ለኢትዮጵያውያኑ የተበረከተ – የሕዳሴ ግድቡ እውቅና

የኢትዮጵያውያኑ ሁሉ የኩራት ምንጭ በሆነው በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ ኢትዮጵያና ዜጎቿ በተደጋጋሚ ተፈትነውበታል። ይሁንና ፈተናው ይበልጥ ጥንካሬ ፈጠረላቸው እንጂ አንዳችም ጊዜ ቢሆን በፈተናው ተሰናክለው አልወደቁም።

በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ ለሚደርሰው ተደጋጋሚ ፈተና ትልቁን ድርሻ የምትይዘው አፍሪካዊቷ ሀገር ግብጽ ስትሆን፤ ዓይነተ ብዙ የሆኑ ፈተናዎችን በመፈብረክ ከጅማሬው እስካሁኑ ሰዓት ድረስ የተቻላትን ሁሉ አድርጋለች። በርግጥ የግብጽ ስጋት የጀመረው፤ ዛሬ አይደለም። በፊትም ቢሆን የዓባይ ወንዝ ጉዳይ ሲያባንናት የኖረ ነገር ነው። ‘ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ትገነባ ይሆን?’ የሚል ስጋት ሲያባንናት ኖሯል።

ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ ለመገደብ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሯ አማካይነት የመሠረተ ድንጋይ ባስቀመጠችበት ወቅት ጥርጣሬዋ እውን ሆኖ ስጋቷ ከፍ ብሎ ግራ ተጋብታ ከርማለች። ስጋቷን በውይይትና በሰጥቶ መቀበል መርህ መቅረፍ ሲገባት ያልተገባ መንገድን መረጠች። በማስፈራራት፣ አንዱን ብሔር ከሌላኛው ጋር በማጋጨትም በሌላ ሌላ ተንኮል አልሆን ሲላት ከአንደኛ አህጉር ወደ ሌላኛው አህጉር ‘ጉዳዬን እዩልኝ ስትል’ ተንከራትታለች። በዚህ መልኩ የግድቡን ግንባታ ለማስቆም ያደረገችው ውጣ ውረድ ሁሉ ከንቱ ድካም መሆኑን የተረዳችው ይህች ሀገር፣ ‘ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠንና ከፍታው ካልተቀነሰ ሞቼ እገኛለሁ’ ስትል ሞገተች።

ነገር ግን ይህ በ2003 ዓ.ም ጅማሬውን ያደረገውና ኢትዮጵያውያኑ እንደ ዓይናቸው ብሌን የሚሳሱለት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አንድ ሺ 800 ሜትር ስፋት ያለው፣ 145 ሜትር ከፍታ ያለው እንዲሁም 74 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ውሃ የያዘ እና በኢጣሊያኑ ኩባንያ ሳሊኒ ተገንብቶ ወደመጠናቀቅ የተቃረበ መሆን ችሏል።

ከአፍሪካ የአንደኝነትን ደረጃ የያዘው ይህ ግድብ፣ ከዓለም ስምንተኛ ደረጃ ላይ ሲሆን፣ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ስም ከፍ እንዲል ያደረገ ነው፤ ከዚህ አኳያ ከሰሞኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የስኬት ሽልማት ካበረከቱላቸው ተቋማት መካከል አንዱ መሆን ችሏል። ይህ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሰባት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ መግለጻቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ድልድይና የፕሮጀክቱ ሙሉ ሥራ በቀጣይ ዓመት የሚጠናቀቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተሰጠውን የእውቅና ሽልማት በማስመልከት ምሁራንን ባነጋገርናቸው ወቅት እንዳሉት ከሆነ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማለት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ክብሯ ነው። ይህ ማለት ደግሞ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አቅሟን የሚወስን ታሪካዊ ክስተት ነው። እውቅናው ለኢትዮጵያውን የተሰጠ ነው።

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ሰማኸኝ ጋሻው እንደሚሉት ለአምስቱ መሥሪያ ቤቶች ሽልማት የመሰጠቱ ፋይዳ ላቅ ያለ ነው። ተቋማቱ በሀገር ደረጃ ሲታዩ የአንድ ሀገረ መንግሥት ህልውና መሠረቶች ናቸው። የመንግሥቱን ቀጣይነትም የሚወስኑ ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው መሥሪያ ቤቶች ናቸው። በተጨማሪም ከሰፊው ሕዝብ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው የአገልግሎት ማዕከላት ናቸው። መንግሥት ለኅብረተሰቡ የሚሰጠው ሁለንተናዊ አገልግሎት ውጤታማነትና ድክመቶች የሚመዘኑት በተቋማቱ ጥንካሬና ድክመት ነው። የመንግሥትን በሕዝብ ዘንድ ያለውን ቅቡልነት በዚሁ ልክ ይወስናሉ። መንግሥትም በላቀ አፈጻጸማቸው የመሸለሙ ምስጢር በእነዚህ ምክንያቶች ይመስለኛል።

እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ለተቋማቱ የተሰጠው እውቅና የሚያስገኘው ፋይዳ አንደኛውና ዋናው ጥቅም ጠንካራና ዘመኑን የዋጀ ተቋማትን መገንባት ያስችላል። ከታሪክ እንደምናየው ጠንካራ ተቋማት ያሉት ሀገር በሁለንተናዊ እድገቱ ውጤታማ ይሆናል። ሁለተኛው ደግሞ ለብሔረ መንግሥት ግንባታው ቁልፍ ሚና ያለው መሆኑ ነው። ይህ ማለት ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ጠንካራ ብሔረ መንግሥት እንዲመሠረት ያስችላል። ሶስተኛው ደግሞ በመሥሪያ ቤቶች መካከል መልካም የሥራ ፉክክር እንዲፈጠር በማድረግ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ማስቻሉ ሲሆን፣ አራተኛው ደግሞ ተቋማቱ ራሳቸውን እንዲፈትሹ ዕድል መስጠቱ ነው። በዚህም ጠንካራ ጎኖቻቸውን የበለጠ ለማጠናከር፤ ድክመቶቻቸውን ደግሞ ለመቅረፍ ያስችላል። በርግጥ የሚሉት የታሪክ ተመራማሪው፣ የተሸለሙት መሥሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ክፍተት የለባቸውም ማለት አይደለም፤ ይልቁን ከሌሎች የተሻለ የሥራ አፈፃፀም ስላስመዘገቡ ነው ብለዋል።

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ዜጋ እና ሥነ ምግባር ትምህርት ክፍል የመልካም አስተዳደርና ልማት መምህር አዳፍረው አዳነ በበኩላቸው፤ ሰሞኑን በሀገራችን በመንግሥት ደረጃ የተከናወነውን “የኢትዮጵያ ተቋማት ስኬት ሽልማት” እንደዚህች ሀገር ዜጋ የሚሰማኝ ነገር ቢኖር በየዘርፎቹ መልካም ሊባሉ የሚችሉ የጅማሮ ስኬቶችን እውቅና ለመስጠትና ለማወደስ የተደረገ የሽልማት ሥነ ሥርዓት አድርጌ ነው ብለዋል። ለዚህም በምክንያት ያስቀመጡት፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ካላት አንጡራ ሀብትና የመበልፀግ ዕድል አንፃር የተመዘገቡት ስኬቶች ጅማሮ እንጂ ፍፃሜ አይደሉም ሲሉ ነው።

እርሳቸው እንደሚሉት ገና ብዙ ይቀረናል። መዳረሻችን እና ስኬታችን ከሀገር አልፎ ለአህጉራችን አፍሪካ ብሎም ለዓለም ማብራት እስኪችል ድረስ የመሥራትና የመለወጥ ጫፍ ሊኖረው ይገባል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህንኑ አፅንዖት ሰጥተው ሲናገሩ ተደምጠዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴው ግድብ እንደ ሀገር ግዙፍ እና የሀገርን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስን ታላቅ ግድብ ነው የሚሉት መምህር አዳፍረው፣ ለሕዳሴው ግድብ ያልተሰጠ እውቅና ለሌላ ለየትኛውም ተቋም ሊሰጥ አይችልም ብዬ አምናለሁ ይላሉ። የሕዳሴ ግድብን ግንባታ ከመጀመር አንስቶ እስካሁን ባለው ሂደት ውስጥ የገጠሙ በርካታ ተግዳሮቶች በሀገር ወዳድና ቁርጠኛ አመራሮች እንዲሁም የሀገር ፍቅር ስሜት በሰነቁ ሠራተኞች ዘንድ ብዙ ዋጋ የተከፈለበት እንደሆነ እውን ነው ሲሉም ያመለክታሉ።

እንደ የታሪክ ተመራማሪው ገለጻ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማለት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ክብሯ ነው ቢባል ማጋነን አይደለም። እንዲህም ሲባል ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አቅሟን የሚወስን መሆኑን አመላካች ነው። በተለይ በፖለቲካው ዘርፍ ኢትዮጵያ የቀጣናውን ጂኦፖለቲካዊ ሚዛን መቆጣጠር እንድትችል ያደርጋል።

ይህ ደግሞ ግብጽ መሠረት ያደረገቻቸውንና በዓባይ ወንዝ ላይ ኢ-ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲኖር የሚደነግጉ የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን ውድቅ ከማድረግ ይጀምራል። በተለይም ሁለቱ የቅኝ ግዛት ውሎች ማለትም፤ እ.ኤ.አ በ1929 እና በ1959 የተፈረሙ ስምምነቶች ሙሉ በሙሉ ከግብጽና ከሱዳን ውጭ ያሉትን የተፋሰስ ሀገሮችን ጥቅም ያሳጡ ነበሩ። በተለይም ደግሞ የዓባይን 85 በመቶ ውሃ መጠን ለምትለግሰው ኢትዮጵያ ይህ ታላቅ ንቀት ነበር። በወቅቱ እንግሊዝ ሁለቱንም የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ማለትም ግብጽ እና ሱዳንን በቅኝ ግዛት ታስተዳድር ስለነበርና ሰፊ የሆነ የመስኖ እርሻ ስለነበራት የዓባይ የውሃ ፍሰት መጠን እንዳይቀንስ በማሰብ በእነዚህ ስምምነቶች አማካኝነት የዓባይን ውሃ ለሁለቱ ሀገራት ብቻ አከፋፍላለች ይላሉ።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ እ.ኤ.አ በ1929 በተደረገው ስምምነት ለግብጽ 48 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ እና በዓባይ ወንዝ ላይ የፈላጭ ቆራጭነት ስልጣን ሲሰጣት፤ ለሱዳን ደግሞ በበኩሏ 4 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ተሰጥቷ ነበር። እ.ኤ.አ በ1959 በተደረገው ስምምነት ደግሞ፤ ግብጽ የውሃ ድርሻዋን ወደ 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ከፍ ስታደርግ፤ ሱዳን በበኩሏ ወደ 18 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ድርሻ ተፈቅዶላት ነበር። ቀሪው 10 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ በትነት እና ሌሎች ምክንያቶች ሊባክን እንደሚችል ታሳቢ ተደርጓል።

ከዚህ እንደምናየው ይላሉ የታሪክ ተመራማሪው ሰማኸኝ፣ ከ11ዱ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ውስጥ 9ኙ በስምምነቶች ውስጥ አልተካተቱም ብቻ ሳይሆን ምንም ዓይነት በውሃቸው የመጠቀም መብት አልተፈቀደላቸውም። ይህ የሌሎች ሀገሮችን ጥቅም በመደፍጠጥ የራስን ሀገር ማዘመን ደግሞ የቅኝ ግዛት ሌጋሲ እሳቤ ነው።

ለዚህ ነው ከታሪክ አንፃር ስንመልከተው፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ በብቃት ስታጠናቅቅ አዲሱን የቅኝ ግዛት እሳቤ (Neocolonialism) በድል እንደተወጣች የምንቆጥረው። በተጨማሪም ከዚሁ ከፖለቲካዊ ጥቅሙ ሳንወጣ፤ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በማድረግ ያላትን ተሰሚነት ታጠናክራለች፤ ለሌሎች የላይኛው ተፋሰስ ሀገራትም ፍትሃዊ የዓባይ ውሃ አጠቃቅምን ታረጋግጣለች። በሌላ በኩል ለቅኝ ግዛት እሳቤ እና ሌጋሲ አራማጅ ለሆኑት ግብጽ እና ሱዳን የሕዳሴው ግድብ በስኬት መጠናቀቁ ሽንፈት ይሆናል ብለዋል።

በኢኮኖሚው ዘርፍ ደግሞ ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ፤ የዓሣ እና ተያያዥ ምርቶችን በማምረት፤ የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎቶችን በማስፋፋት ምጣኔ ሀብታችንን ለማነቃቃት ያግዛል ሲሉም አመልክተዋል።

በማኅበራዊ ዘርፉ ደግሞ በዋናነት የኢትዮጵያውያንን የእርስ በእርስ ግንኙነትን ማጠናከር መቻሉ ነው። እንደሚታወቀው ከዓድዋ ድል በኋላ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዐሻራውን ያሳረፈበት ክስተት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ነው። ይህ ግድብ በአብሮነት የተንሰላሰልንበት ትልቅ ሰንሰለት ነው። ይህ ጠንካራ የአብሮነት መንፈስ ደግሞ ለብሔረ መንግሥት ግንባታው ቁልፍ ሚና ይጫወታል።

ለዚህ ግድብ በሀብት፤ በጉልበት፤ በእውቀት፤ በጊዜና በሕይወት ጭምር ዋጋ ተከፍሎበታል። የተከፈለውን ዋጋ እጅግ ከባድ ካደረጉ ሁነቶች መካከል ደግሞ በዋናነት የቅኝ ግዛት ሥነ ልቦናዊ ውቅር ያላቸው የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጣልቃ ገብነት ተጠቃሽ ነው። በነዚህ እጅግ ውስብስብ ፈተናዎች ውስጥ ሆኖ ግድቡን በስኬት ማጠናቀቅ የዓድዋ ድልን እንደ መድገም እቆጥረዋለሁ። ስለዚህ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ መሸለም መላ ኢትዮጵያዊያንን እንደመሸለም እቆጥረዋለሁ።

መምህር አዳፍረውም ልክ እንደ ታሪክ ተመራማሪው ሰማኸኝ፣ የሕዳሴ ግድቡ ለኢትዮጵያውያን የኩራት ምንጭ ነው ይላሉ። የዚህ ግድብ ግንባታ በብዙ ፈተናዎችና ውጣውረዶች ውስጥ አልፎ ዛሬ ላይ የሲቪል ሥራዎችን በማገባደድ ለሀገራችን ከፍተኛ ተስፋን የሰነቀ የአሸናፊነትን መንፈስ ማላበስ እንደቻለም ያስረዳሉ። የሕዳሴ ግድቡ ከዚህ በተጨማሪ የአንድነትና የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ማረጋገጥ የቻለ ነው ብለዋል።

ስለዚህ ለሕዳሴው ግድብ እንደተቋም እውቅና መስጠት ማለት የሀገሪቱ ሕዝቦች በአንድነትና በቁጭት ከተረፋቸው ላይ ሳይሆን ካላቸው ላይ ቀንሰው ላደረጉት አስተዋፅኦ እውቅና እና ክብር መስጠት ነው ብዬ አምናለሁ ሲሉም አመልክተዋል።

የሕዳሴ ግድቡን ጨምሮ ለተቋማቱ የተደረገው ሽልማትና እውቅና እንደ ሀገር ለመልማትና ለማደግ ያለንን ፍላጎትና አቅም እንደ መንግሥት ዋጋ የተሰጠው ቀዳሚ ተግባር እንደሆነ ማሳያ ነው ያሉት መምህር አዳፍረው፣ መንግሥት ለእነዚህ ተቋማት ሽልማት ሲሰጥ ትርጉሙ ዘርፈ ብዙ ነው ብለዋል። ይሄውም ተቋማቱን ከዚህ የበለጠ ለማትጋትና አደራ ለመስጠት ያለመና ሌሎች ተቋማትም ለሀገር ማበርከት ባለባቸው ልክ እንዲተጉ የማንቂያ ደውል እንደሆነም ገልጸዋል።

እንደ ምሁራኑ ገለጻ፤ ሌሎች ተቋማት ከዚህ ሽልማት ሊማሩ ከሚገባቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ የእነዚህን ተቋማት ልምድ በመቅሰም ለለውጥ መትጋት ነው። የሀገርን ልማት ለማረጋገጥ ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት ደግሞ ሌላው ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል በዚህ የእውቅና ሥነ ሥርዓት ያልተካተቱት መሥሪያ ቤቶች መልካም ተሞክሮዎችን ከተሸላሚዎች በመቅሰም ለቀጣይ ሥራቸው ስኬት እንዲተጉ፤ የሥራ አፈፃፀም ድክመቶቻቸውን ደግሞ እንዲገነዘቡ ያግዛቸዋል።

በሀገራችን ተቋማት ከአካላዊ ቁመናቸው ባለፈ ውስጣዊ አሠራራቸውን በማዘመንና ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ለትክክለኛ እድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ የተቋማዊ መሻሻሎችን (Institutional Re­forms) መንደፍ ይኖርባቸዋል። ተቋማዊ መሻሻሎች ወይም ተቋማዊነት ማለት እንደ ሀገር ያሉንን መደበኛና መደበኛ ያልሆኑ ሕጎችን የአሠራር ሥርዓቶችን እንዲሁም ባህላዊና ማህበረሰባዊ እሴቶችን የተቋማትን የግለሰቦችን እንዲሁም የቡድኖችን ባህሪ በአግባቡና ገዢ በሆነ መንገድ መተግበር ማለት ነው።

አስቴር ኤልያስ

 አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You