የአለም የጤና ድርጅት ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፤በአለም አቀፍ ደረጃ ከ450 ሚሊዮን በላይ የአእምሮ ህሙማን ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል። 25 በመቶ የሚሆነዉ የአለም ህዝብ በህይወት ዘመኑ ቢያንስ አንድ ጊዜ ከቀላል እስከ ከባድ ደረጃ ባለው የአእምሮ ጤና ችግር ይጠቃል።
በኢትዮጵያ የተደረጉ ጥናቶችም እንደሚጠቁሙት፤ እስከ 17 በመቶ የሚደርሰዉ የአገሪቷ ህዝብ በተለያዩ የአእምሮ ጤና ችግሮች እየተሰቃየ ይገኛል። ህክምናውን በሀገሪቱ እየሰጠ ያለው ሆስፒታል አንድ መሆኑ ደግሞ ችግሩን ውስብስብ አድርጎታል።
የአማኑኤል ሆስፒታል በ1930 ዓ.ም በጣሊያን ወረራ ወቅት ነበር። ለአካባቢው ነዋሪዎች አጠቃላይ የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተመሰረተ ነው። ከአምስት አመት በኋላ የኢጣሊያ መንግስት ሀገሪቷን ሲለቅ የአዕምሮ ጤና ችግር ያለባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ማቆያ በመሆን እንዲያገለግል ተደርጓል።
ሆስፒታሉ ለአእምሮ ህክምና ብቸኛ በመሆኑና የሚያስተናግዳቸው ተገልጋዮች ቁጥር ከአመት አመት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲመጣ አገልግሎቱን በሚፈለገው መልኩ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ አስቸጋሪ አድርጎበታል።
የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኢዳኦ ፈጆ እንደሚናገሩት፤ ሆስፒታሉ ከፍተኛ የሆነ የመሰረተ ልማት እጥረት አለበት። በዚህም የተነሳ በአንድ ክፍል ውስጥ ሁለት ባለሙያዎች በተመሳሳይ ሰአት ህክምና ለመስጠት የተገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ሆስፒታሉ በቀን ከሀምሳ ያላነሱ ደንበኞችን ለማስተናገድ ስለሚገደድም ጥራት ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እየተፈጠረበት ይገኛል። ሆስፒታሉ ባለው 300 አልጋ ማስተኛት ከሚችለው በላይ ደንበኞች በመምጣታቸዉ ለአልጋ ወረፋ አንድ ሰው እስከ 17 ቀን ለመጠበቅ ይገደዳል።
የሆስፒታሉ ግቢ የተጨናነቀና ለህክምና አሰጣጥ የማይመች መሆኑ እንዲሁም የተሃድሶ ህክምና ለመስጠት በቂ ቦታና ክፍሎች ያለመኖር አጠቃላይ የህክምና ሂደቱን የተወሳሰበ እንዳደረገው ይገልፃሉ።
በሚያዚያ 2002 ዓ.ም መሰረቱ ተጥሎ በ2009 ዓ.ም ወደስራ የገባውና ለማስፋፊያ የተገነባውም የካ ኮተቤ ሆስፒታል ለህሙማን ምቹ የማገገሚያ ቦታ ስለሌለው ሙሉ አገልግሎት
እየሰጠ ነው ለማለት የማያስደፍር መሆኑን ይጠቁማሉ። የማስፋፊያ ስራዎችን ለመስራት በጤና ጥበቃና በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ስምምነት ላይ የተደረሰ ቢሆንም ሆስፒታሉ አሁን ያለበት ቦታ ለማስፋፋት ምቹ አይደለም። ያሉት ስራ አስኪያጁ አሁን ባለበት ቦታ ይገንባ ከተባለ ሆስፒታሉን ስራ አቁሞ ሙሉ ለሙሉ ማፍረስ የሚሰጠውንም ህክምና ማቆምን ይጠይቃል ነው የሚሉት። በመሆኑም በ2012 ምቹ የሆነ ለማገገሚያ የሚያገለግል መናፈሻ ያለው ዘመናዊ ሆስፒታል ለመገንባት ቦታ እየተፈለገ እንደሆነም ይጠቁማሉ።
በሆስፒታሉ የምርምርና ስልጠና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ክብሮም ሀይሌ በበኩላቸው ህመምተኞች የሚመጡት ከመላው ሀገሪቱ እንደመሆኑ አዲስ አበባ ላይ ያለውን በማስፋፋት ብቻ ችግሩ ሊቀረፍ ስለማይችል ወደ ክልሎችም ትኩረት ማድረግ ይገባል ይላሉ።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በግል የህክምና ተቋማት አገልግሎቱን የሚሰጡ ቢኖሩም የስነ ልቦና አገልግሎት ከመስጠት ያለፈ ስራ አይሰሩም። አብዛኛዎቹ ለህመምተኞች የሚሆን አልጋ እንዲኖር አይፈልጉም፤ አልጋውን አንድ ሁለት ያዘጋጁ ቢኖሩም መፀዳጃ ቤትና ሬሳ ክፍል አካባቢ ያደርጉታል።
እንደ መንግስትም በአዲስ አበባ ባሉት አስራ አንድ ሆስፒታሎች በእያንዳንዳቸው አስራ ሁለት አልጋ እንዲኖር በስትራቴጂ የተቀመጠ ቢሆንም፣ የተገበረው ግን የለም። የፀበል ቦታዎች ሆስፒታሎች ከሚይዟቸው በብዙ እጥፍ የበለጠ ይዘዋል። በመሆኑም በእነዚህ ስፍራዎች ላይ ዘመናዊ አገልግሎት መስጫ ቢቋቋም ችግሩን ለመቅረፍ ትልቅ ፋይዳ አለው። ከዚህ ቀደም በእንጦጦ ማርያም ተጀምሮ ውጤታማ የሆነ ስራ ነበር በመሆኑም ከሀይማኖት አባቶች ጋር በመሆን በዚህ በኩል የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉ ያብራራሉ።
በሆስፒታሉ የአእምሮ ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ዮናስ ላቀው ህክምናው ትኩረት አላገኝም ፤ በአሁኑ ወቅት ወደ ህክምና ተቋም ከሚመጡት የአእምሮ ህሙማን መካከል ከፍተኛ ቁጥር የሚይዙት ጽኑ የአእምሮ ህመም የገጠማቸው ናቸው፤ እነዚህም ከአስር በመቶ አይበልጡም ይላሉ።
እንደ ዶክተር ዮናስ ገለጻ፤ ህብረተሰቡ ለበሽታው ያለው ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ ከፅኑ የአእምሮ ህመም ወጪ ያሉትን በሽታዎች እንደ ችግር አያያቸውም። በመሆኑም ህመምተኞች በችግር ውስጥ ለመኖር ብቻ ሳይሆን ለከፋ ነገርም እየተጋለጡ ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ በአመት ከሰባት ሺ በላይ ሰዎች በዚህ በሽታ ራሳቸውን እንደሚያጠፉ ጥናቶች ያሳያሉ የሚሉት ዶክተር ዮናስ፣ ይሄ ትኩረት ያልተሰጠው ስለመሆኑ አንድ ማሳያ ይሆናል ይላሉ። ‹‹በሽታው ትኩረት ያጣው ግን በማህበረሰቡ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በህክምና ባለሙያዎችም ነው።
አንዳንድ ጊዜ የአእምሮ ህመም ያለባቸው ታካሚዎች ተደራቢ እንደ ስኳር፤ ቀዶ ጥገና፣ ወሊድና ከወሊድ ጋር የተያያዙ ችግር ገጥሟቸው ወደ ሌላ ሆስፒታል ሲላኩ ለመቀበል የሚያንገራግሩና ጨርሶም አንቀበልም የሚሉ በርካታ ናቸው።››ሲሉ አብራርተው፣ግንዛቤ የመፍጠሩ ስራ ማህበረሰቡ ላይ ብቻ ሳይሆን ባለሙያውም ላይም ማተኮር እንደሚኖርበት ያመለክታሉ።
በቤተሰብ ደረጃም ሆነ እንደ ማህበረሰብ የበሽታዎቹን ምልክቶች ማወቅ ሊደረግ ለሚገባው እንክብካቤ ይጠቅማል ሲሉ በሆስፒታሉ የአእምሮ ስፔሻሊስት ሀኪምና ሳይካተሪስት ዶክተር መሀመድ ንጉሴ ይገልጻሉ።
እንደ ዶክተር መሀመድ ማብራሪያ፤ እንደ አጠቃላይ የእእምሮ ህመም ማለት አንድ ሰው በእለት ተእለት እንቅስቃሴው ላይ ተፅእኖ የሚፈጥሩ በአስተሳሰብ ባህሪና በስሜት ላይ የሚፈጠሩ ችግሮች ማለት ነው።
157 ከሚደርሱ የአእምሮ ህመም አይነቶች መካከል በልጆች ላይ የሚስተዋሉት የእእምሮ እድገት ውስንነትና ኦቲዝም በመጥቀስ ሲያብራሩ፣ ሁለቱም ህመሞች ከአእምሮ እድገት መወሰን ጋር የሚያያዙ መሆናቸውን ይገልጻሉ።በልጆች ላይ የሚስተዋሉና በጨቅላነት የሚፈጠሩ ችግሮች መሆናቸውን አመልክተው፣ ሁለቱም ተያያዥነት ያላቸው በመሆናቸውም የአእምሮ ችግር ያለበት ኦቲዝም፤ ኦቲዝም ያለበትም የአእምሮ ችግር ሊኖርበት ይችላል ይላሉ።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤የአእምሮ እድገት ውስንነት ሲኖር ህመምተኛው ላይ ከሚደርሱ ችግሮች መካከል በትምህርትና በስራ ውጤታማ አለመሆን፤ የማገናዘብና ችግሮችን ለመፍታት ቀልጣፋ አለመሆን፤ የማቀድና ውስብስብ ሀሳቦች ላይ ደካማ መሆን እንዲህም አካላዊ እንቅስቃሴ /ልብስ የመልበስ ጫማ ማድረግ /በተወሰነ መልኩ መገደብ ይታያል። ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ የአእምሮ አድገት ውስንነት ሲሆን ድግሞ የፊት ገፅታ ከተለመደው ለየት ሲል በማየት ሊለይ ይችላል፤ ቀላል ደረጃ ያለባቸው የሚለዩት ደግሞ በትምህርት ላይ በሚታይ ችግሮች በተለይ ስድስተኛ ክፍል ሲደርሱ ነው።
ኦቲዝም ሲሆን ደግሞ ቃለ ምልልስ ማድረግ ፣ የገፅታ በአካል ምላሽ (በአካባቢያቸው ያለ ሰው ሲቆጣ ሲደሰት ያለመለየት) ግብረገብነት መጓደል፤ የሚደጋገሙ እንቅስቃሴዎችን ማዘውተር፤ በአካባቢያቸው ለውጥ ሲኖር እንዲሁም ለተወሰኑ ድምፆችና እንቅስቃሴዎች የመረበሽና ስሜታዊ ምላሽ መስጠት፤ ቃላት መደጋጋም፤ ጓደኛ ያለማፍራት፤ ከእኩዮቻቸው የመለየት ብሎም ከማህበረሰቡ ጋር መግባባት ላይ ደካማ መሆን ይታይባቸዋል።
ኦቲዝም በአብዛኛው የሚለየው ከአምስት አመት በኋላ ሲሆን ሁለቱም በሽታዎች መኖራቸው በትክክል የሚታወቀው በምርመራ ብቻ ነው። በሁለቱም በሽታ የተያዙ ሰዎች ራሳቸውን መከላከል ስለማይችሉ ለአካላዊና ፆታዊ ትንኮሳም በስፋት የተጋለጡ መሆናቸው ዋናው ችግር ነው።
የእነዚህ በሽታዎች መነሻ በትክክል ተለይቶ ባይታወቅም በእርግዝና ግዜ የተመጣጠነ ምግብ ባለመመገብና፤የምግብ ማቅለሚያ ኬሚካሎች በብዛት መጠቀም፤ ለሱስ ተጋላጭ መሆን፤ እናት ላይ ያሉ ኢንፌክሽኖች መነሻ ምክንያቶች ናቸው። ከዘህ በፊት የችግሩ ተጠቂ ቤተሰብ ካለ በዘረ መል በመተላለፍ፤ በወሊድ ወቅት የአተነፋፈስን ችግር ጨምሮ ተፈጥሮ ከነበረ፤ ድህረ ወሊድ ደግሞ ማጅራት ገትርና አንዳንድ አደጋዎች ጋር ተያይዞ እንዲሁም የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘትና በዘር ሊከሰቱ ይችላሉ ተብሎ ይገመታል።
ችግሩ በእርግዝና ወቅት የተከሰተ ከሆነ በህክምና ለመመለስ አዳጋች እንደሚሆን ዶክተር መሀመድ ይገልጻሉ። በወሊድ ወቅትና ድህረ ወሊድ ከሆነ ግን ያሉትን ህመሞች ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት በማድረግ በተለይ በእርግዝና ወቅት የአንጎል አድገትን ለማሻሸል የሚረዳውን ፎሊክ የተባለውን መድሀኒት በመውሰድ መከላከል የሚቻልበት እድል አለ ይላሉ።
ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ግን ቀላልና መካካለኛ ለሚባሉት ለአንዳንዶቹ ብሄቪራል ቴራፒ የሚባል ህክምና ሊሰጣቸው እንደሚችል ጠቅሰው፣ በዚህም እያደጉ ሲሄዱ እንደ ማንኛውም ሰው ራሳቸውን ችለው የሚኖሩበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ይላሉ።
በጣም ከባድ ለሆነው ግን ህክምናው ከበድ የሚልና ረጅም አመታትን ሊወስድ የሚችል መሆኑን ጠቅሰው፣የስነልቦና ህክምናና የባህሪ ለውጥ ህክምና እንደሚሰጥም ያመለክታሉ። የሙዚቃ፤ የስፖርት፤ የእደጥበብ ቴራፒዎችም እንዳሉ ይጠቁማሉ።
እንደ ዶክተር መሀመድ ገለጻ፤ግልፍተኛ እና ቁጡ የሆኑት ለሌሎች የአእምሮ ህመሞች ተጋላጭ የመሆን እድል ስላላቸው የመድሀኒት ህክምና ሊሰጣቸው ይችላል። ማህበረቡ ከፍተኛውን እንጂ መካከለኛውንና ዝቅተኛውን የህመም ደረጃ አይለየውም፤ ቢለይም ከህክምና ይልቅ ወደ እምነት ተቋማት የመውሰድ፤ አንዳንዶች ደግሞ ወደ ህክምና ተቋማት ቢወስዱም በፍጥነት ለውጥ ስለማይታይ ተከታትሎ አለመጨረስ ይስተዋላል።
ሳይንሳዊውንም ህክምና አብሮ ማስኬድ ከተቻለ ወደሀይማኖት ተቋማት መሄዱ ጥቅም አለው ዶክተር መሀመድ፣ ዋናው በስፋት የሚስተዋለው ችግር ግን ሀኪም ቤትም የሀይማኖት ተቋምም ሳይሄዱ እቤት ሲቀመጡ ነው ይላሉ።
እንደ ዶክተር መሀመድ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ የተካሄደ የታማሚዎችን ቁጥር የሚለይ ጥናት ባይኖርም እንዳጠቃላይ ከአንድ እስከ ሁለት በመቶ የሚሆኑ ልጆች በኦቲዝም ይጠቃሉ ተብሎ ይገመታል። ከአእምሮ ውስንነት ጋር በተያያዘ ደግሞ እስከ አራት በመቶ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።
በእነዚህ በልጆችና ታዲጊዎች የአእምሮ ጤና ህክምና ላይ የሚሰሩ እንደ ጆይ የኦቲዝም ማእክል ያሉ የተለያዩ ማገገሚያዎች እንዳሉም ጠቅሰው፣ በመንግስት ስር ያለና ይሄንን የሚሰራ የካቲት አስራ ሁለት ሆስፒታል ብቻ መሆኑን ያመለክታሉ። በባለሙያ በኩልም በርካታ የስነ ልቦና ባለሙያዎች ቢኖሩም እስከ አሁን በቻይልድ ኤንድ አዶለሰንስ ሳይካትሪ ላይ የአእምሮ ህክምና ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ባለሙያ ግን አንድ ብቻ እንደሆኑ ዶክተር መሀመድ ተናግረዋል።
የአማኑኤል ሆስፒታል በ1970 ዓ.ም በአድቫንስድ ዲፕሎማ ደረጃ የጀመረውን የምርምርና ስልጠና አገልግሎት በማስፋፋት በጎንደር፣ መቀሌና ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ በዲግሪ ትምህርት እንዲጀምሩ አስችሏል። በአሁኑ ወቅት ትምህርቱ በአስር ዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ ሲሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስተቀር ትምህርቱን የሚሰጡት ከሆስፒታሉ የተመረቁ ባለሙያዎች ናቸው። በተጨማሪም ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በክሊኒካልና የማህበረሰብ ሳይካትሪ የማስተርስ ዲግሪ እየተሰጠ እንደሚገኝ ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ