በጋና አዘጋጅነት በመካሄድ ላይ የሚገኘው 13ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ከቀናት በኋላ ይጠናቀቃል፡፡ በ12ቱ የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች በርካታ ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ የሚታወቁት ግብጽ፣ ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ በዚህ ውድድር ላይም በሜዳሊያዎቻቸው ብዛት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በውድድሩ በመሳተፍ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ደግሞ ዘግየት ብላ የሜዳሊያ ሰንጠረዡን ተጨማሪ ድሎች በማስመዝገብ መቀላቀል ችላለች፡፡
በየትኛውም ውድድር የኢትዮጵያ ስም በኩራት እንዲነሳ ስፖርቱም መለያዋ እንዲሆን ባስቻለው የአትሌቲክስ ስፖርት በተጨማሪ ሜዳሊያዎች በሰንጠረዡ ስሟ እንዲካተት ሆኗል፡፡
የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያም ትናንት ምሽት በ3ሺ ሜትር መሰናክል አትሌት ሳሙኤል ፍሬው አጥልቋል፡፡ በአስደናቂ አሯሯጥ አሳማኝ የበላይነቱን የያዘው አትሌቱ ኬንያዊያን አትሌቶችን በማስከተል 8:24.30 በሆነ ሰዓት ርቀቱን ሊያሸፍን ችሏል፡፡ አብረውት ለተጨማሪ ሜዳሊያ የተፎካከሩት የሀገሩ ልጆች አብርሃም ስሜ እና ሚልኬሳ ፍቃዱ ደግሞ 4ኛ እና 5ኛ ደረጃን መያዝ ችለዋል፡፡
ሌላኛው ኢትዮጵያ ለሜዳሊያ ትጠበቅበት የነበረው ርቀት ደግሞ የ5ሺ ሜትር የሴቶች ውድድር ሲሆን፤ በአስገራሚ አጨራረስ ሁሉንም ሜዳሊያዎች ሊጠቀልሉ ችለዋል፡፡ አረንጓዴውን ጎርፍ በመድገም ተከታትለው በመግባት ቀዳሚ የሆነችው ወጣቷ አትሌት መዲና ኢሳ ስትሆን የገባችበት ሰዓትም 15:04.32 ሆኖ ተመዝግቦላታል፡፡ በዚህ ርቀት እንዲሁም በ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ስኬታማ የሆነችው የ19 ዓመቷ አትሌት እጅግ ተስፋ ከተጣለባቸው አትሌቶች መካከል አንዷ ናት፡፡ መዲናን ተከትላ በመግባት የብር ሜዳሊያውን ያጠለቀችው አትሌት ብርቱካን ሞላ ደግሞ 15:05.32 በሆነ ሰዓት ገብታለች፡፡ 15:07.04 በሆነ ሰዓት በመግባት የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው አትሌት ደግሞ መልክናት ውዱ ናት፡፡ እስከ ትናንት ከሰዓት ድረስም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 2 የወርቅ፣ 2 የብር እና 1 የነሐስ በጥቅሉ 5 ሜዳሊያዎች በማግኘት 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ውጤታማ ከሆነበት የረጅም ርቀት አትሌቲክስ ባለፈ በማይታወቅባቸው የአጭር ርቀቶች ከ100 ሜትር አንስቶ በመሳተፍ ላይ ቢሆንም፤ ማጣሪያውን ማለፍ አልተቻለም፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ በምትታወቅባቸውና ውጤታማ በሆነችባቸው ርቀቶች ግን እንደተለመደው ሜዳሊያዎች ሊመዘገቡ ችለዋል፡፡
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ከ52 ሀገራት የተውጣጡና በሺዎች የሚቆጠሩ ስፖርተኞችን በ30 ዓይነት ስፖርታዊ ውድድሮች ማሳተፍ ከጀመረች ሁለተኛ ሳምንቷን ያስቆጠረች ሲሆን፤ ከጥቂት ቀናት በኋላም ውድድሩ የሚጠቃለል ይሆናል፡፡
ምንጊዜም ለዚህ ውድድር ጠንካራ ቡድን ይዛ በመቅረብ የምትታወቀው ግብጽ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ የበላይነቷን ዘንድሮ በጋናም እየደገመችው ትገኛለች፡፡ ሰሜን አፍሪካዊቷን ሀገር ጨምሮ በበርካታ የስፖርት ዓይነት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ልኡክ በማሳተፍ የሚታወቁት ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካም በተመሳሳይ ለውድድሩ ከተዘጋጁት ሜዳሊያዎች አብዛኛውን መውሰድ ችለዋል፡፡
በዚህ ውድድር ከመጀመሪያው አንስቶ በመካፈል የምትታወቀው ኢትዮጵያ በአንጻሩ ተሳትፎዋ በጥቂት ስፖርቶች ብቻ የተገደበ በመሆኑ ምክንያት ባስመዘገበቻቸው ሜዳሊያዎች ብዛት ከቀዳሚዎቹ መካከል መካተት አልቻለችም፡፡ ነገር ግን ዘንድሮ ባልተለመደ ሁኔታ ለስፖርተኞች የዓለም አቀፍ ውድድሮች የተሳትፎ ዕድልና ልምድ እንዲያገኙ እንዲሁም ሜዳሊያዎችን በማግኘት ባንዲራዋ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በማቀድ በ9 የስፖርት ዓይነቶች ልኡካን ወደ ስፍራው መላኳ የሚታወቅ ነው፡፡
በአጠቃላይ 149 አትሌቶችን ያቀፈው ቡድኑ በአትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ቦክስ፣ ብስክሌት፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ሜዳ ቴኒስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ውሃ ዋና እና ቅርጫት ኳስ ስፖርቶች በመወዳደር ላይ ይገኛል፡፡
ሆኖም ለሁለት ሳምንታት ያህል በአንድ ሜዳሊያ ብቻ የተወሰነ ተሳትፎ ነበራት፡፡ እንደ ውሃ ዋና እና ብስክሌት ባሉ ስፖርቶች የነበረው ፉክክር የውጤታማነት ተስፋ ያሳደረ ቢሆንም፤ ብቸኛው ሜዳሊያ በብስክሌት ስፖርት የወንዶች ከ23 ዓመት በታች በኪያ ሮጎራ ተመዝግቦ የቆየ ነው፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 11 ቀን 2016 ዓ.ም