ለውጦችን እያስመዘገበ ያለው የሲዳማ ክልል የማዕድን ጥናትና ልማት

በቡና፣ በቱሪዝም መስህቦቹና በሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶቹ በስፋት የሚታወቀው የሲዳማ ክልል በርካታ የማዕድን ሀብቶችም አሉት፡፡ በክልሉ ወርቅ፣ የከበሩ ማእድናት፣ ለኮንስትራክሽና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ በርካታ የማዕድን አይነቶች ይገኛሉ፡፡

ክልሉ በአዲስ ክልልነት በቅርብ ጊዜ የተዋቀረ እንደመሆኑ ቀደም ባሉት ጊዚያት በክልሉ ያሉ የማዕድን ሀብቶችን በመለየት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ሥራዎች እምብዛም እልተሰሩም፡፡ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ግን በክልሉ ያሉ ማዕድናትን በጥናት በመለየት ጥቅም ለማዋል ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ እስካሁን በክልሉ ያለውን የማዕድን ሀብት ለማወቅ በተደረገው ጥናት 20 በመቶ ያህሉ የማዕድን ሀብቶችን በጥናት መለየት የተቻለ መሆኑን ከክልሉ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

መረጃው አሁን ላይ በክልሉ ያለውን የማዕድን እምቅ ሀብት ለማወቅ የሚያስችሉ ቀጣይነት ያላቸው ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ያሳያል። የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው የክልሉን የማዕድን ሀብት ልማት አስመልክቶ የሲዳማ ክልል ውሃና ማዕድን ቢሮ የማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን መጩካ እንዳሉት፤ በክልሉ ያሉትን ማዕድናት ለመለየት ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡ ዘንድሮ ዝናብ በመራዘሙ ምክንያት የማዕድን ልየታ ሥራው የተጀመረው በቅርቡ ነው፡፡ ልየታው በኤጀንሲ በራስ አቅም፣ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲና በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ኢንስቲትዩት ነው የሚካሄደው፡፡ በተለይ በከበሩ ማዕድናት ዙሪያ የሚደረጉት ጥናቶች በራስ አቅምና ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡

አሁን ላይ በክልሉ ያሉትን ማዕድናት ለማልማት የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ያመላክታሉ። በዚህም በበጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት በማዕድን ዘርፉ ለማግኘት ከታቀደው አንጻር የተሻለ አፈጻጸም እንደተመዘገበም ይናገራሉ፡፡

በተያዘው የበጀት ዓመት በስድስት ወራት የወርቅ ማዕድን የማምረት ሥራ 15 ኪሎ ግራም ወርቅ ለማግኘት ታቅዶ፤ አምስት ነጥብ አምስት ኪሎ ግራም ወርቅ ማምረት ተችሏል፡፡ በክልሉ እየተመረተ የሚገኘው ወርቅ የደለል ወርቅ የሚባለው ብቻ ሲሆን፤ የኳርዝ ወርቅ በክልሉ መኖሩ ቢታወቅም ገና ጥናት እየተደረገበት ነው፡፡

በማዕድን ዘርፍ በበጀት ዓመቱ በስድስት ወራት ስድስት ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፤ ከፍተኛው ገቢ ከሮያሊቲ ክፍያ የተገኘ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡ በዘርፉ ሥራ አጥ ለሆኑ ሦስት ሺ ሦስት መቶ በላይ ወጣቶች የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸውም አስረድተዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚውሉ እንደተልክ፣ ሮታይል እና ካኦሊን ያሉ ከውጭ ሀገር በከፍተኛ ወጪ የሚገቡ ማዕድናትን በሀገር ውስጥ በማምረት ለኢንዱስትሪዎች በግብዓትነት የማቅረብ ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ በስድስት ወራት ውስጥም 120ቶን የኢንዱስትሪ ግብዓት ማዕድናት ለማምረት ታቅዶ፤ 105 ቶን ማዕድናት በማምረት ለኢንዱስትሪዎች ማቅረብ ተችሏል፡፡

‹‹ኀብረተሰቡን በማዕድን ሀብት ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር የየአካባቢውን ማኀበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋጋጥ የሚያስችሉ የኮንስትራክሽን ማዕድናትም ይመረታሉ ››ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የኮንስትራክሽን ማዕድናት አብዛኛውን ኀብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በስድስት ወራቱ ከ90 በመቶ በላይ የኮንስትራክሽን ማዕድናት በማምረት ለገበያ የቀረበ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

በክልሉ ያለው የማዕድን ሀብት ገና እየተጠና መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፤ በማዕድን ዘርፉ የተሰማሩ በርካታ ባለሀብቶች ጥናት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው፣ አብዛኛዎቹ እስካሁን ወደ ምርት ደረጃ እንዳልደረሱ አመላክተዋል፡፡ በማዕድን ዘርፍ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፤ በተለይ በማዕድን ሥራ የተጎዳውን መሬትን መልሶ በማቋቋም ስምንት በመቶ በላይ የሚሆን የተጎዳ መሬት መልሶ እንዲያገግም መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ የግራናይት ማዕድን በስፋት መገኘቱ ተረጋግጧል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በግራናይት ማዕድን ልማት ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች ፈቃድ ወስደው የምርመራ ሥራ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፤ ባለሀብቶቹ የምርመራ ሥራውን ሲያጠናቅቁ ወደ ማምረት ሥራ እንደሚገቡ አስረድተዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ በክልሉ በርካታ የኢንዱስትሪ ማዕድናትንም ይገኛሉ፡፡ እንደ ተልክ ያሉ (ለሴራሚክ ግብዓት የሚውሉ)፣ ኳርዝ፣ ካኦሊን፣ ዶይሎማይት እና ሮታይል በመባል የሚታወቁት እና ሌሎች ማዕድናት በክልሉ የሚለሙ ናቸው፡፡ በተለይ በዚህ ዓመት ‹‹ሮታይል›› የተሰኘውን ማዕድን ማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ ማኀበራት እያመረቱ ከፍተኛ ገቢ እያገኙ ነው፡፡ ሌሎችም የኢንዱስትሪ ማዕድናት በጥናት የተለዩ ቢሆንም ግን እስካሁን ወደ ሥራ ያልገቡ አሉ፡፡

በቀጣይ እነዚህን ማዕድናት በሥራ ላይ ለማዋል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ ማዕድናት የማውጣት ሥራው ቀለል ያሉትን ማዕድናት ለማልማት በማኀበር በተደራጁ ወጣቶች የሚሰራ መሆኑን ገልጸው፣ ከበድ ያሉትና በማሽኖች መስራት የሚጠይቁትን በዘርፉ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ በማዕድን ልማት ላይ ለመሳተፍ የምርመራ ፈቃድ የወሰዱ በርካታ ባለሀብቶች ያሉ መሆኑን ጠቁመው፤ ፍቃድ ከወሰዱት ውስጥ በግላቸው ሳይሆን ከማኀበራት ጋር በመሆን ያመረቱ ከስድስት በላይ የሚሆኑ ባለሀብቶች መኖራቸውን ያስረዳሉ፡፡

የኮንስትራክሽን ማዕድናት ለማምረት ፈቃድ የወሰዱ በከፍተኛ ደረጃና አነስተኛ ደረጃ ያሉ ብዙ አምራቾች አሉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የኮንስትራክሽን ማዕድናት ማምረት ረገድ በጣም ሰፊ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከኢንዱስትሪ ማዕድናትም አንጻርም እንደ ተልክና ኳርትስ የመሳሰሉት ማምረት የተጀመረ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተያዘው በጀት ዓመት ተጨማሪ ‹‹ሮታየል›› የተሰኘ ማዕድን ማምረት መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ፤ አሁን ላይ በክልሉ የግራናይት ማዕድን ለማምረት ሁለት ድርጅ ቶች በሁለት ቦታዎች ላይ የምርመራ ሥራ መጀመራቸውን ይገልጻሉ፡፡ በዘንድሮ ዓመት የግራናይትና የሊትየም ማዕድናት ፈቃዶች የተሰጡ መሆናቸውን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በግራናይት አምስት ባለሀብቶች እና በሊትየም ሁለት ባለሀብቶች የምርመራ ሥራ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የማዕድን ማምረት ሥራ የተሰማሩት አካላት ቀደም ሲል በክልሉ ማዕድን ልማት ሥራ ከተሰማሩት ወጣቶች ጋር በመቀናጀት የሽርክና ማኀበር መስርተው እየሰሩ ያሉ ማኀበራት መሆናቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ በክልሉ እስካሁን ያለውን ማዕድን ለማወቅ በተደረገው ጥናት 20 በመቶ ያህል የማዕድን ሀብቶችን መለየት ተችሏል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት ይህን 25 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ 750ካሬ ሜትር መሬት ጥናት ለማድረግ ታቅዷል፡፡ ይህን እቅድ ከግብ ለማድረስ የሚያስችል ጥናት ተጀምሯል፡፡

‹‹ክልሉ እንደ ክልል በቅርቡ የተቋቋመ እንደመሆኑ መጠን ቀደም ሲል በስፋት ጥናቶች ስላልተካሄዱ በክልሉ ያለው የማዕድን ክምችት ብዙም አይታወቅም፤ የተሰሩትም የአለኝታ ጥናቶች ናቸው ››ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህም ደግሞ አሁን ላይ በክልሉ ምን ያህል ማዕድን ሀብት እንደሚገኝ ለማወቅ እንዳላስቻለና የማዕድን ልማቱ ችግር ሆኖ መቆየቱን አንስተዋል። በክልሉ ማዕድን ልማት ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች በጥናት የተለየ የማዕድን ሀብት ያለበት ቦታ እንደሚፈልጉ ጠቅሰው፤ ይህን ችግር ለመፍታት ኤጀንሲው በማዕድናት ዙሪያ ጥናት እያደረገና ባለሀብቱም በማዕድን ጥናት እንዲሳተፍ የማበረታታት ሥራዎች እየሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በማዕድን ዘርፉ በማኀበራት ተደራጅተው የሚሰሩ ወጣቶች በፍጥነት ወደ ማዕድን ልማት ሥራ አለመሰማራታቸው ዋነኛ ተግዳሮት መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የማዕድን ልማት እውቀትን፣ የማልማት አቅምን እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡ ማዕድኑን ለማውጣት የሚያገለግሉ ማሽኖች እንዲኖራቸው እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ በማኀበር ተደራጅተው የሚሰሩት ወጣቶች ያላቸው እውቀት፣ አቅምና ደረጃ ዝቅተኛ መሆኑ በፍጥነት ወደ ሥራ ለመግባት እንደገደባቸውም አስታውቀዋል፡፡

የማዕድን ዘርፉ ከሌሎች የሥራ ዘርፎች አንጻር ሲታይ የሥራ እድል በመፍጠርና በፍጥነት ለማደግ የሚያስችል የተሻለ ዘርፍ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዘርፉ የአቅም ውስንነት እየታየ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

የዘርፉ ሌላኛው ተግዳሮት ወርቅ በሚመረትበት አካባቢ የሚደረገው ሕገወጥ ዝውውር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከሚመረተው የወርቅ ምርት አነስተኛ መሆኑ ጋር ተያይዞ የሚታይ ሰፊ ሕገወጥነት ችግር እንደሌለም ጠቅሰው፣ የጥቁር ገበያ ዋጋ ከፍ ያለ መሆን ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግን እንደሚፈልግ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ክልሉ አዲስ በመሆኑ በዘርፉ ያለው የሰው ኃይል አነስተኛ መሆን እና ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ አለመቻል ሕገወጥነት እንዲስፋፋ አድርጎል›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ በክልሉ ለሚደረገው የማዕድን ጥናት የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቪይ ኢንስቲትዩት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ነው፡፡ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ክልሉ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ከኤጀንሲ ጋር አብሮን እየሰራ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ መስራት የሚገባው ሥራ እየሰራ ኤጀንሲውን እየደገፈና በቅንጅት አብሮ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ በዘንድሮም ዓመትም በባለፈው ዓመትም ያጠናውን ጥናት ለኤጀንሲው ለማስረከብ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡

በማዕድን ዘርፉ በሀገር ደረጃ የተያዙ የትኩረት አቅጣጫዎችን ከግብ ለማድረስ ክልሉ እየሰራ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በአገሪቱ ያላትን ብዙ የማዕድን ሀብቶች በጥናት በመለየት መጠቀም እንዲቻል በክልሉ የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

‹‹ማዕድን አገራችንን ማሳደግ የሚችል ብዙ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ በተለይ የከበሩ ማዕድናት በማልማትና እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ለሀገር የውጭ ምንዛሪ ለማምጣት ትኩረት ተደርጎ ይሰራል›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ እንደ ክልልም አገሪቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ አገራት የምታስገባቸውን ማዕድናት በራስ አቅም በአገር ውስጥ በማምረት መተካት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው›› በማለት ያብራራሉ፡፡

‹‹ማዕድን በክልሉ ያለውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ አንዱ ትልቁ አቅም ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡ ወጣቶችም በዚህ ዘርፍ ሲሰማሩ ቶሎ ማደግ እንዲችሉ የሚያስችል ዘርፍ ነው። ወጣቶች በዘርፉ ላይ እንዲሰማሩና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ በሥራ አጥነት በመቅረፍ የዳበረ የኢኮኖሚ አቅም እንዲኖራቸው ማስቻል ነው›› በማለት ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ፡፡

መንግሥት በሀገር በቀል ኢኮኖሚው ትልቅ ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች የማዕድን ዘርፉ አንዱ መሆኑ ትልቅ እምርታ ነው የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በየደረጃው ያለው አመራር በመተባባር በዘርፉ የሚስተዋለውን ሕገወጥነት በመከላከል ማዕድናት ለሀገር ጥቅም እንዲውሉ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል። ኀብረተሰቡም ከማዕድን ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እንዲያገኝ በማድረግ ሀገራችንን ማሳደግ አለብን ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2016 ዓ.ም

Recommended For You