ሙሉ አቅምን መጠቀም!

አንዳንድ ሰው በጨዋታ መሃል ‹‹እኔ የያዘኝ ይዞኝ እንጂ ቀላል ሰው እኮ አይደለሁም›› ሲል ሰምታችሁ ሊሆን ይችላል። እውነት ነው ማንም ሰው ቀላል አይደለም። ማንም ሰው ተራ አይደለም። ማንም ሰው የሚናቅ አይደለም። አቅሙን ስላልተጠቀመበት ነው። ተራ ሕይወት ሊኖር ይችላል። አቅሙን ሲጠቀም ግን ሕይወቱን ይቀይራል። አንተም አሁን ያለህበት ሁኔታ ነገ የምትደርስበትን አያሳይም። አቅምህን ስትጠቀም ደስተኛ ትሆናለህ። ስራህ፣ ትምህርትህ፣ የፍቅር ግንኙነትህ፣ ሕይወትህ ሁሉ ይቀየራል።

ሩሚ የሚባል መምህር ‹‹እንድትበር ነው የተፈጠርከው። ለምን ትንፏቀቃለህ? መብረር መማር አለብህ›› ይላል። መብረር መማር ማለት ደግሞ ሙሉ አቅምህን መጠቀም አለብህ ማለት ነው። ዛፎች ሁሉ አንድ ምርጫ ነው ያላቸው። ወደላይ ማደግ ብቻ! የትኛው ዛፍ ነው ‹‹ኸረ! በቃኝ ከዚህ በላይ አላድግም›› የሚለው? የሰው ልጅ ግን በምርጫ ላይ የተሞላ ነው ሕይወቱ። መቆምም ይችላል፤ ማደግም ይችላል። ባለህበት የቆምከው፤ ባለህበት የምትራመደው ምርጫህ ስለሆነ ነው እንጂ እድለ ቢስና ሰነፍ ሆነህ አይደለም። ግን አቅምህን ስላልተጠቀምክ ነው።

ማደግ ከፈለክ አቅምህን መጠቀም አለብህ። እንዴት አድርጌ ልጠቀም ካልክ ይኸው መንገዱ…..

1ኛ.ትልቁ ሃሳብ ላይ አተኩር

መሃተመ ጋንዲ ‹‹መልካሙን ብቻ ማሰብ አለብህ! ምክንያቱም ያሰብከውን ትናገራለህ፣ የተናገርከው ፀባይህ ይሆናል። ያ ፀባይህ ልማድህን ይወስነዋል። ልማድህ ደግሞ መጨረሻ ላይ ማንነትህ ይሆናና የሕይወት መድረሻህን ይወስነዋል›› ይላል። ስለዚህ ወዳጄ! ለምታስበው አስብ። ትንንሽና ትላልቅ ሃሳቦች ናቸው ሕይወትህን የተቆጣጠሩት። ለማትቀይረው ነገር ነው እየተጨነክ ያለኸው።

አንዳንድ ሰው ኳስ ያይና ‹‹በቃ! እንደው ሮናልዶ እድሜው ገፋ ማለት ነው›› ይላል። ያንተ የሚገፋውን እድሜ አታስብም። ‹‹እንደው ይህች ሀገር መጨረሻዋ ወዴት ነው›› ትላለህ። ያንተስ መጨረሻ ወዴት ነው? አየህ! ትናንሽ ሃሳቦች እነዚህ ናቸው። ትልቅ ሀሳብ ታዲያ ምንድን ነው? ልትል ትችላለህ። ትልቅ ሃሳብ ማለት አንተ ያለህበትን ማወቅ፤ ከዛ የምትደርስበትን ማወቅ፣ ከዛ ካለህበት ወደምትደርስበት መንገድ መጀመር ነው።

ለምሳሌ ቤትህ ቢቃጠል ‹‹እኔ እኮ የሚቆጨኝ ያ! የምወደው ያ! ስንት እቃ የሚይዝበት ፌስታል መቃጠሉ ነው›› አትልም። ስንት ትልልቅ እቃ አለ ቤትህ ውስጥ። ትልልቆቹ እቃዎች ናቸው የሚያስቆጩህ። ትንሷ ፌስታል አታሳስብህም። አየህ! አሁን በሕይወትህ እየተጨነክበትና እያሳሰበህ ያለው ጉዳይ ፌስታል ነው። ትናንሽ ሃሳቦች ተቆጣጥረውሃል። ትልቁን አስብ። ዓላማህ፣ ሕልምህን፣ መዳረሻህን አስብ። ሕይወትህን ትቀይራለህ።

ዓላማ የሚጠቅመው ሕልምህ እንዲሳካልህ ነው። አንተ እንድትቀየር ነው። ለዓላማው ስትል ማንነትህ ይቀየራል። ያንን ሰው ለመሆን ስትል የግዜ አጠቃቀምህን፣ ውሎህንና ማንነትህን ትቀይራለህ። ከዛ ፈጣሪ የሰጠህን ሙሉ አቅም መጠቀም ትጀምራለህ።

2ኛ.ራስን ማወቅ

ያለህን አቅምና ራስህን ከተረዳኸው ምን ላሻሽል፣ ምን ልጨምር ትላለህ። አየህ! አቅም ትገነባለህ። ድክመትህንና ጥንካሬህን ማወቅ አለብህ። ሰዎች ከዚህ በፊት የነገሩህን አስታውስ። አንተ እኮ ጎበዝ ነህ። ያንተ ችግር እኮ ትግስት የለህም። ትቸኩላለህ። ያንተ ችግር ዝምተኛ ነህ። አትግባባም። ያንተ ችግር ዝምብለህ ሰው ታምናለህ ሊሉህ ይችላሉ። ሰዎች ያሉህን አስታውስ። ድክመትና ጥንካሬህን አስታውስ።

ብዙዎቻችን መስታወት ፊት ስንቆም ያለን ውበት ሁለት እጥፍ ሊታየን ይችላል። አየህ! ጥንካሬህ ጎልቶ ሊታይ ይችላል። ጥሩ ነው። ግን ደግሞ ከሰዎች ስማ። ያንተን ጠንካራ ጎን እነሱ በሌላ ጎን ሊያዩት ይችላሉ። ራስህን ስታውቅ አቅምህን ለመጠቀም ትመቻቻለህ። ትቀየራለህ። አሁን እዚች ጋር ነኝ ቀጥሎ እዚህ ጋር እደርሳለሁ ትላለህ። ሕይወትህን ትቀይራለህ። ከሁሉም በላይ ግን ራስህን ስታውቅ ከራስህ ጋር ትፎካከራለህ። ትናንት እዛ ጋር ነበርኩ አሁን እዚህ ጋር ነኝ ትላለህ። ከራስ ጋር ፉክክር ደግሞ ጫፍ ላይ ያወጣሃል። ሙሉ አቅምህን እንድትጠቀም ያደርግሃል።

3ኛ.ግልፅ እቅድ ይኑርህ

ቀንህን፣ ሕይወትህን የምትመራበት የራስህ እቅድ ከሌለህ እግረ መንገድህን ነው የምትኖረው። ስለዚህ እቅድ ከሌለህ እቅድ ያለው ይመርሃል። እቅድ ያለው ሰው አገልጋይ ትሆናለህ። ለምን? አንተ ዓላማ የለህማ። እነርሱ በሕይወትህ ጣልቃ ይገባሉ። ይመሩሃል። ስለዚህ እነርሱ አቅምህን አሟጠው ይጠቀሙታል። አንተ አታወጣውም። ለምን? ግልፅ እቅድ የለህም። እቅድ ይኑርህ ማለት ዛሬ እንዲህ እሰራለሁ፣ ዛሬ እንዲህ ልሰራ ነው የተነሳሁት ትላለህ። ወይ ደግሞ በዚህ ዓመት ዓላማዬና እቅዴ እዚህ ጋር መድረስ ነው። ይሄን ማሳካት ነው ትላለህ።

ባንተ እቅድ ማንም አይገባም። ለዛ እቅድ ስትል ግን አንተ ራስህን ትቀይራለህ። ሙሉ አቅምህን ትጠቀማለህ። ለምን? እቅድ አለህ። አየህ! በሕይወት ውስጥ የምትመራበት መንገድ አለህ። መንገዱን ራስህ ነህ ያሰመርከው። ሌሎች አይደሉም። ስለዚህ ሙሉ አቅምህን ትጠቀማለህ። እቅድ ሲኖርህ የምትሰራበት፣ የምትማርበት ብቻ አይደለም። የምታርፍበት፣ የምትዝናናበትና ከራስህ ጋር የምታወራበት እቅድም ያስፈልግሃል። አቅድ ሲኖርህ ሕይወትህን የምትመራበትን መንገድ ራስህ ነው የምታወጣው። ከዛ ግን ሙሉ አቅምህን ትጠቀማለህ።

4ኛ. ከሚጠበቅብህ በላይ ስራ

አንዳንድ ሰው ይህን ሲሰማ ‹‹እኔ እኮ የምወደውን ሥራ ብሰራ፤ የምወደውን ትምህርት ብማር በሙሉ አቅሜ እሰራለሁ። እንዴት ነው የምጠነክረው ? የምወደውን አይደለም የምሰራው›› ሊል ይችላል። የምትወደውን እስከምትሰራ ድረስ የምትሰራውን መውደድ አለብህ። አየህ! ለማትወደው ስራ ከጠነከርክ ነገ አቅሙ ኖሮህ የምትወደውን ስትሰራ ምን ያህል እንደምትጠነክር አስብ።

በቅርብ በተሰራ ጥናት አሜሪካን አገር ከሚገኙ አጠቃላይ የሽያጭ ባለሞያዎች ውስጥ የዓመት ገቢያቸው ትልቅ የሆኑ ነገር ግን የአምስት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ልዩነት ያላቸው ሁለት ሰዎች ገቢያቸው ከፍ ሊል የቻለው ከብዙ ሰው ጋር ተግባብተውን ብዛት ያለው ስራ ስለሚሰሩ መሆኑ ተረጋግጧል። ነገር ግን የአጥኚዎቹ ትኩረት በሁለቱ የሽያጭ ሰራተኞች መካከል ያለው የገቢ ልዩነት ነበር። አንዱ እንዴት ሊበልጥ ቻለ የሚለው ነበር። ለካ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገባው ሰው ጨመር አድርጎ አምስት ሰው ጋር ይደውል ነበር። በዓመት ሲሰላ ደግሞ ሰውዬው አምስት ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ገቢ እንዲገኝ አድርጎታል።

ስለዚህ ጨመር አድርጎ መስራት ማለት ይህ ነው ሕይወትህን የምትቀይረው አሁን ከምትሰራው ላይ ጨመር ካደረክ ነው። ስምንት ሰዓት ለመስራትም ማንም ይሰራል። ጧት ሁለት ሰዓት ለመግባት ማንም ይባል። አንተ ግን ጨምረህ ስራ። አለቃህ ደሞዝ እንዲጨምርልህ አይደለም። ሙሉ አቅምህን እንድትጠቀም ነው። እንድታወጣው ነው። የትኛውም ስራ ላይ ልትቀጠር ትችላለህ። እንደወታደር መስራት አለብህ። አንተ በሕይወትህ ውስጥ በምትሰራው ምንም አይነት ሥራ ውስጥ ልትሆን ትችላለህ። እንደ ወታደር ስራ። ምንም ነገር አላበላሽም፤ ጠንቅቄ እሰራለሁ ማለት አለብህ። ከሚጠበቅብህ በላይ ስትሰራ ፈጣሪ የሰጠህን አቅም እያወጣህ ነው። እየመነዘርከው ነው።

5ኛ. ፅናት ይኑርህ

ከፍታው ላይ የሚያወጣህ የማይቆም ጥረት ነው። በቃ! ወጥ የሆነና ሁሌም የማታቆመው ጥረት። ድንጋይን የሚሰብረው ጎርፍ አይደለም። ጎርፍ የድንጋዩን አቅጣጫ ነው የሚቀይረው። ድንጋዩን የሚሰብረው ጠብታ ነው። ጠብታው ሲደጋገም ድንጋዩ ይሰበራል። የሆነ ቀን ተነስተህ የለፋኸው ልፋት አይደለም ሕይወትህን የሚቀይረው። ሁሌ የምትለፋው የማያቋርጥ ትንሷ ጥረትህ ግን ከፍታው ላይ ታስቀምጥሃለች።

ካለቪን ኮሌጅ ተሰኘ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ‹‹በዚህ ዓለም ፅናትን የሚተካ ነገር የለም። ተሰጥኦ እንኳን አይተካውም። እውቀትም አይተካውም። ዓለምን የሚቀይሯት የፀኑ ሰዎች ናቸው›› ይላል። ፅናት ማለት ጥሩ ውጤት አገኘህም ቢሆን ሌላኛውን ጥሩ ውጤት ማሰብ ነው። አሜሪካን ሀገር ውስጥ እጅግ የታወቀ አንድ አርክቴክተር አለ። ይህ አርክቴክተር የተለያዩ ሕንፃዎችን ዲዛይን አድርጓል። ኒዮርክ ውስጥ በጣም የሚከበሩ ሕንፃዎች በእርሱ ነው ዲዛይን የተደረጉት።

ይህንን ግን ሰዎች ሲጠይቁ የትኛው ዲዛይንህ ነው በጣም ምርጡ ሲባል ‹‹ ቀጣይ የምሰራው ስራ ነው›› ይላል። ለምን ይመስላችኋል? ፅናት ያለው ሰው ነው። ከዚህ በፊት በሰራቸው ሕንፃዎች መመካት አይፈልግም። ወደፊት በሚሰራው ብቻ! አቅምህን መጠቅም ከፈለክ፣ ሕይወትህን ለመቀየር ከፈለክ፣ ከፍታው ላይ መውጣት ከፈለክ መርካት የለብህም። ቀጥሎ ለሚመጣው መጓጓት አለብህ። ፅናት ያስፈልግሃል።

6ኛ. አቋራጭ መፍትሔ አትፈለግ

ቶሎ መቀየር አትፈልግ። እንዴት አድርጌ በአቋራጭ እዛ ቦታ ላይ ልድረስ አትበል። እንደዛ ካልክ ከሰዎች መጠበቅ ትጀምራለህ። እንትና ቢረዳኝ፣ እንትና እንዲህ ቢያደርግልኝ … ሙስና ሁሉ ታስባለህ። ሰው እኮ ጉቦ የሚቀበለው በአቋራጭ ለመክበር ነው። በሕይወትህ ውስጥ በራስህ ሕይወትህን እንደመቀየር ምን ሚያስደስት ነገር አለ። ለሰው ስታወራ፣ ለልጅህ ስታወራ ደስ ይልሃል። እኔ በጥረቴ ነው የተቀየርኩት፣ አቅሜን አውጥቼ ተጠቅሜ ነው ስትል እኮ ደስ ይላል።

አቋራጭ መንገድ አትፈልግ። ትክክለኛውን መንገድ ማሰብ ስትጀምር በሕይወትህ ለጥያቄዎች መልስ ታገኛለህ። እንዲህ ብታደርግ እኮ ይልሃል አይምሮህ። ለምን ራሴን እንዴት ልቀይር እያልክ ነዋ! ‹‹እንዲህ ብትማር፣ እንዲህ ብትሰራ፣ ለምን አንድ ሁለት ሶስት ስራ አትሰራም፣ ገንዘቡን እንዲህ አታስቀምጥም›› ይልሃል። አቋራጭ መንገድ ጥሩ አይደለም።

7ኛ. የቀየርከውን ነገር ማሰብ

አየህ! ‹‹ትናንትና እንደዚህ ነበርኩ፤ ዛሬ ምን አሻሻልኩ እውቀቴ አደገ፣ ገቢዬ አደገ፣ በስራዬ ላይ ጥሩ ሆንኩኝ፣ በኑሮዬ፣ በትዳሬ ደስተኛ ነኝ፣ ከትናንት ምን ጨመርኩ›› በል። ያሳካኸውን አስብ። ለምን መሰለህ፤ ትላንት እንዲህ ካደረኩ፣ ትላንት እንዲህ ካሳካው አሁንማ ልምዱ አለኝ፣ ጎበዝ ነኝ፣ እቀየራለሁ ትላለህ። አቅምህን ታወጣለህ። ልምድህን አስብ። ያሳካኸውን አስብ።

በሕይወትህ ውስጥ በጣም ወሳኙ ነገር በራስ እርግጠኛ መሆን ነው። ወይም በራስ መተማመን ነው። በራስህ እርግጠኛ የምትሆን ከሆነ ከዚህ በፊት ያሳካኸውን ካሰብክ ነው። ዛሬ እንዲህ አሳክቻለሁ ነገ ደግሞ እንዲህ አሳካለሁ ትላለህ። ልክ እርግጠኛ ስትሆን ሙሉ አቅምህን አውጥተህ መጠቀም ትጀምራለህ። ልክ አቅምህን ስትጠቀም ወደ ተግባር ትገባለህ። እንዲህ ላድርግ፤ እንዲህ ልስራ ትላለህ። ለምን? አቅምህን እየተጠቀምክ ነው። ወደ ድርጊት ከገባህ በላ ውጤቱ ይመጣል። ጥሩ ውጤት ታገኛለህ። አንዱ ቦታ ላይ ያለው ውጤትህ ወደሌላው ይጋባል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን መጋቢት 7/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You