የዓለም ሃገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከሁለት ሳምንት በኋላ በሃንጋሪ ቤልግሬድ ይካሄዳል። በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ መሰናክሎች የዓለም ከዋክብት አትሌቶች በሚፈተኑበት የሃገር አቋራጭ ውድድር እንደ ቀነኒሳ በቀለ ያሉ ጀግና አትሌቶች ተደጋጋሚ ድሎችን በማስመዝገብና የዓለም ክብረወሰን በመስበር ትልቅ ታሪክ አላቸው። ኢትዮጵያም በዚህ ውድድር ትልቅ ስም ያላት ሲሆን፣ በ45ኛው የቤልግሬድ የዓለም አትሌቲክስ አገር አቋራጭ ሻምፒዮናም የሚሳተፉ አትሌቶችን በማዘጋጀት ላይ ትገኛለች።
በውድድሩ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ቡድን 14 ሴት እና 14 ወንድ በአጠቃላይ 28 አትሌቶችን ያካተተ ሲሆን፤ ቡድኑ ከየካቲት 28/2016 ዓ.ም ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። በዚህ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን ከሚወክሉት አትሌቶች መካከል ወጣቱ በሪሁ አረጋዊ የተለየ ትኩረት እንደ ተሰጠው የዓለም አትሌቲክስ በድረገጹ አስነብቧል።
በ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ሁለተኛው ፈጣን አትሌት የሆነው በሪሁ፤ በባትረስ ተካሂዶ በነበረው ሻምፒዮና ያገኘውን የብር ሜዳሊያ ቤልግሬድ ላይ በወርቅ ይተካል ተብሎም እምነት ተጥሎበታል። ለዚህ ምክንያት የሆነው ደግሞ አትሌቱ በተያዘው የውድድር ዓመት በርቀቱ ባስመዘገበው ፈጣን ሰዓት ነው። በሪሁ ከወራት በፊት በስፔን በተደረጉ ሁለት ውድድሮች (የ10 ኪሎ ሜትርና ሃገር አቋራጭ) በሁለት ሳምንታት ልዩነት ተሳትፎ በአሸናፊነት ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው።
ከሳምንት በኋላም ደግሞ በጃንሜዳ ዓለም አቀፍ የሃገር አቋራጭ ውድድር ላይ በአዋቂዎች ዘርፍ በተመሳሳይ ጠንካራ የአሸናፊነት ፉክክር በማድረግ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ነበር ያጠናቀቀው።
ይህም አትሌቱን ካለበት ወቅታዊ አቋም አንጻር በቤልግሬድ አሸናፊ የመሆን እድሉ ሰፊ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል። በአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮና እአአ በ2018 ለመጀመሪያ ጊዜ በ3ሺ ሜትር ውድድር ተሳትፎ ለሃገሩ ወርቅ ያስመዘገበው በሪሁ ሃገርን በማስጠራት ላይ ካሉ ጠንካራ ወጣት አትሌቶች መካከል አንዱ ነው።
በትግራይ ክልል አጽቢ ወምበርታ የተወለደው ይህ ወጣት ኮከብ ከመም ውድድሮች ተሳትፎው ባለፈ በ5ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ 12:49 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ የዓለም ክብረወሰንን ከእጁ ሊያስገባ ችሏል። በቡዳፔስቱ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር ሜዳሊያ የማጥለቅ ጥረቱ ስኬታማ ባይሆንም የተያዘው የውድድር ዓመት ግን በአንጻራዊነት ውጤታማ ሊባል የሚችል ነው።
እንደ መም ውድድሮች ሁሉ በጎዳና ሩጫዎች ላይም ስኬታማ የሆነው በሪሁ በዓለም ሃገር አቋራጭ ሻምፒዮና ለአንድ ጊዜ በኢትዮጵያ በሚካሄደው የሃገር አቋራጭ ውድድር ደግሞ ለአራት ጊዜ ተሳትፏል። በዚህም 1 የብር ሜዳሊያ በዓለም አቀፉ መድረክ ሲያስመዘግብ፤ በሃገር አቀፉ ደግሞ 3 የወርቅና 1 የብር ሜዳሊያዎችን በማግኘት በሃገር አቋራጭ ውድድር ያለውን ብቃት አስመስክሯል። እነዚህ ውድድሮችም በብዙ መልኩ የጠቀሙት መሆኑን አትሌቱ ከዓለም አትሌቲክስ ጋር ባደረገው ቆይታ ጠቁሟል።
እልህ አስጨራሽ ፉክክር በነበረው የባትረሱ (2023) የሃገር አቋራጭ ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ማግኘቱ አስደስቶታል። በዚያ ውድድር የሚካፈሉ አትሌቶች ጠንካራ መሆናቸውን በማመኑ ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ ወደዚያው ያቀና ሲሆን በሩጫው ላይ ባሳየው ትጋትም ለሃገሩ ሜዳሊያ ሊያስገኝ መቻሉንም ያስረዳል።
የተያዘውን የውድድር ዓመት በሚመለከትም ‹‹2024ን የጀመርኩት በጠንካራ ተነሳሽነት እና ከዚህ ቀደም ካሳካሁት የበለጠ ውጤታማ ለመሆን በማቀድ ነው። ይህንን ለማሳካትም ከአሠልጣኜ ይረፉ ብርሃኑ ጋር በመሆን አዲስ አበባ ላይ ጠንካራ ዝግጅት በማድረግ ላይ እገኛለሁ። በዓመቱ በሃገር አቋራጭ ሻምፒዮናው እንዲሁም በፓሪሱ ኦሊምፒክ ሜዳሊያዎችን የማሳካት ዓላማ አለኝ። በእርግጥም እንደማሳካው እምነት አለኝ›› ሲል ገልጻል። በሪሁ በቤልግሬዱ የሃገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይም ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ የሚሳተፍ ይሆናል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 7/2016 ዓ.ም