የችግሮቻችንም ሆነ የመፍትሔዎቻቸው ባለቤት እኛው ነን!

ሕዝብ ማንኛውንም ጥያቄ የመጠየቅ፣ መንግሥትም ከሕዝብ ለሚነሱ ማናቸውንም ጥያቄዎች ጆሮ ሰጥቶ ምላሽ የመስጠት ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግዴታም አለበት። ሕዝባዊ ውይይቶች የዜጎችን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ ዕድል ይጨምራሉ። መንግሥትም የሕዝብ ጥያቄዎችን አድምጦ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዲቻል አስፈላጊነታቸው ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።

ከሰሞኑ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች የተደረጉና እየተደረጉ ያሉ ሕዝባዊ ውይይቶችም ይህንኑ ታሳቢ ያደረጉ ናቸው። በውይይቶቹም በየአካባቢው ያሉ የመልካም አስተዳደር፣ የልማትና ሌሎችም ጥያቄዎች ተነስተው ሰፊ ውይይቶች ተደርገውባቸዋል። ከውይይቶቹም ዜጎች ብዙ እንደሚጠብቁ ይታመናል።

ሕዝባዊ ውይይቶቹ ከጥያቄ ባለፈ ፍሬ እንዲኖራቸው በየአካባቢው ያሉ አመራሮች ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ የተነሱና ምላሽ የተሰጠባቸው፣ ለመፍትሔያቸው ቃል የተገባላቸው ጥያቄዎች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ በቀጥታ ከሕዝብ ጋር የሚገናኙት የወረዳና የቀበሌ አመራሮች የተቀናጀ አሠራር መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ በየአካባቢው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ተረድቶ ሕዝብን በአግባቡ የሚመራ፣ ችግሮችን የሚፈታ ብቁ አመራር ማስቀመጥ አስፈላጊና ግዴታም ነው። ሁሉም ውጤት በመንግሥት ሥራ ብቻ የሚመጣ ባለመሆኑም ኅብረተሰቡ ከአመራሩ ጎን በመሆን ለተግባራዊነቱ በመትጋት ማገዝ ይገባዋል።

ከዚህ ባለፈ ችግሮች በአንዴ ንግግርና ውይይት ብቻ የሚፈቱ ባለመሆናቸው መሰል ሕዝባዊ ውይይቶች በተከታታይ ሊደረጉ፣ ሕዝቡ ከአመራሮች ጋር የሚገናኙበት ሃሳባቸውን በነፃነት የሚገልፁበት መድረኮች ቀጣይነት ሊኖራቸው ይገባል።

ሕዝባዊ ውይይቶቹ ሕዝቡ ጠያቂ ብቻ ሳይሆን የመፍትሔ አካል እንዲሆን የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚያስችሉ ይታመናል። ወካይ ከሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር መወያየት ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣትም ትልቅ አቅም ነው።

ሀገራችንን በልማት ወደ ብልጽግና ለማሻገር ቅድሚያ ለሰላም ሰጥተን መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል። ይህንን እውን ለማድረግ በችግሮቻችን ዙሪያ በግልጽ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ እና ወሳኝ ነው።

ከዚህ አንጻር፣ ሕዝብን እና አመራሩን ፊት ለፊት ያገናኙ ሕዝባዊ ውይይቶች ከሰሞኑ መደረጋቸው ጠቀሜታቸው ከፍ ያለ ነው። በእነዚህ ውይይቶች ዜጎች በሕይወታቸው ፈተና የሆኑባቸውን ነገሮች በቅሬታ ከተሞሉ መዝገቦቻቸው አውጥተው ለመድረክ አቅርበዋል። ከእነዚህ የሕዝብ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች መካከል የሰላም እጦት፣ የኑሮ ውድነት፣ የመሠረተ ልማት ችግርና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ገዝፈው ታይተዋል።

በርግጥ ውይይቶች ለዓመታት ሰሚ ላጡ ዜጎች ጆሮ የሚያውሱ ናቸው። መሰል ልምምዶች በሕዝብና በመንግሥት መካከል መግባባትን የሚፈጥሩ ናቸው። ፋይዳቸውም ላቅ ያለ ነው። መንግሥት የሠራቸውን፣ የሚሠራቸውን ለሕዝብ በአግባቡ ለማስረዳት እና ለማስገንዘብ ዕድል የሚሰጡ ናቸው።

በአለንበት ዘመን በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚፈበረኩ መሠረተ ቢስ መረጃዎችን በማህበረሰቡ ውስጥ የሚፈጥሩትን ግራ መጋባት በትክክለኛ መረጃ ለማረምም ሕዝባዊ ውይይቶች የሚፈጥሩት መልካም አጋጣሚ ትልቅ እንደሆነ ይታመናል። ዘላቂ ሰላምን በውይይት ለማስፈን የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው።

ሰላም ከሌለ ነገ የለም። ስለ ነገ ማሰብም ማቀድም የሚቻለው በሰላም ውስጥ ብቻ ነው። በሀገሪቱ ባለፉት ጊዜያት ይህ ለሁሉ ነገር አስፈላጊ የሆነው ሰላም ጥላ እያጠላበት መጥቷል። በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ሕዝቦች ሰላምና መረጋጋት እርቋቸው ታይተዋል። የእርስ በእርስ ግጭት በርካቶችን ወደ ችግር እንዲገቡ ምክንያትም ሆኗል። ይህ ደግሞ ሀገሪቱንና ሕዝቦቿን ያልተገባ ዋጋ አስከፍሏል።

ውስን በሆነው የምድር ቆይታችን ለፀብ የሚሆን የሚተርፍ ጊዜ እንደሌለን በመገንዘብ ፍቅርና መተሳሰብን ባህል ለማድረግ ቁጭ ብሎ መወያየት ትርፉ ብዙ ነው። መልካም ዕሴቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸሩ መምጣታቸው፣ ሰላምን በሰላማዊ መንገድ ለማፅናት ፍላጎት ማጣታችን፣ ባልተገቡ ምክንያቶች በሚነሱ ግጭቶች ሳቢያ በርካቶች በሕይወት መኖርን እየሻቱ ላይመለሱ አሸልበዋል።

ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑን በመረዳት እንዲሁም የሰላም ዋጋ ምን ያህል ውድ እና የማይተካ እንደሆነ ግንዛቤ መውሰድ ያስፈልጋል። የእያንዳንዳችን ሰላም እንዲጠበቅ የጎረቤታችንን ሰላም መጠበቅ አለብን። የሰላም ዋጋ ከገባን የእኛ ሰላም እንዲጠበቅ በእኛ ምክንያት የሌሎች ሰላም እንዳይታወክ መጠበቅ፣ ሰላማቸውን እንደ ራሳችን ሰላም አድርገን እየቆጠርን በጥንቃቄ መጠበቅ ከቻልን ምድራችን የሰላም መዲና ትሆናለች። መንደሩም፣ ቀዬውም፣ ከተማውም፣ ሀገሩም ሰላም ይሆናል።

በሰላም መደፍረስ ምክንያት ለሚከሰቱ ችግሮች ቀዳሚ ሰለባ የሚሆኑት አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ሕፃናት፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞች መሆናቸው ሲታሰብ የሰላም ዋጋ ምን ያህል ውድና የማይተካ መሆኑ እሙን ነው። ስለ ሰላም የሚሰብኩ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት ተወካዮች አልያም ግለሰቦች በቅድሚያ ራሳቸው ኖረውት ምሳሌ ሆነው መገኘት አለባቸው።

ዛሬም ከተጣበቀን የኋሊት ጉዞና ከድህነት ቀንበር መላቀቅ የምንችለው ሰላማችንን ስንጠብቅ ብቻ ነው። በርካታ ቁጥር ያለው ኢትዮጵያዊ አነሰም በዛም በሚከተለው ሃይማኖት ስለ ሰላም ይነገረዋል። ያንን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ አለበት። የሀገራችን ሰላም እንዲጠበቅ፣ በሀገሪቱ ሰርተን እንድንለወጥ የሰላም አስፈላጊነትን በአግባቡ መረዳት ያስፈልጋል።

ወቅቱ በጾምና ጸሎት ወደ ፈጣሪ የምንቀርብበት ጊዜ ነው፤ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ለሀገራችን ሰላም አብዝተን የምንጸልይበት ሊሆን ይገባል። በሰላም ጉዳይ ሰፊ ጊዜ ወስደው የሃይማኖት አባቶች ምዕመኖቻቸውን ሊመክሩ ሊያስተምሩ ይገባል።

በርግጥ የሃይማኖት ተቋማት ተገቢውን ትምህርት ለተከታዮቻቸው ማስተማር ሃይማኖታዊ ግዴታቸው ቢሆንም ያንን ማድረግ በቻሉ ልክ ግን ሰላምን በሀገሪቱ ማስፈን ይቻላል። በሰላም ጉዳይ ላይ የእምነት ቤቶች ልዩ ትኩረት ሰጥተው ማስተማራቸው፣ ሕዝቡን ማሰልጠናቸው ደግሞ ሀገራዊ ጠቀሜታው ግዙፍ ነው።

ከየትኛውም ምድራዊ ተቋም በበለጠ የሃይማኖት ተቋማት ስለ ሰላም፣ አብሮ ስለመኖር፣ የሌላውን ሕይወት እንደራስ አድርጎ ስለማክበር፣ ባልንጀራን ስለመውደድ እና ሌሎች ወርቅ የሆኑ አስተምህሮቶችን ማስተማር የየዕለት ሥራቸው ሊሆን ይገባል።

ሰላም ዋጋ የማይተመንለት የችግሮች ሁሉ መፍቻ ቁልፍ ነው። አሁን እየታየ ያለውን መልከ ብዙ የግጭት ጠማቂን በመለየት፣ የሰላም መደፍረስ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ጉዞ እንቅፋት መሆኑን በመረዳት፣ በጦርነትና በብጥብጥ የሚፈታ ችግር አለመኖሩን በማወቅ ግልፅ ውይይት ማድረግ ተገቢ ነው።

ከዚህ አንጻር የመንግሥትና የሕዝብ መወያየትና መደማመጥ ለመልከ ብዙ ችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔ ለማፈላለግ ወሳኝ መሆኑ ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም። ለተሻለ ሰላም ሕዝብና መንግሥት ተደማምጠው መጓዝ ይጠበቅባቸዋል። በቀጣይ ተግባራዊ የሚደረገው ብሔራዊ ምክክርም የዚሁ እውነታ አንድ አካል ነው። የቆዩ ችግሮችንና ቁርሾዎችን ለመፍታት ከመጣር ጀምሮ እንዲህ እንደ አሁኑ ከሕዝብ ጋር መወያየት እጅግ ጠቃሚ የሚያቀራርብ፣ የሚያስተዋውቅ፣ ችግሮችንም ለመረዳትና ለመፍታት የሚያገለግል ነው።

መንግሥት አሁን ላይ ከሕዝቡ ጋር እያካሄደ ያለው የፊት ለፊት ውይይት ችግሮቻችንን በመነጋገር ለመፍታት ትልቅ አቅም ቢሆንም፣ ከዚህ ጎን ለጎን በእየለቱ የሕዝብን ድምፅ መስማት የሚቻልባቸውን መንገዶች ማመቻቸት ተገቢ ነው። የድሮ መንግሥታት ‹‹እረኛ ምን አለ›› ይሉ እንደነበረ ሁሉ የአሁን መንግሥታትም ‹‹ሚዲያው ምን አለ›› የሚል እለታዊ ምልከታና ግምገማ ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህ ደግሞ ለሕዝብ ጥያቄ መልስ መስጠት የማይፈልግ የሥራ ኃላፊንም ለምን ብሎ ለመጠየቅ ያስችላል።

ሰሞኑን በተደረጉ ሀገር አቀፍ ውይይቶች የሕዝብ ድምጾች ተሰምተዋል። መንግሥትም የሚወስደውን ወስዶ የግንዛቤ ችግሮችንም ግልፅ አድርጓል። እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን ማንሳት ተገቢ ነው። የመጀመሪያው ተግባራዊ ምላሽ የሚፈልጉ ጥያቄዎችን ወዲያውኑ መመለስ ሲሆን ሁለተኛው እና ዋነኛው ደግሞ እኛስ እንደ ሕዝብ ምን ማድረግ ይገባናል? ብሎ ለተግባር መነሳት ነው።

አሁን ወቅታዊ የሆኑ የሰላም፣ የኑሮና መሰል ችግሮቻችን እኛው ውስጥ ያሉ/ የውጭ ጠላቶቻችን ባልተገባ መልኩ አራግበዋቸው ይሆናል እንጂ/ ምንጮቹ እኛው የሆንባቸው ናቸው። መነሻው እኛው ከሆንን መፍትሔም እኛው ነን። መፍትሔ ማምጣት ግን ትንሽ ጥረትን፣ ትንሽ ትጋትን ብሎም መስዋዕትነትን ይፈልጋል።

ሌባ ሌላ ሰውን ሲሰርቅ ‹‹ነገ በእኔ ነው›› ብሎ ዛሬ ላይ ከማጋለጥ፣ ሙሰኛና ዘረኛ ባለሥልጣን ሲያጋጥም እስከ መጨረሻው መብትን ለማስከበር ከመታገል ይጀምራል። የውሸት፣ አፍራሽና የጥላቻ የማህበራዊ ሚዲያንም ከማውገዝ እና የሚረጩትን መረጃ ካለማባዛት ይጀምራል። እነዚህንና መሰል ነገሮችን ማድረግ ከጀመርን ነገ ታላቅ ታሪክ መሥራት እንችላለን።

በቅርቡ ሀገራችንን ከመፍረስ ያዳነው እኛው ነን። ትልቁን ነገር ችለን እንዴት ትንሹ ያሸንፈናል? ርግጥ ነው ለሁሉም ነገር ጀማሪ፣ መሪ ያስፈልገዋልና መንግሥት የመጀመሩን ኃላፊነት ወስዷል፤ እኛ ደግሞ እንከተል፤ ያኔ ሀገራችን በሁሉ ነገር ትቀድማለች፡፤

ከኢትዮጵያዊነት ወግና ባህል ያፈነገጡ ጉዳዮችን ሰከን ብሎ ማየት ያስፈልጋል። ሰላም በዋጋ አይተመንም። ሰላም ከምንተነፍሰው አየር ያልተናነሰ ዋጋ አለውና ሁሉም ሰላሙን ይጠብቅ።

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You