የሰላም ደጆች ይከፈቱ፣ የጥላቻ መንገዶች ይዘጉ

የሰው ልጅ እዚህ ምድር ላይ በሕይወት ሲኖር እጅግ የሚያስፈልገው ምንድነው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ለ75 ዓመታት የተደረገ አንድ ጥናት ነበር፡፡ በዚህም ጥናት መሠረት ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊው ነገር ፍቅርና ሰላም ሆኖ ከፊት ተቀምጧል፡፡ ለሶስት ትውልድ የቀረበው ይሄ ጥናት የሰው ልጅን ከተፈጥሮ ጋር በማቆራኘት፣ ህልሙንና ምኞቱን፣ ሃሳቡንና ስሜቱን አዋህዶ ባደረገው መሰንበት ፍቅርና ሰላምን የሕይወት ምንጩ ሲል ሰይሟቸዋል፡፡

በጣም የሚገርመው ደግሞ የሰው ልጅ ከዚህ እውነታ ሸሽቶ በተቃራኒ መቆሙ ነው፡፡ አሁን ላይ በዛም በዚህም የምንሰማቸው የሰብዓዊነት ጥያቄዎች፣ እንግልቶችና ስቃዮች ስናይ የሰውን ሰውነት ልንጠይቅ እንገደዳለን?፡፡ ሰላም ከሰማይ የሚወርድ ወይም ደግሞ ስለፈለግን ብቻ ወደእኛ የሚመጣ አይደለም፡፡ ሁሉም ነገር በሕግና ሥርዓት ውስጥ የሚኖር ነው፡፡ ሰላም ለመፍጠርና የሰላም ባለቤቶች ለመሆን ራሱን የቻለ የመነሻ ሥርዓት አለው፡፡ ሰላም በመነጋገር የሚመጣ፣ በአንድነትና በመተሳሰብ የሚፈጠር ነው፡፡

በጦርነት እና በመገፋፋት ሰላምን ለማምጣት የሚሞክሩ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ ፖለቲከኞች ቀድሞውኑ ሰላም ማለት ምን ማለት እንደሆነ ያልገባቸው ናቸው፡፡ በተጨማሪም ሀገርና ሕዝብን እንዴት ባለው በሳል አመራርነት ማዋሃድ የማይችሉ ናቸው፡፡ ጠንካራ ሰዎች ጦርነትን በሰላም ይሽራሉ እንጂ ሰላምን በጦርነት ለማምጣት ሞቶ በመግደል መርህ ነፃ ለመውጣት አይሞክሩም። ጦርነት ነፃ አያወጣም፡፡ ጥላቻ ማንንም ከፊት አቁሞ አያውቅም፡፡ የሀገራችን የታሪክ አንጓ የሰላም ምንጮችን በማድረቅ ኃይል መር በሆነ የፖለቲካ ሽኩቻ ወደዛሬ የመጣ ነው፡፡

በብዙ ተሞክሮ በስለንና ሰልጥነን ጦርነትን መሻር በሚገባን ዘመን ላይ እንኳን ውጊያ ላይ ነን። የምንገድለው እኛ የምንሞተው እኛ፡፡ እኛው በእኛ ማንን ነፃ እንደምናወጣ አልተመለሰልኝም፡፡ ጦርነት በየትኛውም አውድ ላይ ትርጉም ባይኖረውም የወንድማማቾች ግፊያ ግን በጦርነት ውስጥ ትርጉም የሌለው እውነታ ነው፡፡ ጦርነት ትርጉም ካለው ከጠላት ጋር ነው፡፡ ከአንድ ባህር የተቀዳ፣ ከአንድ ምንጭ የጠጣ፣ በአንድ ገበቴና ፎሌ የተቋደሰ፣ ወልዶና ከብዶ የተቀየጠ ሕዝብ እርስ በርሱ ቢጋደል ትርፉ ምንድን ነው ፡፡

ተወያይቶ መግባባት፣ ተነጋግሮ የችግሮቻችንን ምንጮች ማድረቅና ለአዲስ አስተሳሰብ መሰናዳት አሁን ላለው ትውልድ ራሱን ነፃ የሚያወጣበት የመጨረሻ አማራጩ ነው፡፡ ፍላጎቶቻችን ምንም ይሁኑ መነጋገር ከተቻለ ጦርነትን ሽረን ሰላምን በመተቃቀፍና በመጨባበጥ እውን ልናደርጋቸው እንችላለን፡፡ በመግደል ውስጥ ያለ ነፃነት የለም፡፡ በዚህም የጸና ሀገር የለም፡፡

እኛ እንደ ሀገር ህልሞቻችን ትልልቆች ናቸው። ስለሀገርና ሕዝብ ያለን ምኞት ሰፊ ነው፡፡ ነገር ግን የሰፋና የገዘፈ በላጭ ሃሳብ አጥተናል፡፡ ባልሰፋና ባልገዘፈ ሃሳብ ውስጥ የሚታለሙ ህልሞች ደግሞ ያለቀኑ እንደተወለደ ሕፃን ፈጥነው የሚጨነግፉ ናቸው፡፡ ስለሰላም በመምከር፣ ስለአብሮነት በመነጋገር ህልሞቻችን የጋራ እንዲሆኑ ከማድረግ ባሻገር የእኔ የአንተ የሌለበትን ሕዝባዊነት ለመፍጠር አቅም የሚፈጥር ነው፡፡

ጦርነት ሀገር የለውም፡፡ ይዋጣልን ትውልድ የለውም፡፡ በየትኛውም የበቃ ጭንቅላት ቢቃኝ ታሪክ ከማበላሸት፣ አብሮነትን ስጋት ላይ ከመጣል፣ ቂምና ቁርሾ ከማስቀመጥ ባለፈ ማንንም ነፃ አያወጣም። ለዚህ እኛ ታሪክ ህያው ምስክር ነው፡፡ ባለፉ የጦርነት ታሪኮቻችን ዋጋ በመክፈል ላይ ነን፡፡ አሁን ላይ በምናደርጋቸው በየትኛዎቹም ጥላቻ ወለድ መገፋፋቶች ወደፊት ዋጋ እንደምንከፍልባቸው ለጥያቄ የምናቀርበው አይደለም፡፡ ሰላም የሌለበት አሸናፊነት ቀን ቆጥሮ በቂም በቀል መናዱ አይቀርም።

እንደሀገር ብዙ ነገሮችን የቻልን ሕዝቦች ነን። እንደ ዓድዋ ያሉ ማንም ያልቻላቸውን፣ በማንም ያልተሞከሩ ድሎችን ተቀዳጅተናል፡፡ እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በራስ ወጪ፣ በራስ እውቀት፣ በራስ አቅም ያለማንም ርዳታ ከጫፍ ያደረስን ብርቱዎች ነን፡፡ አሁንም በባህር በር በኩል ሌላ ታሪክ ልንጽፍ እየተሰናዳን ነው፡፡ ነገር ግን ስለሰላም ብርቱ ዋጋዎችን ስንከፍል አንታይም፡፡

በንግግርና በምክክር የሄድንባቸው ብዙ ርቀቶች የሉም፡፡ ኃይል ለብሰን፣ ቁጣ አንግበን ጠመንጃ ከመወልበልና ከብዙ እልቂት በኋላ ከመጨባበጥ ባለፈ ከጦርነት በፊት ሰላም በሚል መርህ ውስጥ ስንመላለስ እንብዛም አይታይም፡፡ ይሄ ዓይነቱ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ልምምድ ነው በመጣንበት ልክ እንዳንቀጥል እንቅፋት የሆነን፡፡ ህልማችን እንዳንኖር፣ ምኞቶቻችን ወደመሬት ወርደው ታሪክ እንዳንሰራባቸው ያደረገን፡፡

ሕዝብ ጦርነት አንገሽግሾታል፡፡ ጉስቋሌ ደክሞታል፡፡ የሞት መውጊያን ሽረን ስለሰላም ዋጋ የምንከፍልባቸውን የእርቅና የትብብር መድረኮችን መፍጠር የዚህ ትውልድ ጥልቁ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን በሥራ ላይ ይገኛል፡፡ ሀገራዊ አንድነትን ለመፍጠር፣ የሰነበቱና ሰሞነኛ ቁርሾዎችን በማድረቅ ሀገርን በአዲስ ተሀድሶ ለመምራት ሕዝባዊ መድረኮችን በማዘጋጀት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ነው፡፡ በእርቅና በመተቃቀፍ ወደነገ እስካልሄድን ድረስ በጥላቻ የምናመጣው ለውጥ የለም፡፡

የትም በሌለ የሰውነት ድንበር ፍትህንና እውነትን ለብሰን ሰውና ኢትዮጵያዊ ሆነን ኖረናል፡፡ ማንም በሌለው ክብርና የሰብዓዊነት ጥያቄ ለሌሎች ቤዛ በመሆን የመጣን ነን፡፡ ለራሳችን አናንስም፡፡ ጥንተ ፍቅራችንን መመለስ እስከቻልን ድረስ ጥንተ ብርታታችንን የማንመልስበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ያቃቱንን እንሞክራቸው፡፡ ያቃቱን ነገሮች ዋጋ እያስከፈሉን ነው፡፡ በውይይት ልናስቀራቸው የምንችላቸው ቁርሾዎች ወደጦርነት ወስደውን ብዙ ዋጋ አስከፍለውናል፡፡ በምክክር ልንጨባበጥባቸው በምንችላቸው ልዩነቶች ውስጥ ጦር ተማዘናል፡፡ ያቃቱን እነዚህ ናቸው… እህ ብሎ በማድመጥ… እህ ብሎ በመናገር ያልቻልናቸውን እንቻል፡፡

ተፋቅረንና ተሳስበን የተነሳናቸው የጥንት ፎቶዎቻችን እኛን ነጋሪዎች ናቸው፡፡ በአንድ ገበታ ስንበላ የጻፍናቸው ታሪኮቻችን ምን እንደነበርን መስካሪዎቻችን ናቸው፡፡ ባለፉት ሀምሳ ዓመታት ውስጥ ብዙ ነገር ተበላሽቷል፡፡ አሁን፣ በቅርብ እኮ ነው ኢትዮጵያዊነትን የሻርነው፡፡

ግን ማነው ያበላሸን? ማነው እርስ በርስ እንድንጨካከን ያደረገው? ማነው ማንም ከሌለው ጥንተ ማንነት አቆራርጦ ባለመርባት ውስጥ ያቆመን? ማነው እኔ፣ አንተ፣ የእኔ የአንተ እንድንባባል የፈረደብን? ማነው ወርቆቻችንን በጠጠርና በፋንድያ የቀየረብን? ማነው የፍቅርና የወንድማማችነት ካባችንን አውልቆ በጥላቻ ያቆመን? ማነው እርስ በርስ እንድንፈራራና እንድንሰጋጋ ያደረገን? እኔ ወደ ፖለቲካው እና ፖለቲከኞቻችን ጣቴን እቀስራለሁ። በሴራና በኃይል የተገዛው ፖለቲካችን የችግራችን ሁሉ ምንጭ ነው።

እኔ ታሪክ ቀይረው፣ ትርክት ፈጥረው ወደነገሩን እማትራለሁ፡፡ ለራሳቸው ጥቅም ብዙሃኑን ወዳለያዩ ራስ ተኮሮች አስተውላለሁ፡፡ እኔ ኢትዮጵያዊነትን ሽረው ብሔርተኝነትን በሚያራምዱ ክፉዎች ጥርሴን እነክሳለሁ፡፡ እኔ እውነትን ሽረው፣ ሀሰትን አጉልተው አንዱን በአንዱ ላይ ባስነሱ አእምሮና ልቦች እተክዛለሁ፡፡ ኢትዮጵያን የሚወዱ መስለው በሚጠሉ በነሱ ላይ አመራለሁ፡፡

የሆነው ቢሆንም ኢትዮጵያን ዳግም ለመሥራት ይቻለናል፡፡ በሰላማዊ ተግባቦት በከሰርንባቸው ያለመግባባት ጊዜያቶች ተምረን መጪውን ጊዜ ለለውጥ መጠቀም እንችላለን፡፡ ሰላም እስካለ ድረስ መቼም ቢሆን የሰው ልጅ ከደረቀበት ማቆጥቆጥ ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ትልቁና ሊሰመርበት የሚገባው ቁም ነገር የጥላቻ መንገዶችን ዘግተን የሰላም ደጆችን እንክፈት የሚል ነው፡፡

ዳግም ላለመክሰር፣ ዳግም ወደ ጦርነት ላለመግባት የልዩነት ምንጮቻችንን አድርቀን አንድነትን ማጽናት ለነገ የማናስቀምጠው የቤት ሥራችን ነው፡፡ ብሔራዊ ምክክር እዛም እዚህም ያሉ ነባርና ወቅታዊ ችግሮችን ነቅሶ፣ ከአጀንዳ ልየታ እስከ ተሳታፊ ምልመላ ድረስ ሕዝባዊ ውይይት ሊያደርግ ከጫፍ ደርሷል፡፡ ይሄ መሰሉ እንቅስቃሴ በጦርነት ለደከምነው ለእኛ ተስፋ ሰጪ ምልክታችን ነው። ሰላም ከማምጣት እና ችግር ፈጣሪ ቁርሾዎችን ከማድረቅ አኳያ ሚናው ላቅ ያለ ነው፡፡

እንደ ሀገር አሁን ባለው ፖለቲካ፣ አሁን ባለው ሕዝባዊ መሻት፣ አሁን ባለው የማደግና የመለወጥ ፍላጎት ሰላም መር ንቅናቄ ብቻ ነው የሚያስፈልገን፡፡ በወንድማማቾች ጦርነት ብዙ ነገሮቻችንን ያጣን ነን። ‹ጦርነት ይብቃ ሰላም ይስፈን› በሚል መሪ ሃሳብ ራሳችንን ከድህነትና ከኋላቀርነት ነፃ የምናወጣበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ጥላቻ መርዝ ነው፡፡ ጦርነት በጥላቻ የሚረጭ መርዝ ነው፡፡ መርዙ ከመግደል እና አካል ከማጉደል ሌላ የሰላም መንገዶችን አይከፍትም፡፡ የሰላም መንገዶች በሰላማዊ ሃሳቦች ውስጥ ናቸው። በመሳሪያ ሳይሆን በሃሳብ እንዋጋ፡፡ በመግደልና በመሞት ሳይሆን ለሌሎች በመኖር ውስጥ ኖረን እንለፍ፡፡

ራዕይ ወደመሬት ወርዶ ሀገርን ከድህነት ሕዝብን ከተረጂነት እንዲታደግ ሰላም በሚባል መሠረት ላይ የቆመ ህብረ ብሔራዊ አንድነት ያስፈልጋል። እዛና እዚህ በዘርና በብሔር፣ በጎሳና በቋንቋ ተከፋፍሎ በስጋትና በፍርሀት በሚኖር ሕዝብ መሀል የሚፈጠር ምኞትና ራዕይ ውሃ የማያነሳ ነው፡፡ ለዛም ነው ከሁሉ በፊት ስለሰላም እናውጋ፣ ስለአንድነት እንመስክር የምንለው፡፡ የሀገር ሰላም በግለሰቦች እጅ ውስጥ ነው፡፡ መከራዋም በእጃችን ነው፡፡ የነዛነው የጥላቻ መርዝ ነው እያጠፋን ያለው፡፡ እንድንበረታ ስለሰላም እናውጋ፡፡ የፍቅር ደጃፎቻችንን እንክፈት።

ጠብን በፍቅር የሚሽር፣ ጦርነትን በሰላም የሚቋጭ ፖለቲካዊ ልምምድ የለንም፡፡ በሃሳብ ተረትቶ ጦርነትን ያወጀ እንጂ በሃሳብ ተሸናንፎ ጦርነትን ያስቀረ ፖለቲካና ፖለቲከኛ አላውቅም፡፡ ለዛም ነው የምንገዳገደው፡፡ ለዛም ነው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ስንል በነውረኛ ራሳችን ላይ የምንተርተው፡፡ ራሳችን በለኮስነው እሳት ተቃጥለንና አቃጥለን ዛሬም ድረስ በዛ የእሳት ወላፈን ጠባሳችን የሚታይ ነው፡፡

ጠባሳ በጠባሳ የሆነ ታሪክ ምን ይጠቅመናል? የቻይና አብዮት የተቀየረው ‹ዓይጥ የማትይዝ ድመት ምን ትሰራልናለች? በሚል የተሀድሶ አራማጆች ነው። እኛም ‹ሀገር የማይቀይር ሽኩቻ ምን ይሰራልናል? ስንል የሰላም አብዮትን ማቀጣጠል አለብን፡፡ በጠበበ ሃሳብ ውስጥ ሰፊ ህልም ዋጋ የለውም፡፡

መጀመሪያ ሃሳባችንን እንስፋ፣ ምህድራችንን እናግዝፍ፡፡ ከዛ በኋላ በሰፋ ሃሳብ ሰፋፊ ህልሞች ይፈጠራሉ፡፡ ሀገር በሰከነ ሃሳብና በረገበ ስሜት እንጂ ውረድ እንረድ በሚልና ይዋጣልንን በሚመስሉ ረብ የለሽ የስሜት አዘቅቶች አትመራም፡፡ ድሀ ሀገር፣ ድሀ ሕዝብ፣ በተረጂነት የሚኖር ማህበረሰብ ጦርነትን የምንም ነገር መፍትሔ አድርጎ መያዙ የክፍለ ዘመኑ አስቂኝ ቀልድ ከመሆን አይዘልም፡፡

ዓለም የደረሰችበት ትልቁ የጥናት ውጤት የሰላም ግኝት ነው፡፡ ሰላም በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ያሉን ነገሮች ምንም ዋጋ የሌላቸው እንደሆኑ በተለያየ ጊዜ አንስተናል፡፡ ገንዘብ፣ እውቀት፣ ስልጣን ካለወንድማማችነት ምንም ናቸው፡፡ ይሄን እውነታ ለማረጋገጥ የቅርብ ጊዜውን ዓለም አቀፉን የኮሮና ዘመን ማስታወስ ይቻላል፡፡ ብዙ ሀገራት በሀብት፣ በኃይል በብዙ ነገር ከብረው ያን የጭንቅ ዘመን ማለፍ አቅቷቸው ሲፍገመገሙ አይተናል፡፡

ሌላው በሀገራችንም ሆነ በሌሎች ሀገራት የተነሱን ጦርነቶች፣ የእርስ በርስ ግጭቶችን ማስታወስ ይቻላል፡፡ በቅርቡ በሀገርና ሕዝብ ላይ የደረሰውን ፈተና ማሰቡ የሰላምን ዋጋ ለማወቅ በቂ ነው፡፡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳይማሩ፣ ሠራተኞች ተግተው እንዳይሰሩ፣ ቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ፣ መንግሥት በሀገርና ሕዝብ ላይ ያለውን ኃላፊነት እንዳይወጣ በአጠቃላይ ከዚህ እስከዛ ለማይባል መከራ ዳርጎናል፡፡ ይህንን ተጨባጭ እውነታ እያሰብን ስለሰላም ዋጋ በመክፈል ሀገራችንን እንታደግ፡፡

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You