኩል ምርምር እየተደረገበት ነው። ስለዚህ እንሰት የማይገባበት ቦታ የለም ማለት የሚያስችል ነው።

ከዚህ በተጨማሪ እንሰት የአየር ንብረት ተጽዕኖ እና የምግብ ዋስትና ላይ ያለው ሁኔታ ምንድን ነው? ለሚለው በአግሪካልቸር ኢኮኖሚክስ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች አሉ። ከእነዚህ አራት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ በጣም ትልቅ ሜጋ ፕሮጀክት ነው። እሱም እስቀድሜ ባዮ ስለሪ ያልኩት ሲሆን፣ ይህ ትልቅ ፕሮጀክት በሶስት ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቅ ነው። ሌሎቹ ግን ትንንሽ ቢሆኑም እንሰት ላይ አተኩረን ከምንሰራባቸው ምርምሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- የምርምር ስራችሁን ምን ያህል እያሰፋችሁት ነው? ለምርምር ስራችሁ ምን ያህልስ በጀት አላችሁ?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡– ትኩረት የምናደርገው እንሰት ላይ ነው። አንደኛ ዩኒቨርሲቲያችንም የሚገኝበት ማኅብረሰብ በእንሰት አብቃይነቱም ተጠቃሚነቱም የሚታወቅ ነው። ስለዚህ እኛ የተለየ ኃላፊነት አለብን ብለን እናምናለን። ለምሳሌ የፈርዝዬ ማዕከላችን ላይ እንዳይጠፉ የታደግናቸው (ዝሪያቸውን ያሻሻልንበት) በፊት የነበሩ ወደ 57 ዝርያዎች ነበሩ። አሁን በአዲሱ በተሻሻለው ወደ 71 አሳድገነዋል። የመጀመሪያውን ዝርያ የምናሻሽልበት ጣቢያ ወደ ስምንት ዓመት ስለሆነው የሚተካ ነው። ከዚህ አንጻር የመተካት ሥራዎችንም ሰርተናል።

“ኮል ፎር እንሰት” በሚል ለብቻ ያወጣነው የምርምር ጥሪ ነበር። “ኮል ፎር እንሰት” ስንል የእኛ ተቋም ተመራማሪዎች ከሌላ ተቋም ተመራማሪዎች ጋር ተቀናጅተው ምርምር የሚሰሩበትን እድል ነው የፈጠረ ነው። ስለዚህ እዚህ ብቻ የሚታጠር ሳይሆን እንደ ሀገር አቅም አለን፤ እንሰት ዙሪያ እንሠራለን የሚሉ አቅም ያላቸውን አካላት ጋብዘናል። ነገር ግን ያለቀው ገና ፕሮፖዛሉ ነው። የርዳታ ስምምነት ተፈራርመናል። ከዚህ አንጻር እኛ እድሉን ፈጥረናል። እየሰራን ያለነው በእንሰት ዙሪያ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በርከት ያሉ የእንሰት ዝርያዎችን በማሻሻል ላይ ናችሁ፤ ይህ ዝርያ ወደአርሶ አደሩ ይደርሳል? አገልግሎቱስ ለምግብነት ብቻ ነው?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡- የእንሰት እያንዳንዱ ዝርያ የራሱ የሆነ ልዩ ባህሪ አለው። አንዳንዱ ለምግብነት የሚውል ሲሆን፣ አንዳንዱ ደግሞ ለመድኃኒትነት የሚውል ነው። ቀደም ባለው ጊዜ በተለይ ስብራት ያጋጠመው ሰው ሊጠግነው የሚችል አንደኛው የእንሰት ዓይነት መኖሩ ይታወቃል። ይሁንና ሁሉም የእንሰት ዓይነት ይህን ዓይነት መድኃኒትነት ይሰጣል ማለት ግን አይደለም። በተለምዶ እኛ እንሰት እንላለን እንጂ የሚያውቁ ሰዎች የጠጋኝነት ሚና የሚጫወተውን የእንሰት ዓይነት ስብራት ላጋጠመው ሰው ይሰጡታል።

እንሰት ምግብ ብቻ አይደለም፤ መተኛም ጭምር እንጂ። ለምሳሌ “ጅባ” በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ከእንሰት ምርት የሚዘጋጀው ለመኝታ አገልግሎት የሚውል ነው። ከእንሰት ተረፈ ምርት መተኛ የሚሆን አልጋ ነገር ይሰራል። አሁን አሁን የእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀት እየሆነ እንደሆነ እየተነገረ ነው። በአሁኑ ወቅት በጣም ጠንካራ እና ጥሩ የሚባል የወረቀት ዓይነት ወጥቶታል።

ስለዚህ እንሰት አንደኛ የአየር ጸባይን ተከትሎ የሚመጣን ድርቅ የመቋቋም ብቃት ያለው ተክል ነው። ለምሳሌ ቀደም ባሉ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰቱ ድርቆች እንሰት አብቃይ የሆኑ አካባቢዎች ብዙ እንዳልተጎዱ ይታወቃል። ስለዚህ ይህ ድርቅ የሚቋቋም ተክል በኢትዮጵያ ለተክሉ ተስማሚ የአየር ጸባይ ባለበት ሁሉ ቢስፋፋ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው ብዬ አስባለሁ። ከዚህ ከምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።

በርግጥ እንሰት አብቃይ ከሆኑ አካባቢዎች ውጭ እንሰት አይበቅልም ማለት አይደለም። ተክሉ ያለው አገልግሎትና ልምዱ ስለሌለ ነው እንጂ እንሰት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ተክል ነው፤ ከዚህ አንጻር በዘርፉ እየተሠራ በመሆኑ ወዳልተለመዱ አካባቢዎችም ተክሉ የተለያዩ ምርምሮች እየተካሔደባቸው እንዲስፋፉ እየተደረጉ ናቸው። ይህ መሆኑ ደግሞ እንሰት ጠቀሜታው ከፍ እንዲል የሚያደርጉ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባን ጨምሮ በዋና ዋና ከተሞች እንሰት በጣም ውድ እየሆነ ነው። ምክንያቱም እንሰት ከገጠር ምግብነት ወደ ከተማ ምግብነት እየመጣ በመሆኑ ነው። ለምሳሌ ቆጮ አንዱ ነው። ስለዚህ እኔ የማስበው ትልቅ ትኩረት የሚሻ ተክል ነው ብዬ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ወደአፕላይድ ሳይንስ (ተግባር ተኮር ሳይንስ) የሚደረገው ጉዞ ምን ይመስላል?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡– እኛ የአፕላይድ ሳይንስ እጩዎች ነን። እንዲህም ስል ባለን አቅጣጫ አፕላይድ ሳይንስ ውስጥ ገብተናል። አፕላይድ ሳይንስ ውስጥ ከገቡ የሶስተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ነን። እሱ ሲታይ ደግሞ እዛ ውስጥ እንድንመደብ ያደረገን አንዱ ቤተ-ሙከራችን (ላቦራቶሪያችን) ነው። ሌላው የማስበው የሠራተኛው መገለጫ (የስታፍ ፕሮፋይላችንም) ጥሩ ነው ብዬ ነው። መልክዓ ምድራዊ (የጂኦግራፊካል) ሁኔታችንም የሰጠን ነገር ይኖራል የሚል እምነት አለኝ።

በዩኒቨርሲቲያችን ያለው ስታፍ ብዙ ነው። በሶስተኛ ዲግሪ ደረጃ በርካታ መምህራን አሉን። በላቦራቶሪዎቻችን ደግሞ ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች መጥተው የሚጠቀሙባቸው ናቸው። ሌላው ቀርቶ ከእኛ ቀደምት ናቸው ከሚባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጭምር ወደእኛ መጥተው በላቦራቶሪው የሚጠቀሙ አሉ። ከዚህ የተነሳ በአሁኑ ወቅት በተሟላ መልኩ ወደ ሙሉ አፕላይድ ሳይንስ ለመግባት በርካታ ሥራዎችን እየሠራን ነው። ከእነዚህ መካከል አንደኛው ነገር ስትራቴጂ እየነደፍን መሆናችን ነው። ሁለተኛው ደግሞ የትግበራ ስልት በኮሚቴ እየሠራን ነው። ከዚያ በኋላ ሥርዓተ ትምህርታችንን መከለስ ጀምረናል። ምርምሮቻችንን፣ የማኅበረሰብ አገልግሎቶቻችን አፕላይድ አፕላይድ የሚሸቱ ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነው። ስለዚህ እነርሱን እንደ እዛ ለማድረግ በመጀመሪያ የሰነድ ዝግጅት እየጨረስን ነው። ስለዚህ በ2017 ዓ.ም ላይ በተሟላ ደረጃ እዛ ውስጥ እንገባለን ብለን ተስፋ እንደርጋለን። እስካሁንም ያንን ለማሟላት ሥራዎች እየተሰሩ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ወደ አፕላይድ ሳይንስ ሙሉ ለሙሉ ለመግባት ከዩኒቨርሲቲያችሁ የሚጠበቀው ምንድን ነው?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡– ከእኛ የሚጠበቀው የቴክኖሎጂ ሽግግር ሲሆን፣ እሱ በጣም ወሳኝ ነው። እኔ የምገለጸው ከማኅብረሰብ አገልግሎት አንጻር ነው። ያለሁበትም ቢሮ እሱ ስለሆነ ነው። ከማኅብረሰብ አገልግሎት አንጻር የሚካሔዱት አፕላይድ የሚመስሉ ምርምሮች ናቸው። እንደዛ ሲባል እውቀትን መሠረት ያደረጉ ምርምሮች አያስፈልጉም ማለት አይደለም። ነገር ግን ይበልጥ ትኩረታችን የሚሆነው ወደፈጠራውና ወደተግባሩ ነው።

በመማር ማስተማሩ ዘርፍ ደግሞ የምናበቃቸው ተማሪዎቻችን የተግባር ተማሪዎች ናቸው። ምርምር መሥራት የሚችሉ፤ ግን ምርምራቸው በተግባር የሚገለጥ ነው መሆን ያለበት። የመጨረሻው ውጤቱ እሱ ነው። ከአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች የሚጠበቀው ይኸው ነው እንጂ በተለመደው መልኩ ቲዎሪውን ብቻ አጣጥሞ እጁ የማይሰራ ተማሪ ሆኖ እንዲወጣ አይደለም።

ስለዚህ በተግባር ስልጡን የሆኑ ተማሪዎች ለማድረግ አንደኛ ወርክሾፖቻችን በጣም ማጠናከር አለብን። እሱ ላይ ደግሞ እየሠራን እንገኛለን። ምርምር ጣቢያዎቻችንን በጣም እያጠናከርን ነው። ከዚህ የተነሳ ጥሩ ደረጃ ላይ እንደርሳለን ብዬ እኔም ተስፋ አደርጋለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ቀደም ብለው በቡና እና በፍራፍሬ ላይም ምርምር እያካሔዳችሁ እንደሆነ ጠቆም አድርገዋል፤ ስለዚህ ጉዳይ ቢያብራሩልን ?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡– ከቡና አንጻር ጅማ የቡና ምርምር ኢንስቲትዩት አለ፤ ከእነርሱ ጋር በጋራ ቢሆንም ወደ ስምንት ዓመታት ያስቆጠረና እየሰራንበት ያለ የምርምር ማዕከል አለ። ይህ የምርምር ሥራ የቡና ዝርያን ለማውጣት ነው። እሱ ሁለት ዓመት ነው የቀረው። በምርምር ቋንቋ የመጨረሻ መላመድ ሙከራ (አዳብቴሽን ቴስት) የሚባል አለ። እሱ ከተሠራ በኋላ ሊወጣ የሚችለው ዓይነት “የጉራጌ ቡና” የሚባለውን የተሻሻለ የቡና ዓይነት ሊሆን ይችላል። እኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምናውቃቸው ዓይነት ስሞችን ለማውጣት ነው እቅዳችን።

ከፍራፍሬ አንጻር እየሠራን ያለነው አቮካዶ እና አፕል ላይ ነው። አንዱ ቡና ያለበት ቦታ ላይ አቮካዶን እየወሰድን ነው። ዋናው ማዘር ፕላንት የሚባል አለ። ብዙ ዓይነት ችግኞችን እያባዛን ለማኅበረሰቡ እንሰጣለን። ስለዚህ እያንዳንዱ ቡና ማብቀል የሚችል አርሶ አደር በጓሮው የአቮካዶና የአፕል ዝሪያዎችን እንዲያገኙ ጥረት እያደረግን ነው። ስለዚህ በዚህ ዓይነት ሁኔታ በየዓመቱ እናደርሳለን። ነገር ግን ያኛውን አሳፋፍተን መሄድ እንዳለብን እንገነዘባለን።

የቡናውን የጀመርነው ገና ባለፈው ዓመት ነው። ባለፈው ዓመት ወደ 27 ሺ የቡና ችግኞች ለአርሶ አደሮቻችን ሰጥተናል። ዘንድሮ ደግሞ አራት እጥፍ እናሳድጋለን ብለን አስበናል። ስለዚህ በዚህ ዓመት ወደ አንድ መቶ አስራ ምናምን ሺ የቡና ችግኞች እናደርሳለን ብለን አስበናል። እንዲህ ሲባል ሌሎች የጥላ ዛፎችና የሚበሉ ዛፎች እንደተጠበቁ ሆነው ማለት ነው። ለዚህ ዋቢ የሚባል ለብቻ የራሱ የሆነ ጣቢያ አለን። በዚህ ጣቢያ ብቻ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ችግኞች እናባዛለን።

አዲስ ዘመን፡- ያጋጠሟችሁ ችግሮች ካሉ ቢጠቅሷቸው? ይበልጥ ደግሞ ልትሰሩ ያቀዳችሁት ምንድን ነው?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡– ሁሉም ተቋም ላይ ይበዛል ብዬ የማስበው የግዥ ሥርዓቱን ነው። እኛ ዘንድ ለተመራማሪዎች አስፈላጊ የሆኑ የምንገዛቸው ኬሚካሎች እና ግብዓት የምንጠይቀው በተፈለገው ቁጥር ያህል አይደለም። ለጨረታ የሚሆን አይደለም። አንድ ተመራማሪ ትንሽ ያህል ሚሊ ነገር ነው የሚፈልገውና እሷን ለማግኘት አቅራቢ ማግኘት በጣም ከባድ ነው። የእኛ የግዥ ሥርዓታችን ችግር ባይሆንም ወደምርምሩ ሲመጣ ውስብስብ ይሆንብናል። በብዛት (ማስ) የሚገዛ አይደለም።

ለምሳሌ አንድ ተመራማሪ የሚፈልጋት ነገር በጣም ትንሽ ነች። እሱን ጨረታ ለማውጣት ከባድ ነው። ከዚህ የተነሳ አቅራቢዎችን ማግኘት በጣም ከባድ ነው። ስለዚህ ትንሽ የግዥ ሥርዓቱ ማነቆ ይሆንብናል።

ከዚህ ውጭ የበጀት እጥረቱ ውጭ ባሉ ደጋፊዎች ለማካካስ ነው ጥረት የምናደርገው እንጂ ከመንግሥት ብቻ የምንጠብቀው አይደለም። ምርምር ሲሰራ የግድ ከመንግሥት ትሬዠሪ ሳይሆን ከሌሎች ድጋፍ ከሚያደርጉ ድርጅቶችም ፕሮፖዛል በመጻፍና አጋርነት በመፍጠር ጥረት እናደርጋለን። ስለዚህም እየሰራን ያለነው በእዛ መልኩ ነው። እኔ እንደ ችግር ላነሳ የምችለው የግዥ ሥርዓቱን ነው። እንዳልኩት የግዥ ሥርዓቱ ለምርምር የሚመች አይደለም።

አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው ከሀገር ውስጥ ቀደምት ከሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች እና ከውጭ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡– ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በተለይ ሀገር ውስጥ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ለምሳሌ ከእነ ጅማ ጋር የጅማ ክላስተር ነው፤ ከእነ አርባ ምንጭ ጋር በተለይ ከእንሰት ጋር ተያይዞ አብረን ለመሥራት የጋራ ስምምነት አድርገናል።

አዲስ አበባ እናት ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ ሁሉንም የሚያግዝ ነው። ከሌሎች ማለትም ከደብረ ማርቆስ ጋርም ከእንሰት ጋር ተያይዞ ምንም እንኳ ገና ወደ ተግባር ባይቀይሩትም ወደእነርሱ አካባቢ ለማስፋፋት ትብብር አለን። ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከድርጅቶች፣ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከባዮ ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና ከሌሎችም ጋር የምንሠራው አብረን ነው።

ከውጭ ደግሞ ከቻይና ዩኒቨርሲቲ ጋር ጆይንት የፒ ኤች ዲ ፕሮግራም በፊዚክስ አለን። ሕንድ ላይም አለን። እንዲሁ አውሮፓ እና አሜሪካም በቅርቡ የዩኒቨርሲቲያችን ፕሬዚዳንት ተፈራርመው መጥተዋል። በእስካሁኑ ሒደት ያለን ጥሩ የሚባል ግንኙነት ነው።

አዲስ ዩኒቨርሲቲ እንደመሆናችን መስፋፋት ያስፈልጋል። ስለዚህ ከፍ ያለው ቦታ ላይ እንገኛለን ማለት አይቻልም። አንዱ መሻሻል አለበት ብለን የምናስበው ኢንተርናሽናል ትብብርን ነው። ጥሩ ቢሆንም ብዙ መሻሻል ያለበት ነገር ግን አለ።

አዲስ ዘመን።- ለሰጠን ሰፋ ያለ ማብራሪያ እናመሰግናለን።

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2016 ዓ.ም

Recommended For You