ከቃላት ትርጓሜ በስተጀርባ የሚፈጠሩ ጥፋቶች

በዓለም ታሪክ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የሚለው የፖለቲካ ጽንሰ ሃሳብ የተጀመረው ከኢንዱስትሪ አብዮት መጀመር ጋር ተያይዞ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። ከዚያ በፊት ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የሚባል ቋንቋ በየትኛውም ዓለም ማንም አያውቀውም፤ አይጠቀመውም ነበር።

ኢትዮጵያም ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የሚለውን የፖለቲካ ጽንሰ ሃሳብ ሙሉ በሙሉ የተዋሰችው በኢንዱስትሪ አብዮት ታሸተው ካለፉ ሀገራት ፖለቲከኞች በተለይም ከሶሻሊስቶቹ ከነማርክስ ፣ሔንግልስ ፣ጆሴፍ ስታሊን እና ሌኒን የፖለቲካ ፍልስፍና ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን ቃላቶች የምንተረጉምበት እና የምንጠቀምበት አግባብ ግን ጽንሰ ሃሳቡ ያዋሱ ሶሻሊስቶች እና ኢፔሪያሊስቶች ከሚሰጡት ትርጓሜ የተለየ እና ፈጽሞ ዝምድና የሌለው ነው።

ለመሆኑ ሶሻሊስቶች እና ኢፔሪያሊስቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት እና ምርምር ማዕከል ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የሚሉት ቃላት እንዴት ይተረጎማሉ? በተለይ ብሔር ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኞቻችን ሳይገባቸው እና ሳይቸግራቸው የተዋሷቸውን ቃላቶች እንዴት እየተጠቀመባቸው ነው? ምን የሚልስ ትርጓሜ ሰጧቸው? የሚለውን በወፍ በረር ላስመልክታችሁ። ከዚህ በመነሳትም “በኢትዮጵያ የትኛው ጎሳ ነው ብሔር መሆን ይቻላል?” የሚለውን መልስ ማግኘት ትችላላችሁ።

በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት እና ምርምር ማዕከል አተያይ ብሔር ማለት ምንድን ነው ? የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት እና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም በሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት የመጀመሪያ እትም እንደ አመላከተው ብሔር ማለት “ሀገር ማለት ነው” ሲል ትርጓሜ ሰጥቶታል። ይህ መዝገበ ቃላት በሁለተኛ ደረጃ በሰጠው ትርጉም “ብሔር ማለት አንድ አይነት ቋንቋ ያለው ፤ አንድ አይነት ባህል እና ስነ ልቦናዊ አመለካካት ያለው፣ በታሪክ፣ በኢኮኖሚ የተሳሰረ እና በተወሰነ ክልል ውስጥ የሚኖር ህዝብ ነው” ሲል ያስረዳል።

በሶሻሊስቶች እና በኢፔሪያሊስቶች አተያይ ብሔር ማለት ምንድን ነው ?

በሶሻሊስቶች እና በኢፔሪያሊስቶች አንድ ማህበረ ሰብእ ብሄር ለመባል የግድ ስድስት ነገሮችን ማሟላት እንዳለበት ይጠቁማሉ። ከእነዚህ መካካል አንደኛው ለረጅም ዘመናት በታሪክ የተቀናጁ ማህበረ ሰብእ መሆን አለባቸው የሚል ነው። ከዚህ አንጻር “ብሔር ማለት በዘር ወይም በጎሳ ላይ የተመሰረተ ማህበር ማለት አይደለም” ሲሉ ያስረዳሉ።

ለምሳሌ የጣሊያን ብሔር የተመሰረተው ከሮማዊን፣ ከቲውቶን ፣ከኢትሩስካን ፣ከግሪክ ፣ከአረብ እና ከመሳሰሉት ጎሳዎች ነው ። ግን ጣሊያን አንድ ብሄር ናት። እነዚህ ጎሳዎች ተጠራቅመው የጣሊያን ብሔር የተባሉት የተለያዩ ጎሳዎች በፈጠሩት ስብጥር ሳይሆን ጎሳዎቹ ለበርካታ ዘመናት በታሪክ የተቆራኙ ማህበረ ሰብእ ስለሆኑ ነው። በተመሳሳይ አንድ ጎሳ ብቻ ያለው ማኅበረሰብ ለበርካታ ዘመናት በታሪክ ያልተቀናጀ ከሆነ ብሔር ሊባል አይችልም።

ሌላኛውና ሁለተኛው አንድን ማህበረ ሰብእ ብሔር ሊያስብል የሚችለው ለበርካታ ዘመናት በታሪክ ስለተቀናጀ ብቻ አይደለም። ይልቁንም በታሪክ የተቀናጁት ማህበረሰቦች “የጸና ማህበረ ሰብ” መሆን ሲችሉ ነው።

ሦስተኛው የኢፔሪያሊስቶች መስፈርት ደግሞ ቋንቋ ነው። አንድ ማህበረሰብ ለዘመናት በታሪክ የተሳሰረ እና የጸና ማህበረሰብም ቢሆን አንድ አይነት ቋንቋ መናገር ካልቻሉ ብሔር ሊባል እንደማይችል ያስረዳሉ።

ይሁን እንጂ ይህ ማለት የተለያዩ ብሔሮች ሁልጊዜ እና የትም የተለያዩ ቋንቋዎች ይናገራሉ። አሊያም አንድ አይነት ቋንቋ የሚናገሩ ሕዝቦች ሁሉ አንድ ብሔር ናቸው ማለት አይደለም። በአንድ ጊዜ በተመሳሳይ ሰዓት በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ማህበረሰቦች ተመሳሳይ ቋንቋዎችን ቢጠቀሙም አንድ ብሔር ናቸው ማለት አይደለም።

ለምሳሌ እንግሊዞች እና አሜሪካኖች ሁለቱም የሚናገሩት እንግሊዝኛ ነው። ነገር ግን የተለያዩ ሀገራት ናቸው። በተመሳሳይ ኖርዌጅያኖችና ዴኒሾች ተመሳሳይ ቋንቋ ይናገራሉ። እንዲሁም እንግሊዞች እና አይሪሾች አንድ አይነት ቋንቋ ያወራሉ። ነገር ግን አንድ ብሔር አይደሉም።

ስለዚህ አንድ ማህበረሰብ ብሔር ለመባል አንድ አይነት ቋንቋ ከማናገር ፣ አንድ አይነት ታሪክ ከመኖር እና የጸና ማህበረሰብ ከመሆን ባለፈ በአንድ በተወሰነ የሀገር ወሰን ውስጥ መኖር የግድ ይለዋል። እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን አንድን ማህበሰብ ብሔር ከሚያስብሉት የኢፔሪሊስቶች እና የሶሻሊስቶች መስፈርቶች መካከል “በአንድ በተወሰነ የሀገር ክልል ውስጥ መኖር” የሚለው አንዱ መሆኑ ነው።

ነገር ግን አንድ ማህበረሰብ አንድ አይነት ቋንቋ ፣ ታሪክ ፣ የፀና ማህበረሰብ እና በአንድ ሀገር ስለኖረ ብቻ ብሔር መባል አይችልም። ስለሆነም ብሄር ለመባል በኢኮኖሚ ሥርዓት መተሳሰር የግድ ይለዋል።

በአንድ ማህበረሰብ ብሔር ለመባል የመጨረሻው መስፈርት ደግሞ ማህበረሰቡ አንድ አይነት ስነልቦናዊ ዘይቤ ሲኖረው ነው። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ቃላቶችን የተዋስናቸው ማርክሲስቶች እና ኢምፔሪያሊስቶች አጥብቀው የሚያስጠነቅቁት ከስድስቱ መስፈርቶች አንደኛው ከጎደለ አንድ ማህበረሰብ በፍጹም ብሔር ሊባል እንደማይችል ነው።

ከዚህ በመነሳት በትክክል በኢትዮጵያ ብሔር ሊባል የሚችል ጎሳ ማግኘት ይቻላል ወይ? ከተባለ መልሱ በፍጹም ይሆናል። በአንጻሩ ማርክሲስቶች እና ኢምፔሪያሊስቶች ባስቀመጧቸው መስፈርቶች ከተመዘነ በሀገራችን ኢትዮጵያ ከሚባል ብሔር ውጭ ሌላ ብሔር እንደሌለ በጉልህ መገንዘብ ያስችለናል።

ይህን ስል ከጎሳ ፖለቲካ ውጭ ማየት የማይችሉ ዋልታ ረገጦች ጨፍላቂ ሊሉኝ እንደሚችሉ ቅንጣት ያህል ጥርጣሬ የለኝም። ምክንቱም ለእኛ ሀገር ፖለቲከኞች ብሔር ማለት ቋንቋ እና ጎሳ ብቻ ስለሚመስላቸው የሆነው ሆኖ ግን እኛ ኢትዮጵያዊያን ከማርክሲስቶች እና ከኢፔሪያሊስቶች የተዋስናቸውን ቃላት በቅጡ ሳንረዳ እና ሳንገነዘብ ብሔር ለሚለው ሰፊ ጽንሰ ሃሳብ “ቋንቋ እና ጎሳ” የሚል የራሳችንን የተዛባ ትርጓሜ ሰጥተን ከእኛ ውጭ ፖለቲካ ለአሳር በሚል ተኮፍሰን ራሳችንን እያሞኘን እንገኛለን።

ብሔር እና መሰል ሰፊ የፖለቲካ ጽንሰ ሃሳቦች በቅጡ ያልተረዱ ራሳቸውን በፖለቲከኞች ባቡር ያሳፈሩ ዲስኩራሞች ለበርካታ ዓመታት ተዋልዶ እና የተጋምዶ የኖረን የኢትዮጵያን ማህበረሰብ ለመለያየት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ስመለከት የ1950ዎቹ እና 60ዎቹ ፖለቲከኞች የኢትዮጵያ የታሪክ ስብራቶች አድርጌ እንዳይ አስገድዶኛል።

በመጨረሻም ሳይቸግረን ከውጭ ሀገራት የምንቃርማቸውን የፖለቲካ ጽንሰ ሃሳቦች በቅጡ እንረዳ፤ የሀገራችንን አንድነት በማጠናከር ታሪካዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ! መልዕክቴ ነው።

ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2016 ዓ.ም

Recommended For You