ከዓባይ ግድብ 13ኛ ዓመት ባሻገር፤

 (ክፍል አንድ)

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አፈፃፀም 95 በመቶ፣ የግድቡ አጠቃላይ የሲቪል ሥራው ግንባታ ደረጃ ደግሞ 98 ነጥብ 9 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ከታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በሁለት ተርባይኖች 540 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እያመነጨ ይገኛል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ሰሞኑን እንደገለፁት፣ ግድቡ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የሚያመርተው ኤሌክትሪክ ኃይል 5ሺ150 ሜጋ ዋት ይደርሳል፡፡ አሁን ላይ ግድቡ የያዘው የውሃ መጠን 42 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ሲሆን ሲጠናቀቅ ፤ የሚይዘው ውሃ መጠን ወደ 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ከፍ ይላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ643 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡም ተገልጿል። በዚህም የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት 2003 አንስቶ እስከ ታኅሣሥ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ከሀገር ውስጥ፣ ከውጪ እና ከቦንድ ሽያጭ ልገሳ እና ከልዩ ልዩ ገቢዎች ወደ 19 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ሃብት መሰብሰቡንም ነው አቶ ኃይሉ ገልጸዋል፡፡

በዚህ መልኩ ከፍ ያለ ሕዝባዊ ተሳትፎም፣ የግንባታ አፈጻጸምም የታየበት የዓባይ ግድብ ታዲያ፣ አሁን ላይ ግንባታው የተጀመረበትን 13ኛ ዓመት ለማክበር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ስሰማ ስለ ታላቁ ወንዛችን ዓባይ መለስ ብዬ አንዳንድ ነጥቦችን ለማንሳት ወደድሁ ።

የዓባይ ተፋሰስ የአፍሪካን አሕጉር አንድ አስረኛ ይሸፍናል፡፡ ከዚህ ባሻገር ዓባይ በዓለማችን ከምንጩ እስከ ሜዲትራኒያን ባሕር ድረስ 6ሺህ 700 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ረዥሙ ወንዝ ነው፡፡ የዓባይ ወንዝ ሁለት ታላላቅ ገባሮች አሉት ። የዓባይ ወንዝ በዚህን ያህል ኪሎሜትሮች ሲገለጽ ከቪክቶሪያ ሐይቅ ተፋሰስ የሚነሳው ነጭ ዓባይና ከኢትዮጵያ ተራራማ ቦታዎች የሚመነጨው ጥቁር ዓባይን በማቀፍ ነው፡፡ ሆኖም ለዓባይ ወንዝ 77 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ማለትም 86 በመቶ ከእነ ለም አፈሩ በመገበር ጥቁር ዓባይ እንደ ስሙ ታላቅ ወንዝ ነው ፡፡

ለጥቁር ዓባይ የሀገር ድርሻን ስንመለከት ደግሞ 49 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በመገበር ዓባይ ትልቁን ድርሻ ሲወስድ ፤ ባሮ አኮቦ ወንዝ 17 ቢሊዮን ሜትር ኩብ እና የተከዜ ወንዝ 11 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በዓመት ይገብራሉ፡፡ የጥቁር ዓባይ የፍሰት መጠን ከሀገሪቱ አጠቃላይ ፍሰት ግማሽ ከመሆኑ ባሻገር፤ በጠቃሚ ማዕድናትም የበለፀገ ነው፡፡ ጥቁርና ነጭ ዓባይ ሱዳን ካርቱም ላይ ይገናኙና ዓባይ /ናይል/ ይሆናሉ ፡፡

በአንጻሩ ምንም እንኳ የዓባይ/ናይል ወንዝ የስምንት የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት ሀብት ጭምር ቢሆንም፤ እስከ ዛሬ በብቸኝነት እየተጠቀሙ ያሉት ግን የግርጌ ተፋሰስ ሀገራት የሆኑት ሱዳንና ግብፅ ናቸው፡፡ የጋራ የውሃ ሀብት ቢሆንም የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት እኤአ በ1929 በሱዳንና በግብፅ በቅኝ ግዛት ዘመን በተፈረመ አግላይ ስምምነት የተነሳ መጠቀም አልቻሉም። ምክንያቱም በእንግሊዝ አይዟችሁ ባይነት በተፈረመው ኢ-ፍትሐዊ ውል መሠረት ለሱዳን 4 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ፤ የተቀረውን ማለትም 48 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ለግብፅ ጀባ ብሏል፡፡

ይህ የቅኝ ግዛት ዘመን ውርዴ የሆነ ስምምነት ሱዳንና ግብፅ የራስጌ የተፋሰሱ ሀገራትን በድጋሚ በማግለል በራቸውን ዘግተው እስከ ተፈራረሙበት እኤአ 1959 ድረስ የቀጠለ ሲሆን፤ በእብሪት የተወጠረው ይህ ስምምነት፣ “ከግብፅ መንግሥት ፈቃድ ውጭ የውሃ መጠኑን ሊቀንስ የሚችል የመስኖም ሆነ የኃይል ማመንጫ ሥራዎችን በዓባይ ገባሮችና ሐይቆች ላይ መገንባት አይቻልም፡፡” የሚልም ነው፡፡ ይህ ግብዝነትንና እብሪትን የሚያሳይ ስምምነት ታዋቂው የግሪክ የታሪክ ሊቅ ሔሮዶተስ ” ግብፅ የዓባይ ስጦታ ናት፡፡” የሚለውን ይትበሀል የዘነጋ ነው፡፡ እኔ ግን ግብፅ የዓባይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ስጦታ ናት ብዬ ነው የማምነው፡፡

ይሁን ጥንታዊ ሥልጣኔዋም ሆነ የዛሬ ሕልውናዋ ከዓባይ ጋር የተቆራኘ ሆኖ ሳለ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከራስጌ የተፋሰስ ሀገራት ጋር ተቀራርቦና ተባብሮ የመሥራት ፍላጎት የላትም፡፡ ይህ ፈርዖኖችም ሆኑ የዛሬዎቹ ገዥዎች ምን ያህል ከዘመኑ ጋር የመሄድና መሬት ላይ ያሉ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ለመቀበል ፍላጎቱ እንደሌላቸው ያስረዳል፡፡ ሆኖም ውሎ አድሮ ሱዳን የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ማንሳቷ አልቀረም፡፡ የ1929ኙ ስምምነት ላይ እንደገና መደራደር እንደምትፈልግ ግብፅን መወትወት ጀመረች ፡፡ የ1959ኙ የውሃ ክፍፍል ላይም ጥያቄ ማቅረብ ቀጠለች ፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ የተፋሰሱን ራስጌ ሀገራት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ አዲስ ስምምነት መፈራረም ካልተቻለ ፤ ሱዳንና ግብፅ በአንድ በኩል፤ ኢትዮጵያና ሰባቱ የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት በሌላ በኩል ለግጭት የመዳረግ እምቅ አቅም እንዳለው ቀጣናዊ የውሃ ፖለቲካ ልሒቃን ያስጠነቅቁ ይዘዋል፡፡ ከዚህ አኳያ የጋራ የሆነውን የውሃ ሀብት በጋራ መጠቀም ሲገባ፤ ግብፅ ግን ከማንኛውም ድርድር በፊት የግርጌም ሆነ የራስጌ ሀገራት የ1959ኙ ስምምነት እንዲቀበሉ ቅድመ ሁኔታ ታስቀምጣለች ፡፡

ሆኖም ይህ የግብፅ ቁሞ ቀር ቅድመ ሁኔታ በተፋሰሱ ሀገራት ተቀባይነት አላገኘም። ምክንያቱም ስምምነቶቹ የተፋሰስ ሀገራቱን በተለይ ሀገራችን ኢትዮጵያን ያላሳተፉ ከመሆኑ ባሻገር፤ ስምምነቶቹ የመንግሥታቱ ድርጅት እኤአ በ1997 ይፋ ካደረገው የፍትሐዊ የውሃ ተጠቃሚነት ድንጋጌ ጋር ይጣረሳሉ ። እናም የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ የሆነውን የዓባይ የውሃ ሀብት ለማልማት የግብፅ ፍቃድ አያስፈልጋቸውም፡፡

ምክንያቱም፣ ሱዳንና ግብፅ ዓባይን ለትላልቅ መስኖዎችና የኃይል ማመንጫነት ሲጠቀሙበት በአንጻሩ ሌሎች የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት ወንዙን የሚጠቀሙበት ለአነስተኛ ኃይል ማመንጫነት ብቻ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት የጋራ የሆነውን ሀብት በስፋት አልምተው የመጠቀም ፍላጎት ስለሌላቸው ሳይሆን ዓለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በግብፅ ተፅዕኖ የተነሳ ብድር የመስጠት ፍላጎት ስለሌላቸው ነው ፡፡

በአንጻሩ የተፋሰሱ ሀገራት የሕዝብ ብዛት በከፍተኛ ፍጥነት በመጨመር ላይ መሆኑን ተከትሎ የውሃ፣ የምግብና የኃይል ፍላጎታቸው በእጅጉ እያሻቀበ ነው፡፡ የሚያሳዝነው እነዚህ ፍትሐዊ ያልሆኑ የፋይናንስ ተቋማት ለግብፅ ሲሆን እጃቸው ይፈታል፡፡ በዚህም ጭው ባለ በርሀ ግዙፍ መስኖዎችን፤ ሀገሪቱን ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ያደረጉ ትላልቅ የውሃ ኃይል ማመንጫዎችን ገንብተዋል። በስተሰሜን የሱዳንና ግብፅ ድንበር ላይ ግብፅ በዓለማችን ረጅሙን የዓባይ ወንዝ በመገደብ በግዙፍነቱ ከዓለም 3ተኛ የሆነውን የአስዋን ግድብ ገንብተዋል፡፡

ግድቡን ከመጀመሯ በፊት ማለትም በ1954 ግብፅ ከዓለም ባንክ ብድር፣ ከአሜሪካ ደግሞ እርዳታ ለማግኘት ጠይቃ ተስፋ ተሰጧት የነበር ቢሆንም፤ ከእስራኤል ጋር በገባችበት ውዝግብ የተነሳ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በዚህ የተከፋችው ግብፅ ወዲያው ፊቷን ወደ ሶቪየት ኅብረት በማዞር ባገኘችው ብድር ግንባታውን ማካሄድ ችላለች። የአስዋን ግድብ 10 ዓመት ከፈጀ ግንባታ በኋላ እአአ በ1970 ተጠናቋል። በጊዜው ግድቡ 90 ሺህ ሱዳናውያን ከማፈናቀሉ ባሻገር በቅርስነት ተከልለው የነበሩ ቦታዎችም በውሃ ተውጠዋል ፡፡

በግድቡ ግንባታ ምክንያት የተፈናቀሉ ሱዳናውያንም ከቀዬአቸው 600 ኪሎ ሜትር ርቀው እንዲሰፍሩ ሲደረግ፤ በግድቡ የተነሳ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ግብፃውያን ግን 40 ኪሎ ሜትር ብቻ እርቀው እንዲሰፍሩ ተደርጓል። ግብፅ ይህን ግዙፍ ግድብ ስትገነባ ከሱዳን ውጭ ሌሎች ሀገራትን ማማከር አይደለም እወቁልኝ እንኳ አላለችም፡፡ ሱዳንንም ያማከረቻት አስባላት ሳይሆን በዜጎቿ ላይ የምትፈፅመውን ግፍ እንድታውቀው ይመስላል ፡፡

የአስዋን ግድብ 2ሺህ 100 ሜጋ ዋት በማመንጨት ግማሹን የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ያሟላ ሲሆን፤ ለከፍተኛ መስኖ ልማትም ውሏል፡፡ በዚህ ረገድ ምንም እንኳን ግብፅ እምቅ የኃይል አማራጭ ቢኖራትም፣ ከውኃ የኃይል ማመንጫዎች ውጭ የመጠቀም ፍላጎት የላትም፡፡ አንዳንድ ምንጮች እንደሚጠቁሙት 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን በርሜል የነዳጅ ድፍድፍ ክምችት በምድሯ ቢኖርም በቀን እያመረተች ያለው ከ640ሺህ በርሜል በታች ነው፡፡ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቷ ወደ 2 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ኩብ የሚጠጋ ሲሆን፤ እያመረተች ያለው ግን ወደ 60 ቢሊዮን ኩብ የሚጠጋ ብቻ ነው፡፡ በቀን 547 ሺህ 500 በርሜል የተጣራ ነዳጅ ታመርታለች፡፡

ግብፅ ሰፊ የከርሰ ምድር ውሃ እንዳላትም ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ይህ ሁሉ አማራጭ (ለኃይልም ሆነ ለመስኖ ልማት የሚውል ሀብት) እያላት መላው ስስቷና ቀልቧ ዓባይ ላይ ነው። እሷ የተሻለ አማራጭ ያላት መሆኑን አይኔን ግንባር ያርገው ብላ በየአደባባዩ እየማለች፣ እየተገዘተችና እየካደች፤ ኢትዮጵያ ዝናብን ጨምሮ በርካታ አማራጭ የውሃ ሀብት እያላት ጥቁር ዓባይ ላይ ግድብ የምትገነባው ግብፅን ለማንበርከክና ጂኦ ፖለቲካዊ ሚዛኗን ለመጨመር ነው ስትል በየመድረኩ የአዞ እንባዋን እየረጨች ነው፡፡

ግብፅ የዓባይን የተፈጥሮ ፍሰት በመቀየር በርሀውን ለማልማት 30ሺህ 300 ኪሎ ሜትር የመስኖ ቦዮችን ገንብታለች ፡፡ ከአስዋን ግድብ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ያህል ውሃ በመሳብ ቶሽካ የተባለውን ሰው ሠራሽ ሐይቅ በመገንባት በርሀውን እያለማች ትገኛለች፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግብፅ 3 ነጥብ 76 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ታለማለች፡፡ ከአስዋን ግድብና ከዓባይ ወንዝ ያልተገባ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚነሱ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ሆኖ፡፡ በትነትና በስርገት የተነሳ በየዓመቱ ከ12 እስከ 14 በመቶ የሚደርስ ውሃ ከግድቡና ከመስኖ ቦዮች ይባክናል፡፡ ለዚህም ለመስኖ ከሚያስፈልገው ውሃ በላይ በመጠቀም ማባከንና ጥራት የሌለው የፍሳሽ መውረጃ በግድቡ ላይ ከሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች ይጠቀሳሉ ፡፡

ከአሜሪካው የካምፕ ዴቪድ ስምምነት በኋላ የግብፅና የእስራኤል ግንኙነት በመሻሻሉ፤ የወቅቱ የግብፅ ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት የፍልስጤምና የእየሩሳሌም ችግር የሚፈታ ከሆነ ከዓባይ ወንዝ 365 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ በየዓመቱ ለእስራኤል ለመስጠት ቃል ገብተው ነበር፡፡ ይህ የጂኦ ፖለቲካ የአሰላለፍ ለውጥ ታዲያ በራስጌ የተፋሰስ ሀገራት ላይ ውስብስብ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም ፡፡

ሌላዋ የግርጌ ተፋሰስና ጎረቤት ሀገር ሱዳንም ግድቦችን ገንብታለች፡፡ ለምሳሌ፣ እአአ በ1926 ሴናርን ለመስኖ፣ በ1936 ጀበል አውሊያ ለኃይል ማመንጫና ለመስኖ ገንብታለች፡፡ በ1950 3ኛውንና 420ሺህ ሄክታር መሬት መስኖ የማልማት አቅም ያለው የሮሴሪስ ግድብን፤ እንዲሁም ከእዚህ በተጨማሪ ሌሎች ግድቦችን ገንብታለች፡፡ በዚህም በመስኖ መልማት ከሚችለው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬቷ 1ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታሩን ማልማት ችላለች፡፡ በግብፅና በሱዳን በመስኖ እየለማ ያለ መሬት የዓባይን 86 በመቶ ከምታበረክተው ሀገራችን ጋር ስናስተያየው፣ የኢትዮጵያ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑ ሊያስቆጨን ይገባል፡፡

እንግዲህ ከፍ ብሎ እንደተመለከትነው በዓባይ የውሃ ሀብት ላይ በብቸኝነት እየተጠቀሙ ያሉት ሁለቱ የግርጌ ተፋሰስ ሀገራት በተለይ ግብፅ ናት። በሌላ በኩል የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ የከፋ ድህነት ላይ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የግብርና ድርጅት /ፋኦ/ ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል። ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርታቸው እጅግ ዝቅተኛ ከመሆኑ ባሻገር የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ እንዳልቻሉ ፋኦ ያትታል፡፡ ምንም እንኳን በኢትዮጵያ አሁን ላይ ኢኮኖሚያዊ እድገቱና የግብርና ልማት ሥራው እመርታ እየታየበት ቢሆንም፤ ንጽጽራዊ የአጠቃቀም ችግሩ ግን ገሃድ ነው፡፡

ለምሳሌ፣ በተፋሰሱ ሀገራት የሚገኝ አብዛኛው ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ አይደለም። አማካኝ የሀገራቱ ኤሌክትሪክ የማዳረስ ፍጥነት ከ30 በመቶ የተሻገረ አይደለም፡፡ ከ65 በመቶ የሚልቀው ሕዝቧ ለልጆቹ ማጥኛ፣ ለቤተሰቡ ምግብ ማብሰያና ለምሽቱ ብርሀን የሚያገኝበት የኤሌክትሪክ ኃይል የለውም፡፡ በፀሎቱ የማታ እራትና መብራት አታሳጣኝ ማለቱም የዚህ ገላጭ ብሂል ነው፡፡ የውኃ ኃይል ማመንጫ በተለይ በራስጌ የተፋሰስ ሀገራት ለምቶ ጥቅም ላይ ባለመዋሉ በእድገታቸውና በልማታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ይህ የኃይል እጥረት ዜጎች ፊታቸውን ወደ ከሰልና የማገዶ እንጨት እንዲያዞሩ በማድረጉ ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋን ከማስከተሉ ባሻገር የአየር መዛባትንና ብክለትን እያስፋፋ ይገኛል፡፡ ለዚህ ነው በተመጣጣኝ ዋጋ ኃይል ማቅረብ የግድ የሆነው፡፡

የራስጌ ሀገራት ግብርና በዋናነት የዝናብ ጥገኛ ቢሆንም፣ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአየር ፀባይ ለውጥ የተነሳ በየዓመቱ ሊባል በሚችል ሁኔታ ድርቅ ስለሚከሰት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ፈተና ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ስለዚህ እንደ መስኖ ያለ አማራጭ የውሃ ሀብቶችን በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ የሕልውና ጉዳይ ነው፡፡ የናይልን የውሃ ሀብት በፍትሐዊነትና በኃላፊነት የመጠቀም ጉዳይ ከዓመት ዓመት እየገፋ ከመምጣቱ ባሻገር የተግባር እንቅስቃሴ ተጀምሯል ፡፡

ለአብነት፣ ታንዛኒያ ከቪክቶሪያ ሐይቅ 170 ኪሎ ሜትር በተዘረጋ ቧንቧ ውሃ በመውሰድ በሀገሪቱ በከፋ ድህነት የሚታወቀውን ካሃማ የተባለውን አካባቢ በመስኖ ለማልማት እየሠራች ነው፡፡ ሌሎች የራስጌ ተፋሰስ ሀገራትም ከወንዙ ድርሻቸውን በመጠቀም የውሃ ኃይል ማመንጫና የመስኖ ግንባታዎችን በማካሄድ ረሀብንና ድህነትን ለመዋጋት ቆርጠው ተነስተዋል ፡፡

ለዓባይ ወንዝ ውሃ 86 በመቶውን የምታበረክተው ሀገራችን ኢትዮጵያም ታላቁን የሕዳሴ ግድብ የምትገነባው ከከፋ ድህነት ለመውጣትና የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም ሉዓላዊ መብቷን ለማረጋገጥ ነው፡፡ የዓባይን የ13ኛ ዓመት የግንባታ ሂደትና ውጤቱን ስናስብም እነዚህን ከበስተጀርባው ያሉ ሐቆች በመገንዘብ ሊሆን ይገባል። የዛሬው ምልከታዬንም፣ በዚህ እልባት አደርግና በቀጣዩና በመጨረሻው ክፍል ደግሞ ካቆምሁበት እቀጥላለሁ።

ሻሎም ! አሜን ።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2016 ዓ.ም

Recommended For You