ፍቅርና ወንድማማችነትን እንድንገልጽበት የተሰጠን የወል የፆም ወር

 “ሸገር አዲስ አባ አንቺ ያለሽበት፤

ራጉኤል አይደል ወይ የአንዋር ጎረቤት፤

ቅዳሴና ዛኑን አጥር ቢለያቸው

ፈጣሪ ከሰማይ አንድነት ሰማቸው..

እነዚህን በድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የተቀነቀነው ሁለቱን ሀይማኖቶች የመቻቻልና በጉርብትና የመኖር ልዕልና የገለጸበት ሙዚቃ ስንኞች ለዛሬው ጽሁፌ የመግቢያም፣ የሀሳብ ማጠንጠኛም ጉዳይ አድርጌ ተዋስኳቸው። ያገባደድነው ሳምንት በመጀመሪያው እለት (እለተ ሰኞ) ደግሞ ለሀሳቤ መነሻ ምክንያት ሆነኝ። ምክንያቱም እለቱ በክርስትናም (በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች)፣ በእስልምናም እምነት ተከታዮች ዘንድ በጋራ ፆም የጀመሩበት በመሆኑ ነው።

እምነቱ ቅዳሴና አዛኑን በአንድ ያስተሳሰረ፣ በክርስትናው የዐቢይ ፆም፣ በሙስሊሙም የረመዳን ፆም በእኩል ያስጀመረ ቀን ነው። እንዲህ አይነት አጋጣሚ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ደምቀው የሚታዩበት አንድነትና መተሳሰብ ብሎም የሀይማኖቶች መቻቻል የሚንጸባረቅበት ነው። የተለያዩ ብሄሮች ከተለያዩ ሀይማቶች ጋር ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩባት ሀገራችን ለዓለም የመቻቻል ምሳሌ ሆና የዘለቀችበትን ሕያው ማሳያም ነው።

ሀገራችን ኢትዮጵያ የፍቅርና የመቻቻል ሀገር ስለመሆኗ በርካታ ማረጋገጫዎችን ማንሳት ይቻላል። ከነዚህ ውስጥ አንዱ የሀይማኖት እኩልነት ይጠቀሳል። የተለያዩ ሀይማኖቶች በፍቅርና በአብሮነት የሚኖሩባት ሀገራችን ለብዙዎች የመልካም አብሮነት ምሳሌ ማሳያ ሆና ቆይታለች።

እነዚህ ሀይማኖቶች ከአምልኮ ባሻገር የሚኖራቸው የእርስ በርስ ቤተሰባዊ መስተጋብር የዜጎችን የመቻቻል መንፈስ የሚመሰክር ነው። ይሄ ደግሞ እንደ ሀገር ለአምልኮም ሆነ ለሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ምቹና አስተማማኝ አካባቢ የመኖሩ ውጤት ነው። ብዝሃነትን ከእኩልነት፣ እኩልነትን ከነጻነትና ከፍትሀዊነት ጋር አጣምራ የያዘች፣ ከማንም በላይ ስለሰብዐዊነት ግድ የሚላት ሀገራችን፤ ብዙዎች ስለሰላምና አብሮነት እንዲመርጧት አድርጓታል።

ይህ የኢትዮጵያዊነት ቀለም መጠሪያ ስማችን እስኪሆን ድረስ በአፍሪካ ነጻነትን፣ በዓለም ደግሞ እኩልነትን ለሰው ልጅ ሁሉ የፈነጠቀ ሆኗል። ሂደቱም ማንም የማይጨቆንበትን፣ ማንም የበላይና የበታች የማይሆንበትን ስርዐት ከመገንባትና ለትውልድ ከማቀበል እኩል ስለብዝሃነት ዋጋ የሚከፍልም ጭምር ነው። በመሆኑም ይህ ሕዝባዊ አንድምታ የሀይማኖት እኩልነትን ፈጥሮ፣ በወንድማማችነት አስተሳስሮና አጋምዶ የመቻቻልና የአብሮነት ደሴት አድርጎናል።

ለዚህ ነጻ ሀሳብ እንደዋነኛ ግብዐት የሚሆነን ሰሞነኛው በክርስትናው የአብይ ፆም፣ በእስልምናውም የታላቁ የረመዳን ጾም መገጣጠም ነው። ይሄ ክስተት ልዩ ትኩረት የሚያሰጠው ከፈጣሪ ሰላምንና አንድነትን፣ ጽድቅንና በረከትን እንድናገኝ በአንድ ድምጽ ስለሀገራችንና ሕዝባችን እንድንጸልይ የጋራ ወር ስለሰጠን ነው።

በአንድ ዓላማ በጾምና ጸሎት ፈጣሪ ፊት መቆም በምንም የማይወዳደር የታላቅ ዋጋ ምንጭ ነው። በተለይ ሀገር በብዙ ችግር እየተፈተነች፤ የተስፋ መንገዷንም እየጠረገች ባለችበት በዚህ ጊዜ፣ ክርስቲያንና ሙስሊሙ ፈጣሪ ፊት ለአንድ ዓላማ መቆሙ ይበል የሚያሰኝ ተስፋ ሰጪ ክስተት ነው። እናም ጊዜው ከፈጣሪ ጋር በጽሞና የምንነጋገርበት፣ በስጋችን ዝለት የነፍሳችንን ዋጋ የምናሰላበት የሕዝበ መምዕኑ የከፍታ ጊዜ ነው።

‹ሀገር ማለት ሰው ነው፣ ሰው ማለት ሀገር› የሚል ጥንተ ብሂል አለ። በዚህ አውድ ሀገር ማለት የሰውነት ነጸብራቅ ነው። ሳር ቅጠሉ፣ ሜዳ አፈሩ፣ አእዋፋት አራዊቱ፣ ወንዝ ጅረቱ፣ አድባር አውጋሩ ያለበት የማንነት ወዝና ጠረን፣ የብዙሀነት ስምና መልክ ነው። ከእርስ በርስ፣ ለእርስ በርስ የምንሰጠውና የምንቀበለው የምናጋራውም፤ ከእኔ ለእናንተ ከእናንተ ለእኔና ከእኛ ለሁላችን የሆነ የታሪክ፣ የባሕል፣ የወግና ልማድ፣ የማንነትና የብዙሀነት ውርርስ ነው።

ሰው ማለትስ? ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ ከላይኛው ጋር ተመሳሳይ ነው። ሀገርና ሰው፣ ሰውና ሀገር ተወራራሽ እውነቶች ናቸው። አንዱ ያላንዱ ብቻውን መቆም አይችልም። ሰው ማለት ሀገር ነው ስንል፣ የትኛውን ሰው? የሚለው ጥያቄ ቀድሞ የሚነሳ ነው። ሰው በሚለው የወል መጠሪያ ውስጥ ከተፈጥሮ ውጪ የሆኑ ብዙ ማንነቶች አሉ። ሰው ማለት ሀገር ነው በሚለው ውስጥ የተጠቀሰው ሰው፤ በእምነት፣ በሰብዐዊነት፣ በጨዋነት፣ በወግና ባህል፣ በአብሮነት፣ በመቻቻል፣ በስነምግባር፣ በሕግ፣ በኢትዮጵያዊነት፣ የጸናው ሰው ነው። ይሄ ማንነት ነው ሀገር የሚሆነው።

ኢትዮጵያዊነት ደግሞ ስረ መሰረቱ አብሮነትና መቻቻል ነው። ከሰማኒያ በላይ ብሔር ብሄረሰቦች በጋራ የተሰባሰቡባት፣ የተለያዩ ሀይማኖቶች ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩባትም ጨዋ ሕዝብና ጨዋ ስርዐት ስላላት ነው። ይሄ ስርዐት ወደፊትም ቀጥሎ ከነበረው የተሻለ ኢትዮጵያዊ መስተጋብርን እንደሚሰጠን አምናለው።

ስርዐት የጨዋነት መነሻ ነው። በዚህ ልክ የመቻቻል ተምሳሌት ሆነን በዓለም ፊት የቆምነው ሰብዐዊነትን ያስቀደመ፣ በአብሮነትና በወንድማማችነት ያጌጠ ስርዐት ስለገነባን ነው። እኚህ እሴቶቻችን በመከባበርና በመቻቻል ብዙ ዘመናትን በአብሮነት እንድንራመድ ያደረጉንም ናቸው። እንደ ሀገር፣ እንደ ሕዝብ፣ በበረታ ሕዝባዊነት ተባብረን የቆምነው ግፍን በሚፈራ፣ ለፍትህ ቅድሚያ በሰጠ ሰብዐዊነት ነው። ‹ወደ ሀበሻ ምድር ሂዱ፣ በዛ ሰውን የማይበድል ራሱም የማይበደል የእውነትና የፍትህ ንጉስ አለ› የሚለው የነብዩ መሀመድ መልዕክት ደግሞ የዚህ ዐቢይ ማሳያ ነው።

እንደተባለውም የወቅቱ ሀገረ ገዢ ንጉስ እንግዶቹን በክብር እና በኢትዮጵያዊ መስተንግዶ እንደተቀበላቸው በርካታ የታሪክ ሰነዶች ይዘክራሉ። ከዚህ ጋር አብሮ የሚነሳ አንድ እውነት አለ። በወቅቱ ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱትን የነብዩ ተከታዮች አሳልፎ እንዲሰጣቸው የተለያዩ የውጪ ሀገራት ለኢትዮጵያ ንጉስ ከእጅ መንሻ ጋር ጥያቄ ያቀረቡ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያዊው ንጉስ ግን ይሄን አላደረገም። ይሄ ጥንተ ታሪካችን አሁን ላለው ሕዝባዊ መቻቻል፣ ሀይማኖታዊ መከባበር ፈር የቀደደ የታሪክ ምስክራችን ነው።

ጎረቤታሞቹ አንዋር መስጂድ እና ራጉኤል ቤተክርስቲያን ይሄን የአብሮነት መንፈስ ከማጉላት ጎን ለጎን፤ የኢትዮጵያዊነት ቀለም በመሆን ለወንድማማችነታችን የላቀ ማሳያ ሆነው ኖረዋል። ከጥንት እስከዛሬ ሀይማኖታዊ ትስስርን ከማጉላት አኳያ ተምሳሌት በመሆን በዘፈን፣ በስነቃል፣ በተረት ሲወደሱ ኖረዋል። ወደፊትም ይወደሳሉ። የተሳሰርንበት፣ የተጋመድንበት የፍቅርና የአብሮነት ጥንተ ጠዋታችን በእነዚህ በልዩነት ውስጥ ሆነው በተጣመሩ ምልክቶቻችን የሚወከል ነው።

በዚህ የፆም ጊዜን ግጥምጥሞሽ በፈጠረው ቀንና ወርም የእምነቱ አባቶችና ተከታዮች በአዛንና ቅዳሴ፣ ስለሀገርና ሕዝብ ፈጣሪን ሲማጸኑ፣ አቡንና ኡስታዙ፣ ሸክና ቄሱ ስለሰው ልጆች ሲሉ ፈጣሪን ሲለማመኑ፤ የላቀ ፍቅርና አብሮነቱ የሚገለጥበት፤ ተባብሮ መቆሙ የሚጸናበት እንደሚሆንም አምናለሁ።

ይሄ ማንነት ነው ያለልዩነት ተከባብረንና ተቻችለን የመኖርን ታሪክ የሰጠን፤ የፍትሀዊነትና እኩልነት በአንድ ጥላ ስር ሰፍነው በኢትዮጵያ እንዲኖሩ ያደረገው። በቀጣይም የሚያምርብን በልዩነት ውስጥ አብሮ መቆም ነው። ያለስስት፣ ያለአድሎ ሀገር ለመቀየር፣ ትውልድ ለመቅረጽ የምናደርገው ጥረትም ነው አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያራምደን።

የሁለቱም እምነቶች የጾም ጊዜአቶች በፍቅር ተጀምረው በፍቅር እንዲጠናቀቁ የሁላችንም ምኞትና ፍላጎት ነው። ቂምና ቅያሜ ጥላቻና መለያየት አይደለም በረመዳን ወቅት፣ አይደለም በአብይ ጾም ወቅት በአዘቦትም የማይፈቀዱ ናቸው። እንድንሰጥ፣ ቸር እንድንሆን፣ እንድንተቃቀፍ፣ በጎ እንድናስብ፣ ጥላቻን በፍቅር፣ ቂምን በይቅርታ እንድንሽር፣ የበደሉንን ይቅር እንድንል እምነቱ ያዛል።

ምክንያቱም የሚያየውን ወንድሙን የማይወድ የማያየውን እግዚአብሄርን ወዳለው ቢል ስህተት እንደሆነ መጽሀፍ ቅዱስ ይነግረናል። በእስልምናውም እንዲሁ ይመስለኛል። እናም ጸሎታችን እንዲሰማ፣ ጾማችን፣ ዱዐችን ዋጋ እንዲያገኝ ከሁሉ በፊት በዙሪያችን ካሉት ጋር መግባባት ይኖርብናል።

በሙስሊሙም ሆነ በክርስቲያኑ ጾምና ጸሎት በፈጣሪ ዘንድ ዋጋ የሚያገኙት በፍቅር ሲጀመሩ፣ በፍቅርም ሲፈጸሙ ነው። ፍቅር የሌለበት ሕገ ስርዐት ለውጤት የማይበቃ መሆኑ እሙን ነው። አላህንም ሆነ እየሱስን በፍቅር ካልሆነ በምንም አንደርስባቸውም። ፍቅር ደግሞ ሌሎችን በማፍቀር፣ ከሌሎች ጋር ተስማምቶና ተዋዶ በመኖር የሚገለጽ ነው። በመተሳሰብና በመከባበር በመተዛዘንም የሚታይ ነው። እንዲህ ባለው የአብሮነት ትስስር፣ እንዲህ ባለው የአብሮነት መተሳሰብና መዋሃድ ካልሆነ ከእስራታችን ነጻ መውጣት አንችልም።

አንዋር መስጂድ እና ራጉኤል ቤተክርስቲያን መርካቶ እንብርት ላይ ሆነው ፍቅርን የሚሰብኩ፣ አብሮነትን የሚናገሩ የወንድማማች ሀውልቶች ናቸው። ለብዙዎቻችን የኢትዮጵያዊነት ምሳሌ ሆነው ዘልቀዋል። ለረመዳንና ለአረፋ ጊዜ ሕዝበ ክርስቲያኑ የወንድሞቹን መስገጃ እያጸዳ፤ በጥምቀትና በፋሲካ ደግሞ ሙስሊም ወንድሞች የክርስቲያኑን ቤተ እምነት አጸድ እያሳመሩ ኢትዮጵያዊነት ምን እንደሆነ በተግባር ሲያሳዩ ኖረዋል። እናም እንዲህ እንደ አሁኑ በጋራ ጾማችን ሰሞን ያለውን የወንድማማችነት መተሳሰብ እውነታ በደመቀና በበረታ መልኩ ማስታወስ ይገባል።

ሁለቱ ታላላቅ ሀይማኖቶች በአንድ ዓላማ ፈጣሪ ፊት ሲቆሙ፣ ሲጾሙና ሲሰግዱ፣ ሲቀድሱና አዛን ሲሉ፣ ሲለማመኑና ዱዐ ሲያደርጉ መመልከትን የመሰለ ታላቅ በረከት የለም። መቻቻልና አብሮነት ከምንም በላይ መንፈሳዊነት የሚንጸባረቅበት እንደመሆኑም፤ ይሄ የጾም ወቅት ከነበረን በላይ እንዲኖረን፣ ካሰብነው በላይ እንዲጨመርልን መንገድ የሚከፍትልን አጋጣሚም ነው። እንደሀገር ካለንበት ችግር ወጥተን በሰላምና በደህንነት እንድንኖር ከፈጣሪ ምህረት የምናገኝበትም ጊዜ ነው።

ጊዜው ከመቼውም በላይ ወደላይ የምናይበት፣ በጾምና ጸሎት ከፈጣሪ ጋር የምንታረቅበት ነው። ምክንያቱም በእርስ በርስ መጨካከን ብዙ ነገሮችን አጉድለናል። በትዕቢት፣ በጥላቻ ፈጣሪን አሳዝነናል። በድፍረት፣ በጭካኔ ያለራሮት ደም አፍሰናል፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ወንድማማች ሆነን ቆመን እርስ በርስ ተገፋፍተናል። በመሆኑም ይሄ የጾም ወቅት ታሪካችንን የምናድስበት፣ ከፈጣሪ ጋር በመታረቅ ክብራችንን የምንመልስበት ነው። ሙስሊም ከክርስቲያኑ ለአንድ ዓላማ ወደፈጣሪ ሲጸልዩ፣ ስለሀገርና ሕዝብ፣ ስለሰላምና አንድነት፣ ስለደህንነትና በረከት ሲማጸኑ እንደማየት ደስታ የለም። መሻታችንን ተመልክቶ ፈጣሪ እንዲረዳን የሁላችንም ምኞት ነው።

በሀገራችን ብዙ ችግሮች ተከስተዋል። መነሻው ፍቅር ማጣትና ተነጋግሮ አለመግባበት ቢሆንም ከኢትዮጵያዊነት ያፈነገጡ አንዳንድ ማንአለብኝነትም ለዚህ ችግር እንደዋነኛ ምክንያት ይጠቀሳሉ። ሆኖም ተነጋግረን እንዳንግባባ አእምሮና ልባችንን የዘጋነው ከፍቃደ እግዚአብሄር ስለሸሸን ነው። መፍትሄውም ስክነት፣ እርጋታና ጽሞና ናቸው። ስክነት ከራሳችን ጋር እንድንመክር ያደርገናል።

እርጋታ ከፍተቶቻችንን እንድንመለከት፣ ጽሞና ደግሞ ከፈጣሪ ጋር በጸሎት እንድንገናኝ መንገድ ይከፍትልናል። እናም ይሄ ፆማችንን በአብሮነት እንድንጾምና ፈጣሪንም እንድንማጸን የተሰጠን ወር በምክንያት ነውና፤ በዚህ መልኩ ተጉዘን ፍቅር እና ወንድማማችነትን እንድንገልፅበት የተሰጠን መሆኑን በመገንዘብ በዚሁ ልክ ራሳችንን ልንገልጥ ይገባል። እኔም ጾሙ የበረከትና የተስፋ እንዲሆንልን በመመኘት ላብቃል። ሰላም!

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You