ከዛሬው ችግር ባሻገር ለሚገለጹት የከተማዋ የልማት ሥራዎች

ጉዞአችን ከአራት ኪሎ ወደ ሜክሲኮ ነው፡፡ ከጎኔ የተቀመጡት አንድ የእድሜ ባለፀጋ የመንገዱን ግራና ቀኝ በአግራሞት ይቃኛሉ፡፡ የማናችንንም ትኩረት አልፈለጉም፡፡ አካባቢው አሁን ላይ ያለውን ይዘትና ቀድሞ የነበረውን ሁኔታ እያነፃፀሩ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ነበር የሚናገሩት፡፡ እኔ ግን በጆሮዬ ጨዋታቸውን እያደመጥኩ፤ ሃሳባቸው በውስጤ ከሚፈጥሩብኝ ጥያቄዎች ጋር እያገናዘብኩ ነበር የሰማኋቸው፡፡

እኚህ አዛውንት በአካባቢያቸው ላሉት ሰዎች ሲናገሩ ባደመጥኩት መሠረት፤ አሁን ሳይንስ ሙዚየም የተገነባበት አካባቢ የእህል ወፍጮ አገልግሎት የሚሰጥበት ቦታ ነበር፡፡ በወቅቱ ወፍጮ ቤቱ ለቤተ መንግሥቱ አገልግሎት እንዲሰጥ ነው የተተከለው፡፡ አካባቢው ከፊሉ ጫካ፤ ከፊሉ ደግሞ ሜዳ የነበረ ነው፡፡

ስለ ታሪኩ ለመረዳት ካለኝ ፍላጎት አኳያ ባደረግናቸው የሃሳብ ምልልሶች እንዳጫወቱኝ፤ እርሳቸው በዚህ አካባቢ ኳስ ለመጫወት ያዘወትሩ ነበር፡ ፡ ግርምት የፈጠረባቸውም የዛኔ የሚያውቁት ቦታ እና አሁን ላይ ያለው የአካባቢው ይዞታ ነበር፡፡ በእርሳቸው ዘመን በዚህ መልኩ ከፊሉ ሜዳ፣ ከፊሉ ጫካ ሆኖ የቤተመንግሥት ወፍጮ ቤት የነበረበት ቦታ ታዲያ በእኔ ዘመን የተወሰነ ለውጥ ነበረው፡፡

ምክንያቱም፣ ከሳይንስ ሙዚየም ጀምሮ አሁን ለፓርክ የለማውና ወዳጅነት ፓርክ ተብሎ የተሰየመው ስፍራ፤ ፊትበር በመባል የሚታወቅ፤ ከጭቃ በተሠሩ ቤቶች ውስጥ ሰፊ ቁጥር ያለው ነዋሪ ነው የነበረበት፤ ፊትበር የሚባል ጉሊት(ገበያ) የነበረውም ነው፡፡

በስፍራው የነበሩት መኖሪያ ቤቶችም ጥቂት የሚባሉት ካልሆኑ በስተቀር የተጎሳቆሉ ነበሩ፡፡ ለእይታም ለመኖሪያም የሚስቡ አልነበሩም፡፡ ሆኖም ነዋሪውም አንዳንዱ ተወልዶ አድጎበት፣ አግብቶ፣ የልጅ ልጅም ያየበት ስለሆነ እንከኑ አይታየውም፡፡ ነገር ግን ለመኻል ከተማ ቅርብ በመሆናቸው፣ ቤተመንግሥት አካባቢ እንደመገኘታቸው መገኘታቸው መስህብ አልነበራቸውም፡፡

በተለይ አካባቢው ላይ መጠጥ ቤቶችም በስፋት ስለነበሩ ሁካታና ግርግሩ በዚያው ልክ ነው የነበረው፡፡ ሆኖም አሁን ላይ ሆኖ ሲታሰብ ጭንቅ ያለ ስሜት ያለው አካባቢ እንደሆነ ይሰማን እንደሆን እንጂ፤ በጊዜው ግን ከማህበረሰቡ ጋር የተዋሀደ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በአካባቢው በስም የሚታወቁ ስጋ ቤቶችና ምግብ ቤቶች ብቻ አልነበሩም፤ ይልቁንም የሴተኛ አዳሪዎች ሰፈር ተብለው እንደመለያ የሚጠሩም ነበሩ፡፡ እናም ይህን አካባቢ ነው፣ እንኳን ለማያውቀው ለሚያውቀውም ትዝታው እስኪጠፋው ተለውጦ እኝህን አዛውንት ያስደመማቸው፡፡

እኝህ በሸገር የከተማ አውቶቡስ ውስጥ ያገኘኋቸው አዛውንት፤ አካባቢው ላይ የተገነቡት ሕንፃዎች የነማን እንደሆኑ ጭምር ነበር ታሪክ ሲነግሩኝ የነበረው፡፡ ለምሳሌ፣ አሁን ፒያሳ ጣይቱ ሆቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ስቴድየም አካባቢ ነበር፡፡ ከእኝህ ሰው ጋር በነበረን አጭር የጉዞ ቆይታ እነዚህንና ሌሎችንም በርካታ የከተማዋን ታሪኮች ለመስማት የቻልኩት፡፡

በዚህ ረገድ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያየ ታሪክ ያላቸው በርከት ያሉ አካባቢዎች ተለውጠዋል። እየተለወጡም ነው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ መኖሪያ ቤቶች ሳር ቤት እንደነበሩ፣ የትራንስፖርት አገልግሎቱም ፈረስና ጋሪ እንደነበር፤ ከተማዋ በሂደት እየተለወጠች አሁን የምትገኝበት ላይ እንደደረሰች ደግሞ በታሪክ አዋቂዎች በቃል ከሚነገረው በተጨማሪ፣ የታሪክ ሰነዶችና ድርሳናትም ያስረዳሉ፡፡

ሆኖም በከተሞች እድገትና ለውጥ ውስጥ የሚነሱ ሃሳቦች አልታጡም፡፡ በዚህ ረገድ ሁሉም ጊዜውንና ዘመኑን ማድነቁ፣ ለውጥም ሲኖር ለምን የሚል ጥያቄ ማንሳቱ አይቀሬ ነው፡፡ ከታሪክ ጋር በማያያዝ አንድ ከተማ ከየት ተነስቶ የት ደረሰ ብሎ ለማነፃፀር የሚያስችል ነገር መኖር አለበት የሚል ወገን አለ፡፡ ይህን ሃሳብ የሚያነሱ ሰዎች ሲያልፉና ሲያገድሙ የሚያዩትና የለመዱት አካባቢ ሳያዩት እንኳን በዓይነ ህሊናቸው መግለጽ ይችላሉ፡፡ ለአብነትም ከአራት ኪሎ እስከ ፒያሳ ባለው የሚታወሱ ብዙ ነገሮችን ማንሳት ይቻላል፡፡

ፖስታ ቤት፣ ጆሊባር፣ ሰባደረጃ፣ ራስመኮንን ድልድይ፣ ወደ ፒያሳ ሲሻገሩ ደግሞ ወርቅ ቤቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ የፒያሳ ወርቅ ቤቶች ውበታቸው ፊትለፊታቸው እንጂ በጀርባቸው ያሉት መኖሪያ ቤቶች የተጎሳቆሉ ናቸው፡፡ ለየት የሚያደርገው ታሪክ ወርቅን የሚያክል ሀብት ባረጀ ሰፈር ውስጥ ያለስጋት ለረጅም ዓመት ግብይት መከናወኑ ነው፡፡

በሌላ በኩል፣ የተጎሳቆለ ከተማ በአዲስ መተካት እንዳለበት የሚያምን፣ አስታራቂ ሃሳብ የሚያቀርበው ወገን አካባቢው መለወጡን ይደግፋል፡፡ ነገር ግን የነበረውን ነገር የሚያስታውስ መኖር አለበት የሚል እምነት አለው፡፡ ማስታወሻው በስም ስያሜ፣ አለያም በፎቶግራፍ ሲሆን፤ አንዳንዱም እንደ ፋይዳው ታይቶ የቅርጽ ለውጥ ሳያመጣ ዘመኑን የሚመስል እድሳት ተደርጎለት ለታሪክ ምስክርነት ይኑር የሚል ነው፡፡

ከዚህ አኳያ ሲታይ መልሶ ማልማት ሥራው የሕዝብና የምሁራን ሃሳብ ወይንም አስተያየት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ረገድም መንግሥትን የሚወቅሱም አልጠፉም፡፡ ሊታወቅ የሚገባው በመንግሥት ተደጋግሞ የሚነሳው በተለይም ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር በተያያዘ እንደስሟ ውብና ጽዱ ሆና እንድትታይ፣ በዓለም ካሉ አቻ ከተሞች ጋር የተመጣጠነ የከተማ ይዘት እንዲኖራት፣ ዓለም አቀፍ ኩነቶች የሚከናወኑባት በመሆኗ ጭምር ከተማዋን የሚመጥን የልማት ሥራ ያስፈልጋታል፡፡

ምክንያቱም በእቅድ(በፕላን) ያልተገነቡ ቤቶችና የንግድ ቦታዎች መኖር ለመንገድ መሠረተ ልማት አጠቃቀም አስቸጋሪ አድርገውታል፡፡ የእግረኛና የተሽከርካሪ መንገዶችን ለመለየት እንኳን ያልተቻለባቸው አካባቢዎች ተፈጥረዋል፡፡ በጥቅሉ ከእቅድና ከክትትል ውጪ በዘፈቀደ የተሠሩ ሥራዎች ደግሞ ከተማዋን ዥንጉርጉር አድርገዋታል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ የሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑም በከተማዋ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጥረው ጫና አለ፡፡ ይሄን ጫና ለመቀነስ ደግሞ ዘመኑ የሚጠይቀውን የእድገት መንገድ መከተል ይጠበቃል፡፡ ይሄንን በማድረግ ሂደት የሚነሱ ቅሬታዎች እና የሚፈጠሩ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ሆኖም ከችግሮቹ ባሻገር ያለውን ተስፋ እና የተሻለ ነገር መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡

ለምሳሌ፣ ከመንገድ መሠረተ ልማት ጋር ያለውን ማንሳት ይቻላል፡፡ አሁን ላይ አራት ኪሎ አካባቢ እየተከናወነ ያለው የመንገድ ማስፋት ሥራ ከመጀመሩ ከጥቂት ጊዜያት በፊት የመንገድ ጠርዝ ሥራ ተከናውኖ ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆይ ደግሞ ቴራዞ ለማንጠፍ ጠርዙ ተነስቶ ጠጠር እንዲለብስ ተደረገ፡፡ ጠጠሩ እንደለበሰ ደግሞ መንገዱን የማስፋት አዲስ ሥራ ተጀመረ። ይሄን መሰል ሥራ በአካባቢው እንቅስቃሴ ላይም ሆነ ለሥራ በሚውል ሀብት ላይ የሚያሳድረው ጫናና የሚፈጥረው የሀብት ብክነት አለ፡፡

በመሆኑም እንዲህ ዓይነት ከተማዋን የማስዋብ፣ ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግና ስሟን የሚመጥን ገጽታን የማላበሱ ተግባር የሚበረታታ እና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ቢሆንም፤ እንዲህ ዓይነት ሥራዎች ሲታሰቡ እንደ መብራት፣ ውሃ፣ ስልክና ሌሎችም የኅብረተሰብ መገልገያዎች እንዳይስተጓጎሉ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ፤ እንዲሁም በተደጋጋሚ የዲዛይን ለውጥ ምክንያት የሚፈጠርን የሀብት ብክነት ማስቀረት የሚያስችሉ ተግባራት ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።

ኅብረተሰቡም ሥራዎቹ ከዛሬ ችግር ባሻገር ያላቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በመገንዘብ ለጊዜያዊ ችግር ራሱን ከማስገዛት ይልቅ ሥራዎቹ ፈጥነው እንዲጠናቀቁ የአጋዥነት ሚናውን ሊወጣ ይገባል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ የልማት ሥራዎች ዛሬ ላይ ተቸግሮ ነገን የተሻለ ኑሮ፣ የተመቸ የኑሮ ከባቢን እውን ማድረጊያዎቻችን ናቸው፡፡

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን  መጋቢት 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You