በሰው ሰራሽ አስተውሎት የአፈርን ይዘት የማወቂያ ቴክኖሎጂን የፈጠረ ወጣት

አዲስ የፈጠራ ሥራ ወይም ቴክኖሎጂ የሰው ልጆችን ሕይወት በብዙ መልኩ ቀይሯል። ከትምህርት፣ ከጤና፣ ከግብርና እና ከሌሎች ዘርፎች አንፃርም የሚሰጠውን ጠቀሜታ ሲታይ እጅግ አስገራሚ ደረጃ ላይ እየደረሰ ይገኛል፡፡ የአጠቃቀም ሂደቱን ሲቃኝ እንደ ዘርፎቹ አይነት ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድም ይለያያል፣ ጥቅም ላይ የሚውሉት መሳሪያዎችም እንዲሁ እንደ አገልግሎቱ አይነትና ስፋት ይለያያሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላሉና በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ደግሞ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራ ፋይዳው እጅግ የጎላ ነው።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የማደግ ዕድል ያላት ሲሆን፣ የማኅበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ለመሻሻል፣ ለደህንነት፣ ለትምህርት ተደራሽነት፣ ለግብርና እና ለጤና አገልግሎት እንዲሁም በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን በቴክኖሎጂና በአዲስ የፈጠራ ሥራ መታገዝ የግድ ሆኗል፡፡ በተለይ አሁን አሁን ያለ ቴክኖሎጂ መኖር ከባድ እየሆነ መጥቷል። ከእነዚህ ዘመን አፍራሽ የቴክኖሎጂ ዘርፎች መካከል አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቀደሚውን ስፍራ እየያዘ መጥቷል።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ዘርፎች ምርታማነትን ለመጨመር እንዲሁም አምራች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለማስተሳሰር ቁልፍ ቴክኖሎጂ ነው። ሰው ሰራሽ አስተውሎት በአሁኑ ወቅት በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በጤና፣ በደህንነት እና በግብርና ዘርፎች ምርታማነትን እና ቅልጥፍናን ለመጨመር በከፍተኛ መጠን እያገለገለ ይገኛል። በኢኮኖሚው ረገድም መረጃዎች እንደሚያሳዩት የእዚህ ቴክኖሎጂ ድርሻ በዓለም ገበያ 350 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል። ይህ ቴክኖሎጂ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን እና ሕይወታችንም ሰፊ ድርሻ እየያዘ መጥቷል።

ያደጉትም ሆነ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ቴክኖሎጂው በሚያስፈልጋቸው ዘርፎች እንደ አስፈላጊነቱ እየተጠቀሙበት ችግሮቻቸውን እየፈቱ ይገኛሉ። ኢትዮጵያም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው። የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የግብርና፣ የጤና፣ የደህንነት እና የመሰል ዘርፎችን አቅም ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል።

ወጣት አብዲዋቅ በቀለ ይባላል። ተወልዶ ያደገው በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ ቤተል አካባቢ ነው። ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርቱን በአካባቢው በሚገኘው ኦሜጋ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። በትምህርት አቀባበሉ ጥሩ የነበረው አብዲዋቅ በአስራ ሁለተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ጥሩ ውጤት በመምጣት የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመከታተል በ2009 ዓ.ም ወደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት በኮምፒውተርና ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በዚሁ የትምህርት ዘርፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እየተከታተለ ይገኛል።

ወጣት አብዲዋቅ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የነበረው ቆይታ ምን ይመስል እንደነበር ሲናገር፤ ወደ ጅማ ከተማ ያቀናው በሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ቆይታው አብረውት ከነበሩ ጓደኞቹ ጋር ስለነበር ከአካባቢው መቀየር ውጭ በቶሎ ከሁኔታዎች ጋር ለመላመድ አልተቸገረም። ከልጅነቱ ጀምሮ ብዙ ሰዓቱን ኮምፒውተር ላይ ያሳልፍ የነበረው አብዲዋቅ፤ እክል የገጠማቸው የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን በመጠገን መልሶ ወደ አገልግሎት ያስገባ እንደነበር ይናገራል። ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሲቀላቀልም እንደህልሙ በኮምፒውተር ምህንድስና የትምህርት ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን በመከታተል በዚህ የቴክኖሎጂ መስክ ለሀገሩ መልካም አበርክቶ ጥሎ ማለፍ እንደሆነ ያስረዳል።

ወጣት አብዲዋቅ እንደሚናገረው፤ ኮምፒ ውተር ኢንጂነሪንግ የሶፍትና ሃርድዌር ሳይንስን በቂ ሊባል በሚችል መልኩ የሚያጠና መሆኑ ለሥራው በከፍተኛ ደረጃ አጋዥ ሆኖለታል። ወጣቱ ከአዲሰ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበረው ቆይታ ወደ ምርምርና ፈጠራ ሥራው የገባበትን አጋጣሚ ምን ይመስል እንደነበር ሲናገር፤ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪ በነበረበት ወቅት በጅማ ዩኒቨርሲቲ በሚሰጠው የማኀበረሰብ ተኮር የትምህርት ፕሮግራሙ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር በመሆን የተለያዩ የማኅበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት ጥረት ያደርጉ እንደነበር ያስታውሳል።

ወጣቱ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር በመሆን የማኅበረሰቡን ችግሮች በመለየት መፍትሔ ለማበጀት ጥረት በሚያደርግበት ወቅት የሀገሪቱ የኢኮኖሚ መሰረት የሆነውን ግብርና በማስቀደም በዚህ ዘርፍ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በሰው ሰራሽ አስተውሎት በመመርኮዝ አንድ የፈጠራ ውጤት ይዞ ብቅ አለ። ይህ ሥራውም የአፈር አይነትን በመመርመር ለየትኛው የሰብል አይነት መሆን ይችላል ወይም ምን አይነት ምርት ቢዘራበት የተሻለ ውጤት ይሰጣል፣ ምን አይነት ማዳበሪያ መጠቀም ይገባል የሚሉ እና በአጠቃላይ አፈሩ ምን ይዘት አለው? የሚሉትን ለመለየት የሚያስችል ለመመርመር የሚያስችል የፈጠራ ሥራ ይዞ ብቅ አለ።

በዚህ ሥራው በቅርቡ ነጋድራስ የሚል ስያሜ ይዞ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተካሄደው የፈጠራ ሥራ ውድድር ተሳትፎ የሶስተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ የሶስት መቶ ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት አሸናፊ መሆን ችሏል። በኢትዮጵያ ግብርና ያለው ትልቁ ችግር ምርት ከመዝራት በፊት መሬቱ ምን አይነት ንጥረ ነገር ይዟል የሚለውን በትክክል አለማወቅ ነው የሚለው ባለሙያው፤ በዚህ ቴክኖሎጂ አማካኝነት መሬቱ ያለውን ሀብት ቀድሞ በመለየት ተጨማሪ የሚደረጉ ነገሮች ልካቸው ታውቆ ምርትና ምርታማነትን በሚያሳድግ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደረጋል ይላል።

እንደ ሀገር በተጠና ጥናት በአሁኑ ወቅት በሄክታር የሚገኘው የምርት መጠን እስከ 24 ኩንታል እንደሆነ የሚናገረው አብዲዋቅ፤ ይህንን የምርት መጠን ደግሞ በሄክታር እስከ 49 ኩንታል ማድረስ እንደሚቻል በቅርብ የተሰሩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ የመሬቱ ወይም የአፈሩ ትክክለኛ ምንነት ማወቅ ሲቻል ነው። ለእዚህ ደግሞ ይህ ቴክኖሎጂ ፋይዳው ትልቅ መሆኑን ያስረዳል።

ቴክኖሎጂው እንደ ሀገር ያለው ጠቀሜታ ምን አይነት ነው የሚለውን በተመለከተ የፈጠራ ባለሙያው ሲናገር፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ግብርና እንደመሆኑ በዚህ ዘርፍ የሚደረግ ውጤታማ የፈጠራ ሥራ ችግሮችን በቀላሉ በመፍታት እያንዳንዱ ዜጋ ድረስ የሚዘልቅ ትርጉም ያለው እንደሆነ ይናገራል። ተግባራዊነቱ በተመለከተ ደግሞ፤ ሶፍትዌሩንም ሆነ ሃርድዌሩን በማምራት ለደንበኞች የማቅረብ ሥራ መጀመሩንም ይናገራል፡፡ አፈር ወደ አስራ አንድ የሚደርሱ ባህሪያት (ፎቶታይፖች) phototype ያሉት እንደመሆኑ በግብርና ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ስለመሬታቸው አፈር ማወቅ ስለሚፈልጉት የትኛውም አይነት ነገር በቂ መረጃ በመስጠት አገልግሎት ላይ እየዋለ እንደሆነ ተነግሯል።

ከሌሎች ጋር ለመወዳደርና በግብርና ቴክኖሎጂ ሃርድዌር ማኑፋክቸሪንግ ላይ በቂ አቅም ለመገንባት የሚሆን የፋይናንስ ችግር ለሥራቸው ትልቅ ማነቆ ሆኖ እንደተጋረጠባቸው የሚናገረው ወጣት አብዲዋቅ፤ ይህንን ግዙፍ ኢንዱስትሪ በተገቢው መልኩ ለማዘመን የመንግሥትም የግልም ተቋማት ድጋፍ ወሳኝነት ያለው በመሆኑ ከጎኑ እንዲቆሙ ይጠይቃል።

በአሁኑ ወቅት (ኦሚሹ ጆይ) የተሰኘ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ከጓደኞቹ ጋር በአንድነት መስርቶ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን እየሰራ የሚገኘው የፈጠራ ባለሙያ፤ በዚህ ድርጅት አማካኝነት በሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ላይ በማሰማራት የዜጎችን ኑሮ የሚያሻሽሉ ሥራዎችን ለመሥራት ውጥን እንዳለው ተነግሮ፤ ከግብርና በተጨማሪ በጤናና በፋይናንስ ዘርፎች የሚታይ ለውጥ የሚያመጡና እንደ ሀገር ፋይዳቸው ጉልህ የሆኑ የፈጠራ ሥራዎች ይዞ ለመቅረብ ሰፊ እቅድ እንዳለው ገልጿል።

አብዲዋቅ እንደሚናገረው፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ማሽን ወይም ኮምፒዩተር የሰው ልጆችን ተክቶ ማመዛዘን፣ መማር፣ ማቀድ እና ፈጠራዎችን ማከናወን እንዲችል የሚያደርግ ነው። በዚህ ሁኔታ ማሽኖቹ አካባቢያቸውን እንዲገነዘቡ፣ የተገነዘቡትን እንዲተነትኑ፤ ችግሮችን እንዲፈቱ ያስችላቸዋል። ይህም በተለይ የሰዎችን ንክኪ በመቀነስ ለምርት መጨመር፣ የጊዜ አጠቃቀምን ለማሻሻል፣ ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ እና ውስብስብ ስራዎችን ያለ ከፍተኛ ወጪ ለመፈፀም ያስችላል። ከጊዜ አንፃርም ያለማቋረጥ እና ያለ ምንም እረፍት እንደሚሠራ በመጠቆም፤ ይህም የኅብረተሰብን ኑሮ የሀገርን ዕድገት እንደሚያቀላጥፍ ያስረዳል ብሏል።

አሁን ላይ ይህ ቴክኖሎጅ በሁሉም ዘርፎች ሰፊ ተግባራት ያሉት በመሆኑ ከቅንጦት ይልቅ ለኅብረተሰብ ያለው አስፈላጊነት ግንዛቤ እያገኘ እንደመጣ የሚገልጸው ወጣቱ፤ ቴክኖሎጂው ግብርናን በማሳደግ በሀገሪቱ ለሚታየው የምግብ እጥረት መፍትሔ ከማምጣት ባለፈ በተለይ በአፍሪካ በሽታዎችን ለመቀነስ፣ የጤና እንክብካቤን እና ትምህርትን ለማሻሻል፣ ድህነትን ለመቀነስ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያግዝ ይናገራል።

ወጣት አብዲዋቅ እንደሚያስረዳው፤ በሚመጣው ዘመን ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ለቴክኖሎጂ ሥራና ምርምር ትልቅ ትኩረት ያስፈልጋል። ቴክኖሎጂ የተለያዩ ሀገራት የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በተመለከተ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ። በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለመሳብ ጥረት እያደረጉ ነው። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ መንግሥት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ቴክኖሎጂን ከግምት በማስገባት የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ ብሎም በቴክኖሎጂ ላይ ለተሰማሩ ተቋማትና ግለሰቦች አቅም በፈቀደ መጠን ሁሉ የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ መስራት እንዳለበት ያስገነዝባል።

ኢትዮጵያ በዘርፉ ብዙ መስራት የሚችሉ አቅም ያላቸው ወጣቶች አሏት የሚለው አብዲዋቅ፤ ነገር ግን ጉዳዩ የሚመለከታቸውና በቴክኖሎጂ ዘርፍ በተገቢው መንቀሳቀስ ያለባቸው ተቋማት በዛ ልክ እየሰሩ አይደለም። ቢሆንም በዚህ ዘርፍ እየሰራ ያለው ወጣት የሚደግፈኝ አካል የለም ብሎ መንቀሳቀስ ማቆም የለበትም የራሱን ጥረት ማድረግ አለበት ይላል። እዚህ ደረጃ እስኪደርስ ድረስ መንግሥት ወይም አንድ ተቋም የተለየ ድጋፍ እንዳላደረገለትና በራሱ ባደረገው የግል ጥረት እዚህ መድረስ እንደቻለ የሚናገረው አብዲዋቅ፤ ወጣቶች ባላቸው አቅም የሚታይና ተጨባጭ የሆነ ነገር ለመስራት ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው ገልጿል።

ወጣት አብዲዋቅ ባስተላለፈው መልዕክት፤ አንድ ነገር ለማድረግ ሲታሰብ ሁል ጊዜ ዋጋ መክፈል ይኖረዋል፤ ፀንቶና ተግቶ በመስራት ግን የማይሳካ ነገር የለም፡፡ የሀገሪቱን የወደፊት ዘመን መልካም የማድረግ ኃላፊነትና ግዴታ ያለባቸው የእዚህ ትውልድ ወጣቶች ለዓላማቸው መሳካት መክፈል ያለባቸውን መስዋዕትነት ሁሉ መክፈል እንዳለባቸውና፤ የነገው ራዕያቸውን ከግብ ለማድረስ ቀን እና ሌሊት ሳይሉ ተስፋ ባለመቁረጥ መትጋት እንደሚገባቸው አስረድቷል።

በምግብ እራስን ችሎ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የማገዝ ጉዳይ ከልማዳዊ አሠራር ሥርዓት ማላቀቅ የግድ እንደሆነ የሚናገረው አብዲዋቅ፤ ኋላ ቀር አሠራሮችን በመፈተሽ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ በማድረግ ዘርፉን ለማዘመን እስትራቴጂካዊ አሰራሮች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።

ከከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቅ በኋላ በኢትዮ ቴሌኮም መስሪያ ቤት ተቀጥሮ ሥራውን የጀመረው አብዲዋቅ፤ ይህንን ጥሩ የሚባል ደሞዝ የሚያስገኘውን ሥራ ትቶ ሕልሙን ለማሳከት ወደ ግል ሥራው ለመሰማራት ሲወስን ከጎኑ ሆነው ያበረታቱትን ጓደኞቹንና ቤተሰቦቹን አመስግኗል።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2016 ዓ.ም

Recommended For You