የግድቡ ስኬት – ለባህር በሩ ብርታት

ለዘመናት በእቅድ የተያዘ፣ ከመወለዱ በፊት ማሳደጊያ የሚሆን በጀት የተጠየቀበትና የተነፈገ፤ በመጨረሻም በደፋር ውሳኔ፤ በምጥ የተወለደ እና በገዳዮቹ ፊት በሁለት እግሩ ለመቆም የበቃ ነው፡፡ ውልደቱ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ይሁን እንጂ ጥቂት፤ ለማይባሉ አስርት ዓመታት ሲታሰብበት የቆየ ግዙፉ የኢትዮጵያም የአፍሪካም ልጅ ነው፤ ዛሬ የ13 ዓመት እድሜ ሲኖረው፣ ለጠላቱ የምን ጊዜም ስጋትና ብስጭት፤ ለናፋቂዎቹ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ብርሃን መሆን የጀመረ ነው – የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ/የአባይ ግድብ፡፡

ይህ የውዝግብ ምንጭ የሆነው ግዙፍ ግድብ፣ ለኢትዮጵያውያኑ የጥንካሬ ማሳያ እና ማስተሳሰሪያ ገመድ ሲሆን፣ እንደ እነ ግብጽ ላሉ ለሌሎቹ አውርቶ አደሮች ደግሞ የእንጀራ ገመድ በጣሽ ነው፤ (እንዲህ ሲባል የዓባይን ወንዘ ለራስ ብቻ የተሰጠ ስጦታ አድርገው ዋሽተውና ወሽክተው ለዜጎቻቸው ለሚሰብኩ ለማለት እንጂ የተፈጥሮ ሀብቱን በጋራ ለመጠቀም ጥሩ ልብ ያላቸውን ለማለት እንዳልሆነ ልብ ይሏል፡፡)

የወንዙ መነሻ ራሷ ኢትዮጵያ ሆና ሳለች በአጉል ተረት ተረት አይነት ጨዋታ አንዳች አይነት ንክኪ እንዳይኖራት ለዘመናት ስትከለከል ቆይታለች፡፡ ይሁንና አይኑን አፍጥጦ ለመጣው ተጽዕኖ ፈጣሪ አግባብነት ያለው ምላሽ በመስጠት የማይታሙት ኢትዮጵያውያን፤ በምጥ ለተወለደው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በመረባረብ የተጽዕኖ ፈጣሪ ነኝ ባዩን እቅድና ዓላማ ማከኮላሸት ችለዋል፡፡

ዛሬ እነዚያ ሁሉ ፈተናዎች እና ጫናዎች ታልፈዋል፡፡ በእያንዳንዱ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የግንባታ ሒደት የተለያዩ ማሰናከያ ድንጋዮች እንዲቀመጡ ቢደረጉም፤ እንዲያደናቅፍ ያስቀመጡትን ድንጋይ ሁሉ ለግንባታው ግብዓት በማድረግ በብልሃትና በጥበብ እዚህ መድረስ ተችሏል፡፡ ይባስ ብሎም ከሳሾቻችን እያዩ የሕዳሴ ግድባችን ብርሃን አብርቶልናል፡፡

ይህን የብርሃን ጭላንጭል ማየት የተቻለው ግን በብዙ ክስና ትንኮሳ ከመሆኑም በላይ፤ በጠላቶቻችን በሚዘረጋብን ሴራ ምክንያት በብዙ የውስጥ ፈተናዎች ውስጥ ሆነን መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ እንዲያም ሆነ ግን ብልሆቹ የኢትዮጵያ ልጆች እርስ በእርስ እንድንባላ የተዘረጋውን ወጥመድ በጥበብ በመበጣጠስ ዛሬ ላይ መድረስ ተችሏል፡፡

መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም የ13ኛ ዓመት ልደቱን የሚያከብረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ታዲያ፤ በአህጉር እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በመሆኑ የስኬትና የእውቅና ሽልማት ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡ ይሄም የዘንድሮ ልደቱን ልዩ ያደርገዋል፡፡ ይህ የኢትዮጵያውያን ዐይን ማረፊያና የአሸናፊነት ተምሳሌት የሆነው ታላቁ የኢተትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ ጉዳዩ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ጉባ ወረዳ ልዩ መጠሪያ ከሆነው ከሰርባ እስከ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ድረስ ቀርቦ አስተማማኝ ማብራሪያ የተሰጠበት ልዩ ምልክታችን ነው፡፡

ዛሬ ዋና ላነሳው የፈለግኩት ጉዳይ ኢትዮጵያ ከወራት በፊት ከራስ ገዟ ሱማሌ ላንድ ጋር ያደረገችው የባሕር በር የምታገኝበት የመግባቢያ ሰነድ ስምምነትን ተከትሎ እየተናፈሰ ስላለው ጉዳይ ነው። ይህም የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ልክ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም በጅማሬው አካባቢ እየተነናፈሰ የነበረው ተራ ፕሮፓጋንዳ አይነት ሲሆን፣ በሕዳሴ ግድቡ ላይ በወቅቱ ተራ ፕሮፓጋንዳ ይናፈስ እንጂ ከስኬታማነቱ እንዳላስቀረው ለመጥቀስ ያህል ነው፡፡

ሲሆን ሲሆን፣ በተለይ በምስራቅ አፍሪካና በቀጣናው ያሉ አገራት በኢትዮጵያና በራስ ገዟ ሱማሌ ላንድ መካከል የተደረገው የባሕር በር ማግኛ የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ጠቀሜታው ኢትዮጵያን ብቻ እንዳልሆነ ሊረዱ ይገባቸው ነበር፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ግን አሁን አሁን እየተቆጠረ ያለው የአንዱ እድገት የሌላው ውድቀት ተደርጎ ነው። የአንዱ ሰላም መሆን የሌላው ቁርቁዝና ይመስል መገፋፋት መብዛቱም እየታየ ነው፡፡

ይሁንና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬታማ መሆን ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ለምታደርገው ጉዞ መንገድ ጠራጊ ነው የሚል አተያይ አለኝ፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ለማድረግ አቅደው ያቃታቸው ነገር የለም፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉን ነገር በኃይል የሚፈጽሙ ናቸው ማለት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ በመጀመሪያ ማግኘት የሚሹት የተገባቸውን እንጂ የሌላውን ንብረት አይደለም፡፡ ስኬታማ የመሆናቸውም ምስጢር እሱ ነው፤ በጋራ ሰርቶ በጋር የመልማት ሕልምና መንገዳቸው፡፡

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የባሕር በር ባለቤት እንደነበረች የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ እሱ ሁሉ ቀርቶ ለብዙ ዓመታት ያለ ባሕር በር ኢኮኖሚዋንም ሆነ ሰላሟን ስትገፋ ቆይታለች፡፡ ከእርሷ በጣም በቅርብ ርቀት መጠቀም የሚያስችላት የባሕር በር እያለ እስከዛሬ ድረስ ላልተገባ ወጪ ተዳርጋ ቆይታለች፡፡ ከችግሯ ለመውጣትም በተቻላት መጠን ሁሉ በጎረቤት አገራት የሚገኙ ወደቦችንም ለማልማት ሞክራለች፡፡ አሁንም የጀመረችው መንገድ ይሄው የሕልውናዋን ጥያቄ ምላሽ የመስጠት ጉዞ ነው፡፡

ይሁን እንጂ አፍንጫዋ ስር ባለው የቀይ ባሕር ላይ፣ ከወዲያኛው ጫፍ ኃያላን ናቸው የተባሉ አገራት መጥተው ስፍራውን ሲቆጣጠሩት ያልተነፈሱ አካላት፤ ታትሬ ዜጎቼን በአግባቡ ማኖር እሻለሁ ብላ ቀና ለማለት የፈለገችን ኢትዮጵያ ከወዲህ ወዲያ ለማዋከብ የሚደረግ ጥረት ተገቢ አይደለም፡፡ ይሄን መሰል የክፋት አካሄድም ልክ ሊኖረው፤ የኢትዮጵያን የሕልውና ጥያቄ ምላሽ ማግኘት እንደሚገባውም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያን እድገትና ለውጥ የማትሻው የግብጽ መንገድ ይታወቃል፤ ኢትዮጵያ በዋጋ የፀናቻት የጎረቤት ሱማሊያ ጉዳይ ግን እውነቱን ካለመረዳት፣ አልያም በግብጽና መሰል ኃይሎች ከመነዳት የሚመነጭ ምክንያቱም፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ከሶማሊላንድ ጋር ያካሄደችውን ስምምነት አንዴ “አወዛጋቢ ስምምነት ነው፤” ሲሉ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ “ስምምነቱ ጦርነት ከማወጅ የማይተናነስ ነው” ሲሉ ይደመጣሉ። ከዚህ ባሻገር፣ ሲሻቸው ወደ ግብጽ፣ ሲላቸውም ወደተባባሩት መንግሥታት ድርጅት ጉዳዩን ሲያደርሱ ይስተዋላል፡፡

ይሄን መሰል አካሄድ ደግሞ ያኔ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጅማሮ ላይ ግብጽ ግንባታው እውን እንዳይሆን ስትከተል የነበረውን አካሄድ የሚያስታውስ ነው፡፡ ሆኖም በወቅቱ የግብጽ መቅበዝበዝ የግድቡን እውን መሆን አልገታውም። ምክንያቱም አሸናፊው እውነት ነውና። ለዚህም ነው ግብጽ ብዙ የተዋጋችውና እንዲከስም የጣረችው ፕሮጀክት ዛሬ ላይ ለኢትዮጵያውያን እና ጎረቤቶቻቸው ብርሃንን መሆን የጀመረው፡፡ በዚህም ለወዳጆች ኩራት፣ ለጠላቶች ደግሞ ሃፍረት ሆኖ፤ ከጥፋት መንገዳቸው ተደጋጋሚ ምልልስ ትምህርት የሚወስዱበትን እድል የፈጠረው፡፡

ታዲያ የዓባይ ወንዛችን ስኬታማ መሆን የባሕር በር እንዲኖረን ለምናደርገው ጉዞ አቅም ነው። ከወዲሁ ስኬታማ እንዳንሆን ብዙዎች የተለያየ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ላይ ቢገኙ፤ ትናንትን በትጋትና አልሸነፍ ባይነት ያለፉ ኢትዮጵያውያን ዛሬም ያንን ጽናት እንደሚደግሙት ጥርጥር የለውም፡፡

ዛሬም እንደ ትናንቱ ኢትዮጵያ የማንንም አገር ሉዓላዊነት አትዳፈርም፡፡ ትናንት ከሕዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ብዙ በሴራ የተጠመዱብንን ወጥመዶች በጥበብ በማለፍ እዚህ መድረስ ችለናል፡፡ እርስ በእርስ ሊያጣሉን በብዙ ዋሽተውብናል፡፡ ልክ የዚያን አይነት ሴራ ዛሬም በየመንገዳችን እንደሚጠብቀን ተረድተንና በሕዳሴ ግድብ ላይ ያደረግነውን ትጋት የባሕር በር ለማግኘት በሚደረገው ሒደትም በመድገም ታሪክ ሰሪዎች እንሁን እላለሁ፡፡

ወጋሶ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You