በአሁኑ ዘመን በትምህርት ጥራት መስፈርት መሰረት ጥራት ያለው ትምህርትን ለተማሪዎች መስጠት የሚቻለውና ተማሪዎች ጥራት ያለው ትምህርት የማግኘት መብታቸውን የሚያረጋግጡት ከጎበዝ መምህር ብቻ አይደለም። ከመማሪያና ማመሳከሪያ መጻሕፍት ብቻም አይደለም። ወይም ደግሞ ከሁለቱም ብቻም አይደለም። በርትቶ ከማጥናት ብቻም አይደለም፤ ተማሪዎችም ሆኑ የትምህርት ተቋማት ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉት ከመማር ማስተማር ከባቢም ጭምር ነው።
ከዚህ አኳያ ሲታይ በትምህርት ሚኒስቴር “አምስተኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት መርሃ ግብር” (2008-2012 ዓ.ም) ሰነድ ላይ እንደተገለፀው ከ92 በመቶ በላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መፀዳጃ ቤት እንዳላቸው የገለፁ ሲሆን 60 በመቶ ያህሉ ግን የውሃ አቅርቦት የላቸውም። ከጠቅላላዎቹ 20 በመቶ ብቻ ክሊኒክ ሲኖራቸው፣ የትምህርት ማበልፀጊያ ማዕከል ያላቸው ግማሾቹ ብቻ ናቸው፡፡ በስምንት ክልሎች ለመጀመሪያ ጊዜ በ2006 ዓ.ም የተካሄዱት የውስጥ ኢንስፔክሽኖች እንደሚያሳዩት የሁኔታዎች መሻሻል የታዩ ቢሆንም በአጠቃላይ ግን ትምህርት ቤቶቹ ያሉበት ሁኔታ ከሚጠበቀው በታች ነው፡፡
ይኸው ሰነድ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ጥራት ያለው አካባቢና ትምህርት ማሟላት እንዲቻል ስልታዊ ዕቅድ ማዘጋጀት እንደ ሚኖርባቸው ጠቁሟል፡፡ እያንዳንዱ የትምህርት ቤት ማሻሻያ እቅድ ውጤታማ የትምህርት ቤት ፋሲሊቲዎች ከማሟላትና ጥሩ የትምህርት አካባቢ ለመፍጠር ከማቀድ በዘለለ መሄድ እንዳለበትም ጠቅሷል፡፡ የትምህርት ቤት ማሻሻያ እቅድ ዋናና መሰረታዊ ክህሎት ለተማሪዎች በብቃት መስጠቱን ማረጋገጥ እንዳለበትም አብራርቷል፡፡
ሌሎች እንዳሉ ሆኖ ይህንን በተግባር ስራ ላይ አውሎ የታየው የትምህርት ተቋም ቢኖር አፍሪካ አንድነት ቁጥር 2 የቅድመ አንደኛ ደረጃ (ከኬጂ 1 እስከ ኬጂ 3) እና አንደኛ ደረጃ (ከ1ኛ እስከ 8ኛ) ትምህርት ቤት ነው። ከትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አክሊሉ እሸቱ ጋር ያደረግነው ቆይታም የሚነግረን ይህንኑ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ጋር በመሆን የአፍሪካ ከንቲባዎች የሊደርሺፕ ኢኒሼቲቭ (AMALI) ተሳታፊዎችን አፍሪካ አንድነት ቁጥር 2 የቅድመ አንደኛ ደረጃ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ማስጎብኘታቸውን ርዕሰ መምህር አክሊሉ ነግረውናል። “ጉብኝቱ በዋናነት በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የቀዳማይ ልጅነት ፕሮጀክት አተገባበር ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በማየት ፕሮግራሙን በቀጣይነት ለመደገፍ እንዲቻል ታስቦ የተካሄደ ነው፡፡
የጉብኝቱ ተሳታፊዎች በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ በመዘዋወር የሕጻናቱን የመማሪያ፣ የመጫወቻ እና የማሸለቢያ ክፍሎች፣ መጎብኘታቸውንም በወቅቱ ከወጡ መረጃዎች ለማወቅ ችለናል። የአፍሪካ ሕብረት አዲስ አበባ መመስረትን ተከትሎ በተቋቋመውና ስያሜውንም ከዚሁ ጋር በማያያዝ የተሰየመው አፍሪካ አንድነት ቁጥር 2 የቅድመ አንደኛ ደረጃ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በትምህርት አመራሮች አማካኝነት አዲሱን ስርዓተ ትምህርት መሰረት አድርጎ የተዘጋጀውን የቅድመ አንደኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ለከተማው ትምህርት ቢሮ ሱፐርቫይዘሮች የማስተዋወቅ ስራ መሰራቱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህም በትምህርት ቤቱ ተገኝተው ተቋሙን በመጎብኘት አድናቆታቸውን መግለፃቸውን ርዕሰ መምህር አክሊሉ ነግረውናል። አፍሪካ አንድነት ቁጥር 2 የቅድመ አንደኛ ደረጃ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስለ ውጤታማነቱ የተመሰከረለት መሆኑን የሚናገሩት ርዕሰ መምህሩ “የአንድ ተቋም መመዘኛ በአብዛኛው በብሄራዊ ፈተናዎች በሚያሳልፋቸው ተማሪዎች ሲሆን በዚሁ መነሻነት ትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ በዘንድሮው የአንደኛው ወሰነ ትምህርትም 98 ነጥብ 8 በማምጣት ውጤታማነቱን አሳይቷል፡፡
ከተገልጋይ እርካታ አኳያም አፍሪካ አንድነት ቁጥር 2 የሚያስመሰግን ውጤት ማግኘቱን ከርዕሰ መምህሩ ቢሮ የተገኙ መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን፣ የ2015 ዓ∙ም የአንደኛ ሩብ ዓመት የውስጥ 98 ነጥብ 6 ከመቶ እና የውጭ 97 ነጥብ 4 ከመቶ፤ እንዲሁም የተመሳሳይ ዘመን ሁለተኛ ሩብ ዓመት የውስጥ 98 ከመቶ፤ የውጪ 98 ነጥብ 2 ከመቶ የተገልጋይ እርካታ ዳሰሳ ትንተና ውጤቶች ማሳያዎች ናቸው።
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ታህሳስ 2016 ዓ.ም “ፅዳቱ የተጠበቀ የመማሪያ ስፍራ፣ ለመማር ማስተማር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል” በሚል መሪ ቃል የአምስት ወራት ሳምንታዊ የፅዳት ንቅናቄ ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር በክፍለ ከተማው ወረዳ አራት በሚገኘው በኡላዱላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አካሂዷል፡፡ “ጽዱና ውብ ትምህርት ቤት ለተማሪዎች!” በሚል መሪ ቃል የጽዳት ንቅናቄ ፕሮግራም አካሂዷል፡፡
አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ለምሳሌ በጉለሌ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 7 አስተዳደር ስር የሚገኘው “ሐምሌ አስራ ዘጠኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት” እና ሌሎችም አፍሪካ አንድነት ቁጥር ሁለትም እንደዚሁ የፅዳት ፕሮግራሞች አሏቸው። ተማሪዎቹ ምንም አይነት ቆሻሻን በጊቢ ውስጥ ላለመጣል፤ ተጥሎም ካገኙ አንስቶ ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ በመጣል ለትምህርት ቤቱ ፅዱና ማራኪነት የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ርዕሰ መምህር አክሊሉ ይናገራሉ።
የሥነ-ትምህርት ባለሙያዎች የሚሰጡት ትምህርት ውጤታማ እንዲሆን፤ የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ፤ የተማሪዎች ስነ-ምግባር እንዲሻሻል፤ ሁለንተናዊ የመማር-ማስተማር ስራው የላቀ ደረጃ ላይ እንዲደርስ በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት አመራሮች ተከታታይነት ያለው ድጋፍና ክትትል በማድረግ በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው መምህር አክሊሉ ያሰምሩበታል። ከዚህ አኳያ የአፍሪካ አንድነት ቁጥር ሁለት የቅድመ አንደኛ ደረጃ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በየደረጃው ያሉ ሁሉ ለትምህርት ጥራት ይበጃል ያሉትን እየሰሩ እንዳሉ በርዕሰ መምህሩ ከመገለፁ በተጨማሪ እኛም ተዘዋውረን ተመልክተናል።
1 ሺህ 653 ተማሪዎችን የሚያስተናግደው ይህ ትምህርት ቤት አመራሮችና መምህራን ከተማሪና ወላጅ አደረጃጀት ጋር የቅርብ ግንኙነት በመፍጠር በ“ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ“ የተጀመረውን የትምህርት ተቋማትን ደረጃ የማሻሻል ስራ ውጤታማ እንዲሆን በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውንም ርዕሰ መምህሩ ይናገራሉ።
የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ወደ መንግሥት እንዲዛወሩ በሚደነግገው አዋጅ መሰረት ከ2005 ዓ∙ም ጀምሮ ወደ መንግሥት ትምህርት ቤትነት በተዛወረው፣ በአፍሪካ አንድነት ቁጥር ሁለት የቅድመ አንደኛ ደረጃ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደረጃውን የጠበቀ “ሁለ-ገብ” የስፖርት ማዘውተሪያ መገንባቱን የተናገሩት ርዕሰ መምህር አክሊሉ፤ የግንባታው ወጪ የተሸፈነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “መደመር“ መጽሐፍ ጭያጭ ከተገኘው ገቢ መሆኑንም ገልፀዋል።
በፊት ነበር እንጂ አሁን በአብዛኛው የግብአት ችግር የለብንም የሚሉት ርዕሰ መምህር አክሊሉ እሸቱ፤ በትምህርት ቤቱ በሁለት ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ እና አፋን ኦሮሞ ትምህርቶቹ የሚሰጡ ሲሆን በአፋን ኦሮሞ በሚሰጡ የትምህርት አይነቶች በኩል የተወሰነ የግብአት እጥረት እንዳለም ይናገራሉ።
አፍሪካ አንድነት ቁጥር ሁለት የቅድመ አንደኛ ደረጃ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅድመ መደበኛ ትምህርትንም የሚሰጥ ተቋም እንደ መሆኑ መጠን ጥራቱን የጠበቀ፤ ለሌሎች በምሳሌነት ሊቀርብ የሚችል፤ ፅዳቱ የተሟላና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን መስፈርት ባሟላ መልኩ ሕፃናትን (ከኬጂ 1 እስከ ኬጂ 3) እያስተማረ ይገኛል።
ኬጂ 1 እና 2 ተማሪዎች ያማረ ምንጣፍ ላይ እንደ ፈለጋቸው፣ ተገቢ ባለሙያ ተመድቦላቸው እየተንከባለሉ የሚያነቡ፣ የሚፅፉና የሚጫወቱ መሆናቸው የተነገረንና እኛም የተመለከትን ሲሆን፤ ከምሳ በኋላም ለአንድ ሰዓት ያህል የእንቅልፍ ሰዓታቸውን የሚያሳልፉበት ያማረ መኝታ ክፍል ከተሟላ ፍራሽና ትራስ ጋር መሰናዳቱን ተመልክተናል። ይህም በራሱ ሌሎች ሊወስዱት የሚገባ ተሞክሮ ነው፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተቋሙን በጎበኙበት ወቅት “በአዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት ቁጥር 2 ቅድመ አንደኛ፣ የመጀመሪያ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ለሌሎችም ትምህርት ቤቶች ተሞክሮ የሚሆኑ ናቸው። በማለት ምስክርነታቸውን የሰጡለት አፍሪካ አንድነት ቁጥር 2 ቅድመ አንደኛ፣ የመጀመሪያ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በብዙ መልኩ በተሻለ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል።
ርዕሰ መምህር አክሊሉ እንደሚሉት ደግሞ አንዳንድ – ለምሳሌ የላቦራቶሪ፣ ቤተመጻሕፍት፣ አይሲቲ (ኮምፒውተር) እና የመሳሰሉትን ክፍተቶች ለመሙላትና ከተማሪዎቹ ቁጥር ልክ ለማድረስ ባለ ሀብቶችን በማስተባበር አንዳንድ ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ።
ምቹ የምገባ አዳራሽ የሌላቸውን ትምህርት ቤቶችን ልበ ቀና ባለሀብቶችን በማስተባበር በአጭር ጊዜ አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የሚናገረው የየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር “አሻራችንን በማኖር የየካን ከፍታ እናረጋግጥ” በሚል መሪ ሀሳብ 4ኛ ዙር የ90 ቀናት ሰው ተኮር ፕሮጀክት አካል የሆነው የኮተቤ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ አዳራሽ ግንባታ ታህሳስ 17 ቀን 2016 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡
“የመመገቢያ አዳራሽ እጥረት አለብኝ” እያለ ላለውና ከባለ ሀብቶች ጋር እየመከረ ስላለው አፍሪካ አንድነት ቁጥር 2 የቅድመ አንደኛ ደረጃ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ተመሳሳይ እድል እንደሚገጥመው ተስፋ ማድረግ ይቻላል።
ወላጆችን በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡን ርዕሰ መምህሩ እንደሚሉት ትምህርት ቤት መመራት ያለበት በወላጅ ነው። ይሁን እንጂ ወላጆች ከትምህርት ቤቱ አመራርና መምህራን ጋር እጅ እና ጓንት ሆኖ መስራት ላይ የተወሰኑ ክፍተቶች አሉ። መምህራን ምን ግዜም ከትምህርት ቤት መለየት የለባቸውም። ስለልጆቻቸው በቅርብ በመከታተል ማወቅ አለባቸው። መምህራንን ማማከርና ችግር ካለ በመነጋገር መፍታት ይገባቸዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ ይህ ብዙም አይታይም። በመሆኑም የወላጆች የቅርብ ክትትልና እገዛ ለትምህርት ተቋማት መሻሻል እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ይህ በግል ትምህርት ቤቶች በኩል ሻል ባለ ሁኔታ ሲታይ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ግን ብዙም አይታይም እና ወላጆች ስለልጆቻቸው የቅርብ ክትትል ማድረጉ ላይ ችላ ሊሉ አይገባም።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም