የሕዝብ ቁጥር ሲጨምር፤ ሥልጣኔም ይጨምራል!

5ኛ ክፍል እያለሁ የኅብረተሰብ መምህራችን ‹‹የሥልጣኔ ምንጩ ችግር ነው›› ብሎ የነገረን ዛሬም ድረስ በየአጋጣሚው ትዝ ይለኛል፡፡ ወዲህ ደግሞ ‹‹ችግር ብልሃትን ይወልዳል›› የሚል ሀገርኛ ብሂል አለ፡፡ የቅርብ ጊዜውን የኮቪድ-19 ክስተት ማስታወስ እንችላለን፡፡ ጭንቀት የወለዳቸው ብዙ ብልሃቶች፣ ብዙ ፈጠራዎች ታይተው ነበር፡፡ በእጅ ሳይነኩ በእግር ብቻ የሚከፈት የእጅ መታጠቢያ እስከዚያ ጊዜ ድረስ አላየንም ነበር፡፡ ምንም እንኳን ትልቅ የቴክኖሎጂ ውጤት ነው ባይባልም፤ ቢያንስ ግን በወቅቱ የነበረውን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ዘዴ ነበር፡፡ ሌሎች ተመሳሳይ የፈጠራ ሥራዎችም ነበሩ፤ ችግር ብልሃትን ይወልዳል የሚባለውን ብሂል በተግባር አይተናል፡፡

የሕዝብ ቁጥር ነገር በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት አሳሳቢ ነው እየተባለ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ በተለይም አዲስ አበባ ውስጥ የምንኖር ሰዎች እንደ መገናኛ፣ መርካቶ እና ሜክሲኮ ያሉ አካባቢዎች ስንሄድ የሕዝብ ብዛት ነገር ያሳስበናል። በዚህ ከቀጠለ ከ20፣ 30 እና 50 ዓመታት በኋላ ምን ሊሆን ይችላል? እያልን እንጠይቃለን፡፡ ከዛሬ 20፣ 30 እና 50 ዓመታት በፊት የነበሩ ነገሮችን እያስታወስን ‹‹ያኔ እኮ እንዲህ ነበር!›› እያልን እናወራለን፡፡ የነገሮች ሁሉ መጨናነቅና መወደድ ምክንያቱ የሕዝብ ቁጥር መብዛት ነው ብለንም እናምናለን፡፡

‹‹ልጅ ሲወለድ እጅና እግር ይዞ ነው የሚወለድ›› የሚባል ልማዳዊ አገላለጽ አለ፡፡ ይህን ነገር አቶ መለስ ዜናዊ ስለሕዝብ ቁጥር አሳሳቢነት ተጠይቀው ‹‹የሚሰራ ኃይል ነው የሚወለደው›› በማለት የተናገሩትን እናስታውሳለን፡፡ የሚሠራ ኃይል የሚለው ያስማማል፤ ‹‹ልጅ ሲወለድ ፀጋ ይዞ ይመጣል›› የሚባለው ልማዳዊ እምነት ግን ብቻውን አዋጪ አይሆንም፡፡

የሕዝብ ቁጥር መጨመር ለድህነት ምክንያት የሚሆነው ለታዳጊ ሀገራት ነው፡፡ ምክንያቱም በዘመኑ ልክ የመራመድ ፈጣን ዕድገት የላቸውም፡ ፡ ታዳጊዎችንና ወጣቶችን ወደ ፈጠራ የሚወስድ የተዘረጋ ሥርዓት የላቸውም፡፡ ከሚወለደው ውስጥ አብዛኛው በተወሰኑት ላይ ጥገኛ ይሆናል፡ ፡ የሰለጠኑ ናቸው ለሚባሉት ሀገራት ኑሮን ቀላል ያደረገላቸው የሕዝብ ቁጥር ማነስ ሳይሆን የዘረጉት ሥርዓት ነው።

የሕዝብ ቁጥር መጨመር ለድህነትና ኋላቀርነት ምንክንያት ቢሆን ኖሮ፤ ዓለም ለምን እዚህ የረቀቀ ቴክኖሎጂ ላይ ደረሰች? ለምን ድህነትና ኋላቀርነት እየተባባሰ አልመጣም ነበር?

ልብ በሉ! ከዛሬ አንድ ሺህ ዓመት በፊት የዓለም የሕዝብ ቁጥር ብዛት 50 ሚሊዮን ነበር፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ፣ የአንድ ክልል ሕዝብ ቁጥር ብቻ ከ50 ሚሊዮን ይበልጣል፡፡ ያኔ ግን በዓለም ላይ የነበሩ ሕዝቦች በሙሉ 50 ሚሊዮን ብቻ ነበሩ።

ከዛሬ አንድ ሺህ ዓመት በፊት የነበረውን የሰው ልጅ አኗኗር ልብ እንበል፡፡ ዛሬ ላይ ያሉ የምቾት መገልገያዎች አንዳቸውም አልነበሩም፡፡ ያኔ የነበረው ድህነት ዛሬ የለም፤ ያኔ የነበረው አድካሚ ሥራ ዛሬ የለም፡፡ ያኔ የነበሩ ገዳይ በሽታዎች ዛሬ የሉም፤ ቢኖሩም መፍትሔ ተገኝቶላቸዋል፡፡ ለምን? የሕዝብ ቁጥር በጨመረ ቁጥር የአስተሳሰብ፣ የሥልጣኔ እና የፈጠራ አይነቶችም ስለጨመሩ፡፡ ያኔ 50 ሚሊዮን ሕዝብ በምቾት ማስተዳደር ያልቻለች ዓለም ዛሬ 8 ቢሊዮን ሕዝብ በምቾት እያስተዳደረች ነው፡፡ ምንም እንኳን በሁሉም ሀገራት ምቾት አለ ባይባልም ቢያንስ ከአንድ ሺህ እና ከአንድ መቶ ዓመታት በፊት ከነበረው በብዙ እጥፍ የተሻለ ሁኔታ ላይ ናቸው፡፡

ከዛሬ አንድ መቶ ዓመት በፊት የዓለም ሕዝብ ቁጥር 2 ቢሊዮን ብቻ ነበር፡፡ እነሆ ፍጥነቱ ጨምሮ በ100 ዓመት ውስጥ 6 ቢሊዮን ጨምሯል፡፡ ይህ ማለት ከዚያ በፊት በነበሩት ዘመናት በዚህ ፍጥነት ሳይጨምር ማለት ነው፡፡ በዚያው ልክ ግን የዓለም የሥልጣኔ ቅርጽ በአይነትና በመጠን እየጨመረ ነው። ሥራን የሚያቀሉ እና አኗኗርን ምቹ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች ተፈጥረዋል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ፤ ከዛሬ 50 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ከ50 ሚሊዮን በታች ነበር፡፡ የአኗኗር ሁኔታው ግን ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ከነበረው በብዙ እጥፍ የተሻለ ነው፡፡ በባዶ እግሩ የሚሄድ የለም፣ በእግሩ ሀገር አቋራጭ ጉዞ የሚሄድ የለም፣ በድንጋይ ወፍጮ የምትፈጭ የለችም…. በአጠቃላይ ብዙ ነገሮች ታሪክ ሆነዋል፡፡

ይህ የሆነው የሕዝብ ቁጥር ቢጨምርም፣ በዚያው ልክ የሰው ልጅ ጥበብ እና የአስተሳሰብ ደረጃ እየተሻሻለ ስለሚሄድ ነው፡፡ የሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ አዳዲስ ነገሮችን ይዞ ስለመጣ ነው፡ ፡ በነገራችን ላይ ዝግመተ ለውጥ መጨረሻ የለውም፤ በተለምዶ ግን ዝግመተ ለውጥ ሲባል ከዝንጀሮነት ወደ ሰውነት (ከሆሞ ኢሬክተስ ወደ ሆሞ ሳፒያንስ) ያለው ይመስለናል፡፡ የሰው ልጅ ለውጥ ግን ቀጣይነት ያለው ነው፡፡ ከዛሬ 100 ዓመት በኋላ ደግሞ ዓለም ምን ላይ እንደምትሆን አይታወቅም፡፡

የሕዝብ ቁጥር የድህነት ምክንያት እየሆነ ያለው በታዳጊ ሀገራት ነው፡፡ እንዲያውም ይህንኑም መቋቋም የቻሉት የሰለጠኑት እና ሥርዓት የዘረጉት ሀገራት በፈጠሩላቸው ዕድል ነው፡፡ ዓለም መንደር ስለሆነች በአደጉት ሀገራት በመታገዝ ነው። በዘመኑ ልክ መራመድ እና ሥርዓት መዘርጋት ካልቻሉ የሕዝብ ቁጥር መጨመር የበለጠ ችግር እያመጣባቸው ይሄዳል፡፡

አዲስ አበባን ብቻ ምሳሌ አድርገን እንውሰድ። ከትራንስፖርት ጀምሮ ብዙ ነገሮች የተጨናነቁ እና ሕዝብ የበዛባቸው ናቸው፡፡ በወረፋ ምክንያት አገልግሎት የማይገኝባቸው ጉዳዮች ብዙ ናቸው።ይህ የሆነው ግን ምቹ አሠራርና የተገነባ ሥርዓት ስለሌለ ነው፡፡ መፍትሔውም ሥርዓት (ሲስተም) መፍጠር እንጂ የሕዝብ ቁጥር መቀነስ አይሆንም። ያም ሆኖ ግን ሥርዓቱ ሳይዘረጋ የሕዝብ ቁጥሩ እየጨመረ ከሄደ፤ በችግር ላይ ችግር እየተደራረበ ነው የሚሄደው፡፡ የሥልጣኔ ዕድገታችን ባለበት ላይ ቆሞ የሕዝብ ቁጥር ብቻ የሚጨምር ከሆነ ችግሩ እየተባባሰ ይሄዳል፡፡ የወሊድ መቆጣጠሪ እና የቤተሰብ ምጣኔ በግለሰብ ደረጃ የሚበረታታ እና ዘመናዊነት ቢሆንም እንደ ሀገር ግን ዘላቂ መፍትሔ አይሆንም፡፡ በእርግጥ ሀገርን የሚገነባው የግለሰቦች ሁኔታ ነው፡፡ ቢሆንም ግን እንደ ሀገር አስተማማኙ ነገር የሰለጠነ ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ እንደ ቻይና ያሉ ሀገራት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ይዘው ነው የዓለም ልዕለ ኃያላትን እየተገዳደሩ ያሉት፡፡

የሰው ልጅ የአስተሳሰብና የንቃት ደረጃ እየጨመረ፣ እየተሻሻለ መሄድ አለበት፤ ከእነዚህም አንዱ የወሊድ ምጣኔን መተግበር ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህም በላይ ግን በከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ውስጥ ምቾት ያለው ሕይወት መኖር የሚያስችል የሰለጠኑ ሀገራትን ሥልጣኔ መውሰድ ነው፡፡

የሕዝብ ቁጥር ሲጨምር የሥልጣኔ ደረጃችን ካልጨመረ የድህነት ምክንያት ይሆናልና በዘመኑ ልክ እንራመድ!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You