በቀጣይ የሴቶችን ቀን ስናከብር …

ዓለማችን እንደየቀለማቸው ብዙ የሚዘከሩ ዕለታት አሏት፡፡ ቅዱሳን ይዘከራሉ፣ ጀግኖች ይወደሳሉ፣ ሊቃውንት ይታወሳሉ፣ ሰማዕታት ይታሰባሉ…፡፡ የነጻነት ቀን፣ የድል ቀን፣ የእናቶች ቀን፣ የአረጋውያን ቀን፣ የላባደሮች ቀን፣ የአርበኞች ቀን፣ የሕፃናት ቀን፣ የሰማዕታት ቀን… ይከበራሉ፤ ይታሰባሉ፤ ይዘከራሉ፡፡

ዛሬ በብዕር ልሳን ‹‹ማርች 8›› ወይም የሴቶች ቀን መች መከበር ተጀመረ? እንዴት መከበር አለበት… ከመሳሰሉ ሃሳቦች ዘለል ብለን የኢትዮጵያውያን ታዳጊና ወጣት ሴቶች እንደነጮቹ ሴቶች ለአደባባይ አንሰናል ከሚል ስሜት ተነስተው ነው ማክበር ያለባቸው? ወይንስ የቀደሙ ኢትዮጵያውያን ጀግኒቶቻቸውን ክብር ማስመለስና እነርሱን አርአያ ማድረግ ነው ያለባቸው በሚለው ላይ ነው፡፡

በርግጥ በእኛ ሀገር ብሒል ‹‹ሴት ለማጀት ወንድ ለችሎት›› የሚል ይህንና መሰል ትርጓሜን ያዘሉ ሃሳቦች አሉን፡፡ ይህ ዓይነት አስተሳሰብ እሾህና አሜኬላ ሆኖ ከመንገድ ያላስቀራቸው ዛሬም ቢሆኑ በርካታ እህቶችና እናቶች በየመስኩ ሞልተዋል፡፡ ማርች 8 በዓለም ላይ የሚከበርበት ዐበይት ምክንያት የወል ሰውነትን መሠረት በማድረግ ሰብአዊነት ሳይጣስ፤ ክብረ ሕሊና ሳይነካ፤ ዕውቀት፣ ክህሎትና ጥበብ በፈቀደ መጠን እኩል ሠርቶ ለመግባት ተወዳዳሪና በልክ መኖርን ለማስፈን የታሰበ መልካም ዕይታ ነው፡፡ ይህ የዓለማችን የጋራ ግንዛቤ ሲሆን በተለየ መልክ ግን የሴቶች ቀንን ተመስርቶ የቀደሙ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ብቃትንና ማንነትን ማየቱ የተሻለ ነው፡፡

በቅርብ ትናንታችን የአንደኛ ዓለም ሀገራት የሚባሉት እንኳ እንደነርሱ የሰው ልጅ የጋራ ኑረት ጅማሮ አስተሳሰብ፣ ከአደንና ፍሬ ለቀማ ዘመናቸው ጀምረው እስከ 19ኛው ክ/ዘ መባቻ ድረስ በዘር፣ በቀለምና በጾታ ጽንፍ የደረሰ አድሎና ልዩነት ነበራቸው፡፡ በዓለም ላይ ትናንትም ቢሆን እኩልነት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ በምልዓት ሲተገበር ኖሯል ማለት አይደለም፡፡ ለዚህም አሜሪካውያን፣ ምዕራባውያን፣ መካከለኛውና ሩቅ ምሥራቃዊያንንም ጨምሮ ከጥንት ጀምሮ ሴቶችን ወደ አደባባይ ያመጡበት ታሪክ አናሳ ነው፡፡

ዛሬ ላይም ቢሆን በእነዚሁ የአደጉ ሀገራት በፖለቲካው፣ በምጣኔ ሀብቱ፣ በወታደራዊ አመራሩ እና በመንግሥት አስተዳደሩ ሥልጣን ላይ ቁንጮ መሆን የወንዶች የበላይነት ሚዛን ይደፋል፡፡ በቀላሉ የዓለማችን ቢሊየነሮች፣ የሀገር መሪዎች፣ ጀነራሎች፣… ወንዶች ናቸው፡፡ ሌላው ቢቀር ጥሩ ዶላር የሚያሳፍሰውን የወጥ ቤትን ሥራ ‹‹ሼፍ›› የሚል የሙያ ቅፅል ይዘው ገበያውን ተቆጣጥረውታል፡፡ ደመወዝ የሌለውን ልጅ ለማሳደግና ቤት ለመምራት የሚያለፋውን ሥራ ‹‹የቤት እመቤት›› በሚል ሽፋን ይታለፋል እንጂ ለአደባባይ የበቁ እንኳን ጥቂት እንስቶች ናቸው፡፡

ዓለም ማርች 8ን ሲያከብር የሚያሳምኑ ነገሮች ስላሉት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን የሴቶች ቀን ማክበር ነው ወይንስ ለዓለም የሚተርፉ ጅግኒቶችን በመዘከርና አርዓያነታቸውን በመከተል ታላቅነታቸውን መጋራት ነው የሚቀድመው? ድፍን ዓለም ከእያንዳንዱ ሀገር አርዓያ የሚሆኗቸውን ሴቶቻቸውን በጋራ ይዘው ቢመጡ እንኳ ኢትዮጵያ ያላትን ያህል የጎላ ተጽእኖ ፈጣሪ ያላቸው አይመስልም፡፡

ለምሳሌ ያህል አብነት የሚሆኑንን ጥቂቶችን ከምናስታውሳቸው፤ ንግሥት ካሶፒን እናገኛለን፡፡ ይህች ንግሥት የዓለም ሴቶች በከዋክብትና በፕላኔት፣ በፀሐይና በጨረቃ መካከል ያላቸውን መሠረታዊ ልዩነቶች በቅጡ ሳይረዱ ወደሰማይ በማንጋጠጣቸው ብርሃንና ሙቀትን ከመጠቀም ሳይዘሉ፤ እርሷ ግን የከዋክብትን አሰላለፍ ከነሠራዊታቸው ታጠና፣ ትመረምርና ትራቀቅ ነበር፡፡ ለዚህም ብቃቷ ስሟን በታሪክ የወርቅ መዝገብ አስከትባለች፡፡

ሌላዋ ደግሞ ከክርስቶስ ልደት ከ1000 ዓመታት በፊት የዛሬ 3000 ዓመት ላይ በዓለም ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ኢትዮጵያዊት ንግሥት ተከሰተች፡፡ ታላቁ መጽሐፍ ንግሥት አዜብ ይላታል፡፡ ይህች ፈርጥ ታላቋን ኢትዮጵያን ታስተዳድር፣ ትመራ ነበር፡፡ በሀብቷም ወደር የማይገኝላት ነበረች፡፡ ንጉሥ ሰለሞን በዘመኑ ከተቀበለው ስጦታ የንግስተ አዜብን ያህል የሰጠው እንደሌለ በታላቁ መጽሐፍ /በመጽሐፍ ቅዱስ / ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ በዕውቀቷም ቢሆን እንደዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እምነት የንግሥተ አዜብን ያህል ሴት አዋቂ ዓለም አላስገኘችም ብሎ ያምናል፡፡

ምክንያቱም ጠቢቡ ሰለሞን ከርሱም በፊት ሆነ ከርሱም በኋላ እንደርሱ ያለ ጠቢብ አይነሳም ተብሎለታል፡ ፡ ታዲያ ይህን ከሰው ልጆች በጥበቡ ልዩ የሆነውን ሰው በእንቆቅልሽ ፍልስፍናዋ ልትፈትነው መቻሏ ከርሷም በፊት ከርሷም በኋላ እንደርሷ ያለ ጠቢቡን የምትፈትን ሴት ዓለም አታስገኝም ማለት የሚቻል ሥነ አመክንዮ ይመስላል፡፡ በመልኳም ቢሆን ንጉሡ ሕጋዊ ሚስቶችና ቆነጃጅት ዕቁባቶች በብዙ አኀዝ ቢኖሩትም በውበቷ ልቡን አርዳዋለች፡፡ እንደ እንግዳ ብቻ ተቀብሎ አልሸኛትም በማኅጸኗ ዘር ቋጥሮ ቀዳማዊ ምኒልክን በርሷ በኩል ሰጥቶናል እንጂ፡፡

ልክ እንደ ሁለቱ ፈርጦች እንደ ከዋክብት በደመቁ ሥራዎቻቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ እንስት ኢትዮጵያውያን አሉን፡፡ እንደ እቴጌ ሰብለ ወንጌል፣ እንደ እቴጌ ምንትዋብ፣ እንደ እቴጌ ጣይቱ፣ እንደ ባለቅኔዋ ሊቅ እማሆይ የቅኔ ወንበር ዘርግተው ያስተማሩ ፣ እንደ የሙዚቃ ፈርጧ እማሆይ ጽጌ ማርያም እንዲሁም ከአፍሪካ እስከ ሩቅ ምሥራቅ ያሉ ሀገራትን ያስተዳደሩ የንጉሥ እንደራሴ ሕንደኬዎች ሞልተዋታል፡፡

በቅርቡ 100 ዓመታት ውስጥ እንኳን ከተዘመረላቸው እስካልተዘመረላቸው ሀገር ያፈራቻቸው አርበኞች፣ ምሁራን፣ የሳይንስና የኪነ ጥበብ ሰዎቻችን ያሉን ፈርጦች ቀላል የሚባሉ አይደሉም፡፡ ሌላው ቢቀር እንደ ኢትዮጵያዊ እናቶቻችን ጀግንነት ልናይ እንችላለን፡፡ ልጅ ያሳደጉበትና መልካም ሰው ለማድረግ የለፉበት ጥበብ፣ ቤት ያስተዳደሩበት ብቃት፣… ዋጋው ስንት ይሆን? የትኛው ጀግንነት ይመልስውና ይክሰው ይሆን? ይህን ያህል አርዓያነትና ታላቅነት እንዴት ችላ ይባላል? ከዚህ አንጻር የእናት መታሰቢያ ቀኗ ስንት ይሆን?

የሴቶችን ቀን ሌሎች ቢያስቡት ስለፍትሐዊ ዕድልና እኩልነት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ዛሬ ላይ ከጀግኖቻቸው ተናጥበው እንጂ ሴትን ማግነንና ለአደባባይ ማብቃት ለኢትዮጵያውያን አዲስ አይደለም፡፡ ከቀሽም እዬዬ በመላቀቅ የትናንቶቻችንን ሴቶችና ሥራዎቻቸውን ወደፊት ብናመጣና ዛሬም በፈርጦቻችን ላይ ማጌጥ ቢቻል ቀኑን በእጥፍ ማክበር ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ሴቶች ሀገር የሰሩ፣ ዳር ድንበር የጠበቁ፣ በጥበባቸው ዓለምን ያስደመሙ… እንደሆኑ ታሪክ ዘግቦ አስነብቦናል፡፡

ዛሬ አብዛኛው ወጣት ኢትዮጵያውያን ሴቶች የአርዓያነት መንገድ ምን ይመስላል ቢባል መልሱ ቀላል ነው፡፡ የአሜሪካውያንና የአውሮፓውያን የሲኒማውና የሙዚቃው ኢንዱስትሪ፣ የፋሽንና የስፖርቱ ዓለም ሰዎች ልቦናቸውን ሰልቧቸው ራሳቸውን አብነት የሚሆኑ ጀግኒቶችን አስረስቷቸዋል፡፡ ትኩረታቸውም የነጮቹ የአልባሳት ቅዳቸው፣ የጸጉር ስታይላቸው፣ የፊት ቀለማቸው፣ የቋንቋ ቅላጼያቸው፣ የአረማመድ ቄንጣቸው፣ የአምልኮ ትሩፋታቸው… በአጭሩ የዕለት ተዕለት የኑሮ ዘይቤያቸውን ክፉና ደጉን ሳይለዩ ሾላ በድፍን መከተል ሆኗል፡፡ በዚህ ከብዙ መልካም ሃሳቦችና ጥበባት ከሀገር ልጆች ምሳሌዎቻቸው ተናጥበው ይታያሉ፡፡

ጥንትም ሆነ ዛሬም አብነት የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ግን አሉታዊ ትርጓሜ ያላቸው ብሒሎችና የማኅበረሰብ ሥርዓቶችን ተገዳድረውና አልፈው ለሁሉ የሚተርፍ ሰብእናን ገንዘብ አድርገዋል፡፡ ከዓለም ሴቶች ቀድመው ከወንድ እኩል መሆን ስላሳዩን ወደ ራስ ሰው መመለስና አብነት አድርጎ መኖር መልካም ዕድል ነው፡፡ ዛሬም በተለያዩ ተጽዕኖዎችና በግንዛቤ ማነስ እና በፍትሕ ማጣት ጭምር ሴቶች /እናቶች፣ እህቶችና ሕፃናት/ ላይ የሚያጠይም ድርጊትና ሃሳብን ሁሉም በአንድ እጅ ሊታገል ይገባል፡፡

በይበልጥ ግን የአርዓያነት ድርሻ ያለባችሁ የተለያዩ የሕይወት ተግዳሮቶችን ሰንኮፍ መንግላችሁ የጣላችሁና ሕልማችሁ ላይ የደረሳችሁ በተለያዩ የሙያ መስክ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ያላችሁ ሴቶች ግድ ይላችኋል፡፡ ለዚህም ታዳጊና ወጣት ሴቶችን ከሕይወት ልምዳችሁ፣ ካለፋችሁበት ውጣ ውረድ፣ ከደረሳችሁበት ስኬት … ልታስተምሯቸውና የሕይወትን መንገድ ልትጠቁሟቸው ይገባል፡፡ ‹ሴትን ማስተማር ቤተሰብን ማስተማር ነው › ይባላልና የሕፃናትን መሪ መንገድ ጠቋሚ ዕውቀት ለጋሽ፣ ተስፋ ሰጪ… የሆኑ እናቶችንና እህቶችን ማፍራት ከምንም በላይ መልካም ሀገርና ዜጋን መገንባት ነው ፡፡ ለእንዲህ አይነት ሕልም በመኖር ማርች 8ን ማሰብ አብዝቶ ማትረፍ ነው፡፡

መኩሪያ አለማየሁ

አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2016 ዓ.ም

Recommended For You