ጀግናው ዑመር ሰመተር

‹‹ከአገሬ አፈር የሚደባልቅ ቤልጅግ እና ጎራዴ ይዤ እንጂ ጫት ተሸክሜ የምመጣ እንዳይመስልህ!›› በሚለው ንግግራቸው በብዙዎች ዘንድ ይታወቃሉ፤ ጀግናው ዑመር ሰመተር! የዚህ ሳምንት ክስተት ናቸውና ታሪካቸውን እናስታውሳለን።

ከዚያ በፊት ግን በዚህ ሳምንት ብዙ ሌሎች ክስተቶች አሉና በአጭር በአጭሩ እናስታውሳቸው።

ከ135 ዓመታት በፊት መጋቢት 1 ቀን የተጀመረውን የመተማ ጦርነት ባለው ሳምንት በዝርዝር አይተናል። በዕለቱ በጥይት የተመቱት አጼ ዮሐንስ 4ኛ ሕይወታቸው ያለፈው በዚህ ሳምንት መጋቢት 2 ቀን 1881 ዓ.ም ነበር። ደርቡሾችም እየተከታተሉ የአጼ ዮሐንስ አራተኛን አስከሬን ይዘው፤ አትባራ ወንዝ ላይ የነበሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ጥቃት አድርሰው፣ መጋቢት 3 ቀን 1881 ዓ.ም የአጼ ዮሐንስ አራተኛን ጭንቅላት ወሰዱ።

ከ4 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ዓለምን አስጨንቆ የነበረው ኮቪድ-19 ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ ይፋ ሆነ። በእያንዳንዱ ሰው የሕይወት ታሪክ ውስጥ አስጨናቂ ትዝታ ያለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እነሆ የታሪክ አካል ሆኖ አጋጣሚዎቹ ሲታወሱ ይኖራሉ።

ከ112 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 5 ቀን 1904 ዓ.ም የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አባት የሆኑት ጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ተወለዱ። አክሊሉ ሀብተወልድ ኢትዮጵያን ወክለው ከኃያላን አገራት ጋር ተከራክረዋል፣ በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያን ጥቅም አስከብረዋል። በዚህ ጥረታቸው በዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ በአርዓያነት ይጠቀሳሉ።

ከ61 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 5 ቀን 1955 ዓ.ም ባለፈው ጥር ወር በአፀደ ሥጋ የተለየን እና ‹‹ተንቀሳቃሹ ቤተ መጻሕፍት›› በሚል ቅጽል ስም የታወቀው ገነነ መኩሪያ ተወለደ።

ከ148 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 7 ቀን 1868 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር ካደረገቻቸው ጦርነቶች መካከል አንዱ የሆነውና በኢትዮጵያ አሸናፊነት የተጠናቀቀው የጉራዕ ጦርነት ተካሄደ።

ከ96 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 7 ቀን 1920 ዓ.ም ካርል ሄይንዝ በም (‹‹የሰዎች ለሰዎች›› በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራች) ተወለዱ። ሰዎች ለሰዎች (ሜሽን ፎር ሜሽን) ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎችንና የበጎ አድራጎት ሥራዎችን በመሥራት ይታወቃል።

አሁን ወደ ጀግናው ዑመር ሰመተር ታሪክ እንለፍ።

‹‹ከአገሬ አፈር የሚደባልቅ ቤልጅግ እና ጎራዴ ይዤ እንጂ ጫት ተሸክሜ የምመጣ እንዳይመስልህ!›› የሚለው ንግግራቸው በቃል ጭምር ይነገርላቸዋል። ፋሽስቱን ጣሊያን መግቢያ መውጫ ካሳጡ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ጀግኖች አንዱ የሆኑት የምሥራቁ አርበኛ ደጃዝማች ዑመር ሰመተር፤ ከ80 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 6 ቀን 1936 ዓ.ም ሕይወታቸው ያለፈ የዚህ ሳምንት ክስተት ናቸው።

በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የተጋደሉትና ደማቅ የጀግንነት ታሪክ የፃፉት ጀግናው አርበኛና ግዛት አስተዳዳሪ ደጃዝማች ዑመር ሰመተር በ1871 ዓ.ም በኦጋዴን አካባቢ ካልካዩ በተባለ ሥፍራ ተወለዱ። ለአካለ መጠን ከደረሱም በኋላ የኤልቡር አካባቢ ገዢ በመሆን አገልግለዋል። ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የደረሰባትን ሽንፈት ለመበቀል የያዘችውን የረጅም ጊዜ ዓላማ ለማሳካት ባደረገችው ወረራ ወቅት በምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ከደጃዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት ጋር ተሰለፉ። ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር የጫረችው የወልወል ጠብ የተከሰተው ደግሞ ዑመር ሰመተር በነበሩበት በምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ነበር።

ኢጣሊያ በ1888 ዓ.ም ዓድዋ ላይ የደረሰባትን ሽንፈት ለመበቀልና ኢትዮጵያን የኢጣሊያ ምሥራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛት አካል ለማድረግ ለ40 ዓመታት ያህል ስትዘጋጅና ጊዜ ስትጠብቅ ቆየች። እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1922 ወደ ሥልጣን የመጣው ቤኒቶ ሙሶሊኒ፣ ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን የውርደት ማቅ እንደሚበቀልና ኢትዮጵያ የኢጣሊያ ቅኝ ግዛት አካል እንደምትሆን መዛት የጀመረው ገና በጠዋቱ ነበር።

ለዚህም እንዲያመቸው የኢጣሊያ መንግሥት ራስ ተፈሪ መኮንን ኢጣሊያን በጎበኙበት ወቅት ‹‹ቪቫ ኢትዮጵያ›› እያለ ወዳጅ መስሎ ሸነገላቸው። እስከ አፍንጫው የታጠቀ በርካታ ጦር በኤርትራና በሌሎች የኢጣሊያ ምሥራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛት አካባቢዎች ላይ ያከማች ጀመር። የጦሩን ውጤታማነት አስተማማኝ ለማድረግም ሐኪሞችን፣ ሰላዮችንና ሌሎች ሙያተኞችን አብሮ አጓጓዘ። ኢትዮጵያውያን የግዛት ባላባቶችን በጥቅም በመደለል ማስኮብለሉንና መረጃ መመንተፉንም ተያያዘው። በጨካኝነታቸው የታወቁትን እነ ኢሚሊዮ ዴ ቦኖ፣ ፒየትሮ ባዶሊዮ፣ ሩዶልፎ ግራዚያኒና ሌሎች የጦር አለቆችን ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ላከ።

ጣሊያን ይህንን ዝግጅት ካጠናቀቀች በኋላም ኢትዮጵያን የምትወርበት አጋጣሚ መጠባበቅ ጀመረች። በዕለተ ረቡዕ፣ ኅዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም የኢጣሊያ ወታደሮች በኢትዮጵያ እና በእንግሊዝ ሱማሌላንድ (Brit­ish Somaliland) መካከል ያለውን ወሰን ለመከለል የተላኩትን ሰዎች ይጠብቁ በነበሩት የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ጥቃት ከፈቱባቸው። (ኢጣሊያ በአካባቢው ያለው የኢጣሊያ ሱማሌላንድ ግዛቷ ስለሆነ ወታደሮቿ በአካባቢው ነበሩ)

ውጊያ ተደረገና በሁለቱም ወገኖች በኩል ሰውነት ቆሰለ፤ አካል ጎደለ … የሰው ሕይወት ጠፋ።

ኢትዮጵያም ስሞታዋን ለኢጣሊያ መንግሥት ስታቀርብ፤ የኢጣሊያ መንግሥት ይባስ ብሎ የተበደለ መሆኑን በመግለፅ የሚከተሉትን ‹‹የመደራደሪያ ጥያቄዎች›› አቀረበ።

አንደኛ፤ የወቅቱ የሐረርጌ ገዢ የነበሩት ደጃዝማች ገብረማርያም ወልወል ድረስ ሄደው እዚያ የሚገኘውን የኢጣሊያ የጦር መሪ በኢትዮጵያ መንግሥት ስም ይቅርታ እንዲጠይቁ፣ አንድ የኢትዮጵያ የጦር ጓድ ለኢጣሊያ ሰንደቅ ዓላማ ሰላምታ እንዲሰጥ፣ በኢትዮጵያ በኩል ለተደረገው የማጥቃት እርምጃ ኃላፊ የሆኑት ባለሥልጣኖች ሁሉ ተይዘው የኢጣሊያን ሰንደቅ ዓላማ እጅ ነስተው እንዲሻሩና ተገቢውን ቅጣት በአስቸኳይ እንዲያገኙ፣

ሁለተኛ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለቆሰሉት፣ አካላቸው ለጎደለውና ለሞቱት የኢጣሊያ ወታደሮች ካሣ የሚሆን 200 ሺህ ማርቴሬዛ (ጠገራ ብር) እንዲከፍል እንዲሁም

3ኛ፤ በኢጣሊያ ወታደሮች ላይ ጥቃት ፈፅመው ከባድ ጥፋት ያደረሱት ዑመር ሰመተር ተይዘው ለኢጣሊያ መንግሥት እንዲሰጡ … በማለት የለየለት የትዕቢት ጥያቄ አቀረበ።

የኢትዮጵያ መንግሥትም የኢጣሊያን ሃሳብ ሳይቀበል ቀረ፤ ጉዳዩ በእርቅ እንዲያልቅ ለማድረግ ቢጥርም ሳይሳካ ቀረ። ከዚህ በኋላ ፋሺስት ኢጣሊያ ለ40 ዓመታት ያህል ስትዘጋጅበት የቆየችውን እቅድ እውን ለማድረግ በሁሉም አቅጣጫዎች ኢትዮጵያን መውረር ጀመረች።

በዓለም አቀፍ ሕግጋት ፈፅሞ የተከለከሉ የጦር መሣሪያዎችን (የጦር አውሮፕላን፣ የመርዝ ጋዝ፣ …) ጭምር በመጠቀም በኢትዮጵያውያን ላይ እጅግ በጣም ከባድ የሆነ የጦር ወንጀል ፈፀመች።

ኢጣሊያ የኢትዮጵያን ግዛት እወስዳለሁ ብላ ወልወል ላይ የጫረችው እሳት በሁለቱም ወገኖች ላይ ጉዳት አድርሶ ነበር። በኋላም እርቀ ሰላም አወርዳለሁ ብላ ቃል ስትገባም ድርድር ስታቀርብ የግጦሽ መሬት ከኢትዮጵያ ግዛት ተቆርሶ እንዲሰጣት ስትጠይቅ ‹‹በኢጣሊያ ወታደሮች ላይ በደል የፈፀመው ዑመር ሰመተር እጁ ተይዞ ተላልፎ ይሰጠኝ›› ብላ ጠይቃ ነበር። ዑመር ሰመተርም ይህን ሲሰሙ ‹‹ከሀገሬ አፈር የሚደባልቅ ቤልጅግና ጎራዴ ይዤ እንጂ ጫት ተሸክሜ የምመጣ እንዳይመስልህ›› ብለው በመመለስ ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ከመውረር እንድትታቀብ ደጋግመው ያስጠነቅቁ ነበር።

በወልወል የተጫረው እሳት በሰሜንም ቀጠለ፤ በመላው ሀገርም ተዳረሰ። ዑመር ሰመተር ከደጃዝማች አፈወርቅ ወልደሰማዕት ጋር በመሆን የፀረ ፋሺስት ትግሉን ተያያዙት። በተለይም የሠለጠነው የዑመር ሰመተር ጦር ገርለጉቤ ከተባለው ስፍራ ላይ መሽጎ ስለነበር እየተወረወረ ጠላትን መውጫ ቀዳዳ በማሳጣት ታላቅ ጀብዱ ፈፅሟል። ኤልቡር በተባለው ቦታ ላይ ዑመር ሰመተር በስድስት ባታሊዮን የጠላት ጦር ተከበቡ። የሠራዊታቸውን አቅምና የጦሩን ሁኔታ ተመልክተው ቦታ ለቀቁ፤ አንዳንድ ሰዎችም መሣሪያ አስረከቡ። ከአምስት ወራት በኋላ ዑመር ሰመተር ጦራቸውን አጠናክረው ሱማሌውን፣ አማራውን፣ ትግሬውን፣ ኦሮሞውን እንዲሁም ከሌላው የአገሪቱ ግዛት የተውጣጣውን ኅብረተሰብ አስከትለው በ1930 ዓ.ም ገደማ አንድ ሌሊት በጠላት ጦር ላይ አደጋ ጣሉ። ስድስቱም ባታሊዮን የጣሊያን ጦር የሞተው ሞቶ ሌላውም ተማረከ። መሣሪያዎቹንም ማረኩና ተመልሰው ሺላቦ ላይ ሰፈሩ።

አሁንም የኢጣሊያ ጦር ሺላቦ ድረስ እየመጣ ቢያስቸግር እንደገና ገጥመው ድል አደረጉት። ብዙ የጠላት ጦር አባላትንም ገደሉ። ዑመር ሰመተር ከደጋው የኢትዮጵያ ክፍል በሚላክላቸው የሰው ኃይል፣ መሣሪያና ስንቅ እየተጠናከሩ እንደገና ቆራሄ ላይ ከጠላት ጦር ጋር ገጥመው አመድ አደረጉት። በመጨረሻም ከጠላት ምሽግ ውስጥ ገብተው የጨበጣ ውጊያ በማካሄድ ታላቅና የማይረሳ ገድል ፈፅመዋል።

ከዚህ በኋላ ወደ ደገሃቡር ተመልሰው ከበላይ አዛዦቻቸው ጋር ተገናኙ። በዚህም ወቅት የጦሩ የአንዱ ክፍል አዛዥ የነበሩት ደጃዝማች ገብረማርያም የዑመርን ጀግንነት ተመልክተው በኦጋዴን አውራጃ ካሉት የአካባቢው ተወላጆች ወታደር መልምለው እንዲቀጥሩ ፈቀዱላቸው። በዚህም ጊዜ የፊታውራሪነት ማዕረግ ተሰጣቸው። ፊታውራሪ ዑመር ሰመተር ጠላትን በማንበርከክ በገርለጉቤ፣ በቆራሄ፣ በሃነሌ … የሚያስደንቅ ጀብዱ ፈፀሙ። ደጃዝማች አፈወርቅ ከሞቱም በኋላ ወታደሩን እያረጋጉ ሲዋጉ ቆይተው በመጨረሻ እርሳቸውም በስድስት ጥይት ቆስለው ስለነበር ወደ ጂግጂጋ ተመለሱ። ፊታውራሪ ዑመር ሰመተር የደረሰባቸው ቁስል እጅግ ከባድ ስለነበር ለጦርነት መሰለፍ ከማይችሉበት ደረጃ ላይ ደረሱ። የጦር መሣሪያ የሚገኝበትን ዘዴ እየቀየሱ፣ ሕዝቡም ካለው የማረሻ በሬና ሌላም ቁሳቁስ እያዋጣ በመሸጥ ጥይትና ጠመንጃ እየገዛ ትልቅ ውጤት አስገኝቶ ነበር።

በኋላም ቁስላቸው እጅግ እየበረታባቸው ስለሄደ ወደ ሐርጌሳ መሰደድ ግድ ሆነባቸው። ከሐርጌሳ ተነስተው ኬንያ ገቡ። ከኬንያ ወደ ለንደንም ተወስደው ነበር። ከዚያም የቀረውን የጦርነት ጊዜ በስደት ላይ ሆነው ካሳለፉ በኋላ ነፃነት ሲመለስ ወደ ሀገራቸው ገቡ። ስድስቱ ጥይት በአካላቸው ውስጥ እንዳለ ነበር ወደ ሀገራቸው የተመለሱት።

ነፃነት ከተመሰለ በኋላ አርበኛው ሁሉ እየፎከረና እያቅራራ ጀግንነቱን ሲያስመሰክር ፊታውራራ ዑመር ሰመተር በምድረ ኦጋዴን ከጦር የተረፉ ጀግኖች ናቸው ካሉበት በመብራት ያስፈለጓቸው። ቀጥሎም የደጃዝማችነት ማዕረግ ተሰጣቸውና የኦጋዴንና ጂግጂጋ ገዢ ሆኑ።

ይሁን እንጂ በአካላቸው ውስጥ ያሉት ጥይቶች እረፍት ነሳቸው፤ ቁስሉም እያመረቀዘ አስቸገራቸው። በሐረር ከተማ ሐኪሞች ባሉበት ቦታ ሁሉ እየተዘዋወሩ ቢታከሙም መዳን ግን አልቻሉም።

ደጃዝማች ዑመር ሰመተር ለአገራቸው ትልቅ ቁም ነገር ሠርተው መጋቢት 6 ቀን 1936 ዓ.ም፣ በተወለዱ በ65 ዓመታቸው አረፉ። ሥርዓተ ቀብራቸውም በሐረር ከተማ ውስጥ በወታደራዊ ክብር ተፈጽሟል።

ደጃዝማች ዑመር ሰመተር ከመሞታቸው በፊት እንዲህ ብለው ነበር። ‹‹ … የአገሬን ሕዝብ የፈጀው ጠላት በጀግኖች ክንድ ተረግጦ ሲወጣ በዓይኔ ተመልክቻለሁ። የመገዛት፣ የመዋረድና የመረገጥ እድል ምን እንደሆነ ዐይቻለሁ። እንደተራራ ንብ በየምሽጉ እየገቡ የሚነድፉ ኢትዮጵያውያን ዘር በመሆኔም ኮርቻለሁ። በታሪክ የሰማሁትን የዓድዋ ጀግኖች ጀብዱ ለማስመስከር ልጆቻቸው በኦጋዴን የጣሊያንን አንገት ሲቆርጡ አይቻለሁ። የዚህ ሕዝብ ልጅ በመሆኔ አሁንም እኮራለሁ። የማዝነው ግን መላው ሱማሌዎች ተባብረው የአንዲት ኢትዮጵያ ልጅ ሆነው በአንድ ሰንደቅ ዓላማ ስር ሲጠቃለሉ ሳላይ በመሞቴ ነው። በመቃብርም ውስጥ ምኞቴ ይህ ነው። ››

ደጃዝማች ዑመር ሰመተር የባሕል፣ የሃይማኖትና የቋንቋ ልዩነት ለሀገር አንድነት መሰናክል መሆን እንደሌለባቸው ሲያስገነዝቡም ‹‹ … ቅኝ ገዢዎች በፈጠሩት ክፉ ሴራ አንዳንድ ሀገሮች እየተለያዩ ኖረዋል። የተለያዩትም በመጀመሪያ ከታሪክ ጋር ያልተያያዘ ድንበር በማበጀት፤ ቀጥለውም በሃይማኖትና በጎሳ እየተመካኘ ነው። ባሕል፣ ሃይማኖትና ቋንቋ አንዱን ወገን ከሌላው ሊለዩ የሚችሉ ምክንያቶች አይደሉም። በሕንድ በመቶ የሚቆጠሩ ሃይማኖቶችና ቋንቋዎች አሉ ሲባል ሰምቻለሁ፤ በሌሎቹም ሀገራት እንዲሁ። ይሁን እንጂ ሰዎች የተለያየ ቋንቋ በመናገራቸው ከመሠረታዊ ታሪክ ሊፈናቀሉ አይገባም። አሁንም ኢምፔሪያሊስቶች በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ የሚሸርቡት ሴራ ለታሪክ የተጋለጠ ነው። ጠላትን ተባብረን ከሀገራችን ያስወጣን ኢትዮጵያውያን ቅኝ ገዢዎች ቀብረውት የሄዱት ቦንብ ቀኑን ጠብቆ እየፈነዳ ወገን ከወገኑ ሊፋጅበት አይገባም። እኛ ሱማሌዎችም ከሌሎች ሱማሌዎች ጋር ተባብረን ከአንዲት ኢትዮጵያ ጋር ተቀላቅለን በሠላም መኖር አለብን።

ኦጋዴን በጦር ሜዳ፣ በሐረርም ጠቅላይ ግዛት በአስተዳዳሪነት ስላለሁ እንዳሁኑ የአልጋ ቁራኛ ሳልሆን ከሰሜን፣ ከምዕራብ፣ ከደቡብ እንዲሁም ከመሐል ኢትዮጵያ የመጡ የሀገሪቱን ተወላጆች ተመልክቻለሁ። ከነደጃዝማች ነሲቡ እና ከነደጃዝማች አፈወርቅ ጋር ሆኜ ተዋግቻለሁ። ሌላውን ኢትዮጵያዊ ከኦጋዴን ሱማሌ ወይም ከሌላው ሱማሌ የሚለየው አንዳችም ነገር አይቼ አላውቅም። ባሕል፣ ሃይማኖትና ቋንቋ ሌላ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ምኞቴ በምሥራቅ ክፍላችን ያሉ የተበታተኑ ሱማሌዎች አንድ ሆነው ኢትዮጵያዊነታቸውን ሲያስከብሩ ይታየኛል። በጠመንጃ ሰደፍ ያስወጣነው ጠላት መልኩን ለውጦ ከእናት ሀገር ሊለይ ታሪክ ሠራሽ ሳይሆን ሰው ሠራሽ ችግር እየፈጠረ ነው። ሕዝባችን ይህን ተረድቶ አንድነቱን ማጠናከር አለበት …›› ብለው ተናግረው ነበር።

እነሆ እኝህን ጀግና ታሪክ ሲዘክራቸው ይኖራል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን መጋቢት 8/2016

Recommended For You