የዓባይ ግድብ የኤሌክትሪክ ማመንጫው ግንባታ በሰባት ወራት ይጠናቀቃል

– ድልድዩና ሙሉ ሥራው በቀጣይ ዓመት ያልቃል

አዲስ አበባ:- የዓባይ ግድብ ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታው በሰባት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ አስታወቁ። በዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ድልድይና የፕሮጀክቱ ሙሉ ሥራ በቀጣይ ዓመት እንደሚጠናቀቅም ጠቁመዋል።

የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ እንዳመለከቱት፤ ቀንና ሌሊት በሚሠሩ ባለሙያዎች አማካኝነት የግድቡ ግንባታ የሲቪል ሥራው 99 በመቶ ተጠናቋል።

ዋናው የግድቡ ክፍል 107 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የኮንክሪት ሙሌት እንደሚይዝ የተናገሩት ኢንጂነር ክፍሌ፤ ከዚህ ውስጥ አንድ በመቶው ሥራ ብቻ እንደሚቀር አስረድተዋል።

ኢንጂነር ክፍሌ እንዳስታወቁት፤ የግድቡ የኤሌክትሮ ሜካኒካል በተለይም የተርባይንና ጄኔሬተር ተከላ ሥራው 78 በመቶ ተጠናቋል።

እያንዳንዳቸው 375 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ያላቸው ሁለት ተርባይን ዩኒቶች በተለያዩ ጊዜያት መገጠማቸውን ያስታወሱት የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ፤ ቀሪ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ተርባይኖች በቀጣይ ወራት ተራ በተራ እየገቡ ይገጠማሉ ብለዋል።

በበርካታ ፈተናዎችና ጫናዎች ሳይበገር ግንባታው የቀጠለው የግድብ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎቹን ተርባይኖች ሥራ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ሲሉ አስረድተዋል።

የግድብ የውሃ ማስተላለፊያ አሸንዳዎች ግንባታ ከ85 በመቶ በላይ መድረሱን ኢንጂነር ክፍሌ አመላክተው፤ በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ 95 በመቶ መድረሱን አስታውቀዋል።

የግድብ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግንባታ በሰባት ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ ቢሆንም፤ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ድልድይና ሙሉ የፕሮጀክቱ ሥራው በቀጣይ ዓመት ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ሲሉ ተናግረዋል።

አጠቃላይ ሥራዎችንም በ2017 ዓ.ም በማጠናቀቅ የመላው ኢትዮጵያውያን ኩራት የሆነውን የዓባይ ግድብ ከፍጻሜው ለማድረስ አስፈላጊው ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ የኢትዮጵያ ተቋማት የጥራት ተሸላሚ መሆኑ በግንባታው ሂደት ለሚኖረው የሠራተኞቹ ተሳትፎና አጠቃላይ በግድቡ ግንባታ ድጋፍ ለሚያደርጉ አካላት በሙሉ ተጨማሪ የሞራል አቅምን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለዓባይ ግድብ አስተዋፅኦዎችን በቀላሉ ማበርከት የሚያስችል www.mygerd.com የተሰኘ ድረ ገጽ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

የግድብ ግንባታ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ ተጥሎ እንደተጀመረ የሚታወስ ሲሆን፤ የግንባታው 13ኛ ዓመት ከሁለት ሳምንት በኋላ በደማቅ ሥነ-ሥርዓቶች እንደሚከበር ይጠበቃል።

ጌትነት ተስፋማርያም

አዲስ ዘመን  መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You