ሕግ ጠባቂው ሕግ ሲጥስ

በ1996 ዓ.ም በወጣው የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ ምዕራፍ ሁለት አንቀጽ አምስት ስር በመልካም ጠባይና በቤተ ዘመድ መካከል የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በሚመለከት ከተደነገጉት እና በግብረ ሥጋ ነጻነት እና ንጽህና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ከሚመለተው ርዕስ ስር ካሉ ድንጋጌዎች መካከል የግብረ ሥጋ ድፍረት በደል አንዱ ሲሆን በአብዛኛው ሴቶች እና ወንድ ሕጻናት የዚህ በደል ተጠቂ ናቸው።

አስገድዶ መድፈር ወንጀልን የሚደነግገው የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 620 የአስገድዶ መድፈር ወንጀልን ሲደነግግ “ማንም ሰው የኃይል ድርጊት በመጠቀም ወይም በብርቱ ዛቻ ወይም ሕሊናዋን እንድትስት በማድረግ ወይም በማንኛውም ሌላ መንገድ ራሷን እንዳትከላከል በማድረግ ከጋብቻ ውጭ ከአንዲት ሴት ጋር የግብረ ሥጋ በደል የፈጸመ ግለሰብ ከ 5 ዓመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል። ቅጣቱ ከብዶ እስከ 20 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችልበትን ምክንያት በአንቀጽ 620 ንዑስ ቁጥር 2 እና ተከታዮቹ ላይ የዘረዘረ ሲሆን እነዚህም የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶች:-

1/ ወንጀሉ የተፈጸመው ከ13 ዓመት በላይ ሆና 18 ዓመት ያልሞላት ልጅ ላይ እንደሆነ

2/ በደፋሪው መሪነት፣ ቁጥጥር ወይም ሥልጣን ሥር ባለ እንደ ሕክምና ቦታ የትምህርት እና የማረሚያ ቦታዎች ላይ በምትገኝ ሴት ወይም በደፋሪው ጥገኝነት ወይም ቁጥጥር ስር ባለች ሴት ላይ የተፈጸመ እንደሆነ

3/ በአዕምሮ ሕመም ምክንያት ወይም በሌላ በማናቸውም ምክንያት የድርጊቱን ምንነት እና የሚያስከትለውን ውጤት ለማወቅ የማትችል ሴት ላይ የተፈጸመ እንደሆነ

4/ አስገድዶ መድፈሩ የተፈጸመው በማሰቃየት ወይም ቁጥራቸው ከአንድ በላይ በሆኑ ወንዶች በሕብረት የተጸመ እንደሆነ ቅጣቱ ከብዶ ከ 5 ዓመት እሰከ 20 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ይደነግጋል። ይህን ድንጋጌ ልናነሳ የወደድነው በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን በያያ ጉለሌ ወረዳ የሚኖር ሕግ አስከባሪ የፈፀመውን የወንጀል ታሪክ ልናስነብባችሁ ስለሆነ ነው። ኮማንደሩ ማኅበረሰቡን ከወንጀል ድርጊት መጠበቅ ሲገባው ራሱ ወንጀል ሲፈፅም የተገኘበትና ለዚህም የተወሰነውን ውሳኔ በዚህ መልኩ አቅርበነዋል መልካም ቆይታ።

ወጣቷ ሀዊ

በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን በያያ ጉለሌ ወረዳ ነው የተወለደችው። ገና በአፍላ እድሜያቸው በፍቅር የወደቁት ወጣቶች እናት አባታቸውን አሳምነው በአንድ መኖር እንደ ጀመሩ ነበር የተረገዘችው። ገና ፍቅራቸውን አጣጥመው ሳይጨርሱ ልጅ የሰጣቸውን ፈጣሪ እያመሰገኑ፤ ልጃቸው ገና በእናቷ ማኅፀን እያለች ስም እያወጡ ነበር የጠበቋት። ይች ብርቅዬ ልጅ ብዙም ሳታስቸግር ወደ ናፈቋት ወላጆቿ ስትመጣ ልእልታችን መጣች ብለው ተቀበሏት። ወጣቶቹ የልጅነት ልጃቸውን እያሳደጉ ባላቸው ትንሽ መሬት ላይ እየሰሩ በፍቅር ይኖሩ ነበር።

ከመጀመሪያ ልጃቸው ሐዊ በኋላ በየዓመቱ ልጆች እየወለዱ የወጣትነት እድሜያቸው ሳያበቃ የስድስት ልጆች እናትና አባት ሆኑ። የሐዊ እናት ልጆች በአናት አናት በመውለዷ የተነሳ ጤና አጣች። የሐዊ አባትም ባለችው ትንሽ መሬት ላይ ጠንክሮ ቢሰራም መሬቱ ከቤተሰቡ የእለት ጉርስ አልተርፍ ብሎ ያሳቀቃቸው ገባ።

ወደ ከተማ ወጣ ብሎም ቀን ስራም ሆነ ያገኘውን ስራ ሰርቶ ቢመለስም የቤተሰቡን ደስታ መመለስ ተሳነው። ቤተሰቡ በፍፁም ድህነት ውስጥ መውደቁን እየተመለከተች ያደገችው ልእልት እድሜዋ 16 ሲሆን ነበር ከተማ ወጥታ በመስራት ቤተሰቧን ለመደገፍ የወሰነችው። እናቷ ስሯ ሆና እንድትማር ብትፈልግም ሐዊ ግን እየሰራሁ እማራለሁ ሩቅ አልሄድም በማለት በወረዳቸው ያለች የገጠር ከተማ በሆቴል ተቀጥራ እየሰራች ማታ ማታ ትማር ጀመር።

የፅዳት ሰራተኛ ሆና በሆቴሉ የተቀጠረቸው ይህች ወጣት ቀኑን ሙሉ ስትሰራ ውላ አመሻሽ ላይ ደብተራን ይዛ ትወጣለች። የሆቴሉን ማደሪያ ስለምትጠቀምም መመለስ ግድ እየሆነባት ነበር በምሽት ሹልክ ብላ መኝታ ክፍሏ የምትገባው።

ወጣቷ የትምህርቷ ነገር ስለማይሆንላት መሸተኛው ወጥቶ ሴቶቹ መጥተው መኝታ እስኪጋሯት ድረስ ደብተራን ይዛ ስታነብ ታመሻለች። ከዛም ማልዳ ተነስታ ወደ ተለመደው ስራዋ በመግባት የምታገኛትን ገንዘብ ለወላጆቿ ትልካለች። አንድ ዓመት በዚህ ሁኔታ የቆየችው ወጣት ከስምንተኛ ወደ ዘጠነኛ ክፍል በጥሩ ውጤት አለፈች።

በዚህም ደስተኛ ሆና ስራዋን እየሰራች መማር ላይ ትኩረት አደረገች። በሆቴሉ በቂ ምግብም ስለምታገኝ ሰውነቷ መለስ እያለ ከአፍላ ወጣትነት ጊዜዋ ላይ በመሆኗ አይነግቡ ሆነች። የእናትና አባቷ መጥሪያ የሆነው ልእልት የሚለውን ስሟን የምትመስለው ወጣትም በአጋጣሚ የተመለከቷትን ሁሉ የምታስደነግጥ ቆንጅዬ ወጣት ሆነች። የሆቴሉ ባለቤትም እየሳሱላት ብዙም ወጣ ገባ እንዳትል ይመክሯት ነበር።

ከእለታት አንድ ቀን ግን የመኝታ ክፍሎቹን በሙሉ አፅድታ የተቀየሩ አንሶላዎችን በማጠብ ላይ እያለች ነበር በአንድ ኮማንደር አይን የገባችው። ሕግ ሊያስከብር ስርዓት አልበኞችን ሊቀጣ መንግስት የሰጠውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ወጣቷ ላይ ያልተገባ ነገር ፈፀመ።

ስልጣኑን ላልተገባ ተግባር የተጠቀመው ኮማንደር

ባለትዳር ነው፤ የልጆች አባት። እሱም የሚሳሳላቸው እንደ አይኑ ብሌን የሚመለከታቸው ሴት ልጆች ያሉት ሰው ነው። ልጆቹና ባለቤቱን በክፉ የሚመለከትበት ላይ የማያዳግም እርምጃ የሚወስደው ይህ ሰው የሌላ ሰው ልጅን ለመንካት ግን አላቅማማም ነበር።

ወጣቷን ልጅ ገና እንዳያት ነበር የራሱ ለማድረግ የተመኛት። የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት አዛዥ የሆነው ይህ ሰው በፀባይ ጠይቆ እምቢ ከተባለ ግን በግድ ሊያደርገው እንደሚፈልግ ከሁለት ግብረ አበሮቹ ጋር ተመካከረ። ልጅቷ ቤተሰቧን እየረዳች የመማር ሕልም ስለነበራት ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌላት ቆፍጠን ብላ አሳወቀች።

ይህ ጉዳይ ያልተዋጠለት ኮማንደር ሁለት ግበረ አበሮቹን አስተባብሮ መንግስት የሕብረተሰቡን ደህንነት እንዲጠብቅበት የሰጠውን መሳሪያ በመጠቀም ሕልመኛዋ ወጣት ላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈፀመባት።

ወጣቷ ልጅ እንደለመደችው ከትምህርት ቤት መጥታ እያጠናች ነበር። ልጅቷ አብረዋት የሚያድሩ ሴቶች ስለሚመጡ በሩን ሳትቆልፍ ነበር የምትቀመጠው። ይሄንን ያረጋገጠው ወንጀለኛ አካባቢው ጭር ማለቱንና ልጅቷ ብቻዋን መሆንን በማወቅ ይህንን እኩይ ተግባር ሊፅሙባት ችለዋል።

ከሙዚቃው ጩሀት በልጦ የልጅቷ ድምፅ መሰማት ስላልቻለ እንጂ የሚያስጥላት አታጣም ነበር። ነገር ግን ሕግ አስከባሪው ከግብረ አበሮቹ ጋር ሕግን ሲጥስ ማንም አልደረሰላትም ነበር። ሁሉ ነገር ተጠናቆ እኩለ ሌሊት ሲቃረብ ነበር የልጅቷ መደፈር የታወቀው። በወቅቱ በአካባቢው የነበረው ሕግ አስከባሪ ራሱ ደፋሪው ስለነበር በነጋታው ነበር ሌሎች ፖሊሶች ጆሮ ኮማንደሩ የሰራው እኩይ ተግባር የደረሰው። ፖሊስም እንደ የሕግ አስከባሪ ይህንን ተግባር መፈፀሙን እንደሰማ ነበር በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራውን የጀመረው።

የፖለስ ምርመራ

የሕግ አካላት የተፈፀመው ወንጀል ፖሊስ ጆሮ እንደደረሰ ነበር ጉዳዩን ለማጣራት ሆቴል የተገኙት። በወቅቱ የተፈፀመውን በመመልከትና የሕክምና ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ኮማንደሩ እንደፈፀመም ተጣራ። ኮማንደር ተሾመ ከበደ የተባለው ግለሰብ እድሜዋ ከ15 እስከ 16 ዓመት የሆነች የግል ተበዳይ ሐዊ ጉታ በወረዳ ፍታለ 01 ቀበሌ ተቀጥራ በምትሰራበት ሆቴል ውስጥ ሕዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 5 ሰዓት በሚሆንበት ጊዜ በሽጉጥ በማስፈራራት አስገድዶ መድፈሩ ታወቀ።

ኮማንደሩም የአስገድዶ መድፈር የወንጀል ድርጊቱን እንዲፈፅም ተባባሪ የነበሩት ኮማንደር ደረጀ ታምሩ እና አቶ ደረጀ ሀይሉ ተሳትፎ ማድረጋቸውን የተበዳይዋ ቃል እና በተጠርጣሪዎቹ ላይ በተደረገ ምርመራ ሊታወቅ ችላል። ፖሊስ መረጃውን አጠናቅሮ አንደጨረሰ የሰሜን ሸዋ ዞን ዓቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤት አቀረበ።

የአቃቤ ሕግ ክስ ዝርዝር

የሰሜን ሸዋ ዞን ዓቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤትም አንደኛ ተከሳሽ የግል ተበዳይን አፍንጫዋን ከመታ በኋላ ከሁለተኛ ተከሳሽ ጋር ወደ መኝታ ክፍሉ ማስገባታቸው ተጠቁሟል ። በኋላም ሁለተኛ እና ሶስተኛ ተከሳሾች በሩን ዘግተው ሲሄዱ አንደኛ ተከሳሽ ወንጀሉን መፈፀሙ ታዉቋል። በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ የምርመራ መዝገቡን በሰውና በሰነድ ማስረጃ በማጠናከር ታህሳስ 23 ቀን 2016 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መስርቷል።

ውሳኔ

የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ ሲመለከት ቆይቶ በተከሳሾቹ ላይ የጥፋተኝነት ብይን ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ አንደኛ ተከሳሽ ኮማንደር ተሾመ ከበደ በ8 ዓመት ሁለተኛ ኮማንደር ደረጀ ታምሩ እና ሶስተኛ አቶ ደረጀ ሀይሉ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በገደብ የአንድ ዓመት እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል።

ይህም ማለት ሁለተኛ እና ሶስተኛ ተከሳሾች ከማረሚያ ቤት የወጡ ሲሆን በተሰጣቸው የአንድ ዓመት የጊዜ ገደብ ውስጥ የወንጀል ድርጊት ከፈፀሙ ብቻ የአንድ ዓመት እስራቱ እንደሚፀና ተገልጿል። ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ በተሰጠው የፍርድ ውሳኔ ላይ በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ለመጠየቅ የውሳኔ ግልባጭ እየጠበቀ እንደሚገኝ ገልጿል።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን መጋቢት 7/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You