በርካታ የሀገራችን ተዋናዮች ከፊልም ለቲያትር የተለየ ፍቅር አለን ይላሉ። ቲያትር ቀጥታ ከተመልካች ጋር ያገናኛልና ዛሬስ መድረክ ላይ ምን ይፈጠር ይሆን? በሚል ሁሌ ልብ ያንጠለጥላል። ደግሞም ከሳምንት ሳምንት ሳያወላዱ ለመድረክ ታምኖ መድረክ ላይ መገኘትን ይሻል። ይህ ሁሉ መስዋዕትነትን ቢያስከፍልም በሀገራችን ከቲያትር የሚገኘው ገቢ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ለዚህም ይመስላል በርካታ የሀገራችን የትወና ዘርፍ ሰዎች ቲያትር መጀመሪያቸው፤ ወደ ዝና መውጫቸው እንጂ የሚቆዩበት ሲሆን የማይታየው።
በሀገራችን የሚገኙ በርካታ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በሀገራችን ″ስለቲያትር የለፋ አንድ ሰው ጥሩ″ ቢባሉ በጋራ የሚጠሩት “ተፈራ ወርቁ″ የሚል ይሆናል። ውልደቱና እድገቱ አዲስ አበባ፣ ቀጨኔ መድኃኒያለም ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን አፍሪካ አንድነት፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ተከታትሏል።
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ በክበባት የነቃ ተሳትፎ ነበረው። የቲያትር “ሀ ∙ ∙ ∙ ሁ″ን እንዲቆጥር በሕይወቱ ውስጥ ሁለት ተስፋዬዎች ትልቅ ቦታ ተጫውተዋል የመጀመሪያው የእውቀት መምህሩ ተስፋዬ ሲማ ነው። የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ከሚማርበትና አራት ኪሎ ከሚገኘው ዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ወደ ሰፈሩ፣ ቀጨኔ መመላለስ የዘወትር ተግባሩ ነበር። በዚህ መሐል ተስፋዬ ሲማ ያስተምርበት የነበረው ቅድስት ማርያም አካባቢ የተለጠፈ “የቲያትር ፍላጎት ያላችሁ ለመሠልጠን ተመዝገቡ″ የሚል ማስታወቂያ ያያል። ለመመዝገብ አላመነታም፤ ተመዝግቦም በርካታ የሥልጠናው ፈላጊዎች ነበሩና በፈተና ተጣርተው ካለፉ ጥቂቶች መሐል አንዱ በመሆን ወደ ስድስት ወር ለሚጠጋ ጊዜ የተሠጠውን ሥልጠና በብቃት ተከታትሏል። በቆይታውም መሠረታዊ የቲያትር ትወና፣ ዝግጅትና የአጻጻፍ ሥልትን ተምሯል። ሥልጠናውን ሲያጠናቅቅ የሎሬት ፀጋዬን “እናት ዓለም ጠኑ” ቲያትር ለታዳሚዎች ተውኖ ተመርቋል።
ከዚህ በመቀጠል የክብር ዶክተር ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ጋ በመሄድ ተጨማሪ እውቀት ቀስሟል። እዛ የመጀመሪያ የመድረክ ሥራው የሆነው ″ሕይወት በየፈርጁ″ ቲያትር ላይ በሀገር ፍቅር አዳራሽ የመተወን እድል ተፈጥሮለታል። ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ የክልል ከተሞች በመዘዋወር ቲያትር ላይ የመሳተፍ እድል ነበረው። ሁለቱ ተስፋዬዎች ለሥራው አስፈላጊው ሥነ-ምግባር እንዲኖረው፤ ሙያውን እንዲወደው አስተዋፅዖ ማድረጋቸውን ያነሳል። ከሁለቱ ተስፋዬዎች በተጨማሪ ከጋሽ አያልነህ ሙላት ጋርም ቀንዲል ቤተ-ተውኔት እያለ በተዋናይነት መሥራቱን ያስታውሳል።
ከተስፋዬ አበበ ክበብ ከወጡ በኋላ የቀሰሙትን እውቀት የሚተገብሩበት መድረክ እንዲሆናቸው በማሰብ ከጓደኛው ብርሀኑ ታዬ (ናፒ) ጋር በመሆን በሀገራችን የመጀመሪያ ቲያትር በሆነው ″ፏቡላ″ የቲያትር ክበብን አቋቁመው መንቀሳቀስ ጀመሩ። በዚህ ሂደትም በርካታ ታዳጊዎችን አቅፈው ወደ መንቀሳቀስ ተሸጋግረዋል። ተሳክቶላቸው በትልቅ መድረክ ቲያትርን ባያሳዩም በየቀበሌ አዳራሾች በመዘዋወር ድራማዎችን ተጫውተዋል። በወቅቱ የቲያትር ቡድኑ አባል ከነበሩት መካከል ተሻለ ወርቁ፣ ቴዎድሮስ ለገሰ፣ ደምሴ በየነ፣ ቅድስት ገብረሥላሴ ተጠቃሽ ናቸው። በሂደት ክበቡ ወደ “ገድሉ አሰግድ የቲያትር ክበብ″ ተሸጋገረ።
ተፈራ ቲያትር ይወዳል፤ ነብስያው ወደ ተዋናይነቱ ብሎም ወደ አዘጋጅነቱ እየሄደ መሆኑ ተሰምቶታል። ቲያትርን መሥራት መፈለግ የሱ ብቻ ፍላጎት ሳይሆን አብረውት እውቀት የቀሰሙ፤ ብሎም በክበብ የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች ፍላጎት መሆኑን ለመረዳት አልከበደውም። ቲያትርን ለመጫወት በሀገራችን የሚገኙት በጣት የማይሞሉ ቲያትር ቤቶች መቀጠር ለበርካቶች ብቸኛ አማራጭ ይመስል ነበር። ቲያትር ቤቶቹ ሁሉንም የመቅጠር አቅም እንደሌላቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። እዚህ ጋ በግል ፕሮዲውስ የሚያደርጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ሚና ይጎላል። ችግሩ ማን መዋዕለ ንዋዩን አፍስሶ፤ ቲያትር ያዋጣኛል ብሎ ፕሮዲውስ ያድርግ። በዘርፉ በርካታ ተዋናይ፣ ደራሲ ብሎም አዘጋጅ አለ። በቂ ቀርቶ ጥቂት የሚባል ፕሮዲውሰርም ማግኘት ከባድ ነበር። ታዲያ ያኔ ያለውን ክፍተት ለመሙላት በማሰብ ″ተስፋ የኪነጥበብ ኢንተርፕራይዝ″ን መሠረተ። ታዲያ ይህ መሆኑ ከትወናውና ከዝግጅቱ አርቆት ቆይቷል። ለቲያትር ካለው ክብር የተነሳ የቲያትር ፌስቲቫል ለበርካታ ጊዜያት አዘጋጅቷል። ከዚህም ባሻገር “ተስፋ አዋርድ″ን በማዘጋጀት ትያትረኞችን በመሸለምም ይታወቃል።
በተፈራ የተቋቋመው ተስፋ የኪነጥበብ ኢንተርፕራይዝ በያዝነው ዓመት 25ኛ የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች በማክበር ላይ ይገኛል። ኢንተርፕራይዙ በ25 ዓመታት ቆይታው 27 ቲያትሮችን ፕሮዲውስ በማድረግ ለተመልካች አቅርቧል። “የቲያትር ተመልካች ሸሽቷል”፤ “የሲኒማ እድገት ቲያትርን ውጦታል”፤ “የቴሌቪዥን ድራማዎች ቁጥር መጨመር የቀነሰውን የቲያትር ተመልካች ቁጥር ይበልጥ አሽቆለቆለው” በሚባልበት ወቅትም ተፈራና ቲያትር ላይለያዩ ቃል የተገባቡ ናቸውና በርካቶች ትግሉ መሯቸው ከመድረኩ ቢርቁም እሱ ግን ለቲያትር እንደታመነ ቆይቷል። በዚህም በሙያ ወዳጆቹ ዘንድ “ተፈራ ለቲያትር የታመነ″ የሚል ሥያሜን አስችሮታል።
ባለፉት 25 ዓመታት ኢንተርፕራይዙ 27 ትያትሮችን ፕሮዲዩስ አድርጎ ለእይታ ያቀረበ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር በበጀት እጥረት ምክንያት ያቋረጠው “የቴዎድሮስ ራዕይ″ ቲያትር ይገኝበታል። ቲያትሩ መጀመሪያ በአማራ ክልል ፕሮዲውሰርነት በባሕርዳር፣ ሙላለም አዳራሽ ሲታይ ቆይቶ በድጋሚ በብሔራዊ ቲያትር አማካኝነት ከአንድ ዓመት በላይ ማሳየት ተችሏል። ትያትሩ ከ150 በላይ ተዋናዮች የሚሳተፉበትና ስለኢትዮጵያ አንድነት የሚያወሳና በብዙኃኑ የሚወደድ ነው። ሆኖም ብሔራዊ ቲያትር በወጪው መብዛት ምክንያት ከአንድ ዓመት በላይ ማሳየት አልቻሉም። ይሄ ቲያትር ተቋርጦ እንዳይቀር በሚል ተስፋ ኢንተርፕራይዝ የቲያትሩን አዘጋጅና ደራሲ ጌትነት እንየው በማናገር በኢንተርፕራይዞች ባልተለመደ መልኩ ማሳየት ችለዋል።
ቲያትሩ መድረክ ላይ በነበረበት ወቅት ከቲያትሩ የመግቢያ ዋጋ በተጨማሪ የተወሰኑ ድርጅቶች ስፖንሰር በመሆን አግዘዋል። በዚህም ለ150ውም ተዋናዮች፣ ለደራሲውና ለአዘጋጁ፤ እንዲሁም፣ ለቲያትር ቤቱ ክፍያ በመፈጸም ምንም እንኳን ኢንተርፕራይዙ ትርፍ ባያገኝም፣ በኢንተርፕራይዝ ደረጃ በርካታ ተዋናይ የሚሳተፍበት ቲያትር ማሳየት እንደሚቻል ለማሳየት መሞከራቸውን ይናገራል። በሀገራችን ኢንተርፕራይዞች ዘንድ ቁጥብ ገጸ-ባሕሪ ያላቸው ቲያትሮችን መምረጥ እንደ ዓላማ የተያዘ መሆኑን በመጥቀስ የእሱ ኢንተርፕራይዝ ግን በትንሹ ስድስት ሰው ከማሳተፍ አንስቶ እስከ 150 ሰው የሚተውንበት ቲያትር እንደሚያሳዩና የቲያትር ተመልካቹ ጥሩ ቲያትር በማየት መደሰት አለበት የሚል አቋም እንጂ ከትርፍ አንጻር ብዙ እንደማይጨነቁ ያነሳል።
የቴዎድሮስ ራዕይ፣ የሌሊት ሙሽሮች፣ ሠማያዊ ዓይን፣ የብዕር ሥም፣ ጥቁር ፈተና፣ የተዋቡ እጆች፣ ፍርሀት፣ ምስጢረኞቹ፣ ያመረቀዘ ልብ፣ የጠለቀች ጀንበር፣ ሩብ ጉዳይ በተስፋ ኢንተርፕራይዝ አማካኝነት ለዕይታ ከበቁ ትያትሮች ጥቂቶቹ ናቸው። ተስፋ የኪነጥበብ ኢንተርፕራይዝ በተለይ በ90ዎቹ ከቲያትርም ባሻገር ትልልቅ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን በማዘጋጀት ትልቅ ሥም ገንብቷል። ኢንተርፕራይዙ ባዘጋጀው ኮንሰርት ላይ ከሙዚቃው ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ አንስቶ እስከ ትንሹ ጥላሁን በመባል እስከሚታወቀው አብነት ግርማ ድረስ ያልሠራ ድምፃዊ የለም። በጥቂቱ ለማስታወስ ያህል፤ ጎሣዬ ተስፋዬ፣ ዓለማየሁ ሂርጶ፣ ቴዲ አፍሮ፣ ላፎንቴኖች፣ ፀጋዬ እሸቱ፣ ተፈራ ነጋሽ፣ ፍቅርአዲስ ነቅዓጥበብ፣ ምኒሊክ ወስናቸው፣ ታምራት ሞላ አብረዋቸው ከሠሩ በርካታ ድምፃውያን መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። ኢንተርፕራይዙ በ1990ዎቹ አንድ ድምፃዊ ካሴት አወጣ ሲባል ኮንሰርት በማሠራት ይታወቃል። ያኔ በዋናነት ኮንሰርቶች ይዘጋጁ የነበሩት በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ነበር። በመሐል በዋጋ መጨመርና ኢንተርፕይራዙ ወደ ቲያትር ይበልጥ በማድላቱ ከሙዚቃ ኮንሰርት ጋር ተለያይተው ቆይተዋል። ተፈራ አሁን ግን እንደ ድሯቸው የሙዚቃ ኮንሰርቶችን ለማዘጋጀት መዘጋጀታቸውንና ለዚህም ከዚህ ቀደም ያካበቱት ልምድ እንደሚያግዛቸው ያነሳል።
ተስፋ ኢንተርፕራይዝ ላለፉት 25 ዓመታት በኪነ-ጥበብ ዘርፍ፤ በተለይ በቲያትርና ሙዚቃ ሰፊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል። በተለያየ ጊዜ የተመሠረተበትን ዓመት ማክበር ቢፈልጉም በተለያዩ ምክንያቶች ይህን ማድረግ ሳይችሉ ቆይተዋል። ዘንድሮ ግን የ25ኛ ዓመት ክብረ-በዓላቸውን ከመስከረም ጀምሮ ማክበር ጀምረዋል። ከበጎ ዓላማዎች ጀርባ የማይጠፋው ተፈራ የድርጅቱን 25ኛ ዓመት ክብረ በዓል በበጎ ሥራ ማክበር ጀምሯል።
ከታኅሣሥ 22 እስከ ታኅሣሥ 28 ቀን 2016 ዓ.ም “በሊፍት ከፍዬ እሳፈራለሁ፤ በጎዳና የሚኖሩ ወገኖቼን አነሳለሁ” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ በተመረጡ ሞሎችና ትላልቅ ፎቆች የሕንጻውን ባለቤቶች በማስፈቀድ ተገልጋዮች አነስተኛ ክፍያ እየከፈሉ እንዲሳፈሩ በማድረግና በዛውም ከታዋቂ አርቲስቶች ጋር የሚተዋወቁበት መድረክ በመፍጠር የተገኘውን ገቢ ለሜሪጆይ እንዲሆን የራሳቸውን አስተዋፅዖ ማበርከት ችለዋል።
የድርጅቱን 25ኛ ዓመት ክብረ በዓል ዓመቱን ሙሉ የመቀጠል እቅድ ሲኖራቸው በዚህም ቲያትር የማሳየት፣ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን የመሥራትና የተለያየ ዝግጅቶችን የማዘጋጀት እቅድ ይዘዋል። የመጨረሻው በዓል ግንቦት 26 በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር ሲሆን፤ ከዛ ቀድሞ ሚያዝያ 28 የቲያትር ፕሮግራም ይኖራቸዋል።
ድርጅቱ ቲያትር ላይ እንደመቆየቱ የተመረጡ ቲያትሮችን የማሳየትና ክብረ በዓሉ ቲያትርን ማዕከል ያደረገ እንዲሆን ታቅዷል። በ25ኛ ዓመት የበዓል መዝጊያ ፕሮግራም ላይ አንጋፋ ባለሙያዎች የሚከበሩበትና የሚሸለሙበት ከድርጅቱ ጋር አብረው የሠሩ ድርጅቶች የሚሸለሙበት የምስጋና ፕሮግራም በመሆን ግንቦር 26 ቀን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር በሙዚቃና በቲያትር በታጀበ መልኩ ተጋባዥ ሰዎች ባሉበት ለማክበር ማሰባቸውን ይገልጻል።
የጥበብ ዓለምን ሲቀላቀል ጅማሬው በትወና ቢሆንም አሁን ግን ዋነኛ የተፈራ መታወቂያው ፕሮዲውሰርነቱና የቲያትር አዘጋጅነቱ ሆኗል። በርካታ ትያትሮች ላይ በትወና ሲሳተፍ የቆየ ቢሆንም በቴሌቪዥን መስኮት ግን “ዳና″ ድራማ ላይ ብቻ መተወኑን ይናገራል። ቢሆንም ድራማው ረዥም ጊዜ በመቆየቱና የተለየ ገጸ-ባሕሪን ይዞ በመተወኑ ከአንዳንድ ተመልካቾች ጠፋህ የሚል አስተያየት ይደርሰዋል። ሆኖም በርካታ ድራማዎችን ባለመሥራቱ ለብዙኃኑ እንግዳ መሆኑን፤ የሱ እውቅና በብዛት በዘርፉ ያሉ ሰዎች ጋር እንደ ሆነ ይናገራል። በርካታ ቲያትሮች ላይ ተውኗል፤ ቲያትር አዘጋጅቷል፤ ጽፏል። ከዚህም ባሻገር የሙዚቃ ኮንሰርቶችን በማዘጋጀት ይታወቃል። ያም ቢሆን ከትወና ዓለም መራቁን በማስመልከት “በብዙኃኑ ዘንድ ጠፋህ የምባል ተዋናይ አይደለሁም፤ ምክንያቱም ቲያትሮች ላይ እንጂ በፊልምና በቴሌቪዥን ትወና ብዙ አልሠራሁምና” ይላል። ሆኖም የቲያትር መድረኮች ላይ በተዋናይነት የመመለስ እቅድ አለው።
ለበርካቶች ቲያትር መነሻቸው እንጂ መድረሻቸው አይደለም። ለተፈራ ግን ቲያትር መነሻው ብቻ ሳትሆን መድረሻውም ነች። ″በርካቶች ከገቢውም ጋር ተያይዞ መዳረሻቸው ፊልም ሲሆን እያየን ነውና አንተስ ምን አስበሀል?″ አልነው። እሱ ግን አሁንም ሀሳቡ ከቲያትር አልወጣም። “እኔ ቲያትር በጣም እወዳለሁ፤ ለዚህም ቲያትርን እንድወድ ያደረጉኝ መምህራንም አሉ። ከዚህም በተጨማሪ ከልጅነቴም አንስቶ በብዛት የሠራሁት ቲያትርን ነው። ” ይላል። ስለዚህም ሀሳቡ ቢሳካላት ቲያትርን ፕሮዲውስ ከማድረግም በዘለለ የግል ቲያትር ቤት እስከማቋቋም ያልማል። ኢንተርፕራይዙ 25 ዓመት የቆየ ቢሆንም ምን አለው? ሲባል መልሱ ምንም ነው። ሥም ከመትከል ውጭ ከኢኮኖሚ አንጻር የተጠቀመው ነገር አለመኖሩን ያነሳል። ያም ቢሆን ያለማቋረጥ መሥራታቸውንና ሌላው ቀርቶ በኮቪድ ጊዜ ተመልካች ባልነበረበትም ወቅት ቲያትርን መሥራት ቀጥለዋል። በርካታ ተዋንያንና ሌሎች ባለሙያዎችም በኢንተርፕራይዙ አማካኝነት የመሥራት እድል ማግኘታቸውና መታወቃቸው እርካታ ይሰጠኛል ይላል።
በአሁኑ ወቅት በብሔራዊ ቲያትር የሎሬት ፀጋዬ ድርሰት የሆነው “ሀሁ ወይም ፐፑ″ ቲያትር በቀድሞ መምህሩ ተስፋዬ ሲማ ተዘጋጅቶ በተስፋ ድርጅት ፕሮዲውስ ተደርጎ ብሔራዊ ቲያትር በመታየት ላይ ይገኛል። ድርጅቱ ከተመሠረተበት ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ ያለማቋረጥ ቲያትር እያሳየ ዘልቋል። ለዚህም ሙያውን መውደድና ማፍቀር ካልሆነ በስተቀር የተለየ የኢኮኖሚ ጥያቄም፤ ጥቅምም አልነበረውም። ቲያትርን ትቶ ወደ ሌላ ዘርፍ መሄድ የማይታሰብ ሆኖበታል። አንድ ጊዜ ፊልም መሥራታቸውን በማስታወስ ፊልም ለኛ የሚሆን አይደለም″ በማለት መተዋቸውን ይናገራል።
25 ዓመት ሙሉ ከቲያትር ጋር ቢቆራኙም በርካታ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ያነሳል። የተዋናይ ልምምድ ተጠናቆ መድረክ የሚጠብቅ ቲያትር በግምገማ መውደቅ፤ የተዋናይ መቅረት ከፈተናዎቹ መሐል ይገኙበታል። ከዚህ ቀደም “ወርቃማ ፍሬ″ የተሰኘ ቲያትር ዝግጅቱ ተጠናቆ በአዲስ አበባ ቲያትርና ባሕል አዳራሽ ለገምጋሚዎች ሲቀርብ “ቲያትር ቤታችንን አይመጥንም″ በሚል እንዳይታይ መወሰኑን ይናገራል። በዚህ ሰዓት ለቲያትሩ የተመለመሉ ተዋናዮች ረዥም ጊዜ ሰጥተው ተለማምደዋል፤ ለቲያትሩ የሚያስፈልጉ በርካታ ግብዓቶች ግዢ ተፈጽሟል። ሆኖም ከምንም በላይ ያሳሰበው የተዋናዮቹ ሞራል ነበር፤ የለፉት ተዋናዮች ለፍተው ሜዳ ከሚቀሩ በሚል በወቅቱ ይሠራበት በነበረው ሜጋ ቲያትር ለተወሰነ ጊዜ እንዲታይ አድርጓል። ረዥም ጊዜውን ለቲያትሩ ሰጥቶ የተለማመደ ተዋናይ ቲያትሩ ወደ መድረክ ሊወጣ ሲል መታመም ከሳንካዎቹ መሐል ይገኝበታል። በመንግሥት ቲያትር ቤቶች ያለው ዝቅተኛ የመግቢያ ዋጋ በዘርፉ ለመቆየት አበረታች አለመሆኑን ይናገራል።
ያኔ ተፈራ ኮንሰርት በሚያዘጋጅበት ወቅት ከአንጋፋ ድምፃዊያን አንስቶ ገና ብቅ ያሉ ድምፃውያንን ከማሳተፉም ባሻገር በኮንሰርቶቹ ላይ የአስቂኝ አለባበስ ትርዒት፣ የጥርሰ ወላቃዎች ውድድር፣ የዳንስ ውድድር በተጓዳኝ በማዘጋጀት ኮንሰርቱን ወደ አዝናኝ ሁነት የመቀየር ልምድ ነበራቸው። በተጨማሪም በድምፁ እንጂ በመልክ የማይታወቅ የነበረውን አለምነህ ዋሴ መድረክ መሪ እንደሚሆን በማስተዋወቅ፤ እንዲሁም በ“የማዕበል ዋናተኞች″ የሬዲዮ ድራማ ዝነኛ የነበሩት በገጸ-ባሕሪ ሥማቸው እፁብና ጌትን እንግዳ እንደሚሆኑና የተለያዩ የማስታወቂያ መንገዶችን ስለሚጠቀም የሱ ኮንሰርት ሁሌ ሙሉ ነበር። በቀጣይ ወደ ጠፉበት ኮንሰርት በመመለስ ኮንሰርቱን እያዘጋጁ በሚያገኙት ገቢ ቲያትሩን የመደጎም እቅድ አላቸው።
ተፈራ ለቲያትር ካለው ፍቅር እኩል የሚነሳው በኪነ-ጥበብ ዓለም ያሉ ሰዎች ሲቸገሩ ቀድሞ በመድረስ ነው። ለዚህም በቅርቡ በሞት ያጣነው ዳይሬክተር አሸብር ሀብታሙ በሕመም ምክንያት ሥራ ፈቶ ችግር ላይ በወደቀበት ወቅት ቀድሞ ከደረሱት ሰዎች መሐል አንዱ ነው። ያኔ የቴዎድሮስ ራዕይ ቲያትርን የአንድ ቀን ገቢ ለሱ እንዲውል በማድረግ ለሙያ ባልደረባው አጋርነቱን በተግባር አሳይቷል። ለሙያ ባልደረቦቹ የሚደርሰው “በችግሬ ሰዓት ይደርሱልኛል ብዬ ሳይሆን ለሕሊናዬ ብዬ የማደርገው ነገር ነው። ሆኖም የዚህን ውጤት በቅርቡ እናቴ ያረፈች ጊዜ አይቸዋለሁ። ” ይላል። የሱን ኃዘን ኃዘናችን ነው ብለው ከጎኑ የተገኙ ባልደረቦቹ በመብዛታቸው የተነሳ አስር ቀን ሙሉ ድንኳን ሳይፈርስ ኃዘን ለመቀመጥ ተገደዋል።
ለግለሰብ ችግር ከመድረስ ባሻገር ለሀገራዊ ዓላማም መድረስ የተፈራ መታወቂያው ነው። ″ሩብ ጉዳይ″ ቲያትር በተፈራ ወርቁ ድርጅት እይታ ላይ የሚገኝ ቲያትር ነበር። በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተከስቶ በነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት የተጎዱ ወገኖችን ለማሰብ “ሩብ ጉዳይ ለሀገር ጉዳይ” በሚል በትያትሩ ደራሲ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ የሚመራ የጋዜጠኞች ቡድን ሀሳቡን ይዞ የቲያትሩ አዘጋጅና ፕሮዲውሰር የሆነው ተፈራ ጋር ይመጣሉ። በሀሳቡ በመስማማት ሀሳቡን በጋራ አበልጽገው የቲያትሩ ተዋናዮች ጭምር ከፍለው ያዩት የመጀመሪያው ቲያትር በመሆን በርካታ ገቢ ማስገኘት ተችሏል። ተፈራም አዘጋጅና ፕሮዲውሰር ነኝ ሳይል ቲያትሩን ከፍሎ ታድሟል። ከቲያትሩ የተገኘውን ገቢ በአይነት እቃ በመግዛት ለተቸገሩ ወገኖች ቦታው ድረስ ማድረስ ችለዋል። በአሁኑ ወቅት ተፈራም ሆነ ኢንተርፕራይዙ የድርጅታቸውን 25ኛ ዓመት ማክበር ላይ ሙሉ ትኩረታቸውን ማድረጋቸውን በማንሳት በዓሉ እንደተጠናቀቀ በአዳዲስ ቲያትሮችና የሙዚቃ ዝግጅቶች ለመምጣት እየተዘጋጁ መሆኑን ይናገራል። እኛም እንኳን ለ25ኛ ዓመት የምስረታ በዓላችሁ አደረሳችሁ! በማለት አበቃን።
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን መጋቢት 8/2016