ከዓባይ ግድብ 13ኛ ዓመት ባሻገር፤

የተለያዩ ቆየት ያሉ የጥናትና የምርምር ወረቀቶች መሠረት ሀገራችን ኢትዮጵያ በመስኖ መልማት ከሚችለው መሬት ውስጥ ግማሽ ያህሉ የሚገኘው በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ ነው። የሚያስቆጨው ደግሞ እስካሁን የለማው ከ6 በመቶ አለመብለጡ ነው። እንደሚታወቀው የሀገራችን ግብርና የዝናብ ጥገኛ ነው። ኢትዮጵያም የአፍሪካ የውሃ ማማ በመባል ብትታወቅም፤ በየዓመቱ ሊባል በሚችል ሁኔታ በድርቅ እየተጠቃች ነው።

በተለይ በየአስር ዓመቱ ይከሰት የነበረው ድርቅ በበልግና በመኸር በዓመት ሁለት ጊዜ ሲጎበኘን እየተመለከትን ነው። በዚህ ያልተስተካከለና የሚቆራረጥ ዝናብ ምክንያት የሚከሰት ድርቅ ደግሞ ሚሊዮኖች ለምግብ እጥረት እንዲዳረጉ እያደረገ ነው ። ይሄ የሚሆነው ግን ኢትዮጵያ የዓባይ እናት ብትሆንም፣ ከግማሽ በላይ በመስኖ መልማት የሚችለው መሬቷ በዚሁ ተፋሰስ ቢገኝም፣ ወንዙን እና መሬቷን ለግብርና ልማት ሥራ ማዋል ሳትችል በመቆየቷ ነው።

ይሄን ላለማድረጓ የራስ ድክመት ካልሆነ በስተቀር፤ የዓባይ ወንዝን እንዳትጠቀም እንቅፋት የሚሆን ስምምነት ከማንም ጋር የላትም። በውል እንደሚታወቀውም ሀገራችን ከግብፅም ሆነ ከሱዳን ጋር የዓባይን ወንዝ በጋራ መጠቀም የሚያስችል ስምምነት እንኳን የላትም። ሆኖም ለዓባይ/ናይል ወንዝ 86 በመቶውን ውሃ የምታበረክተው ኢትዮጵያ፤ በ1929ኙም ሆነ በ1959ኙ የቅኝ ገዢ ስምምነት የማትገዛ/የማይመለከታት እንደመሆኑ ከ1950ዎቹ ጀምሮ በወንዙ ላይ የኃይል ማመንጫና የመስኖ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ተደጋጋሚ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች ።

እኤአ ከ1958 እስከ 1963 ድረስ አሜሪካ በኢትዮጵያ በኩል የዓባይን ወንዝ ለማልማት በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ ነበረች። ጉዳዩ ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅ የለም እንዲሉ ሆኖ እንጂ፤ የዛሬውን ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ጨምሮ 33 የመስኖና የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በተለያዩ አከባቢዎች አጥንታ እንዲለሙ ምክረ ሀሳብ አቅርባ ነበር። ከእነዚህ ጥናቶች ሥራ ላይ የዋለው እኤአ በ1972 ዓ.ም የተገነባውና 128 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው የፊንጫ የውኃ ኃይል ቀዳሚ ነው ማለት ይቻላል ።

ኢትዮጵያ በአንድ በኩል ድርቅ፣ በሌላ በኩል ፈጣን የሕዝብ ቁጥር እድገት ያለባት ሀገር ናት። ከዚህ አኳያ የውሃ ሀብቷን አልምታ መጠቀም አለባት። ለዚህም የመስኖ መሠረተ ልማትን በማስፋት እያደገ የመጣውን የሕዝብ ቁጥርና የምግብ ፍላጎቷን ለማጣጣም መትጋት፤ ሕዝቧን ከተመፅዋችነት ማላቀቅ ይጠበቅባታል። ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለምታደርገው ሽግግር፣ እንዲሁም በኩራዝ ጭስ ለሚጨናበሰው ከ60 ሚሊዮን ለሚበልጠው ሕዝቧ የኤሌክትሪክ ኃይልና መብራት ለማቅረብ እንደ ዓባይ ያሉ ዓመቱን ሙሉ የሚፈስሱ ወንዞቿን ገድባ መጠቀም የሞት ሽረት ትንቅንቅ እየሆነ መጥቷል ።

ኢትዮጵያ ወንዞቿን ተጠቅማ ልማቷን ከማፋጠን ባሻገር፤ ለተፋሰሱ ሀገራት የኃይል አማራጭ የመሆን እምቅ የተፈጥሮ ፀጋ አላት። ይሁንና እስከቅርብ ዓመታት ድረስ በድህነቷ እንዲሁም ከዓለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ብድርና ድጋፍ ለማግኘት የምታደርገው ጥረት በግብፅ የተቀናጀ ስውርና ይፋ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ የተነሳ እቅዷ ሁሉ ይጨናገፍባት ስለነበር ግዙፍ የኃይል ማመንጫዎችንና ታላላቅ የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታዎችን ማካሄድ ሳትችል ቀርታለች። የሚያሳዝነው ለኢትዮጵያ ሲሆን የሚታጠፈው የዓለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እጅ ለግብፅ ሲሆን ግን ያለስስት ይዘረጋል። ለጋስ ይሆናል ።

ግብፅም ይህን በመጠቀም ኢኮኖሚዋን ማሳደግ ችላለች። በዚህም የሀገር ውስጥ ጥቅል ምርቷ 235 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ፤ የዜጎቿ የነፍስ ወከፍ ገቢ 2ሺህ 440 ዶላር ደርሷል። የኢትዮጵያ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት ከ164 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሲገመት፤ የነፍስ ወከፍ ገቢዋ ደግሞ ወደ 1500 ዶላር ይገመታል። ከዚህ የድህነት አረንቋ ወጥቶ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የተፈጥሮ ሀብቷን በተለይ የውሃ ሀብቷን በአግባቡ ማልማት ይኖርባታል።

ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ያላት የሕዝብ ብዛት ከግብፅ ሕዝብ ቁጥር ስለመብለጡ ይነገራል። ይሄ ደግሞ የምግብና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያስፈልገው ሕዝብ ቁጥር እና ይሄን ለማሟላት መሠራት ያለበትን ሥራ ለመረዳት የሚያስችል ነው። እናም ከግብፅ በላይ የውሀ ሀብቷን ለመስኖና ለኃይል ማመንጫ መጠቀም ይኖርባታል ማለት ነው። በግዛቷ ስር ያለ የውሃ ሀብቷን መጠቀም ደግሞ ሉዓላዊ መብቷ ነው። ሆኖም የፋይናንስ እጥረትና የቴክኖሎጂ ውስንነት ዘርፉን ለማልማት የተያዘውን እቅድ ፈታኝ ቢያደርገውም ተጨማሪ የውሃ ኃይል ማመንጫዎችንና የመስኖ አውታሮችን መገንባት ቅድሚያ የተሰጠው ተግባር ሆኖ ይቀጥላል። ቁልፉም የእድገትና የልማት ግብ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሁለንተናዊ መልኩ ድህነትን መቅረፍ ነው።

በ2003 ዓ.ም ከሱዳን ድንበር 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ግንባታው የተጀመረውና ለኃይል ማመንጫነት የሚውለው፣ 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ የሚይዘው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እድገትንና ልማትን በማፋጠን ዜጎችን ከድህነት የማላቀቅ ራዕይን ሰንቋል ። ግድቡ በቀን እስከ 6ሺህ ሜጋ ዋት፣ በዓመት 15ሺህ 130 ጊጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አለው። በዚህም የሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎትን በማርካት ለምስራቅ አፍሪካ በተለይ ለራስጌ ተፋሰስ ሀገራትም የማቅረብ እቅድ አለው ።

ግድቡ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኘውን የታዳሽ ኃይል ተደራሽነት ያሳድጋል። የዓለም ባንክ ጥናት እንደሚያመለክተው ከሰሐራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የታዳሽ ኃይል ሽፋን ከ15 በመቶ በታች ሲሆን፣ የሀገራችን 3 ነጥብ 5 በመቶ፣ የሱዳን 41 ነጥብ 3 በመቶ፣ የግብፅ 97 ነጥብ 6 በመቶ ነው ከሰሐራ በታች ያሉ ሀገራት የኤሌክትሪክ ሽፋን 24 በመቶ፤ የኢትዮጵያ ከ45 በመቶ ያልበለጠ፣ የሱዳን ከ57 በመቶ ያልበለጠ ሲሆን፤ የግብፅ ሽፋን ግን 100 በመቶ ደርሷል ።

በዓባይ/ናይል ውሃ አጠቃቀም ላይ ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶችን በመጥቀስ ብቸኛ ባለመብትና ተጠቃሚ እኔነኝ በማለት የያዘችው ግትር አቋም የራስጌ ሀገራት በዓለማቀፍ ሕግ የተረጋገጠላቸውን ውሃውን በፍትሐዊነት የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብት የሚጥስ ስለሆነ በንግግርና በውይይት ካልተፈታ ለግጭት ሊዳርግ ይችላል ተብሎ እየተፈራ ነው።

የዓባይ ወንዝ እርዝመት 6ሺህ 650 ኪሎ ሜትር ይጠጋል። የተጠቃሚው ሕዝብ ቁጥር አንድ ላይ ቢደመር ወደ አምስት መቶ ሚሊዮን ይደርሳል። ኢትዮጵያ እና ግብፅን በዲፕሎማሲው መስክ በተደጋጋሚ በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲገናኙ እና እንዲነጋገሩ አድርጓል። ሆኖም ግብፅ የምታቀርበው ሀሳብ ሰጥቶ ለመቀበል ዝግጁ አለመሆኗን በተደጋጋሚ አሳይቷል። ግብፅ የህዳሴው ግድብ 40 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውኃ በየዓመቱ ይልቀቅ በሚል ያቀረበችው ሐሳብ በአብነት ይወሳል። የኢትዮጵያ ወገን ተደራዳሪዎች ልዑካን መሪ አምባሳደር ስለሽ በቀለ ተቀባይነት የሌለው ጥያቄ መሆኑን በጊዜው ምላሽ ሰጥተዋል። የናይል ወንዝ ለኢትዮጵያ፤ ግብፅ እና ሱዳን የመኖር እና ያለመኖር ጥያቄ እንደኾነ በበርካታ ታዛቢዎች ይነገራል። እናም ሦስቱ ሃገራት ተገናኝተው ፍትሐዊ አጠቃቀም ላይ ቁጭ ብለው መነጋገር ይጠበቅባቸዋል ።

ግብጽ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ከባዱ የክረምት ወቅት ሲጀምር እየጠበቀች ተፅዕኖ ማሳደር ይችላሉ በምትላቸው ሀገራትና ተቋማት በኩል በውሃ አጠቃቀሙ ዙሪያ አሳሪ ስምምነት እንዲደረግ ግፊት ስታደርግ ቆይታለች ። ግብፅና ሱዳን፣ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ኢትዮጵያ ግድቡን መሙላት አትችልም የሚል ተቃውሞና ማስፈራሪያቸውን ቢገፉበትም ኢትዮጵያ 4ኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት አጠናቃለች። በግድቡ የተወዛገቡት ኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን ተከታታይ ድርድርና ውይይት ሲካሄዱ ቢቆዩም እስከአሁን ይህ ነው ከሚባል ስምምነት ላይ አልደረሱም።

ሱዳንና ግብፅ ሦስቱ ሀገራት በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በሚያደርጉት ድርድር ከአፍሪካ ኅብረት ውጪ ሌሎች ሀገራትና ዓለማቀፋዊ ተቋማት እንዲሳተፉ በተደጋጋሚ ሲወተውቱ የቆዩ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ግን በአደራዳሪነት ከአፍሪካ ኅብረት ውጪ ማንንም እንደማትቀበል እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ግን ሊኖሩ እንደሚችሉ ስትገልጽ ቆይታለች በዚህም በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነትና በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ታዛቢነት ሲካሄድ የከረመው ድርድር ተጨባጭ ስምምነት ላይ መድረስ ሳይችል ቀርቷል። ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ድርድር ሰበብ የዓባይን ወንዝ ተጠቃሚነቷን የሚገድብ ስምምነት እንደማትቀበል በተደጋጋሚ ገልጻለች ።

ኢትዮጵያ በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም የመጀመሪያ የግድቡን ሙሌት በማካሄዷ ሳቢያም የትራምፕ አስተዳደር ለሀገሪቱ ከሚሰጠው እርዳታ ላይ ቅነሳ እንደሚያደርግ በማስታወቅ ሀገሪቱ ከአሜሪካ ታገኝ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ ማስቀረቱ አይዘነጋም። በዚያው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የተካሄደውን 2ኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ተከትሎ ግብፅና ሱዳን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ለተከሰተው አለመግባባት በተመሳሳይ ጉዳይ ቀደም ሲል ባልታየ ሁኔታ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አቤቱታ አቅርበው፤ ምክር ቤቱ ሐምሌ 2013 ዓ.ም በጉዳዩ ላይ ለመምክር ተሰበስቦ ነበር።

ኢትዮጵያም በህዳሴው ግድብ ጉዳይ የፀጥታው ምክር ቤት መወያየቱን እንደማትቀበለው በማስታወቅ ጉዳዩ ቀደም ሲል በተያዘበት የአፍሪካ ኅብረት በኩል መቋጫ እንዲያገኝ ጠይቃለች። ይህ ጥያቄዋ ተቀባይነትን አግኝቶ ምክር ቤቱ ጉዳዩ በአፍሪካ ኅብረት በኩል ሊታይ ይገባል የሚል ውሳኔ ማሳለፉ አይረሳም። ሆኖም ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው ግብፅ ይሄን ሀሳብ ለመቀበል ዝግጁ አልሆነችም ።

እንደ ማጠቃለያ

ለዓባይ/ናይል ወንዝ 86 በመቶ ውሃ የምትገብረው ኢትዮጵያ ፍትሐዊ በሆነ አግባብ ውሃውን የመጠቀም መብቷ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። ይሁንና ግጭትንና አለመግባባትን ለመፍታት ሰባቱ የራስጌ የተፋሰስ ሀገራት የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ አዳዲስ ውሎች ሊተኩ እንደሚገባ የሚጠይቀውና በ2002 ዓም የተፈረመውን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (Cooperation Framework Agreement / CFA) ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል ።

ስምምነቱን የተፈራረሙ ሀገራት ብሩንዲ ኬኒያ፣ ዑጋንዳ፣ ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያና ሩዋንዳ ሲሆኑ የትብብር ማዕቀፉ የናይልን ወንዝ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መጠቀምን የሚያረጋግጥና ዋስትና የሚሰጥ ቋሚ ኮሚሽን እንዲቋቋም የሚጠይቅም ነው። ዳሩ ግን ሱዳንና ግብፅ ይህን የትብብር ማዕቀፍ ለመፈረም ፈቃደኛ ባይሆኑም በ2007 ዓ.ም በግብፅ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተፈረመውን የመርሆዎች መግለጫ (Declaration of Principles) ፈርመዋል ።

በዚህ ስምምነት ሱዳንና ግብፅ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን የተቀበሉ ሲሆን ኢትዮጵያም ግድቡ በግርጌ ተፋሰስ ሀገራት ማለትም በግብፅና በሱዳን ሊያሳድረው የሚችል ተፅዕኖ ወይም ጉዳት ካለ ጥናት እንዲደረግ ተስማምታለች። በዚህ ስምምነት ላይ ተከታታይ ውይይቶች የተካሄዱ ሲሆን ተስፋም ተጥሎባቸው ነበር። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ትብብር አብነት የሚሆንና የራስጌ ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ስለሆነ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል። ግብፅም በግድቡ ውሃ አሞላል ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ጀምራ ወደነበረው ድርድር ብትመለስ ሀገራቱን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል መግባባት ላይ መድረስ ይችላል ።

ሻሎም ! አሜን ።

አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You